እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም፣ ዓድዋ … የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ የመጣው የኢጣሊያ መንግሥት/ጦር በኢትዮጵያዊያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቁን ተከናነበ። ጣሊያኖች ዓድዋ ላይ ድል ከሆኑ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደ መግታት ብለው ነበር። ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሽሮታል፤ ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀት በግማሽ ቀነሰው፤ ከዓድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነ አካቴው የአፍሪካን ምድር ለቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ደፈረ። ይህ ሁሉ ግን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር።
ከእንግሊዝ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያሏቸውን ቅኝ ግዛቶች የምታስተዳድረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ መኖር አልቻለችም። ከዓድዋ ሽንፈት 30 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አምባገነኑ የፋሺዝም አቀንቃኝ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ራሱን እንደ ሮም የቀድሞው ንጉስ ጁሊየስ ቄሳር በመቁጠርና “የኢጣሊያን ክብር ለዓለም አሳያለሁ” በሚል የረጅም ጊዜ ተስፋ የቅኝ ግዛት ዘመቻውን ሊያሳካ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው። ነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ኢጣሊያውያን በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የነበራቸውን ትኩረት ለማስቀየር፣ እየጨመረ ለመጣው የኢጣሊያ ሕዝብ የማስፈሪያ ቦታ ለመፈለግ እንዲሁም በአውሮፓ መድረክ የከሸፈበትን የመስፋፋት ፖሊሲ ለማካካስ ቅኝ ግዛትን አማራጭ አድርጎ ተነሳ። ከሁሉም በላይ ግን ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ሙሶሊኒ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ።
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎችና በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ ‹‹ከእንግዲህ አላውቃቸውም›› አለች። ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች።
ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም። ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። የኢትዮጵያውያን ‹‹እምቢኝ ለአገሬ! ድል ለእናት ኢትዮጵያ፤ ሽንፈትና ሞት ለኢትዮጵያ ጠላት!…›› ባይነት የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲባረር አደረገው። ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ከፃፉና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ አንዱ ነበሩ።
መንገሻ ጀንበሬ የተወለዱት ግንቦት 13 ቀን 1884 ዓ.ም ጎጃም ውስጥ፣ ሜጫ፣ ጉታ አውራጃ አካባቢ ነው። አባታቸው ደጃዝማች ጀንበሬ እምሩ የሜጫ፣ የዴንሳ፣ የጉታና የአገው ምድር ባላባት በመሆን ለብዙ ዓመታት አካባቢውን አስተዳድረዋል። ደጃዝማች ጀንበሬን ጨምሮ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው ሁሉ የደጃዝማች ማዕረግ ነበራቸው። መንገሻ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ብልህና አስተዋይ እንዲሁም በአልሞ ተኳሽነታቸው ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው፤ በበገና ድርደራ እና በፈረስ ግልቢያም የሚታወቁ ነበሩ። ለአደንና ለውሃ ዋናም ልዩ ፍቅር ያላቸው ጀግና ነበሩ።
መንገሻ በተወለዱ በዘጠኝ ዓመታቸው አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ከአያታቸው ደጃዝማች እምሩ ቤት ሆነው የቤተ ክህነት ትምህርት ተከታተሉ።
ከዚያ በኋላም አያታቸው ደጃዝማች እምሩ ሲያርፉ ከአጎታቸው ደጃዝማች ሽፈራው እምሩ ጋር በመሆን የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችንና የአስተዳደር ስልቶችን እየተማሩ አደጉ። የመንገሻን ጀግንነትና ብልሃት የተመለከቱት አጎታቸው ደጃዝማች ሽፈራው፣ ከሚያስተዳድሩት ግዛት በመቀነስ ቆላ አቦሌ የሚባለውን ግዛት እንዲያስተዳድሩ ሾሟቸው።
መንገሻ በ32 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ በማግኘታቸው የቡሬ ዳሞት አውራጃንና የሰከላ አካባቢዎችን ማስተዳደር ጀመሩ። በመልካም ፀባያቸው፣ በአስተዋይነታቸው እና ለአገራቸው ባላቸው ልዩ ክብር ምሥጉን ሆኑ። የሚያስተዳድሩት አካባቢ የፀጥታው ችግር የሌለበት፣ በሁሉም ዘንድ የሚወደድ ባሕርይ እንዳላቸው በመታወቁ ሜጫን እንዲያስተዳድሩ ትልቅ ኃላፊነት ተሰጣቸው። ደጃዝማች መንገሻ በወቅቱ እሳቸው በሚያስተዳድሩት ግዛት ውስጥ ፍርድ የሚያጓድል፣ ድሃን የሚበድል፣ መንገደኛን የሚዘርፍና በአጠቃላይ ሕገ ወጥ ተግባራትን የሚፈጽም ሰው ሲኖር በፍጥነት ፍርድ በመስጠት የሚታወቁ ነበሩ።
በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ደጃዝማች መንገሻ በግዛታቸው ማለትም በሜጫ አውራጃ አካባቢ የሚገኘውን ጦር አስከትለው ከራስ እምሩ ጋር በትግራይ በኩል በመዝመት ለአገራቸው በጀግንነት ተዋግተዋል። ከማይጨው ውጊያ በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞችም ወደኋላ በማፈግፈግና እንደገና በየአካባቢው የሚገኘውን የጎበዝ አለቃ እያስተባበሩ ጠንካራ ውጊያ ለማድረግ ሲዘጋጁ ደጃዝማች መንገሻም የአገው ምድር፣ ሠከላ፣ ሜጫ፣ ጉታ፣ አቸፈር፣ አለፋ ጣቁሳ አካባቢ አርበኞችን በማስተባበር ከወራሪው ጋር መፋለም ጀመሩ።
የጎጃም አርበኞች ራሳቸውን አደራጁ፤ የጦር መሪዎችንም ሾሙ። በዚህ መሰረትም የዘጌ ምድብ ጦር መሪ ፊታውራሪ አምባው ገብረ መድህን፤ የዘጌ መትረየስ ተኳሾች መሪ ፊታውራሪ ከልካይ ሐበሻ፣ የአቸፈር ቆላ ይስማላ ጦር መሪ ፊታውራሪ ደምለው ተፈሪ፤ የአቸፈር ቆላ ይስማላ ጦር መሪ ፊታውራሪ አውደው ሐበሻ፣ ዋና አማካሪና የፕሮፖጋንዳ ስራ ኃላፊ ፊታውራሪ ጊላ ጊዮርጊስ እቁበ ሲሆኑ ከነዚህም በተጨማሪ በሹመቱ ውስጥ ብዙ ታዋቂ ጀግኖችና የጎበዝ አለቆች ነበሩ።
በ1929 ዓ.ም የመጀመሪያ ወር ላይ የጎንደርና የጎጃም አካባቢ የፋሺስት ጦር የበላይ አዛዥ የደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬን መጠናከርና በየአካባቢው የጦር አለቆችን መመደባቸውን ሲሰማ እጅግ ደነገጠ። ይህን የአርበኞችን መጠናከር ሊቋቋምልኝ ይችላል ብሎ ያሰበውን የጦር አዛዥ ሹም ሽር በማድረግና በርካታ ሰራዊት በመመደብ ጦሩ በከተሞች ተወስኖ ምሽግ ይዞ፣ ኃይሉን አጠናክሮ እንዲከላከል አዘዘ።
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ቢቸናን፣ ራስ ኃይሉ ደብረ ማርቆስንና ሞጣን እንዲሁም ራስ በዛብህ ደግሞ ዳሞት አካባቢን በማካለል የጠላትን ጦር ዓረፍት ነሱት። ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ ከደጃዝማች በላይ ዘለቀና ከሌሎች የውስጥ አርበኞች ጋር በመሆን በከፍተኛ መናበብና መቀናጀት እየተፋለሙ ቀጠሉ።
በአምስት አመቱ የአርበኝነት የትግል እንቅስቃሴ ወቅት የተለያዩ ወታደራዊ ቴክኒኮችን በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም የሆኑ አርበኞችና በሕዝብ የተመረጡ የጦር መሪዎች ነበሩ። ከነዚህ ተቀባይነት ከነበራቸው የጦር መሪዎች መካከል ራስ አበበ አረጋይ በሸዋ፣ የጎጃሙ በላይ ዘለቀ፣ የአርማጭሆው ውብነህ ተሰማ፣ ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ፣ ነጋሽ በዛብህ፣ ልጅ ኃይሉ በለው ይጠቀሳሉ።
ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ እጅግ ሩህሩህና በውጊያ የተማረኩ ፋሺስቶችንና ባንዳዎችን ጭምር በጥንቃቄና በርህራሄ እንዲያዙና እንዲጠበቁ ከማድረግ ውጭ የከፋ ቅጣት የማይፈፅሙ ሩህሩህ ሰውም ነበሩ። አርበኞች ነፃ ባወጧቸው አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብም ገበሬው እንዲያርስና እንዲያመርት፣ ነጋዴውም እንዲነግድ፣ ቀሳውስቱም ሰዓታትና ቅዳሴውን እንዳያጓድል፣ በሕዝቡ ላይ ምንም ዓይነት በደል እንዳይፈፀም ዳኞችን ሰይመው በበላይነት ይመሩ ነበር።
ደጃዝማች መንገሻ አስደናቂ የጦርና የደህንነት መረጃ አመራር ችሎታም ነበራቸው። የጠላትን እንቅስቃሴ ከውስጥ የሚያወጡና ከውጭ የሚጠቁሙ የመረጃ ሰዎች የሚገናኙባቸው ምስጢራዊ የግንኙነት መዋቅር ዘርግተውም ከመሪ አርበኞች ጋር ይገናኙ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ጉታ ገበርማ›› በተባለው ቦታ ከጠላት እጅ የተማረኩ መገናኛዎችንና የመልዕክት ማስተላለፊያ መስመሮችን አገናኝተው አቶ ጊላ ወልደ ጊዮርጊስ (በኋላ ደጃዝማች) በሚባል ብልህ ሰው የሚመራ የስለላና የፕሮፖጋንዳ ኮሚቴ አቋቁመው ነበር፡። በእነዚህ የመገናኛ መሳሪያዎችም የጠላትን እንቅስቃሴ ማዳመጥና የጠላትን የምልክት መገናኛ ኮዶችን መጥለፍ ተችሎ ነበር።
ደጃዝማች መንገሻ በሰላሙ ጊዜ ሩህሩህና ደግ አስተዳዳሪ የመሆናቸውን ያህል በጦርነት ጊዜ ደግሞ ቆራጥ የጦር መሪ እንደነበሩ ታሪካቸው ይመሰክራል። በውጊያ ወቅት የሚያሳዩት ቅልጥፍናና ቆራጥነት የተዋጊ አርበኞቻቸውን ወኔ ከፍ የሚያደርግና በቁጥርም ሆነ በጦር መሳሪያ ብልጫ ያለውን የፋሺስትን ሰራዊት ድል በማድረግ ምርኮ የሚያስቆጥሩ ጀግና የጦር መሪ እንደነበሩ ተደጋግሞ ተመስክሮላቸዋል።
ብልሃትም ሌላው መለያቸው ነበር። በአንድ ወቅት በባሕር ዳር አካባቢ በወራሪው ኃይል ተማርከው የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ከጠላት መንጋጋ መውጣት መቻላቸውን ታሪካቸው ያስረዳል። ከባህር ዳር ከተማ እንዳይለቁ ተብለው የቁም እስረኛ ተደርገው በነበረበት ወቅት የሰከላ፣ የፋግታ፣ የሜጫ፣ የአገው ምድርና የአቸፈር ሕዝብ በምስጢር እየተሰበሰበ የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር ለማጥቃት ይነጋገር ነበር። ሕዝቡም ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬን የጦር መሪ እንዲሆኑ ወሰነ። ጉዳዩ ለደጃዝማች መንገሻ ተነገራቸው። ደጃዝማች መንገሻም በሀሳቡ ተስማምተው በዘዴ አምልጠው ከወጡ በኋላ ሕዝቡን አስተባብረው በፋሺስት ላይ ሸፈቱ።
ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ወቅት ከ40ሺ በላይ አርበኛ በመምራት ባደረጉት ተጋድሎ በበርካታ (ከ30 በላይ) ቦታዎች ከፋሺስት ጦር ጋር ተዋግተው አኩሪ ድሎችን አስመዝግበዋል። እነዚህ ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለባቸውና አስደናቂ የጀግንነት ጀብዶች የተፈፀመባቸው ውጊያዎች የእነደጃዝማች መንገሻና አርበኞቻቸው የአገር ፍቅር ስሜትና ጀግንነት በተግባር የተገለጠባቸው አኩሪ የታሪክ አሻራዎች ናቸው።
በሰኔ ወር 1932 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር ጣሊያን ከናዚ ጀርመን ጋር ማበሩን ተከትሎ የእንግሊዝ መንግሥት በነበረው የስዊዝ ቦይ ላይ የሚተላለፉ የኢጣሊያ መርከቦች ስንቅ፣ ትጥቅ፣ ሰራዊትና ነዳጅ ጭነው እንዳያልፉ ከለከለ። ይህ የእንግሊዝ እርምጃ የኢትዮጵያን አርበኞች በማበረታትና የፋሺስቶችን አቅም በማዳከም ረገድ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አበርክቷል። እናም ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ መሪነት ባደረጓቸው አኩሪ ተጋድሎዎች አማካኝነት በርካታ የጎጃም አካባቢዎች ከወራሪው ጦር ነፃ መውጣት ቻሉ።
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያዊያን አርበኞች ትግል ክፉኛ ተዳክሞ በነበረበት ወቅት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከሱዳን ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንደ ጀመሩ የጠላት ኃይል በቡሬ ከተማ በተጠናከረ ሁኔታ ምሽግ ሰርቶ ጠበቃቸው። ይህ የጠላት ኃይል መወገድ ነበረበትና ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ ከዳሞቱ መስፍን ደጃዝማች ነጋሽ በዛብህ ጋር ተቀናጅተው በማጥቃት የጠላት ጦር ቡሬን ለቅቆ እንዲወጣ አደረጉት። በመቀጠልም የፋሺስት ኃይል ሙሉ ጎጃምን ለቅቆ ለመውጣት ተገደደ። ንጉሰ ነገሥቱም በደብረ ማርቆስ በኩል አድርገው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ።
ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬም በቢትወደድነት ማዕረግ በጎጃም እንደራሴነት በማገልገል ላይ ሳሉ በ1937 ዓ.ም ወደ ሸዋ፣ አዲስ አበባ ተዛውረው በህግ መወሰኛው ምክር ቤት እንደራሴነት እስከ 1938 ዓ.ም ድረስ ካገለገሉ በኋላ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ።
ደጃዝማች ቢትወደድ መንገሻ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉ በሰሜኑ ግንባር በሽሬው ጦርነት በቦንብ ፍንጣሪ የቆሰለው አካላቸው ቁስሉ እያመረቀዘ ሲያሰቃያቸው ቆይቶ በእረፍት እጦት ምክንያት በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው በ1942 ዓ.ም አረፉ። ስርዓተ ቀብራቸውም በከፍተኛ ክብር በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስተ ማርያም ካቴድራል ተፈፅሟል። ደጃዝማች ቢትወደድ መንገሻ ዳንግላ ከተማ ውስጥ በስማቸው ትምህርት ቤት ተሰይሞላቸዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2014