እንደምን ሰነበታችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን አንባቢዎች፤ የዛሬ አራት አመት ገደማ ዶክተር ዐቢይ፣ የለውጥ ችቦ ለኩሰው በድል አድራጊነት በጨለማው 27 አመት ጥፍር ነቃይ ስርአት ማክተሙን ሲያበስሩልን፤ የክርስቶስን መስቀል ተሸክመው እንደመጡ ያህል ቆጥረን በእልልታና በሆታ ሐገር ምድሩ እስኪጠበን ድረስ ከአፍሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ ከአውሮፖ እስከ ሚዲልኢስትና እሩቅ ምስራቅ፣ ሳይቀር እልል ብለናል:: እርሳቸው ይዘው የተነሱት የመደመር አስተሳሰብም የሟችና የገዳይ አንድነት ሳይሆን፤ መደመር ፍልስፍና ነው በማለት አስደምመውናል:: ፍልስፍና ደግሞ ጥበብ በመሆኑ አሮጌን ስርአት ቀብሮ አዲስ ስርአት ለማዋለድ የምንከተለው የፍልስፍና ርዮታአለም መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጥ እንደሰማነው የፍልስፍና ዋና አላማውም ስርአትን ማስፈን መሆኑን አስረግጠው ሲያበስሩልን የኢትዮጵያ ትንሳኤን ለማየት የጓጓው ሁሉ የንቢቱን ቲሽርት እየቀየረ የዶክተር ዐቢይን ፎቶግራፍ ደረቱ ላይ ያልለጠፈ አልነበረም፡፡
ዋናው የመደመር አላማ ሰዎችን በሰላማዊና፣ ፍትሀዊ በሆነ ህብረተሰብ ውስጥ በጋራ ተባብረው ተደጋግፈው እንዲኖሩ የሚያስችል የአዲስ ስርአት አዋላጅ መሆኑን በሐሳብ ደረጃ ተስማምተናል:: ምክንያቱም የሰው ልጆች እንደመሆናችን መጠን ሁልግዜም አዳዲስ ነገርን ማየት ብቻ ሳይሆን አዲስ ስርአትም በአስተማማኝ ሁኔታ አገራችን ላይ ተመስርቶ ለማየት በመፈለጋችን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታ ሰክሮ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሆ ሲል፤ ከአኩራፊው የሕወሓት ቡድንና ሸኔ በቀር ያልደገፈ አልነበረም:: ይህንን መካድም አይቻልም፡፡ ጭራሽ የምስራቁ አለም ፍልስፍና መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ የሐበሻ ተወላጆች የኮከባቸውን ሀያልነት በመጠቀም ወደ አረቡ አለም በመገስገስ የምድራችንን የፍልስፍና መንገድ ቀይሠዋል፣ እየተባለ በታሪክ ተመራማሪዎች ሲነገር ብዙዎቻችን ቀልድ ይመስሉን የነበሩት እውነተኛ ታሪኮች በእኛ ትውልድ በጠቅላይ ሚ/ር አብይ የመደመር ፍልስፍና ልናረጋግጥ እንችላለን በሚል ተስፋ ሁላችንም ቆመን የዛሬ አራት አመት አጨብጭበናል፡፡
ይሁን እንጂ ይሁዳ በ30 ዲናር ፈጣሪውን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ፤ ደስታችንን አጣጥመን ሳንጨረስ ለጥቅማቸው ሲሉ ሰው ሳይሆን አገር አሳልፈው የሚሰጡ ኃይሎች (የትግራይ ወያኔዎችና ሸኔ) በከፈቱብን የህልውና ጦርነት ምክንያት በኢትዮጵያ የለውጥ ታሪክ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን አይተን ዋጋ ከፍለንበታል:: በመከራና በጦርነት፣ በስደትና በመፈናቀል፣ በርሀብና በበሽታ ከብርሐን ተስፋ በተቃራኒም ህይወትና ሞትን መውደቅና መነሳት የፈተናና የድል ተምሳሌትነትን ያየንበት የኛ ትውልድ መስታወት በመሆኑ አሁንም ቢሆን ለውጡን ከነ ድክመቱ የምንደግፍበት በቂ ምክንያት አለን፡፡ በሐገር ውስጥና በመላው አለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያኖች በወያኔ አረመንያዊ አገዛዝ ስንገፋ ኖረናል፡፡
በአንጻሩ ያሳለፍነውን የ27 አመት የመከራ ዘመን ብዙዎቻችን ፈፅሞ አንረሳውም፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን ወገኖቻችን ይደርስባቸው የነበረውን ሰቆቃ ቆዳቸው እስኪ ገፈፍ ድረስ የተገረፉትን ስቃይና እስራት ሳንጨመር፤ ስርአቱን ለመሸሽ ሲሉ ከአገር ለመሰደድ በሊቢያ በርሀ ሲያቋርጡ አንገታቸውን የተቀሉት ወንድሞቻችችን ዛሬም ነገም ፈፅሞ አንረሳቸውም፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ከወያኔ ባልተናነሰ ሁኔታ ለመከራችን መብዛት በጥቅማጥቅም የተገዙት ሆድ አምላኪ ባንዳ የቀድሞ ባለስልጣኖች ተልኳቸው ለመወጣት እንደ ይሁዳ ሐገር ከድተው አሳልፈው ለባእዳን እየሰጡን፣ በአሜሪካን ኮንግረስና በአውሮፖ ፓርላማዎች ሲያስከስሱን የነበሩ የወያኔ ቅጥረኞችና የሸኔ አሸባሪዎችን ታግለን አፈር ከድሜ አስገብተን በደም ቀለም የተፃፈ ታሪክ ጀርባቸውና ግንባራቸው ላይ አትመን በድል አድራጊነት ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ይዘን እየገሰገስን ነው፡፡
ሆኖም ግን የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ዶሮ ሳይጮህ ያደረጉት ክህደት አገሪቱን ወደ እልቂትና ወደ ትርምስ ለማምራት በሰሜኑ ጦር ላይ የወሰዱት የክህደት ጭፍጨፋ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት አሁንም ድረስ የሐገሪቱ ሰላም በቅጡ አልተረጋጋም:: እንዲያውም ያሳለፍነው የአንድ አመት ተኩል ጦርነት አልበቃ ብሎ ለሁለተኛ ዙር ጦርነት እየተዘጋጁ ጦር እየሰበቁ የጦር መሳሪያ እየወለወሉብን መሆኑን እንሰማለን፡፡ መንግስት ለሰላም የሚያደርገው የተለሳለሱ እርምጃንም እንደ ፍርሀትና እንደ ተሸናፊነት ቆጥረው ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ እንዳይደርሰው ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡
አሁንም በመቀራረብ መወያየትና መፍትሔ መሻት ሲቻል ፀብ ያለሽ በዳቦ የሚለው በደብረ ጽዮን አማካኝነት የሕወሓት ዲስኩር ላይ እንደተናገሩት ከመንግሥት ጋር በተለያዩ ወገኖች አማካይነት ንግግር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል:: ሆኖም ግን ንግግሩ ለድርድር የማይቀርቡ ጉዳዮች እንዳሉበት ጠቁመው በንባብ አሰምተውን አዳምጠናል። በዚህም መሠረታዊ የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው ያሏቸውን አምስት ጉዳዮችን ዘርዝረዋል። “በመጀመሪያ ደረጃ በሠራዊታችን ላይ አንደራደርም አሉ። አሁን ያለው ብቻ ሳይሆን ገና እንጨምርበታለን:: ስለዚህ በሠራዊታችን ጉዳይ ላይ ድርድር ብሎ ነገር አይታሰብ ብለውናል። ከዚህ በኋላም ኃይላችንን ይዘን ነው የምንኖረው” በማለትም አቋማቸውን ነግረውናል።
በተጨማሪም በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የታወቁ የትግራይ ክልል ወሰን ጉዳይ፣ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ መውጣት፣ የትግራይ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ጉዳይ እና በትግራይ ሕዝብ ላይ በደል የፈፀሙ ግለሰቦች ተጠያቂነት ለድርድር አይቀርብም በማለት አቋማቸውን ግልፅ፣ አድርገዋል። በድርድሩም ጥረቶች ውስጥ እነዚህ አምስት ቅድመ ሁኔታዎች ዋነኞቹና ሊጣሱ የማይገቡ የድርድር ነጥቦች መሆናቸውን ጠቅሰው “ሰጥቶ መቀበል” የሚባለው ጉዳይ እዚህ ላይ አይሰራም” በማለት ለወደፊቱን ለሚደረገው ሐገራዊ ውይይትም ሆነ የሰላም ድርድር. ለማጨናገፍ. በአተካሮ የተሞላ ሀሳብ ሰንዝረዋል። በኔ እምነት ይህ የጤንነት ምልክት አይመስለኝም:: የምትሔድበት እንዳይጠፋህ የመጣህበትን አትርሳ ይባላል፡፡
በእርግጥ ምኞት አይከለከልም የደብረ ፅዮንም ሆነ ደጋፊዎቻቸው፣ ሊያውቁት የሚገባ ጉዳይ ግን ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ ትነሳለች:: እንደ ንጋት ፀሀይ በርታ እንደ ውድቅት ጨረቃ ደምቃ እድሜ ከሰጣቸው ኢትዮጵያ ተነስታ ይመለከታሉ!:: ኢትዮጵያ በላይዋ ላይ ያለውን የወያኔና የሸኔ ቆሻሻ ጥቀርሻን አፅድታ ትነሳለች፡፡ ኢትዮጵያ ካጋጠማት ክፉ የዘረኝነት ደዌ ተላቃ እንደገና እንደ ብርቅዬ አልማዝ ሆና ታበራለች:: ኢትዮጵያ ከወረራት የመከራ ከበባ ተላቃ፤ ልጆችዋን ካስመረራቸው ክፉ አሳቢና እኩይ መርገምት ነፃ ወጥታ ከተሰደዱበት የአለም ዳርቻ ልጆቿን ሰብስባ በአምላኳ ሀይል የአፍሪካ ራዕይ የአለም ተስፋ ሆና እንደገና ትነሳለች፡ ፡ ወደፊት አለም በስምምነት የሚያከብራት ውብ ሐገር አስገራሚ ታዕምራት የሚታዩባት ለአለም ሁሉ የተሰጠች የተቀደሰች ሐገር ሆና ከፍ ትላለች::
በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ ኮሎናሊዝምን ያንበረከከች የጥቁር አልማዞች ሐገር ኢትዮጵያ፣ የአሪኪዎለጂ ምስጢሮች ሲወጡ የአፍሪካ መዲና ዋና ከተማ አዲስ አበባ በብሔራዊ ጀግኖች አደባባዮቿ ያሸበርቁበታል፡፡ ሁሉም ለጀብድ የተዘጋጁ በሚመስሉ በጥንታዊ ብሔራዊ ጀግኖች የተጋድሎ ታሪክ በሚዘክሩ ሐውልቶች ኢትዮጵያ ደምቃ እያበራች ትከበራለች፡፡ እነዚህ በቅኝ ግዛት ያልተገዙና በታሪክ ባለሐብት ጥቁር አልማዞች አለምን የሚያስደምሙበት ቀን እሩቅ አይሆንም፡፡ አለም የሰው ልጅ ጨራሹን የኒኩለር ቴክኒዎሎጂ እየሰማ መጨነቁን አቁሞ በዚች በተቀደሰች ሐገር ቱሪስት ሆኖ እየጎረፈ ሲጎበኛት ጣፋጭ ምግቦቿን በእጃቸው ቆርሰው እየተደነቁ መመገብን ሲመርጥ አብረን የምናይበት ቀን እሩቅ አይደለም:: ስለዚህ እውነትን እንጂ ጊዜን ተደግፈህ አትቁም ጊዜ ባለበት አይቆምም ይሔዳል ይመጣል፡፡ ከጊዜ ጋር ለመራመድ ደግሞ የምትሔድበት እንዳይጠፋህ የመጣህበትን አትርሳ፤ እኔም ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ፡፡ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን::
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም