በገጠሩ የአገራችን ክፍል ዛሬም ድረስ የዘለቀ የማህበራዊ ሕይወታችን ማሳያዎች መካከል ቡናን እየተጠራሩ አብሮ የመጠጣት ባህላችን ይገኝበታል። ተከታታይ ፊልም እያዩ እቤት ውስጥ ከመቀመጥ ተራበተራ እየዞሮ ከጎረቤት ጋር ቡና መጠጣት ከፍያለ ትርጉም መሆኑን የሚያሳይ ባህል። በየቀኑ አብሮ ከጎረቤት ጋር ቡና የሚጠጣበት፤ አብሮ የሚኖርበት መድረክ። በየጊዜው በመድረኩ ላይ ብዙ ሃሳቦች ተነስተው ይጣላሉ።
ሰዎች ለውሳኔ የሚረዳቸውን ምክር ይቀያየራሉ፤ የፈራው እንዲበረታ፣ የተሳሳተውን ለማረቅ የሚሆን ምክር ከአንዱ ወደሌላው ይተላለፋል። በብዙ ጉዳዮች ላይ የመረጃ ልውውጥም ይደረጋል። በአጭሩ አብሮነት ትርጉም የሚሰጥበት ስፍራ ልንለውም እንችላለን። በየሰፈሩ ካሉ የጎረቤታሞች መድረኮች ወደ አንዱ ዛሬ ጎራ ብለን ከሚለዋወጡት የሃሳብ መዓድ ለራሳችን የሚጠቅመንን ለመውሰድ አስበናል። የውይይታቸው መነሻ ግብጽ ስትሆን መዳረሻቸው ደግሞ ኢትዮጵያ ያካደረጉ ጎረቤታሞች።
‘ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የነደፈችው፤ ኢትዮጵያን በብዙ አቅጣጫ አዳክሞ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት እንዳይሳካ የማድረግ ውጥን አለ’ በሚል ውይይት ተጀምሮ የጦፈ ክርክር ላይ ደርሷል። የክርክሩ ተካፋይ የሆነ አንዱ ጎልማሳ ሃሳብ በቁጭት እየሰጠ ነው፤ «ግብጽ ይህን ሁሉ ነገር በአዙሪት ለማድረግ ከምትሄድ ለምን በአጭሩ ጦርነት አትገጥመንም? ኢትዮጵያ እስከመቼ ድረስ የግብጽ ሰለባ ሆና ትኖራለች? በቃ ጦር ተማዘን ይለይልን፤ የምን ፈራተባ ነው!» አለ።
የጎልማሳውን ሃሳብ ተከትሎ ሌሎች ጎረቤታሞችም የየራሳቸውን መስነዘር ቀጠሉ። «ምን ሆነሃል፤ ግብጽ ቀጥተኛ ጦርነት ምን ያደርግላታል? እኛን እርስበእርስ እንድንባላ ካደረገች እኛ የእርሷን ጦርነት እየተዋጋን ስለሆነ ለምን ጠመንጃ መዛ ዜጓቿን ታስጨርስ? እኛ ነን እንጂ የእርሷ መጠቀሚያ ስንሆን ቆመን መመልከት ያልቻልነው» ሲል በቁጭት ተናገረ።
ሌላይቱ የቡናው ህብረት ተካፋይ የሆነች የልጆች እናትም ቀጠል አድርጋ «እኔ የማይገባኝ ነገር እውን በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ከሌላ አገር ጋር ጦርነት ውስጥ ብትገባ ከዚህ ቀደም ጣሊያንን በተዋጋንበት ወኔ የምንዋጋ ይመስላችኋል? አሁን ይህ ወጣት ወኔ ኖሮት የውጭ ወራሪ ኃይልን መመለስ ይችላል? እርስ በእርሳችን ለመጨራረስ ካልሆነ እንደው ማን ይሙት ተደራጅቶ የሚመጣን የውጭ ኃይል ለመመከት የሚያስችል አቅም አለን? በተለይ የወኔ አቅም፤ የአገር መውደድ አቅም።
ያሰቡትን ካላሳካሁ እምቢ የሚያስብል አቅም፤ በግለት ውስጥ ሆኖ ለመስዋዕትነት የመቅረብ አቅም። ይቅርታ አድርጉልኝና አይደለም ለጦርነት የሰፈራችንን ጽዳት ለመጠበቅ የሚያስችል ወኔ የለንም» አለች። የቡና መድረኩ ክርክር ከግብጽ ተነስቶ ስለ «ወኔ» ሆነ። ቡና የማቀበሉን ኃላፊነት ወስዳ ቡና እያቀረበች ያለች ታዳጊ የአስራሁለት አመት የስድስተኛ ክፍል ተማሪዋ ስለ ወኔ የተነገረው ውስጧን ከነከነው። በትምህርት ቤት የተማረችው ኢትዮጵያውያን የውጭ ወራሪ ኃይልን መክተው መመለሰቸውን፤ ጣሊያንን ማንበርከካቸውን፤ ዓድዋ የነፃነታቸው ምልክት አድርገው መኖራቸውን ወዘተ።
ዛሬ በቡናው መድረክ ላይ የሚሰማው ነገርግን ትናንት የተማረችው ተረትተረት የሆነ መሰላት። በትናንት እና በዛሬ መካከል ግጭት በውስጧ ተፈጠረባት። ነገ መምህሯን ለመጠየቅ ራሷን አዘጋጀች። ወኔ ስለከዳው ትውልድ፤ እርስበእርሱ እየተባላ እንደሆነ ክስ ስለሚቀርብበት ትውልድ ጠይቃ ትናንትንና ዛሬን ለማስታረቅ አሰበች። በወኔ እርስበእርስ ለመጣላት ምክንያት የሚፈልግ፤ በወኔ ግን አንዳች ቁምነገር መሥራት አይችልም የተባለው ትውልድ አካል በመሆኗም ቅሬታ ተሰማት። በውስጧ ያለው ህልም አንዳች ቁምነገር መሥራት ነውና።
ወኔ፤
ዛሬ ስለ ወኔ እናንሳ። ወኔ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ያሰበውን ለማሳካት በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ አቅም የሚሰጥ ኃይል አድርገን ልንተረጉመው እንችላለን። አነቃቂው ቡና እና የአካባቢ ሰዎች የሚፈጥሩት መነቃቃት በወኔ ብዙ ነገሮች እንዲሉ አድርጓቸዋል። ከቡናም ሆነ ከሌሎች አነቃቂ ነገሮች ባሻገር በራዕይ በኩል አድርጎ የሚፈጠረው ወኔ ያለውን ፋይዳ እያሰብን ስለ ወኔ ነጥቦችን እናነሳለን።
አስቀድመን ዙሪያችን ብንቃኝ ሁለት ሰዎችን እናገኛለን። ወኔ ያላቸው እና ከወኔ የተፋቱ ሰዎች። ሁልጊዜ ችግርን የሚያወሩ የወይኔ ሰዎችና ለመፍትሔ የሚኖሩ በወኔ የሚነሱ ሰዎች። ዛሬ እንደ ማህበረሰብ ለውጥ የምንፈልግባቸው አንድ ሺ አንድ ጉዳዮች ቢኖሩንም ይህን ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ወኔ ያላቸው ሰዎችን መቁጠር ብንጀምር ግን የምንቆመው ብዙም ሳንርቅ መሆኑን ማሰብ አይከብድም። «ትውልዱ ወኔው የተሰለበ ነው» የሚለውን ክስ በጥሞና ብናስበው ሁላችንንም የሚመለከት መሆኑ እርግጥ ነው።
ማናችን ስለማን አስተያየት እየሰጠን እንደሆነ ግልጽ ስለሆነ። ራሳችን ስለራሳችን እንደ ትውልድ መሆኑ ሊጠፋን ስለማይችል፤ ወይንም ሊጠፋን ስለማይገባ። ትውልዱ በለውጥ መንፈስ ተነሳስቶ አካባቢውን ቀይሮ፤ በድምሩ አገሩን ወደ ተሻለ አቅጣጫ አስገብቶ ማየትን ህልም ያደረገ ሰው በትውልዱ መክሰር ብዙ ቢል ሊፈረድበት አይችልም።
ከግለሰብ እስከ …፤
ወኔን ከግለሰብ ጀምሮ እንዲኖር ማስቻል የተገባ መሆኑን እንረዳለን። የውስጥ መነቃቃትና ያሰቡትን ለመፈጸም የሚያደርግ ኃይል ስለሆነ በግለሰብ ደረጃ ካልተገኘ ከግለሰብ በላይ ባለ የትኛውም ስብስብ ሊገኝ አይችልም። እንደግለሰብ በውትድርና ውስጥ ያለፉ ሰዎች ወኔያቸው ከሌላው ማህበረሰብ የተለየ ሆኖ መገኘት ወኔን በግለሰብ ደረጃ ለማምጣት የሚያስፈልገውን ሥራ በግልጽ ያሳያልና። ወታደሩም በወታደርነት ከመጠቀሱ በፊት እንደ ማንኛውም ተራ የማህበረሰቡ አባላት መካከል ስለነበረ።
ውትድርና ያለ ወኔ የሚታሰብ ባለመሆኑ በውትድርና ሳይንሱ አማካኝነት ሊሰጠው የሚገባ ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራበታል። ምክንያቱም ውትድርና በቀጥታ ከሞት ጋር መገናኘትን የሚጠይቅ ስለሆነ፤ ሞትን መድፈር ደግሞ ያለወኔ ሊታሰብ የሚችል ባለመሆኑ። ጠንካራ ወኔ ያለው ብዙ የታጠቀውን ትጥቅ ማስፈታት የሚያስችል አቅም ኖሮት በጦርነት ታሪኮች ውስጥ ተጽፎ ስለሚገኝ።
በመሆኑም በጦርነት ውስጥ በወኔ የደረጁ ጀግኖችን ማየት ቀላል ነገር ነው፤ ምክንያቱም ሥራው የሚጠይቀው በመሆኑ በየቀኑ የሚሠራበት ሥራ በመኖሩ። በውትድርናው በጀግንነት የሚጠቀሱትን ያህል ግን በንግድ፣ በመንግሥት ሥራ ውስጥ እንዲሁም በሌሎች እንቅስቃሴዎች ውስጥ በወኔ የሆኑ ሰዎችን ማግኘት ቀላል ሥራ አይደለም። በአንድ ድርጅት ውስጥ መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት የሚደረግን ሥራ በምናይበት ጊዜ የመጣው ለውጥ በመሪው በወኔና ድፍረት የተሞላ ውሳኔ ውጤት መሆኑን እንረዳለን። የመሪነት የሥራ መደብ ለመሪው ድፍረትን አይሰጥም ነገርግን ድፍረት ለመሪው የመሪነት የሥራ መደብን ያሰጠዋል እንጂ።
ከግለሰብ እስከ አደባባይ ወኔ ያለው ትርጉም ትልቅ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው። አንባቢ ሆይ፤ ሕይወትህን በተበረታታ፣ በተነቃቃና በወኔ እየመራህ ነው? ካልሆነ ለምን ብለህ ጠይቅ? ሥራህም ሆነ ማህበረሰባዊ አገልግሎትህንም እንደእዚያው።
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በርካታ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ወደ ውጤት የማይመጡበትን ምክንያት ስንፈትሽ ልንዘረዝረው የምንችለው ብዙ ነገር ቢኖርም የወኔ መጉደል የራሱ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል ግን ሊካድ አይችልም። ሰዎችን በፍቅር የማገልገል ወኔ የሌለው ሰው በትንሽ ነገር ሰውን ወደ ማመናጨቅ ሊገባ ይችላል። ትልቅ ህልም ያለው ሰው ህልሙን እውን ለማድረግ የሚያስችል ወኔ ከሌለው እንዲሁ መዳረሻው የሃሳብ ዝርዝር ብቻም ይሆናል።
ስለሆነም ወኔ ያለውን ቦታ በአግባቡ ተረድተን ስለ ወኔ የምናነሳቸውን ነጥቦች አንባቢው ለትምህርቱ እንዲሆነው አንድ ብለን እንጀምር። ጥቂት ነጥቦችን በወኔ እናቀርባለን፤ አንባቢው በወኔ አንብቦ አብሮን “በወኔ፤ ከወኔ” ይበል።
- የወኔ መገኛው ስፍራ የትነው? ግቡስ?
ወኔ የት እንደሚገኝ ጠይቅና ምላሽ አግኝ። ወኔ ከውጫዊ ሰውነትህ ላይ ቢፈለግ አይገኝ። ወኔ በውጫዊ አካልህ ላይ በተለያዩ መንገዶች የሚገለጥ ሊሆን ይችላል እንጂ በተጨባጭ ያለው ግን በውስጥህ ነው።
እንደ መሪ የምትጋፈጠው ማንኛውም ፈተና የሚጀምረው ከውስጥህ ነውና በውስጥ ወኔ ሊፈጠርም ሆነ ሊሞት እንደሚችል መረዳቱ ይኑርህ። ወኔህን የሚፈትነውም ፈተና ከእዚህ የተለየም አይደለም። ፈተና ሲመጣ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ተስፋን መንጠቅ፤ ወኔን መስለብ፤ ጽናትን መሸርሸር ነው። የሳይኮቴራፒስት ባለሙያ የሆነው ሼልደን ኮፕ የተባለው ሰው ሁሉም ከባድ የሚባሉ ጦርነቶች ክፍያቸው ከውስጥ ነው ብሎ መናገሩ ለዚህም ይመስላል። ከውስጥ የሚሆን ከፍያ! የወኔን ግብ ስናስብ ፍርሃትን እናነሳለን።
በወኔ የምትጋፈጠውን ነገር እንዳትጋፈጥ ፊትአውራሪ ሆኖ የሚመጣው ፍርሃት ስለሆነ። ወኔ ማለት የፍርሃት አለመኖር ማለት አይደለም፤ ነገርግን የምትፈራውን ነገር ማድረግ ማለት ነው። ስለፈራህ ወኔ የለህም ማለት አይደለም፤ የፈራኸውን በማድረግ ውስጥ ወኔህ ሥራውን ይሠራል ማለት እንጂ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ ሲል አወጀ ትልቁ የሰው ልጆች መለኪያ በምቾት ጊዜ የሚገኙበት አቋም ሳይሆን በተግዳሮትና ግራአጋቢ ወቅቶች የሚቆሙበት ስፍራ ነው።
እያልን ያለነው አሁን ግልጽ ነው፤ በጣም ግለጽ። ወኔ ግብ ልታደርግ የሚገባህን ነገር ማለትም ፍርሃትን አውልቀህ ጥለህ ማድረግ እንድትችል የሚያደርግ መሆኑን የሚያስረዳ። ግራአጋቢ በሆኑ ወቅቶች ማድረግ ያለብንን ከማድረግ እንዳንመለስ የሚያደርግ ኃይል መሆኑን የሚገልጽ።
ወኔ የሚመራው በመርህ እንጂ በይሆናል አይደለምና ከመከራው ባሻገር የሚቃኝበት ቅኝት አለው። ስለምን ጉዳይ ምን አቋም መያዝ እንዳለብህና አቋምህን እንዴት እንደምታራምድ ማሰብ እንድትችል ልትሆን ይገባል። ስለምን ጉዳይ አቋም ይዘህ እንደምትቆም የማታውቅ ከሆነ ውጤታማ ሰው ልትሆን አትችልም። ሕይወት በአቋም የምትኖርለት ነገር ውስጥ የምትደምቅ በመሆኑ። በጽናት ስለምትቆምበት ነገር የሚኖርህ መሰጠት በሌሎች ፊት ጠንካራ ሆነህ የምትሳልበትን አቅም የሚጨምር ነው። ለዚህ ደግሞ ወኔ የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው። ወኔ በግለሰብ ደረጃ ታጥሮ የሚቀመጥም ሳይሆን የሚባዛም የሆነ ለእዚሁ ነው። 2. የወኔ ብዜት ስለ ወኔ ማሰብ ያለብን ሌላኛው ነጥብ
ወኔ የሚባዛ መሆኑን የሚያስረዳ ነው። ወኔ ይባዛል፤ ከአንዱ ወደሌላው። የአበበ በቂላ በባዶ እግር ሮጦ አሸናፊ መሆን በአገራችን አትሌቲክስ ላይ ያለው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ማራቶንን በባዶ እግር ሮጦ ለመጨረስ መወሰን የሚፈልገው ውሳኔ በወኔ ውስጥ ብቻ ካልሆነ በምን ሊገኝ ይችላል? ወኔ ከአንድ ሰው ወደሌላ ሰው፤ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ የሚዘዋወርነው።
ወንጌላዊ ቢል ግራም እንደተናገሩት ወኔ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍ ነው። በአንድ ሰው ላይ የሚታይ ወኔ በሌሎች ላይ ያለውን ያበረታታል። በመሪዎች ላይ የሚታይ ወኔ ተከታዮችን ያነቃቃል፤ ሰዎችም መሪያቸውን እንዲከተሉም ያነሳሳቸዋል።
አብዛኛው ሰው በሕይወቱ ውስጥ ቦታ ካላቸው ሰዎች ጋር መሞጋገት እምብዛም አይፈልግም ማለትም ከሠራተኛ፣ የሥራ ባልደረባ፣ ቤተሰብ ወዘተ ጋር። ነገርግን መጋፈጥ ባለብህ ቦታ ስትጋፈጥ ለእውነት፤ ለመርህ፤ ለሕግ የሚገዙ ሰዎችን እያበዛህ ነው፤ ወኔ የሚባዛ ስለሆነ። ይህ በአንተ ሕይወት ውስጥ እውነት ከሆነ ያመለጡህን በወኔ ያልተመለከትካቸውን ነገሮች ቁጠርና ዛሬ ስለመፍትሔው ተነሳ።
3. ወኔ በሕይወታችን ውስጥ ምንያህል ይለካል?
ወኔ በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ድርሻ ለክተን በቁጥር ማስቀመጥ ብንችል ምንኛ ዕድለኛ በሆን ነበር። ያንን ማድረግ ባንችልም ማሰብ ግን የምንችልባቸው ቀዳዳዎች አሉ። ስለ ሕይወትህ ምን ያህል የተነሳሳህ ነህ? በሥራ ቦታ፤ በቤተሰብ ውስጥ፤ በግል ሕይወትህ ወዘተ ውስጥ ያለውን መነሳሳት መነሻ በመፈተሽ ምላሽ መፈለግ ይቻላል። ምናልባትም የሥራ ባልደረቦችህን እና የትዳር አጋርህን በመጠየቅ ወደ ምላሹ መቅረብ ይቻላል።
በእኔ እምነት ግን ነገሮችን በወኔ ማድረግ በሕይወታችን ያሰቡትን ማሳካት ግማሽ መንገድ ነው። በእያንዳንዱ ሰው ጉዞ ውስጥ ተጽእኗቸው ከፍተኛ የሆኑ ብዙ ነገሮች መኖራቸው ባይካድም ወኔ ግን ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው። ፍርሃት የሰውን ጉዞ እርቀት የመወሰን አቅሙ ለውይይት አይቀርብም። ወኔ ፍርሃትን ገፎ ያሰቡትን ለማሳካት አስቸጋሪ የሆነውን መንገድ ደልዳላ ያደርጋል።
የሮማን የታሪክ አዋቂ እንደጻፈው ምቾትን የመጠበቅ መሻት የታላቅና ምርጥ ድርጅቶች ፈተና ነው። ነገርግን ወኔ ያለው ተጽእኖ በተቃራኒው ነው፤ በርን የሚከፍት እናም ዋናውን ምርጥ ጥቅምን የሚያመጣ፡ በማለት ይገልጻል። ወኔ በሕይወታችን ውስጥ ያለው ልኬት የሕይወታችን ጉዞ መወሰን የመቻል ያህል ነው ብለን ምላሽ ብንሰጥ አንሳሳትም። ወኔ መልካም ጅማሬን ብቻ ሳይሆን የተሻለ ነገንም የሚሰጥ ነው።
መልካም ጅማሮን የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ነገርግን እንደጅማሬያቸው ነገዎቻቸው ሳይሆኑ የሚቀሩ። ምክንያት ከተባለ የሚገኘው መልስ የወኔ ማነስ ሆኖ ስለሚገኝ። አንባቢ ሆይ በወኔ ለማደግ ካለህበት ሁኔታ ወጥተህ ለመዘርጋት ሞክር። ብዙ ሰዎች ለማድረግ የሚፈሩትን በሰዎች ፊት ቀርበህ ንግግር አድርግ። የምትሠራው ሥራ ምንም ይሁን ምን ፍርሃትን የሚፈጥር ነገር መጋፈጥህ ነውና ዋናው ነገር አድርገው። ወደ አዲስ የሥራ ሕይወት ለማምራት ፍርሃት ሊሰማህ ይችላል።
ሥራህን መተውና አዲስ የሥራ መስመር ውስጥ መግባት እንዳለብህ የምታምን ከሆነ አሁን የምትጋፈጥበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። በሚገባ በሁኔታው ላይ ለማሰብ ጊዜን ውሰድ። ከትዳር አጋርህ፣ ከግል-መካሪህ እናም ከታማኝ ጓደኛህ ወይንም ጓደኞችህ ጋር አውራበት። ይህን ማድረግ ትክክለኛው ተግባር ከሆነ አድርገው። በወኔ ነገርህን ብትፈጽም ወደ ድል ትደርሳለህ።
የምትከተላቸውን መሪዎች መከተል ከመጀመርህ በፊት ከወኔ አንጻር ገምግማቸው። በወኔ የራስህን ሥራ መሥራት፤ ከወኔ አንጻር የምትከተለውን መወሰን። መዳረሻህ በሕይወትህ ያሰብከውን አሳክቶ ማለፍ ስለሆነ ወኔ ትክክለኛው መነጽር ነው። ዛሬም በወኔ፤ ከወኔ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014