በስፖርት ውጤታማ ለመሆን መሰረትን በታዳጊዎች ላይ መጣል አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን በፓይለት ፕሮጀክት በማቀፍ ሃገርን የሚወክሉ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት በመስራት ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቶቹ ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ 27 የሃገሪቷ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በእዚህም በሁለቱም ጾታ በጥቅሉ 810 የሚሆኑ ታዳጊዎች በስልጠና ላይ ይገኛሉ።
ይህንንም ተከትሎ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ፕሮጀክቶቹ ባሉባቸው አካባቢዎች ተገኝተው ጉብኝት በማድረግ የስልጠና ቁሳቁስ እገዛ አድርገዋል። ስልጠናው ከተጀመረ አንስቶ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለመመልከት የቻሉት ፕሬዚዳንቱ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ የተመለከቱ መሆኑን ፌዴሬሽኑ በድረገጹ አስነብቧል።
ከወዲሁ ትልቅ ተስፋ እያሳዩ ካሉት ታዳጊዎች መካከልም ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አባል ለመሆን የቻሉም አሉበት። ሌሎች ደግሞ በከተማቸው የውስጥ ውድድሮች ላይ ተካፋይ በመሆን ላይ ይገኛሉ። እንደአጠቃላይ ግን ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን ሁኔታ ለመመዘን የሚያስችል ውድድር የቴክኒክ ኮሚቴው በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት በሃምሌ ወር የሚደረግም ይሆናል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ስፖርቶች መሰል ፕሮጀክቶች ሲቋቋሙ አስቀድሞ የሚደረግባቸው ዝግጅት አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ውጤታማ ሳይሆኑ መቅረታቸው ግልጽ ነው። ፌዴሬሽኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችለው በስፖርቱ እምቅ አቅም ያላቸው አካባቢዎችን የመለየት ኃላፊነቱን ለክልሎች ነበር የሰጠው። ከዚያም የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ የተሳተፈበት ምርጫ በማድረግ የስልጠና ጣቢያዎቹ ሊቋቋሙ ችለዋል። ስልጠናውም በፊፋ እና በካፍ ባለሙያዎች በሰለጠኑ አሰልጣኞች እየተሰጠ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
ከመጫወቻ ኳሶች እና ከስልጠና ቁሳቁስ ጋር በተያያዘም፤ ፌዴሬሽኑ ‹‹አንድ ኳስ ለአንድ ሰልጣኝ›› በሚል መርህ በአግባቡ የተሟላ ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። በመሆኑም አንድ ሺ ጥራታቸውን የጠበቁ ኳሶች ከሞዛምቢክ እንዲገዙ በማድረግ በተጨባጭ እያንዳንዱ ሰልጣኝ አንድ ኳስ እንዲያገኝ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
ሌሎች የስልጠና ቁሳቁስም በተቻለ አቅም ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህንንም አስመልክቶ ፕሬዚዳንቱ ‹‹ሰልጣኞቹ ወደ ስራ የገቡት በተሟላ ሁኔታ አይደለም። እኛም አስፈላጊው ነገር እንዲሟላላቸው ጥረት እናደርጋለን። ከዚህ አንጻር ከዚህ ቀደም የስልጠና ትጥቅ አሁን ደግሞ የመጫወቻ ኳስ እያሟላን ነው›› ማለታቸውንም ድረገጹ አስነብቧል።
ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ አሁንም ድረስ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ችግር ይታያል። በመሆኑም ከክልል ስፖርት ቢሮዎች እንዲሁም ከተማ አስተዳደሮች ጋር መነጋገራቸውንና ይህም እንዲቀረፍላቸው ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል።
አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ላይ በቂ ሜዳዎች አሉ፤ ይሁንና የሚያዙት በሌሎች አካላት በመሆኑ ለታዳጊዎቹ ስልጠና ለማመቻቸት አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም የመጠቀሚያ መርሃ ግብር እንዲያዝ ምክክር ተደርጓል። ከማዘውተሪያ ስፍራዎች ባለፈ ሰልጣኞች የላብ መተኪያ ያገኙ ዘንድ ፌዴሬሽኑ ከክልልና ከተማ አስተዳደሮች ጋር ተወያይቶ ቃል ተገብቶለታል። ወላጆችም የታዳጊዎቹ ትምህርት ላይ ትኩረት ከማድረግ ባለፈ ከስልጠና መልስ ምግባቸው ላይ እንዲያተኩሩም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ፌዴሬሽኑ ካቋቋመው ፕሮጀክት ባለፈ በአንዳንድ አካባቢዎች በራሳቸው ተነሳሽነት በትክክለኛው የእድሜ እርከን ተስፋ ሰጪ የሆነ ስልጠና ሲሰጡ የተመለከቷቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ይህንንም መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ የስልጠና ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን የፕሮጀክቱ አካል እንዲሆኑ የተደረገ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ይህ ፕሮጀክት በጊዜያዊነት የሚያዝ እንዳልሆነና በዘላቂነት የሚሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። ይልቁኑ ለአራት ዓመታት በስልጠና ላይ ቆይተው በእድሜ እርከን ለሚቋቋሙ ብሄራዊ ቡድኖች ግብዓት በመሆን በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተካፋይ ይሆናሉ። ታዳጊዎች ላይ መስራት የፌዴሬሽኑ ስራ አለመሆኑንም ጠቅሰው፣ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የታዳጊዎች እግር ኳስ ልማት የተቀናጀ ስራ እንደሚፈልግ ጠቁመው፣ በአንድ መቆም ያስፈልጋል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2014