ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ደህና ናችሁ? ትምህርትስ እንዴት ነው? በደንብ እያጠናችሁ ነው? ጎበዞች። ልጆች በተለይ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆናችሁ መቼም ዛሬ የፋሲካ በዓል እንደሆነ ታውቃላችሁ። አዎ እናንተም ለረጅም ጊዜ ስትፆሙ ቆይታችሁ ዛሬ ፆመ ልጓሙን ፈታችኋል። በፆም ወቅትም በአብዛኛው ስትመገቧቸው የነበሩ ምግቦች የእህል ዘር፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ናቸው።
በእነዚህ ረጅም ጊዜያት የሰውነታችሁ የምግብ መፍጨት ስርአት የለመደው እነዚህኑ የእህል ዘሮችንና የአትክልትና ፍራፍሬ ምግቦችን ነው። እናም በፋሲካ በዓል በአብዛኛው የተለመደውና የሚቀርበው የእንስሳት ውጤት የሆነው ስጋና ስጋ ነክ ምግብ ነው። በፋሲካ በዓል ከእነዚህ የስጋ ውጤቶች በልዩ ልዩ መልኩ የተዘጋጁና ቅባት የበዛባቸው ምግቦች ለምግብነት ይውላሉ።
በፆሙ ምክንያት ለረጅም ጊዜ የእህል ዘሮችን፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ስትመገቡ ቆይታችሁ በቀጥታ እነዚህን የስጋ ውጤቶችንና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ወደ መመገብ ስትሽጋገሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባችሁ የስነ ምግብ ባለሙያዎች ይመክሯችኋል።
ልጆች፣ በፋሲካ በዓል ስጋና ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን ከመጠን በላይ መመገብ ቅባት የሚፈጩ ኢንዛይሞች ላይ ስራ ማብዛት ስለሚሆንና በኢንዛይሞቹም ላይ ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል የጤና መታወክ ሊያጋጥማችሁ ይችላል። ስለዚህ እነዚህን ምግቦች በመጠኑ መመገብ ይኖርባችኋል።
እንደውም ልጆች የስነ ምግብ ባለሞያዎች በበአል ወቅት ስጋውንና ቅባታማ ምግቡን ከሌሎች የእህል ዘሮች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ጋር በማመጣጠን መመገብ ለጤና ተስማሚ ነው ይሏችኋል። እናንትም ይህን በማድረግ ድንገት ሊያጋጥም ከሚችል የጤና ችግር ራሳችሁን መጠበቅ ትችላላችሁ።
ነገር ግን ልጆች ቅባት የበዛባቸውን ምግቦችና የስጋ ተዋፅኦዎችን ከመጠን በላይ ብትመገቡ በሰውነታችሁ ውስጥ ትርፍ ምግብ ስለሚከማች ላለተፈለገ ውፍረት ሊያጋልጣችሁ ይችላል። ይህ ውፍረት ደግሞ እንደልብ ሊያንቀሳቅሳችሁና እንደሌሎች ጓደኞቻችሁ ላያጫውታችሁ ይችላል። ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ ተጨማሪ የጤና ችግር ሊያጋጥማችሁ ይችላል።
ስለዚህ ልጆች ከቻላችሁ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ምግብ በመጠኑ ተመገቡ። ወይም ደግሞ የተዘጋጀውን ምግብ ከሌሎች የእህል ዘሮች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ጋር አመጣጥናችሁ ተመገቡ። ይህን ካደረጋችሁ ጤናችሁን መጠበቅ ትችላላችሁ። ወላጆችም ብትሆኑ ልጆቻችሁ የበዓል ምግቦችን በመጠኑ እንዲመገቡና አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲወስዱ አድርጓቸው።
በነገራችን ላይ፣ ልጆች እስኪ ስለ አሳለፋችሁት ፆም የምታውቁትን ንገሩን ብትባሉ ምን ብላችሁ ትናገራላችሁ? “ይህ ፆም ጠላታችን ዲያቢሎስ ያፈረበት፣ ትዕቢት፣ ስስት፣ፍቅረ ንዋይ ድል የተደረጉበት፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፆም እንፆም ዘንድ ባርኮ የሰጠን ታላቅ ፆም ነው። ” ትላላችሁ አይደል፤ በጣም ጥሩ ልጆች በጣም ጥሩ። አዎ፣ ይህን አቢይ ፆም የምንፆመው በኦርቶዶክስ ሀይማኖት ይህ ትርጉም ስለተሰጠው ነው። አሁን ገባችሁ አይደል? ጎበዞች።
እንግዲህ ልጆች በዛሬው እለት በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ያለው የፋሲካ በዓል የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆን እመኝላችኋለሁ።
መልካም የፋሲካ በዓል!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም