በስፋት ሲነሱ ከነበሩ እና መገናኛ ብዙኃኑን አጨናንቀው ከከረሙ ጉዳዮች መካከል የሕዝብ የውይይት መድረክ ላይ ይነሱ የነበሩ አቤቱታዎች ተጠቃሾች ናቸው:: በሕዝቡ የተነሱ አቤቱታዎችን በማዳመጥ እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎች ካሉ ለመጠየቅ እና አሁንም ድረስ እየቀረቡ ባሉ ቅሬታዎች ዙሪያ ምን እየተሠራ ነው? በማለት አራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሞላ ንጉሥን ጠይቀን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል::
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ በከተማ ደረጃ ከተደረገው ውይይት በተጨማሪ በየክፍለ ከተማው እና በወረዳዎች ውይይት ተካሂዷል:: በዋናነት ተነሱ ብላችሁ የለያችኋቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ሞላ፡- እርግጥ ነው:: በስምንቱም ወረዳዎች እና በክፍለ ከተማ ደረጃ ውይይቶች ተካሂደዋል:: በውይይቶቹ ላይ የተነሱትን ጉዳዮች ለቅመን ይዘናል:: ወደ ሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች በማከፋፈል በዕቅድ ተይዞ እንዲሠራበት እያደረግን ነው::
አዲስ ዘመን፡- አገልግሎት አሰጣጥን በሚመለከት ሰፊ አቤቱታ ሲቀርብ ነበር:: ከመታወቂያ ጀምሮ አገልግሎት ለማግኘት ያለው ችግር በዝርዝር ሲገለፅ ሰንብቷል:: ለመሆኑ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ በቀረቡ አቤቱታዎች ዙሪያ ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ሞላ፡- በየመድረኩ የተነሱትን በየዓይነታቸው ለይተናል:: ከሰላም እና ፀጥታ ጋር ተያይዞ የተነሳውን፣ ከአመራር ብልሽት ጋር፤ ብቻ ሁሉንም ለይተን ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ተወያይተናል:: ጥያቄዎቹ ሊመለሱ የሚችሉት በዕቅድ ነው:: ከክፍሎቹ ጋር በመወያየት በዕቅድ መሠረት መመለስ ተጀምሯል:: በእኛ አካባቢ አንዱ ትልቁ ቅሬታ የሚቀርብበት በልማት የሚነሱ ሰዎችን የተመለከተ ጉዳይ ነው:: ለምሳሌ፣ የሸገር ቁጥር ሁለት የወንዝ ዳርቻ ላይ በሚነሱ ቤቶች ዙሪያ አቤቱታ ይቀርብ ነበር:: ነዋሪዎቹን አስነስቶ በፍጥነት ምትክ አለመስጠት ያጋጥም ነበር:: ስለዚህ መጀመሪያ ያደረግነው ሕጋዊ ሆኖ ቤት ያለውን ሰው ቤት ሳንሰጠው አናነሳም ብለን ወስነናል::
ስለዚህ የቀበሌ ቤት የመረጡ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት የመረጡም ሆኑ የግል ቤት ያላቸው ምትክ ቦታ የሚሰጣቸው መሬት ሳይሰጣቸው አይነሱም:: ለምሳሌ 19 ሰዎች የቀበሌ ቤት መርጠው ነበር:: ባለን አቅም 15 ቤት ማቅረብ ችለናል:: ለምሳሌ ሁለት ክፍል ያለው ቤት ከተነሳ መሠጠት ያለበት ሁለት ክፍል ቤት ነው:: ነገር ግን ሁለት ክፍል ተነስቶ አንድ ክፍል ከተገኘ እና ተነሽው ፈቃደኛ ከሆነ ያው ፈቃደኛ በመሆኑ ይሠጠዋል:: ፈቃደኛ ካልሆነ ግን ተመሳሳይ ቤት እስኪገኝለት እንዲለቅ አናስገድደውም:: በዚህ መሠረት ስምንቱ ተረክበው ገብተዋል::
ለእኛ ፈታኝ የሆነው ጥገኛ ነዋሪውን የምናደርገውን ማጣታችን ነው:: እንደሰው ሕፃን ይዘው ማደሪያ ሲያጡ ያሳዝናሉ:: ሕጋዊ እንዳይደረጉ ለሕጋዊዎቹም እጃችን ላይ ቤት የለም:: በዚህ መሠረት የሚቸገሩ ሰዎች አሉ:: የሚያለቅሱ ሰዎች አሉ:: ከሌሎች ዝቅተኛ ነዋሪዎች ጋር ተወዳድረው እንዲስተናገዱ እያረግን ነው:: አንዳንዱን ጥያቄዎች ግን መመለስ አንችልም:: 105 አቤቱታ ቀርቦ የመለስንላቸው ከአስር አይበልጡም:: በተነሳው ጥያቄ ልክ ፈጣን መልስ እየተሰጠ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ከቀረበ፣ መልሳችን መመለስ የማንችላቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ የሚል ነው:: ዋናው ግን የምንችለውን ያለአድሎ ለመፈፀም ጥረት እያደረግን ነው:: ያልተስተናገዱ ሰዎች መኖራቸውን መካድ አንችልም::
አዲስ ዘመን፡-እነዚህ የተቸገሩ ሰዎችን ለመደገፍ ሌሎች አማራጮች የሉም? ለምሳሌ ቤት የሠሩም ሆኑ ቤት ያገኙ የቀበሌ ቤት ለቀው ሲወጡ በቤቱ ይኖር የነበረ ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ እና ቤተሰብ የመሠረተ በዛ ቤት ኑሮውን መቀጠል እንደሚችል ሰርኩላር ዞሯል:: እየተሠራበትም ነው:: ለእነዚህ የልማት ተነሺዎችስ ለምን ሌሎች አማራጮች ሊገኝላቸው አልቻለም?
አቶ ሞላ፡- በእርግጥ በረዥም ጊዜ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የታሰበው በቤት ግንባታ ላይ የግል ዘርፉን በማሳተፍ ነው:: መንግሥት ቤት እየሠራ ማከፋፈል አይችልም:: ስለዚህ በሽርክና እና በሌሎችም መንገዶች ቤቶችን ለመሥራት የታቀዱ ትልልቅ ዕቅዶች አሉ:: እነዚህ በረዥም ጊዜ የሚሳኩ ናቸው:: አሁን ሊሆን የሚችለው ያለችውን ያለአድሎ ችግር ላለባቸው መስጠት ነው:: እርሷ የምትኖረው ደግሞ ስትለቀቅ ነው:: ወይ ቤት ደርሷቸው እና ሠርተው የሚለቁ ወይም ደግሞ በሕገወጥ የያዙ ሰዎች ካሉ እነርሱን በማስለቀቅ እንሰጣለን:: የቀበሌ ቤት ሲኖር አብሮ የነበረ ቤተሰብ እንዳይለቅ ተብሏል:: አሁን ለወንዝ ዳርቻ የልማት ተነሺዎች ግን ሕጋዊዎቹ ምትክ ይሰጣቸዋል:: ነገር ግን ያስጠጓቸውን ሰዎች ትተው ይሔዳሉ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ አቤቱታ ያቀርባሉ:: ቤቱ ደግሞ ይፈርሳል:: ሌላው ግን በተደጋጋሚ የሚቀርቡት አቤቱታዎች የቀበሌ ቤት ይሠጠን የሚል ነው::
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ላይ ስር የሰደደ የመኖሪያ ቤት ችግር መኖሩ ይታወቃል:: በዚህ ምክንያት ለሙስና የተጋለጠ ስለመሆኑም ይነገራል:: የሕዝብ ውይይት መድረኮች ላይ በስፋት ቤት እና ሙስናን የተመለከቱ አስተያየቶች ሲሰጡ ነበሩ:: አሠራሩ ከሌብነት የፀዳ እንዲሆን ምን ያህል እየተሠራ ነው? እዚህ ላይ ከቤት ጋር ተያይዞ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተጨማሪ ክፍያን ማስከፈል የሌለባቸው የዜግነት አገልግሎቶች ሳይቀሩ የሚገኙት በሙስና ስለመሆኑ እና አሁን እንደውም በተደጋጋሚ ይህ እንደሚፈፀም ይታማል:: ስለዚህ ምን ይላሉ?
አቶ ሞላ፡- ሰጪም ተቀባይም ተጠያቂ ስለሚያደርጋቸው ድርጊቱን የሚፈፅሙት ተደብቀው ነው:: ስለዚህ ማድረግ የምንችለው በአሠራር መከላከል ነው:: ለምሳሌ፣ በጣም ችግረኛ የሆኑ ሰዎች እንዴት ይለዩ ሲባል፤ መለየት የሚጀመረው ከታች ከነዋሪው የሚጀምር ምስክርነት ተሰጥቶበት እና ተለይቶ ሰፊ ውይይት አድርገውበት እና ተስማምተውበት ያስተላልፋሉ:: በነዋሪው የተለየው ደግሞ በወረዳ ካቢኔ ፀድቆ ለክፍለ ከተማ ቤቶች ቀርቦ ይሠጣል:: ይሔ አንደኛው ነው:: ሌላኛው ደግሞ የተለያየ ችግር ያለባቸው ለከተማው ካቢኔ ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ::
ከኃላፊነት ጋር ተያይዞ ወይም የተቸገሩ ሲያጋጥሙ፤ ከከተማ አስተዳደሩ መደበኛ ደብዳቤ ይመጣል:: በዛ መሠረት ይስተናገዳል:: በዚህ መልኩ አሠራር ተከትለን እየሠራን ነው:: በእኛ ክፍለ ከተማ ግን በቀጥታ አጋጥሞን አንድ ሰው እንዲህ ሲቀበል አይተናል የሚል የተረጋገጠ በመረጃ እና በማስረጃ ላይ የተደገፈ ነገር የለም:: ነገር ግን ቅሬታዎች ይነሳሉ:: ለምሳሌ፣ ከእኔ በኋላ ለመጣ ሰው ቤት ተሰጠው የሚል አቤቱታ ይቀርባል:: አንዳንዶች ደግሞ ‹‹ያስወጡን ያለአግባብ ነው›› የሚሉም አሉ:: አሁን አቤቱታ የማስተናገጃ ቀን የተለየ ምንም ዓይነት ስብሰባም ሆነ ሌላ ሥራ የማይሠራበት ሲሆን፤ አቤቱታ አቅራቢዎችም በሙሉ በኅብረት አንዱ የሌላውን ችግር እየሰማ እንዲናገሩ እየተደረገ ነው::
ወረዳ በድሎናል ካሉ እዛው ሁሉም እያየ ፊት ለፊት ስልክ ተደውሎ ሁሉም ሊሰማ በሚችል መልኩ በወረዳ ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት ይካሔዳል:: ጥያቄ ይቀርባል:: እዛው ምላሽ ይሠጣል:: አሁን እልከዋለሁ ባልከው መሠረት ፈጽም ይባላል:: እንዲዚህ እያደረግን ሥራችንን ግልፅ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን:: አሁን አንዳንድ ጊዜ አቤቱታ አቅራቢዎች አንድ ላይ ሲናገሩ አንዱ የሌላውን ችግር አይቶ የኔ በሌላ ጊዜ ይደርሳል እስከማለት የሚደርሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: አንዱ ተጨናንቀናል ሌላ ቀይሩልን ሲል አንደኛው የምንኖረው ሸራ በተወጠረ ቤት ነው የሚል ሲያጋጥም የምንኖረው ተጨናንቀን ነው የሚለው ሰው ጥያቄውን ባይተወውም ይዘግይ ብሎ ትቶ ይሔዳል::
በተቻለ መጠን የአሠራር ብልሹነትን ለመከላከል መጀመሪያ አሠራርን ማየት ያስፈልጋል:: እኛ አሁን ላይ አቤቱታ ሲቀርብ የምንሰማው ሁላችንም ነን:: ያለምንም መደባበቅ እኔ ብቻ ሳልሆን ምክትሉ እና አማካሪዎች እንዲሁም ሌሎች አቤቱታ አቅራቢዎች እየሰሙ ፊት ለፊት ይቀርባል:: በተቻለ መጠን አሳታፊ ለማድረግ ጥረት እያረግን ነው:: ነገር ግን የሁሉንም አካላት ተሳትፎ ይጠይቃል:: ሕዝብን ማንቃት ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- ከመኖሪያ ቤት በተጨማሪ የመሥሪያ እና የመሸጫ ሼዶች ፍትሐዊ ክፍፍልን በሚመለከት ተደጋጋሚ ሮሮዎች ይደመጣል:: ለምሳሌ አንድ ሰው ሶስት እና አራት ሼድ ሲኖረው ሌላ መሥራት የሚችል ነገር ግን የመሸጫም ሆነ የመሥሪያ ቦታን መከራየት የማይችል ሰው አንድም ሳያገኝ የሚቀርበት ሁኔታ አለ:: ይህንን በተመለከተ ምን ይላሉ?
አቶ ሞላ፡- ትክክል ነው:: በሕዝብ መድረኩ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ሀብት ያፈሩ ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው አሁንም ድረስ ሼዶችን የያዙት ለምን አይለቁም የሚል አቤቱታ ቀርቧል:: ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ምን ያህል ሰው መቼ ሼዶችን ወሰደ ምን ያህል ሃብት ፈጠረ የሚለውን እያጠናን ነው:: በሌላ በኩል አሁን የሠራናቸው ትንንሽ ሱቆች አሉ:: እነሱ ላይም እንደባለፈው ዓይነት ስህተት እንዳይሠራ በተቻለ መጠን በትክክል ለሚገባው ሰው እንዲደርስ ልክ የቀበሌ ቤት ላይ እንደተሠራው አሁንም ከማኅበረሰቡ እንዲመጣ እየተሠራ ነው:: ነገር ግን ራሱ ሰው መተሳሰብ አለበት:: ሃብት ከፈጠረ ለሌላው ሰው መልቀቅ ሲኖርበት ይዞ ከቆየ ከባድ ነው:: አሁን ቀድሞ ያዩዙት ልቀቁ ሲባሉ እነርሱ ራሳቸው አልቃሽ ይሆናል:: እነርሱ ራሳቸው የቅሬታ አቅራቢዎች ይሆናሉ:: እውነት ነው ይሔ ሕዝብ የሚያነሳው ጥያቄ መፈታት አለበት:: ነገር ግን ሁሉም ማሰብ መረዳት እና መተጋገዝ አለበት::
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቷ በነበረው ጦርነት፣ በዓለም ደረጃ ባጋጠመው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፤ እንዲሁም በተከሰተው የዓለም የፖለቲካ ቀውስ እና በሌሎችም በተለያዩ ምክንያቶች የኑሮ ውድነቱ ማኅበረሰቡን እያንገላታው ነው:: ይህም የሕዝብ መድረኩ ላይ በዋነኛነት ትልቅ አቤቱታ ሆኖ ሲቀርብ ነበር:: በእናንተ በኩል ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ሞላ፡- የኑሮ ውድነቱን ችግር ለማቃለል ዋነኛው ዘላቂ መፍትሔ አቅርቦቱን መጨመር ነው:: በእርሱ ላይ በአገር ደረጃ ምርት መጨመር ላይ የሚሠራ ይሆናል:: ነገር ግን አሁን ላይ በክፍለ ከተማው ሰው ሰራሽ ችግርን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው:: ይሔ በስግብግብነት የሚፈጠረውን ችግር ለማቃለል ቤት ለቤት አሠሣ በማድረግ በአንድ ወር ውስጥ ወደ ስምንት ሺህ የንግድ ሱቆች ተፈትሸው 264ቱ ላይ ያለአግባብ ለገበያ መዋል ያለበትን ምርት አከማችተው ተገኝተዋል:: አንድ ሺህ 511 ሊትር ዘይት፣ 15 ኩንታል ስኳር ተገኝቷል:: ስለዚህ አንዱ ሰውሰራሽ እጥረትን ለመቀነስ ሠርተናል:: በተጨማሪ ስኳርና ዘይት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ምርቶችን የሚያቀርቡ በክፍለ ከተማው ባሉ 10 የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበር በ56 ሱቆች የተለያዩ ምርቶች እየቀረቡ ነው:: እዚህ ላይ ምርት ቶሎ እንዲሠራጭ ማድረግ ነው:: ሸማቾች ጋር የገቡ ምርቶች ቶሎ ኅብረተሰቡም ሆነ ሱቆች ጋር በፍጥነት እንዲደርሱ ማድረግ ተችሏል:: በአካል በመሔድ ሱቆችን ለማየት ሞክረናል::
አሁን ወደ ሱቆች ስንሔድ ስኳር ብዙ ችግር አይደለም፤ በቅርብ ይገኛል:: ሙሉ ለሙሉ ችግሩ ተቀርፏል ባይባልም፤ ይሻላል ብሎ መውሰድ ይቻላል:: ሁለተኛ የከተማ አስተዳደሩ ወደ 100 ቢሊዮን ብር ለሸማቾች ድጎማ አድርጓል:: ይህ ተዘዋዋሪ ገንዘብ ነው:: እኛ ወደ 100 ሚሊዮን አግኝተናል:: ይሔ ጤፍ እና ስንዴ ብቻ የሚገዛበት ነው:: ሸማቾች ከአርሶ አደሩ በቀጥታ አምጥተው እንዲያስቀምጡ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው:: በዚህ መሠረት በ87 ሚሊዮን ብሩ እህል ገዝተንበታል:: በዚህ መሠረት ነጭ ጤፍ 7ሺህ 751 ኩንታል፤ ሰርገኛ 7ሺ 67 ኩንታል ገዝተናል:: ቀይ ጤፍም 2ሺህ አንድ መቶ ኩንታል ገዝተናል::
የዋጋ ልዩነቱ ነጭ ጤፍ ከእኛ የሸማቾች ማኅበራት 4 ሺህ 750 ሲሸጥ፤ ውጪ ግን 5 ሺህ 300 ብር እየተሸጠ ነው:: ሰርገኛም 4ሺ 300ብር ሲሆን፣ ውጪ 4ሺህ 600 ብር እየተሸጠ ነው:: ቀይ ጤፍም ተመሳሳይ ልዩነት አለው:: ስለዚህ በትንሹ የአራት መቶ እና የሶስት መቶ ብር ልዩነት አለ:: ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲታይ በቂ እና እርካታን የፈጠረ ነው ማለት አይደለም:: ነገር ግን ለመሥራት እየተሞከረ ነው::
እሁድ ገበያም በክፍለ ከተማችን በሁለት ቦታዎች ላይ የአርሶ አደር እና የፋብሪካ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው:: እስከ አሁን ወደ 9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የተለያዩ ዓይነት ምርቶች ሽያጭ ተካሂዷል:: እስከ አሁን ስድስት ኪሎ እና ጊዮርጊስ አካባቢ ባለው ሽያጭ ብቻ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በተጨማሪነት ሾላ አካባቢም እየተጀመረ ነው:: ዝም አልተባለም ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው::
አዲስ ዘመን፡- በክፍለ ከተማው እየተስተዋለ ያለውን እና በተደጋጋሚ እየተጠቀሰ የሚገኘውን የፀጥታ ችግር በሚመለከትስ ምን እየተሠራ ነው? ሰሞኑንም ተባብሶ ስለመቀጠሉ ይነገራል:: በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሞላ፡- ከፀጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ስንጠቁም ቶሎ አይደርሱልንም የሚል ከኅብረተሰቡ በፀጥታ ኃይሉ ላይ አቤቱታ ቀርቧል:: ከላይ እንደተገለፀው በእነርሱ በኩልም የቀረቡባቸውን አቤቱታዎች ቆጥሮ በመግለፅ አውቀው እንዲሠሩበት አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል:: በፊት የሕልውና ዘመቻ ጦርነት በነበረበት ጊዜ የፀጥታ ኃይሉም ሆነ ኅብረተሰቡ ጥበቃውን በብሎክ ሳይቀር አጠናክሮ ነበር:: አሁን ግን የተወሰነ መላላት አለ:: ይህንን ችግር ለመፍታት ማኅበረሰቡም ጥበቃውን እንዲያጠናክር፤ የፀጥታ ኃይሉም ጥያቄ ሲቀርብለት ቶሎ የሚደርስበት ሁኔታ እንዲፈጠር እየሠራን ነው::
አዲስ ዘመን፡- የመሬት ወረራ ላይ ሰፊ ችግር እየተስተዋለ ስለመሆኑ ይነገራል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ እናንተ ጋር ያለውን ችግር ለመቅረፍ ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ሞላ፡- በሌሎች ክፍለ ከተሞች ላይ እንዳለው የተጋነነ ባይሆንም አሁንም በተለይ በወንዞች ዳርቻ አካባቢ እኛ ክፍለ ከተማ ላይም የመሬት ወረራ ችግሮች አሉ:: አንዱ የምናፈርሰው ሕገወጥ የሆነው በወንዞች አካባቢ የሚስተዋለው ነው:: ከ20 በላይ ቤቶችን አፍርሰናል:: ተቸግረው መሥራታቸውን ቢገልፁም ሕገወጥነት መስፋፋት ስለሌለበት እያፈረስን ነው:: በየቦታው ሸራ ወጥረውም የሚሠሩ እና የሚኖሩ አሉ:: ለምሳሌ ቴድሮስ አደባባይ አካባቢ አፍንጮ በር አካባቢም ሸራ ወጥረው የሚኖሩ አሉ:: እርሱን ችግር ለመፍታት እንሠራለን::
አዲስ ዘመን፡- መሬት ነክ ጉዳዮች በክፍለ ከተሞች ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ለምን ይቀርባሉ? ቤት ከሌለ ቤት የለም ተብሎ በግልፅ የማሳወቅ ሥራ ለምን አይሠራም:: ለምን ችግሮች እንዲፈቱ የከተማው አስተዳደር ድረስ ጥያቄያችሁን አትዘልቁም? በኢኮኖሚ በኩል ያለውንስ?
አቶ ሞላ፡- ሁሉም ነገር የመጣው ሁሉ በአንዴ እንደማይፈታ ኅብረተሰቡም ያውቃል :: የሚያስፈልገው በቅርብ ጊዜ የሚሆነውን ይሆናል:: በቅርብ ጊዜ የማይሆነውን አይሆንም በማለት ምላሽ እየሰጠን ነው :: አሁን እያደረግን ያለነው እሱን ነው። አሁን የተነሳውን የቤት ችግር እናንሳ የጋራ መኖሪያ ቤት እንሰጣለን ተብሎ በ1997 ተጀምሮ ነበር :: ነገር ግን ተመዝጋቢዎቹ ምላሽ ሳያገኙ በ2005 ሌላ ምዝገባ ተካሔደ:: በዚያ ዓመት የተመዘገበው በጣም ግዙፍ ቁጥር ነው :: እሱ ገና አልተነካም :: ስለዚህ የቤት ችግር ውስብሰብ እና ሰፊ ነው:: ይህን ችግር ሺህ አመት ብንቆይ እንኳ በዚህ አካሔድ አንፈታውም :: ስለዚህ እንዲህ አይነቱ ችግር የአሰራር ለውጥ ያስፈልገዋል:: በመሆኑን በብዛት ይህን ችግር ለመቅረፍ የግል ባለሃብቱን ለማሳተፍ እየተሠራ ነው:: መታወቅ ያለበት ግን ዝም ብሎ ችግሮችን መስማት ብቻ ሳይሆን አማራጮችን ማሰብ ያስፈልጋል::
አሁን እየተነሳ ያለው የኑሮ ውድነትም ቢሆን መፍትሔው አገራዊ ምርቱን መጨመር ነው:: ለምሳሌ ከውጪ ከምናመጣቸው ነገሮች አንዱ ስንዴ ነው:: ስለሆነም በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ከውጭ የምናመጣውን ስንዴ ማቆም አለብን ተብሎ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው :: ለኢኮኖሚ ችግሮች በቂ ምላሽ መስጠት ያልተቻለው ፍላጎት እና አቅርቦቱ ባለመመጣጠኑ ነው :: እንደዚህ አይነቱን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ መነጋገር እና መግባባት ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- ጊዜዎትን ሰጥተው ለቃለ ምልልሱ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ!
አቶ ሞላ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም