ሰሞኑን የስቅለት በዓል ላይ መሆናችንን ታሳቢ አድርገን፤ ስቅለት የወንጀለኛ መቅጫ ሆኖ የሚቀርብበት ዘመንን አስበን በሌብነት ላይ ስቅለትን በኢትዮጵያ ብንተገበር በየቀኑ ስንት ስቅለት ይኖር ይሆን? ከሚል ጥያቄ ይህን እንባባል።
አስቀድመን የሌብነትን ትርጉም እናንሳ። ሌብነት ምን ትርጉም ያስፈልገዋል ያው ሌብነት ነው ብሎ ከሚሰጠው ቀላል ትርጉም ወደ ተጨባጭ ከእለት ወደ እለት ትርጉም እንውሰደው። ከህጻን እስከአዋቂ በቀላሉ የሚረዱትን ነገር እንዴት ጥያቄ አድርጎ ማቅረብ አስፈለገም ያስብልም ይሆናል።
ፋብሪካው ውስጥ ክርክሩ ጦፏል። እንደሚታሰበው ሁሉም የሌብነትን ትርጉም የተረዳ በሚመስልበት ሁኔታ ውስጥ አንድ ሰው የለም ትርጉማችን ይለያያል ሲል በዙሪያው ካሉት ጋር ሙግት ገጠመ። አብረው ምሳ የሚበሉ በሻይ ሰዓትም ሰብሰብ ብለው አውጥተው የሚያወርዱ የአንድ ፋብሪካ ሰራተኞች ናቸው። አመታትን በፋብሪካው ውስጥ ቆይተው በህይወታቸው ብዙ ነገሮችን አሳልፈዋል። አንዳቸው ስለሌላቸው ታሪክ ቁጭ ብለው እንዲመለከቱ አስቀድመው የተወሰኑ እንደሆኑ እስኪቆጥሩ ድረስ ረጅምን የህይወት ጉዞ አብረው ዘልቀዋል። መኖሪያቤታቸው ፋብሪካውን ታሳቢ አድርጎ በተሰራው ካምፕ ውስጥ ነው። ከፋብሪካው ወደ ቤት፤ ከቤት ወደ ፋብሪካው ሲሄዱ የታክሲ ወጪ የሌለባቸው አብረው ውለው አብረው በተመሳሳይ እርቀት ላይ የሚያድሩ የሥራ ባልደረቦችና የአንድ መንደር ነዋሪዎች ናቸው።
ክርክራቸው የሌብነት ትርጉምን በመፈለግ አቅጣጫ ላይ ነው። የሌብነት ትርጉማችን አንድ አይደለም የሚለው ባልደረባቸው የታዘበውን ከውስጡ አድርጎ ስለሌብነት ብዙ ያስባል፤ ብዙም ይናገራል። “ልጅ እያለን እርስበእርስ ቀላል የሆኑ ነገሮችን እንሰራረቅ ነበር፤ ካደግን በኋላ ደግሞ እድሚያችንን የሚመጥን መሰራረቅን እንሰርቃለን” ይላል። “አንዳንዱ ስርቆትን ሲያስብ የሚያስበው ሙሰኛውን ብቻ ነው። አዎ፤ ሙሰኛው ሌባ ነው። ነገርግን ከትልቁ ሌባ መለስ በብርም ከብር ውጪም በሆነ መንገድ የሌብነት ትርጉም ውስጥ የምንገኝ ብዙ ነን ብሎ ያስባል። ማንስ ነው ከሌብነት ራሱን የጸዳ እንደሆነ አድርጎ የሚያስብ?” ብሎም ይሞግታል። “የቢሮ ሰዓት ፌስቡክ ለማየት እኮ ስርቆት ነው፤” ይላል።
“ድርጅቱ የወር ደሞዝ ወርን ጠብቆ ሲከፍል የደሞዝ መክፈያ መለኪያ ያደረገው ጊዜን ነው። ጊዜ መለኪያ ካልተደረገ የወሩ ድምር የስራ ሰዓታት ለድርጅቱ የተሸጡ ናቸው ማለት ነው። ይህን የተሸጠ ሰዓት ለግል ጉዳይ መጠቀም ሌብነት ነው፤ ትርጉም ያልተሰጠው ሌብነት። በሌብነት መዝገበቃል ውስጥ በግልጽ የማይታይ ነገርግን በድምር ውጤቱን አገርንም ሆነ ተቋምን ብዙ የሚያከስር ሌብነት። በአንድ የተሸጠ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የማይመለከተው አካል ገብቶ ማስታወቂያውን ቢያስነገር ስርቆት ነው፤ ምክንያቱም የከፈለበት ሳይሆን ያልከፈለበት ማስታወቂያ የተስተናገደ ስለሆነ። የድርጅት ሰዓትም ለድርጅቱ ዓላማ ብቻ አለማዋል በቅጡ ለሚያስብ ሰው ስርቆት ስለመሆኑ አስረጂ አያስፈልገውም።” ይላል የክርክር ድምቀት የሆነው የማህበረሰብ ንቃት መጨመር ለለውጥ ትልቅ እምነት እንዳለው የሚያምነው የፋብሪካው ሰራተኛ።
ከድርጅት ሰዓት ባሻገር ሌብነትን ሊያሳዩ የሚችሉ አያሌ ተግባራት በየቀኑ እንደሚፈጸሙ አንባቢው ልብ ሊለው ይችላል። ለሌብነት ክፍያው ስቅላት ቢሆን በየቀኑ ስንት ሰው ይሰቀል ይሆን ለሚለው ጥያቄ ግላዊ ምላሻችንን ዳግም እየመረመርን ሌባው መጀመሪያ የሚሰርቀው ራሱን መሆኑን እናንሳ።
ሌባው ራሱን ሲሰርቅ
“ሌባው ማንን ይሰርቃል?” ቢባል ትክክለኛው መልስ “እራሱን ነው” ይላል የምናብ ታሪካችን የፋብሪካው ሰራተኛ።
የሌብነት ድምር ውጤት ከራስ ላይ መስረቅ ቢሆንም በሌባው አዕምሮ የተሳለው ተቃራኒው ስለሆነ ሌብነቱን ባሳካ ጊዜ ውጤት ያስቆጠረ እንደሆነ ያስባል። ስለትንሹም ሆነ ስለትልቁ ሌባ አንስተን ብናወራ በጊዜ ሂደት ውስጥ ያለው ውጤቱ ከራስ ሰርቆ መገኘትን እንደሆነ እንረዳለን።
ጥቂት ማሳያዎችን አንስተን ጥያቄውን ለአንባቢው እናቅርብ። በትዳሩ ላይ የማገጠ ሰው የፈጸመው የመማገጥ ተግባር ዛሬ ነገ ታወቀብኝ እያለ በስጋት ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል። ነገርዬው የታወቀ ቀን ደግሞ በቤቱ ውስጥ የፈራው ነገር ሆኖ ይመለከታል። የፈራው በሆነ ጊዜ ሁሉም በቀረብኝ ሲል የሚቆጥራቸው የረዘሙ ቀናት ይወለዱበታል፤ የጸጸት ቀናት። በትዳሩ የማገጠው ሰው በስተመጨረሻ የሰረቀው ከማን ነው?። የራሱን የልብ መተማመን ማጣት ስርቆቱ ከማን መሆኑን ያሳያል? የራሱን በሰላም ትዳሩን መምራት አለመቻል ዋናው ተሰራቂ ማን እንደሆነ ይነግረናል? የራሱን በቤተሰቡ ውስጥ በነጻነት መኖርን ሲነፈግ በተጨባጭ ተጎጂ ሆኖ የሚገኘው ማን እንደሆነ ያሳያል? አንባቢው ራሱን በዚህ ሰው ቦታ ላይ አድርጎ ይመልከትና ሌባው ከማን እንደሰረቀ ብያኔን ይስጥ። ጸሃፊው ግን ሌባው ራሱን እንደሰረቀ ያምናል።
በሥራ ቦታው በግዢ ስራ ላይ የተሰማራ ግለሰብ በግዢ ሂደቱ ላይ በሌብነት ነገሮችን የሚያከናወን ቢሆን፤ በሌብነት እጁ ስለሚገባው እቃ ብሎ ያልሆነ ነገር እንዲገዛ የሚያደርግ ቢሆን፤ እውን ይህ ሰው ስለስራው በልበሙሉነት በባልደረቦቹ ፊት መመላለስ ይችላል? እውን በቅርቡ ያሉ ሰዎች የሚያደርገውን የማያውቁ ሊሆኑ የሚችሉበት እድል አለ? የሚያውቁ ቢሆን ምናልባትም የሚተባበሩት እንዲሁ እኒህ ሰዎች ስለሞራል፣ ስለ ህግ የበላይነት፣ ስለ ስፖርት፣ ስለ እምነት፣ ስለ ትዳር ወዘተ አብረው መነጋገርና መወያየት ይችላሉ? እናሳ እኒህ ሰዎች የተሰረቀባቸው በነጻነት ሃሳብን የመከፋፈል፤ በሰው ፊት ሰው ሆኖ የመታየት ነገርስ በምን ይመለሳል?
ለአንድ ሥራ ብቁ ያልሆነ ሰው በዘመድ በኩል ወይንም በሌላ እጅ መንሻ አንድ መስሪያቤት ውስጥ ቢቀጠር፤ ዛሬ ነገ ሚስጥሬ ታወቀ ከሚለው ስጋት ጀምሮ በብቃት ባልተገኘበት ስራ ውስጥ በሚፈጥረው ጉድለትና የስራ ጥራት ማነስ ምክንያት ወዘተ የሚኖረው በልበሙኑት ስራውን አለመስራት ስርቆት የተከናወነው በማን ላይ ነው?
እጅግ የበዙ የስርቆት ማሳያዋችን መደርደር እንችላለን። የስርቆትን ትርጉም በሚገልጸው ደረጃ አድርገን ስንመለከት መዳረሻው ተሰራቂው ጋር ስንደርስ ሌባው ባሰበበት ተቃራኒ ተሰራቂውን እናገኘዋለን። አዎ፤ ሌባው በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያገኘው ነገር ይኖራል፤ ነገርግን በመሰረታዊነት ሌባው ራሱ ተሰራቂ ነው። ሌባው ሰላሙን፣ ጤንነቱን፣ ከሰዎች ጋር ያለውን መስተጋብር፣ በልበሙሉነት አንድን ነገር ቀርጾ የመንቀሳቀስ አቅምን፣ እድገትን፣ የሞራል ልእልናን፣ ወዘተ የሚሰርቅ ነው። ሰዎች እኒዚህን ነገሮችን ከተሰረቁ ራሳቸውን በመጠጥና በአጉል ነገሮች ውስጥ የመደበቅ መንገድን የሚከተሉ ስለሆነ በቀኝ እጁ የተቀበለውን ገንዘብ በግራ እጁ ያወጣዋል። በጊዜ ሂደት የእኒህ ነገሮች የጤናና የቤተሰብ መዋቅርን የማዳከምና የማፍረስ እንዲሁም የህይወትን አቅጣጫም የሚቀይሩ ሆነው ይገኛሉ። አዎን ሌባ ሌላውን ይሰርቃል፤ በዋናነት ግን ራሱን ይሰርቃል! አንባቢው ደጋግሞ ለራሱ ይበለው፤ አዎን ሌባ ሌላውን ይሰርቃል፤ በዋናነት ግን ራሱን ይሰርቃል!!
የወረቀት ላይ ሌብነት ባለንበት ዘመን ሙያዊነት እያደገ የመጣበትን ሁኔታን በጉልህ እናስተውላለን። ስራዎችን በሚመለከተው ባለሙያ ለማሰራት ለባለሙያ የመክፈል ባህል እየመጣ ነው። በጠቅላላ እውቀት ስራዎችን ከመስራት ሙያን ማእከል አድርጎ በትኩረት መስራት የተሻለ አሰራር መሆኑም በሰፊው ተቀባይነት ያገኘም ይመስላል።
ከሙያዊ እድገት ጋር አብሮ እያደገ የመጣው ሙያዊ የወረቀት ላይ ሌብነት ነው። ባልተገባ መንገድ የተዘረፈን ገንዘብ፤ ኦዲተር እንዳያገኘው በሚያስችል ሁኔታ ሙያን ተጠቅሞ ወረቀት ሲሰራለት እርሱ ወረቀት አገዝ ሌብነት ልንለው እንገደዳለን። አንድ ድርጅት የውስጥ ቁጥጥር ስርዓትን ተግብሮ ነገርግን የቁጥጥር ስርዓቱ ሌብነትን መያዝ እንዳይችል የሚያደርግ የወረቀት ላይ ሌብነት የበረከተበት ዘመን ውስጥ እንገኛለን። በአለምአቀፍ ትልልቅ ተቋማት ላይ የሚሰሙ የምርመራ ሪፖርቶች ሙያን ተገን ያደረጉ የበረከቱ ቅሌቶች/scandals የሚያጋጥሙ መሆኑን ነው። ወደ አገራችን የተለመደው የቁጥጥር ስርዓትን አልፎ የሚሰራውን ስርቆት ከሚያሳዩት መካከል የፕሮፎርማ ስርዓት ተጠቃሽ ነው። ሦስት ፕሮፎርማ ሰብስቦ የተሻለ ዋጋ ሊሰጥ የሚችልን ለማግኘት የተዘረጋ ስርዓት ከአንድ ነጋዴ ሶስት ፕሮፎርማ በማግኘት የቁጥጥር ስርዓቱ እንዳይሰራ ማድረግ እንደ ማሳያ ሊቀርብ የሚችል ነው። በየህክምና ባለሙያ ገቢውን ለመጨመር ሲል በሙያዊ መረዳቱ የማያምንበትን ምርመራ እንደሚያዝ የሚቀርበው ወቀሳ አድማሱ የሰፋ ነው። ይህም ሌላው የወረቀት አገዝ ሌብነት ማሳያ ነው። በምህንድስና፣ በመንገድ ስራው፣ በባንኮች የብድር አሰጣጥ ስርዓት ውስጥ ወዘተ የሚከናወነውን ስንመለከት የምናየው የወረቀት ላይ ሌብነት መዋቅራዊ እየሆነ መምጣቱን ነው።
የመንግሥት፣ የህዝብ እንዲሁም የግል ተቋማት እንዴት አድርገው የወረቀት ላይ ሌብነትን ለማስቀረት አስበው የማይሰሩ ከሆነ በወረቀት ጋጋታ ውስጥ ሌብነት ስር እየሰደደ፤ ለሌብነት የሚመች ከባቢ እየተፈጠረ ይሄዳል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ መንገድ ላይ ሞባይል መንትፎ ከሚሮጠው ቀማኛ በከፋ ሁኔታ ከረባት አድርጎ፤ በንግግሩ መካከል የእንግሊዘኛ ቃል ጣል ጣል የሚያደርግ ወረቀት አገዝ ሌብነትን የሚያደርግ አንቱታ የተሰጠው ሰው ከፍተኛ ነው። ለአንድ ስራ ውል እስከመግባት ጀምሮ እስከ ውሉ አፈጻጸም ድረስ የወረቀት አገዝ ሌብነት በስፋት ይተገበራል። መፍትሔውን ማሰብ እንደ አገር በሌብነት ምክንያት የከፋው ላይ ከመድረስ በፊት ያግዛል።
የሌብነት መስፋት እንደ መንስኤ ከሚቀርቡት ነጥቦች መካከል የግብረገብ ትምህርት አለመኖር፣ የእምነት ተቋማት በተከታታዮቻቸው ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ማሳደር አለመቻል፣ አገራዊው የስልጣን አያያዝ ሂደት ከመነሻው በሌብነት ላይ የተመሰረተ መሆን፣ የኢኮኖሚ እድገት ውስንነትና የሰው ልጅ የሚካፈለው ሃብት እያነሰ መምጣት ወዘተ ተብሎ ይቀርባሉ። ከመነሻው ሥልጣን ሲሰራ የሚለውን ነጥብ እናንሳና ሌሎቹን በሌሎች ጊዜዎች ልናነሳቸው እንደምንችል በማሰብ ወደ ማጠቃለያው እንቃረብ።
ከመነሻው ሥልጣን ሲሰራ በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉም ስርዓቶች ተገጣጥመው በአንድ ሳንባ መተንፈስ ወደሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ህዝብ የሚተዳደርባቸው ስልጣኖች በግልጽነትና ከሌብነት በጸዳ መንገድ መያዝ እንዳለበት ይታመናል፤ በአገራችንም ህገመንግሥት ውስጥ ይህን ለማሳካት የሚያስችል ድንጋጌዎች ይገኛሉ።
የአንድ አገር ህዝብን ማገልገያ ስልጣን የሚሰራበት መንገድ በማህበረሰቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ የሆነ ተጽእኖ ያለው መኖሩ ማህበረሰቡ የሚከተለው እሴትን በሰፊው ለመግራት እድልን ይሰጣል። በህዝብ ይሁንታ የተሰራ ስልጣን በህዝብ ይሁንታ እንደሚወርድ ሲታሰብ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴውም ከሌብነት የጸዳ የመሆን እድሉ ሰፊ እንደሆነ በርካታ የምርምር ስራዎች ያሳያሉ።
በየደረጃው ውሳኔ ሰጪነት የሚመነጭበት ስልጣን ምንጩ ብቃት ሲሆን፤ መውጫና መውረጃው ነጥቡ ውጤት ሲሆን በጤናማ መንገድ ስልጣንን ለመስራት የሚረዳ ሆኖ ይታያል። በጤናማነት ስልጣን ባልተሰራበት ሁኔታ የሚፈጠረው የሌብነት ደረጃ መዋቅራዊ እንዲሁም የቢሮክራሲው አንድ አካል ተደርጎ ሊጠቀስም ይችላል። ግልጽነት በሰፈነበት አሰራር ውስጥ ሌብነት እድል ስለማያገኝ ሌብነት እየቀጨጨ የመሄድ እድል አለው።
ከዓለማችን የትላንት እንዲሁም የአሁን ዘመን ታሪክ የምንረዳው ስልጣን በቤተሰብ ደረጃ በተያዘበት ሁኔታ ስልጣን በእጁ ያለቤተሰብ ስልጣንን እንዳሻው የመጠቀም እድሉ ሰፊ ስለሆነ ስርቆት በተቀናጀ ሁኔታ በቤተሰቡ ኔትዎርክ ሊመራ እንደሚችል ነው። ግልጽነት በቤተሰቡ ቁጥጥር ውስጥ ስለሚገባ ማለት ነው። አምባገነን መንግሥታት ውስጥም በተመሳሳይ ሁኔታ ከቤተሰብ በከፋ ሁኔታ ገዢው ቡድን ስርዓት ውስጥ ያሉ ሰዎች ስልጣንን በመጠቀም በሌብነት ውስጥ በሙሉ አካላቸው ለመገኘት በሚያደርጉት ሂደት ሌብነት እውቅና የተሰጠው የተወሰኑ አካላት መብት ሆኖም ይገኛል። ህዝብ በገዛ ፈቃዱ መሪውን የሚመርጥበትና የሚያወርድበት ስርዓት እስካልተረጋገጠ ድረስ ሥልጣን የሚሰራበት መንገድ ለሌብነት የራሱን አስተዋጾ ማድረጉን ይቀጥላል።
ዛሬ እንደ አገር የገባንበት ቢሮክራሲውን የተቆጣጠረው ሌብነት ላይ መፍትሔ እንዲመጣ ስልጣንን በንጽህናና በግልጽ መንገድ የመያዝ ባህልን ለማዳበር መስራት ይኖርብናል። ወጣቶቻችንን ነገ አገራቸውን ወደ መልካም ለመምራት ህልም የሚያደርጉት ዛሬ ያለውን በመመልከት መሆኑን በመረዳት። የመፍትሔው መንገድ ትውልድ ተኮር ሊሆን የተገባው ነውና።
ትውልድ ተኮር መፍትሔውን ሳይውል ሳያድር ትላንት ሌብነትን በስቅላት ፍርድ ለመከላከል የሞከሩ አሉ። በአገራችንም ሌብነትን መጸየፍ እንዲቻል ሌባው የሰረቀውን እየተናገረ በህዝብ መካከል እንዲንቀሳቀስ ይደረግ እንደነበር ታሪካችን ይነግረናል። ያለፈው ትውልድ ሌብነት በተለያዩ መንገዶች ለመከላከል ያደረገው ጥረት ያመጣለትን ውጤት በመመርመር ለአሁኑ ሊወሰድ የሚገባውን ትምህርት ማግኘት ያስፈልጋል።
ትውልድ ተኮር መፍትሔን ለአገራችን ለመፈለግ ስናስብ ዛሬ ላይ በዙሪያችን ያሉትን እንዲሁም በእናታቸው ሆድ ውስጥ ያሉትን በተጨባጭ እያሰብን መሆን አለብን። ትውልድ ተኮር መፍትሔን በምናስብበት ጊዜ ማህበረሰባዊ ለውጥ በጥቂት ሰዎች ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ በሰፊው መስራት እንዳለብንም የሚያሳይ ነው።
ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ ለውጥ ያስፈልገዋል ሲባል በእውቀት የሆነ ለውጥ መሆኑ እሙን ነው። ሌብነትን አሰቃቂ ከሆነ ፍርድ በላይ በእውቀትና በመረዳት ለመቀየር መሞከር አዋጭ ይመስላል። ይህ ማለት በሌብነት ውስጥ እንዳሻቸው እየኖሩ ያሉትን የማእረግ ስም እየሰጠን ባሉበት እንዲቀጥሉ እንፍቀድ ማለት ግን አይደለም። እነርሱን ወደ መስቀል እንሂድ ብንል ደግሞ ስቅለት በየቀኑ ስለሚሆን። በየቀኑ ብቻም ሳይሆን በየደቂቃውም፤ በየሰከንዱም ሊሆን ስለሚችል፡!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014