የተፈጥሮ በረከት የሆነውን ጨው የሰው ልጅ ለምግብነት ሲገለገልበት ለብዙ ዘመናት መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ጨው አሁንም የምግብ ማጣፈጫ፣ ለእንስሳት ማድለቢያ፣ ከዛም አለፍ ብሎ የቆዳ ማለስለሻ በመሆን በተለያየ አገልግሎት ላይ ይውላል።ጨው እንዲህ ለምግብ ማጣፈጫ ከማዋሉ በተጨማሪ ሰዎች በሙከራ የተለያየ ውጤትም አግኝተውበታል። ለአብነትም ቀለማቸው በቀላሉ የሚለቁ አልብሳት ጨው በማድረግ ቀለሙ እንዳይለቅ፣ ንብ በነደፈበት የሰውነት ክፍል ላይ በማድረግ ህመምን ማስታገስ፣ ዘይት ላይ የሚፈጠር እሳትን ለማጥፋት፣ የተወሰነ ጨው በውሃ ውስጥ በማድረግ የተበላሸ እንቁላል ለመለየት፣ እንደ ሽሮ፣ በርበሬ ያሉ ደረቅና ሌሎችም ምግቦችን ለረጅም ጊዜ ለማቆየት የሚሉት ከሚሰጠው ጥቅም ጥቂቶቹ ይጠቀሳሉ። እንዲህ ያሉ ግኝቶች በባህልም በሳይንስም የተደገፉ ናቸው። ከሰው ልጅ ጤና ጋር በተያያዘም ስለጨው አደገኛነት ክርክሮች ይነሳሉ።ጥንቃቄው ተገቢ ቢሆንም ያለ ጨው ምግብ መመገብ አይመከረም።ጨው በተገቢው ሁኔታ መታከም ያለበት ከተፈጥሮ የሚገኝ ውድ ስጦታ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች አበክረው ይናገራሉ። በመሆኑም በጥንቃቄ ከምግብ ገበታ መራቅ የለበትም ነው ምክራቸው።
እንዲህ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያስገኘው በንጥረ ነገሮች የበለፀገው ወይንም ሶዲየም ክሎራይድ የተሰኘው ጨው ገንዘብ በሌለበት በጥንት ዘመን መገበያያ ሆኖ በማገልገል እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ የተሰጠ ሀብት መሆኑም አይዘነጋም። የታሪክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤በቻይና፣ በግሪክ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ ጭምር ውድ የንግድ ቅመም ሆኖ ያገለግል ነበር። በሜዲቴራኔያን ዙሪያ እንዲሁም በሮማ መንግሥት፣ ጨው እንደ ገንዘብ (አሞሌ) አገልግሏል። በኢትዮጵያ በተመሳሳይ እንደገንዘብ መገበያያ ሆኖ ግልጋሎት መስጠቱን የሀብቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዘመኑ በነበረው የመጓጓዣ ችግርና ከባድ ታክስ(ግብር) በመጣሉ፣ አሞሌ ጨውም ከምንጩ እየራቀ በመሄዱና በተለያዩ ምክንያቶች እንደተወደደ ይነገራል። እንደመረጃዎቹ ከአፋር በነፃ የሚቆፈረው አሞሌ ከተማና ቤተመንግሥት ሲደርስ ውድና ብርቅም ይሆን ነበር። የወርቅ ሳንቲም በአሞሌ ማምረቻ ሥፍራ ከ120 እስከ 130 ጥርብ አሞሌ ሲገዛ በሸዋ የመግዛት አቅሙ ከአምስት እርጥብ የዘለለ እንዳልነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በክረምቱ ደግሞ መጓጓዣ ስለማይመች የበለጠ ይወደዳል። ውሎ አድሮ ወቅትን ተከትሎ የሚኖረው የዋጋ መዋዠቅና የመቅለጥ እንዲሁም የመሰበር ባህሪው አሞሌን እንደመገበያያ መጠቀሙ ከባድ አድርጎት እንደነበርና ጎን ለጎን ይካሄዱ የነበሩ ንግዶችም ተጽእኖ በመፍጠር አበርክቶ እንደነበራቸው ታሪክ ያስታውሳል።አሞሌ በጂማና ከፋ መንግሥታት ጭምር በስፋት ያገለግል እንደነበር የ19ኛው ክፍለ ዘመን ተጓዦች መግለጻቸውን፣ ተጓዦቹ አሞሌ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ በመላው ኢትዮጵያ ያገለግል እንደነበር ታሪኩን ከሰነዱት ያገኘነው መረጃ ያስረዳል። ጨው በጦርነት ጊዜ ለሰብል ማበላሻነት በማዋል የቅጣት መሣሪያም ሆኖ ማገልገሉ ይነገራል።
የጨው ሀብት ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ አንዳንዴ የጥቅም ግጭት ሲያስከትልና ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት ኖሮትም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚያመራበት አጋጣሚም መኖሩ ይታወሳል። ስለጨው ጥቅም ታሪካዊ ዳራ እንዲህ ማስታወስ የወደድነው ከጥንት ስልጣኔ ጀምሮ ለሰው ልጅ ጥቅም በመስጠት እስካሁን የዘለቀው የጨው መገኛ የሆነው ውቅያኖስ ምን ያህል ቦታና ዋጋ ተሰጥቶት በአገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍ ያለ ጥቅም እንዲኖረው እየተሰራበት ነው የሚለውን ጉዳይ ማንሳት ስለወደድን የትኩረታችን አቅጣጫ አድርገነዋል።
በጨው ሀብት መገኛና ጥቅሙ ዙሪያ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ጀማል አህመድ ጋር ባደረግነው ቆይታ እንዳሉት፤ ጨው ልክ ከምድር ውስጥ እንደሚገኘው ነዳጅ፣ የምድር ውስጥ እንፋሎት ወይንም ሙቀትና እንደሌሎች የጂኦሎጂ ሀብቶች ውስጥ ይመደባል። የጨው ሀብቱም የአሞሌና የሐይቅ ሲሆኑ፣ ሀብቱ የላይኛው ክፍል (አፐር)፣ የታችኛው(ሎወር)ተብሎ ለሁለት ይከፈላል። የጨው ሀብቱም የተለያየ ሲሆን አገልግሎቱም ይለያያል። ለተለያየ ኢንደስትሪ ግብአት በመዋል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው እንደፖታሽ ያለው ጨው ይጠቀሳል። ይህም አለታማ ጨው (ሮክ ሳልት) የሚባለው ሲሆን፣ ዳሉል ውስጥ ይገኛል። በጥንቱ አሞሌ የሚባለው ማለት ነው። የአሞሌ ጨው ደረቅ ነው። በባህላዊ የጨው አምራቾች አራት ማዕዘን ያለው ቅርጽ ይወጣለታል።የሀብት ክምችቱም ከፍተኛ መሆኑ በዘርፉ ተመራማሪዎች ተረጋግጧል። የላይኛው ክፍል (አፐር) ብቻ 180ሜትር ጥልቀት ድረስ ጨው እንደሚገኝ ይገመታል። ሌላኛው ከሐይቆች የሚገኘው የጨው አይነት ነው። በትነት መልክ እንዲወጣ በማድረግ ነው የሚመረተው።ከሐይቅ ውስጥ በግፊት ኃይል (ፓምፕ) በማድረግ በተዘጋጀ የጉድጓድ የማምረቻ ስፍራ ውስጥ እንዲጠራቀም በማድረግ ውሃው በትነት እንዲወጣ ይደረጋል። ውሃው ተኖ የሚቀረው ነው ጨው ሆኖ ጥቅም ላይ የሚውለው። በጉድጓድ ውስጥ ተጋግሮ የሚቀረው ጨው በሰው ጉልበት በባህላዊ መሳሪያዎች በቁፋሮና በመፍለጥ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል። የአገሪቱ 95 በመቶ የጨው ግብአት በአፋር ክልል ከአፍዴራ ነው የሚገኘው።
የሐይቅ ውሃ ጨዋማ እንዲሆን የሚያደርገው ተፈጥሯዊ ይዘቱን በተመለከተም መምህር ጀማል እንዳስረዱት፤ አፍዴራ ጨው ምንጩ ምንድነው ሲባል የተለያዩ መገለጫዎች አሉት።አካባቢ የሚገኘው አፈር በራሱ ጨዋማ ነው። ገባር የሆኑት በዙሪያው የሚገኙት ወራጅ ወንዞች ከአካባቢው አጥበው ወደ ዋናው ሐይቅ የሚያስገቡት እና ዝናብም ሲጥል ለጨው ሀብት ክምችቱ አስተዋጽኦ አለው። እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ናቸው አካባቢውን የጨው ሀብት ባለቤት ያሰኙት።
የጨው ሀብቱ የሚነጥፍበት ክስተት ይኖር እንደሆንም መምህር ጀማል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ሀብቱ ይነጥፋል የሚል ግምት የለም። መጋቢ ወንዞች መኖራቸው ስጋቱን ይቀንሰዋል። አፍዴራ ላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ቁጥራቸው እስከ 750 አምራቾች ይገኛሉ። እነዚህ አምራቾች በኃይል ስበት(በጀነሬተር) ከሐይቁ ውስጥ በመሳብ ሲጠቀሙ ከፍተኛ ውሃ ነው ከሐይቁ ውስጥ የሚያወጡት።መጋቢዎች በመኖራቸው ሐይቁ ጨዋማ ውሃ የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ከምድር በታች ያገኛል። የሐይቅ መጋቢ ወንዝ እስካለ ድረስ የሀብት ምንጩ ይቀጥላል።
እንደ መምህር ጀማል ማብራሪያ ይህ በጂኦሎጂ ውስጥ የሚካተተው የጨው ሀብት የኢንደስትሪ ግብአት (ኢንደስትሪያል ሚኒራልስ) ያለው ሲሆን፣ ለአብነትም ፖታሽ፣ ሳልት፣ጂፕሰም ይጠቀሳሉ። መምህር ጀማል ከአፋር ክልል ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሀብቱ ስለመኖሩ እርግጠኛ ባይሆኑም ለጨው መገኘት ሐይቅ ብቻ ግዴታ አለመሆኑን ይገልጻሉ።በአፋር ክልል ውስጥ አፍዴሬ በሚባለው ወደ አሰብ መስመር በሚወስደው ዲቼቶ አካባቢ ከሰመራ ከተማ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዶቢን የሚባል አካባቢ እንደሚመረት ተናግረዋል። ግን ምርቱ ወቅታዊ ነው። ከአፋር ክልል ውጭ በሶማሌ ክልል ውስጥ ምርቱ እንደሚከናወን ነው መረጃው ያላቸው።
መምህር ጀማል ይህ በታሪክም በጥቅምም ትልቅ ስፍራና ቦታ የሚሰጠው የጨው ሀብት እንደአገር ትኩረት ተሰጥቶታል ብለው አያምኑም። ብዙ ነገር በቴክኖሎጂ ታግዞ በሚሰራበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ጨው በባህላዊ የአመራረት ዘዴ ነው የሚከናወነው።ግብይቱም እንዲሁ በባህላዊ ነው። እርሳቸው እንዳሉት፤ በአመራረቱና ዙሪያው አፍዴራን ጨምሮ በክልሉ ሶስት ዋና ዋና ቦታዎች ስለሚገኘው የጨው ሀብት ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል። የጥናት ውጤቱንም የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መድረክ ተዘጋጅቶ አቅርበዋል። ጨው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ታይቷል ብለውም አይገምቱም። እንደርሳቸው እምነት ጨው ለምግብ ማጣፈጫ ከመዋል ባለፈ ጥቅሙ አልፎ አይታወቅም። ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ኬሚካል አምራች ኢንዱስትሪዎች አንዱ ግብአታቸው ጨው ነው። እንደሳሙና ያሉ የንጽህና መጠበቂያዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት ሶዳአሽ የጨው ግብአት ውጤት ነው። የቆዳ ፋብሪካዎችም የጨው ግብአት በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። በረዶ የሚያስቸግራቸው የሌላው ክፍለ ዓለማትም በግግር በረዶ የሚሸፈነውን አስፓልት አቅልጠው ለማስወገድ የሚጠቀሙት የጨው ግብአት ነው። ይህን የጨው ሀብት በአገር ውስጥ ከመጠቀም ባለፈ በውጭ ንግድ ውስጥ አንዱ ግብአት አድርጎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት የአገር ኢኮኖሚን ማሳደግ ይቻላል።
በተለይ መካከለኛው ምሥራቅ የሚባሉ አገራት ግብአቱን በብዛት ይፈልጋሉ። ከማምረት እስከ ግብይት ያለው በጥራት እንዲከናወን በማድረግ ከግብአቱ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል።እንደመምህሩ ሌሎች ምርቶችም ታሳቢ ተደርጎ በጨው ላይ በሰፊው መሰራት ይኖርበታል።ከዘርፉ የሚገኙት እንደጅብሰም፣ ሶዳአሽ፣ ፖታሽ ክሎራይድ ያሉ ግብአቶች ለመጠቀም እንዲቻል የአመራረት ሂደቱ አሁን ከሚሰራበት መውጣት ወይንም መቀየር ይኖርበታል።አመራረቱ ሲዘምን በጥራት ይመረታል። ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ይህን ታሳቢ ያደረገና በዘርፉ ለሚገኘው አምራችም ሆነ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚሆን የሰርቶ ማሳያ ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ትግበራ ለመግባት በሚያስችለው ሂደት ላይ ይገኛል።ፕሮጀክቱ የገበያ ትስስሩም እንዲሻሻል የሚያግዝ ሆኖ ነው የተቀረፀው። ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱን የሚያከናውነው ከክልሉ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አስፈጻሚ ተቋማት ጋር ነው።
ከመምህሩ አጠቃላይ ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው ጨው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም ትኩረት ያልተሰጠው ዘርፍ ነው ማለት ይቻላል። የማምረት ሂደቱ ባለመዘመኑና የሚሰጠው ጠቀሜታም ተለይቶ ለተገቢው አገልግሎት ማዋል ባለመቻሉ እንደአገር ይህ ነው የሚባል ጥቅም ከዘርፉ ተገኝቷል ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ይልቁንም ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ የጨው ውጤቶች በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ወደአገር ገብተው ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምርምርና ጥናት ማካሄድ፣ የምርምር ግኝቶችም ፖሊሲ አውጭዎች ጋር እንዲደርስ ማድረግ ነው። ወደ ሥራ መለወጥ ደግሞ በዘርፉ ላይ ከሚገኘው አስፈጻሚ አካል ይጠበቃል። ምርምሩን የሚያካሂደውና የሚተገብረው ተናብበው በመስራት ወደ ጥቅም እንዲለወጥ ማድረግ ከተቻለ በጦርነትና በተለያየ ምክንያት በዚህ ወቅት የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማበረታታት አንድ ዘርፍ ሆኖ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን በጨው ዙሪያ ያለው መረጃ ያመለክታል።
በተለያየ ጊዜ ይሰራጩ የነበሩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአፋር ክልል እየተመረተ የሚወጣው ጨው የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉበት። በተለይም ለቆዳ ኢንዱስትሪ የሚውል ጨው ላይ ቅሬታዎች እንደነበሩም ይታወቃል። ለሰው ጤና ተስማሚ የሆነ ጨው ማምረት ላይም ክፍተቶች መኖራቸው እንዲሁ ይነሳ ነበር። መንግሥትም እልባት ለመስጠት የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጉ ይታወሳል። በቅርቡም የጨው ግብይትና ከዜጎች ጤና ጋር በተያያዘ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር እና ማዕድን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከባለሙያዎች ጋር በትብብር ጥናት አድርገው ግብአት ማግኘታቸው በዚሁ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና አስፈጻሚ ተቋማት ከአፋር ክልል ጋር በተደረገ ውይይት በጥናቱ ላይ መግባባት ላይ መደረሱ ተመልክቷል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም