የጫኝና አውራጅ ሥራ ለጫኝ አውራጆችም ለመንገደኞችም ጥሩ ነገር ነው። ለጫኝና አውራጆች ሥራ ነው፤ ገቢ ያገኙበታል። ለመንገደኞች ደግሞ መያዝ የማይችሉትን ዕቃ የሚያስይዙበትና የቱን ይዤ የቱን ልተወው ከማለት የሚወጡበት ነው። መጫንና ማውረድ ሥራና የበርካታ ዜጎች የኑሮ መሠረትም ነው።
የጫኝና አውራጅ ሥራ በአብዛኛው በመናኸሪያዎች፣ በእህልና መሰል በረንዳዎች በስፋት ይሠራል። በመሠረቱ ዕቃን ከመኪና ማውረድና ማውጣትን ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊከውነው አይችልም። የተጓዦችን ዕቃ መጫንና ማውረድ፣ እህል፣ ሲሚንቶ፣ ወዘተም ካለ ጭኝና አውራጅ ሊሆኑ አይችሉም። ሥራዎቹ በዚህ ሥራ የተሠማሩ ሰዎችን ይፈልጋሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ሥራው እየተስፋፋ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከተማ የማስፋፊያ ስፍራዎች በተለይም እንደ ኮንዶሚኒየም ባሉ መንደሮች ተስፋፍቷል።
ይሁንና ጫኝና አውራጆች የሚጠይቋቸው የተጋነኑ ክፍያዎች፣ ሳይፈቀድላቸው ወይም በዋጋ ሳይግባቡ የንብረት ባለቤቶች ሳይፈልጉ እኛ ነን ማውረድም መጫንም ያለብን እያሉ የሚሉበት ሁኔታ ከባለንብረቶች ጋር አለመግባባት እንዲከሰት ከማድረጋቸውም በላይ ለግጭትም ሲዳርግ የሚችል ሁኔታ እየፈጠረ ነው የሚሉ ጥቆማዎች ይደመጣሉ። ወንጀሎች እየተፈጸሙ ስለመሆናቸውም መረጃዎች ያመለክታሉ። አሁንም በጫኝ አውራጆች ላይ ሮሮዎች በርክተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የማስፋፊያ መንደሮች በተለይም በኮንዶሚኒየሞች አካባቢ ወጣቶች ተደራጅተው ይህን ሥራ እንሠራለን በሚሉ ወገኖች፣ ዝርፊያ በሚመስል መልኩ እየተፈጸመ ያለው የክፍያ ጥያቄና ውዝግብም በእጅጉ ያሳስባል።
ይህን ሁኔታ ለማብራራት ከሁለት ዓመት በፊት ያስተዋልኩትን አንድ ገጠመኝ እጠቅሳለሁ። በ2012 ኅዳር ይሁን ታኅሣሥ ወር አካባቢ ነው። አንድ ጓደኛዬ ቱሉዲምቱ አካባቢ ወደ ተከራየው ጋራ መኖሪያ ቤት አካባቢ ሄድን። አካባቢው ገና እየደርስን እያለ ከ10 የማያንሱ ወጣቶች መኪናው ግርርር ብለው ሰፈሩበት። መኪናው ቦታው ደርሶ እንደቆመም ከባለንብረቱ ጋር ገና ንግግር ሳይጀመር ወጣቶቹ ጭነቱን መፍታት ጀመሩ። እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሞኝ ስለማያውቅ የአካባቢው ሰዎች ለትብብር የመጡ መስሎኝ በቅንነታቸው ተገርሜም ነበር።
ጓደኛዬ አሠራሩን ስለሚያውቅ ከማውረዳቸው በፊት ዋጋ ለመደራደር ማባበል ጀመረ። ጫኝና አውራጅ መሆናቸውን ሳውቅ ‹‹እኛው እናወርደዋለን፤ አያስፈልግም!›› አልኩ። እውነት ለመናገር አብዛኛውን ዕቃ በእኛው አቅም ሊወርድ የሚችል ነበር። ለእዚህም ጭምር ነው እኛ ለምን አናወርደውም ያልኩት። በመንገድና በአንዳንድ ፕሮጀክቶች የራስ ኃይል የሚባል ነገር እንዳለ ታውቃላችሁ፤ ሌላ ተቋራጭ የማያስፈልግበትን ሁኔታ ለማመልከት። እኔ በራስ ኃይል ለማውረድ ነበር ፍላጎቴ። በቤተሰብ አቅም።
ለካ በዚያ አካባቢ ዕቃውን በጫኝና አውራጅ ማስወረድ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። ጓደኛዬም ግዴታ መሆኑን ስለሚያውቅ መደራደሩን ቀጠለ፤ የሚገርመው ድርድሩም በልመና ነው። የሚገርመው ነገር በዋጋ ሳይስማሙ ግማሽ ያህል የሚሆነው ዕቃ ወርዷል። የእነርሱ ጥያቄ ‹‹ቤቱን አሳየን!›› የሚል ብቻ ነው። እኔም ነገሩ ወዲያው ገባኝና የራሳቸው ጉዳይ ብዬ ዝም አልኩ። ሲጨቃጨቁ ቆይተው የሰጣቸውን ሰጥቷቸው ጉዳዩ ተቋጬ!
በኋላ በሚገባ ሲያስረዱኝ እኔ አጋጥሞኝ ስለማያውቅ እንጂ በየትኛውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ነዋሪው ቤት ቀይሮ ሲገባ እንደዚሁ ነው። ለካስ በየአካባቢው ይህንኑ ሥራ የሚጠባበቁ ወጣቶች አሉ።
ችግሩ ከዚህም በላይ የከፋ እየሆነ ነው። ቤት ተከራይተው ወደ ኮዶሚኒየም መንደር የሚገቡ ሰዎች ይህን ውዝግብና ዘረፋ በመስጋት በውድቅት ዕቃቸውን ከነበሩበት ቦታ ጭነው በውድቅት ወደ አዲሱ ቤት እስከ መግባት ደርሰውም እንደነበር አውቃለሁ። አሁን እሱም መቻሉን እንጃ።
ነገሩን ያስታወሰኝ ከትናንት በስቲያ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ጫኝና አውራጅን በተመለከተ ለሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የሰጡት መረጃ ነው። ምክትል ኮማንደሩ ‹‹ቁሳቁሶችን እኛ ብቻ ነን የምናወርደው፣ እኛ ብቻ ነን የምንጭነው›› ብለው በሰው ንብረት ራሳቸው ይወስናሉ። በሌላ በኩል ተመጣጣኝ ክፍያ አይጠይቁም፤ የሚያስማማና የሚያቀራርብ ክፍያ አይጠይቁም። የሚገርመው ደግሞ እርስበርስ የሚጣሉበት ሁኔታም አለ። በዚህ መሃል ንብረት ይወድማል፤ የአካል ጉዳት ይደርሳል። ምንም በማይመለከተው ሰው ላይ ጉዳት ይደርሳል። ባለቤቶችን ያስጨንቃሉ፤ ‹‹እኛ ካላወረድነው እናወድመዋለን›› እስከ ማለትም ይደርሳሉ ሲሉ ነበር ያብራሩት።
እንግዲህ ሰው በራሱ ንብረት ማዘዝ አልቻለም ማለት ነው። ይሄ ሥራ ሳይሆን ወደ ዘረፋነት የተጠጋ ነው። ‹‹እኛ ካላወረድነው እናወድመዋለን›› ማለት ከውንብድናና ዘረፋ አይተናነስም። ሰውየው ምናልባት የጠየቁትን ገንዘብ መክፈል የማይችል ከሆነስ።
የተጋነነ ዋጋ መጠየቃቸው ሌላው ቅሬታ ነው። ዕቃው ከተገዛበት ዋጋ በላይ ክፍያ የሚጠይቁም እንዳሉ ይነገራል። ይህ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል የከፋ እየሆነ እንደመጣ ያስገነዝባል። ይህን በግድ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ ባለቤቱም ቆሞ አይመለከትም፤ ‹‹እንዳትነኩ›› የሚል እልህ መጋባት ውስጥ ይገባል።
ኮማንደሩ በዚህ ጉዳይ ላይ በተሠሩ ወንጀሎች የታሰሩ፣ ጉዳያቸው በሕግ እየታየ ያሉ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ እንዲህ ዓይነት ጥፋቶችን ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ይሄ እርምጃ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ዕቃው የግድ ተሸካሚ የሚያስፈልገው ከሆነ እኮ እነሱን ከመጠቀም ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም። መጫንና ማውረድ የግድ ጫኝና አውራጆችን ይፈልጋል። በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ብዙ ወለሎችን መውጣት ሊኖር ስለሚችል ዕቃዎችን በቀላሉ ማውጣት የሚቻለው በእነዚህ ወገኖች ነው፤ ስለዚህ ጫኝና አውራጆች መፈለግ የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አስገዳጅም ነው። የሚያስፈልገው ወጣቶቹ ሥርዓት ይዘው የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ብቻ ነው።
ጫኝና አውራጆች ሊፈልግ የሚገባው ግን ባለቤቱ እንጂ በጫኝና አውራጅነት እንሠራለን የሚሉት ወጣቶች መሆን የለባቸውም። ወጣቶቹም ተሸካሚ የማያስፈልገውን ዕቃ ሁሉ ካልያዝን እያሉ መጣላት ለራሳቸውም ለሥራቸውም አይጠቅማቸውም።
ስለዚህ ሥራው በስምምነትና በተመጣጣኝ ዋጋ መሠራት አለበት። ሁለቱንም ወገኖች የሚጠቅመው ይኸው ነው። ካለበለዚያ ግጭት ሊከተል ይችላል፤ ግጭቱን የሚመነዝሩ ወገኖች ደግሞ ሌላ ግጭት የሚፈጥሩበት ዕድል ይፈጠራል። እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን ፖሊስ በቅርበት ሊከታተል ይገባዋል።
በነገራችን ላይ እነዚህ ጫኝና አውራጆች ከእዚህ ሥራቸው ውጪም መንግሥትና ሕዝብን እየጠቀሙም መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። በሕጋዊ መንገድ ቢሰሩ እና ጥሩ ለሰሩትም ምሥጋና እና ዕውቅና ቢሰጣቸው መልካም የሆኑ ጫኝና አውራጆችም አሉ። ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ለሸገር እንደገለጹት፤ ብዙ ሕገ ወጥ ዕቃዎች ሲዘዋወሩ በእነዚህ ጫኝና አውራጆች ጠቋሚነት ተይዘዋል። የጦር መሣሪያ ወደ ግለሰብ ቤት ሲገባ እና ከግለሰብ ቤት ሲወጣ የማወቅ ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችልም መገንዘብ ይገባል። በሕጋዊ መንገድ በኃላፊነት በሚያገለግሉት ጫኝና አውራጆች የጦር መሣሪያዎች ሲዘዋወሩ የተያዙበት ሁኔታም ለእዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህም የጫኝና አውራጅ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የሚያስረዳ ሌላ መረጃ ነው።
እናም ጫኝና አውራጆች ሥርዓት ይዘው እንዲሠሩ ማድረግ ላይ አተኩሮ መሥራት ያስፈልጋል። ሕጋዊ የሆኑ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው ጫኝና አውራጆች እንዳሉ ሁሉ አግባብ ባልሆነ መንገድ የሚሄዱ አሉና ከድርጊታቸው እንዲታረሙ ማድረግ ይገባል። የማይታረሙም ከሆነ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው።
ኅብረተሰቡ ከሕገወጦቹ ጫኝና አውራጆች መታደግ ይገባል፤ አሁን ሮሮው በዝቷልና። ኅብረተሰቡን በመታደግ አብዛኞቹን ጫኝና አውራጆችንና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረውን ይህን ሥራ መጠበቅም ይቻላል። ይህን ሥርዓት በማስያዝ በኩል ሥራውን የሚመራው መንግሥታዊ አካል ኃላፊነት አለበት። ፖሊስም ችግር ሲፈጠር ሪፖርት የሚደረግለት እንደመሆኑ ክትትሉን ማጥበቅ፤ የኅብረተሰቡን ቅሬታ አዳምጦ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014