ልጆች እንዴት ናችሁ፡፡ ትምህርትስ እንዴት ነው። እየተማራችሁ ነው? በደንብ እያጠናችሁ ነው? ጎበዞች! በደንብ ካጠናችሁ ጥሩ ውጤት ታመጣላችሁ፡፡ ጥሩ ውጤት ያመጣ ተማሪ ደግሞ ወደሚቀጥለው የክፍል ደረጃ ይሸጋገራል፡፡
ልጆች ለመሆኑ በትምህርት ቤት ከምታገኙት እውቀት በተጨማሪ ከወላጆቻችሁ የምታገኙት እውቀትና ምክር ለወደፊት ሕይወታችሁ መቃናት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውስ ታውቃላችሁ? አዎ! ወላጆቻችሁ ከትምህርት ቤት መምህሮቻችሁ ባልተናነሰ ያላቸውን ልምድና እውቀት ለእናንተ በማካፈል ተጨማሪ እውቀት እንድታገኙ ያግዟችኋል፡፡ በተለይ ደግሞ የተሟላ ሰብእናን ተላብሳችሁና በመልካም ስነ ምግባር ታንጻችሁ እንድታድጉ የወላጆቻቸሁ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡
ታዲያ ወላጆቻችሁ እናንተ ልጆቻቸው በመልካም ስነ-ምግባር፣ ስብእናና ስነልቦና ታንፃችሁ እንድታድጉ የሚያደርጉት አንድም ከሃይማኖታቸው በቀሰሙት ትምህርት ሁለትም ከሕይወት ልምዳቸው ወይም ፈጣሪያቸው ከሰጣቸው ፀጋ በመነሳት ነው። አንዳንድ ወላጆች ደግሞ የተማሩ ከሆኑ በሕይወት ዘመናቸው ያካባቱትን እውቀት ተጠቅመው እናንተን ይቀርፃሉ፡፡
ልጆች! እናንተ ሙሉ ስብእና እንዲኖራችሁና እድገታችሁም የተሟላ እንዲሆን ብሎም ሙሉ ችሎታችሁን እንድትጠቀሙበት ገና ከፅንስ ጀምሮ እርዳታውና ክትትሉ ያስፈልጋችኋል፡፡ የዚህ እድገት ወሳኞቹና ትልቁን አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ደግሞ ወላጆቻችሁ፣ አሳዳጊዎቻችሁና ከእናንተ ጋር ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች ናቸው፡፡
ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የአኗኗር ዘይቤውና ሕይወት እየተቀየረ በመምጣቱና ዓለም ወደ ዲጂታል ዘመን እየተቀየረች በመምጣቷ ወላጆቻችሁ ከዚህ ጋር በሚሄዱ ክሂሎቶች ራሳቸውን ማብቃት ይኖርባቸዋል፡፡ እናንተ የተሟላ ስብእና ይዛችሁ እንድታድጉ በልጆቻቸው አስተዳደግ ዙሪያ ተጨማሪ እውቀት ያስፈልጋቸዋል፡፡
ዊዝኪድስ ዎርክሾፕ ሶሻል ኢንተርፕርይዝ የተሰኘውና ‹‹ፀሐይ መማር ትወዳለች›› በሚለው የቴሌቪዥን ፕሮግራም የሚታወቀው ድርጅት ደግሞ በቅርቡ ወላጆች በኢንትርኔት አማካኝነት በልጆቻቸው ስብእና ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚቀስሙበትን መንገድ አመቻችቷል።
ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በተለይ ደግሞ ከአእምሮ ሊሂቃኖች፣ ከስነ ልቦና ባለሙያዎች፣ ከመምህራን ጋር በመሆን ለወላጆች በጥናት ላይ የተመረኮዙ ኮርሶች በኢንተርኔት አማካኝነት ይሰጣል፡፡ ወላጆችም በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የልጆቻቸውን በራስ መተማመንና የስሜት ክሂሎት ለማሳደግ የሚያስችሏቸውን ክሂሎቶች ያገኙበታል፡፡
በዋናነት ፕሮግራሙ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸው በተለያዩ የእድገት ደረጃዎች ምን አይነት ስሜቶችን እንደሚያሳዩ፣ እንዴትስ እነሱን መርዳት እንደሚችሉ፣ ምን አይነት ስነ ልቦና እንዳላቸውና ይህንንም እንዴት ማበልፀግ እንደሚችሉ፣ ምን አይነት አካላዊ እድገት እንደሚያመጡና ከነዚሁ ጋር በተያያዙ ያሉ መረጃዎችን በህፃናት ሀኪሞች፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎችና የአእምሮ ሀኪሞች አማካኝነት በአጭሩ የሚያገኙበት ነው፡፡
እናንተም ልጆች ወላጆቻችሁ የወላጅነት ትምህርት ፕሮግራሙን ለመከታተል እንዲችሉ በቅድሚያ http:// www.t4f.et በተሰኘው የድርጅቱ ድረ ገፅ ውስጥ ገብተው
እንዲመዘገቡ ንገሯቸው፡፡ በመቀጠልም የመረጡትን የልጆች ሰብእና ለመገንባት የሚያስችላቸውን ነፃ የክሂ ሎት ኮርሶችን መከታተል እንደሚችሉ ይጠቁ ሟቸው። ከ200 ብር ጀምሮ በመክፈል መከታተል የሚፈልጓቸው የሕይወት ክሂሎት ኮርሶችም በድረ-ገፁ ላይ እንደሚያገኙ ግለፁላቸው፡፡
ይህን ካደረጋችሁ ልጆች ወላጆቻችሁ በሁለንተናዊ የልጆች ስብእና ግንባታ ዙሪያ የተሟላ ክሂሎት ስለሚኖራቸው እናንተን በዚህ መንገድ ቀርፆ ለማሳደግ አይቸገሩም፡፡ እናንተም በመልካም ስብእናና ስነ ምግባር ታንፃችሁ በማደግ አገራችሁ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ነገ ታሻግራላችሁ፡፡ መልካም እለተ ሰንበት!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2014