ኢኮኖሚ ከሚደገፍባቸው ዋንኛ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው፤ የፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ። በዓለም ገበያ ከፍተኛ የማዋዕለ ንዋይ ዝውውር የሚደረግበትና ገበያና ገበያተኛው በቋሚነት የሚገናኙበት፣ ትርፍና ትርፋማነት ከፍተኛ ዕድገት የሚስተዋልበት፣ ተጠናክረው ከሰሩበትና ከፍተኛ ውጤት የሚገኝበት ዘርፍ ነው። ለዚህም ነው አገራት አገር በቀል የሆኑ የፋሽን ምርቶች ላይ በስፋት በመስራት ከራሳቸው አልፈው ወደሌሎች አገራት በመላክ ተጠቃሚነታቸው ለመጠቀም ብርቱ ጥረት የሚያደርጉት።
አገራዊ ምርት መጠቀም ጥቅሙ አያሌ ነው። አገራት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ አውጥተው ወደ አገር የሚያስገብዋቸው የፋሽን ኢንዱስትሪ ምርቶች በአገር ምርት መተካት ቢችሉ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ እንደሚሆን አያጠያይቅም። በውጭ አገር የሚመረቱ አልባሳትና ሌሎች የፋሽን ኢንዱስትሪ ግብዓቶች በአገር ውስጥ ምርት መተካት ቢቻል የውጭ ምንዛሪ ወጪን ከመቀነሱም ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የሥራ እድል መፍጠርና የፋሽን ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማነቃቃት ያስችላል፡፡
አገራት በራሳቸው የሚመረቱ አገር በቀል ምርቶች በህዝባቸው ተመርጦ ይለበስ ዘንድ ያበረታታሉ ለዚህም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። እንድ ህንድ፣ ፓኪስታንና፣ ቻይና ለዚህ ዋንኛ ተምሳሌት ናቸው፡፡እነዚህ አገራት ማህበረሰባቸውን አገራዊ ምርትና አገልግሎት እንዲጠቀም በማድረግ ያላግባብ ይወጣ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ከማዳናቸውና ኢኮኖሚያቸውን ከመደገፍ ባለፈ ለዜጎቻቸው ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። በተጨማሪም አገራዊ ባህላቸው የተንፃባረቀበት ምርት ማሳደግ ችለዋል። በዚህም ዘርፈ ብዙ የሆነውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ችለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአገር ምርት የመጠቀም ባህል ካላቸው መሰል አገራት ልምድና ተሞክሮን በመተግበር አገራዊ ምርቷን በማሳደግና ከውጭ የሚመጣውን የፋሽን ኢንዱስትሪ ግብዓቶች መቀነስ እና አገራዊ የፋሽን ምርቶች መጠቀም ላይ ትኩረት አድርጋ መስራት እንደሚጠበቅባት የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ዲዛይነር ሜላት እዚህ ላይ አስተያየትዋን ትሰጣለች፤ ለፋሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት አገራዊ ምርት የመጠቀም ባህል ላይ ተጠናክሮ መሰራት የሚኖርበት መሆኑን ትገልፃለች፡፡
ማህበረሰቡ ለአገራዊ ምርቶች የተሻለ አመለካከትና ፍላጎት ካለው አምራቹ አዳዲስና የተሻሉ ዲዛይኖችን ከጥራት ጋር የማቅረብ እድል ይፈጠርለታል። በዚህም ተጠቃሚውም አምራቹም ብሎም አገር ይጠቀማሉ። በአልባሳት ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ከውጭ የሚመጡ ልብሶች እንደሚዘወተር የምትጠቅሰው ሜላት ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ በማስወጣት አገራዊ ጥቅምን ይቀንሳል።
ከውጭ የሚገባው የፋሽን ምርት መቀነስ ይባክን የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባሻገር አገር በቀል የፋሽን ኢንዱስትሪዎች ለማነቃቃት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ከዚህ ባለፈው ባህል ተኮር የሆኑ አልባሳት በስፋት ተሰርተው ገበያ ላይ እንዲገኙ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል። የሚሰራውና የሚያመርተው ባህሉንና ወጉን የሚያውቅ እንደመሆኑ ስሪቱም ባህል ነክ የመሆን እድል ይፈጥርለታል።
አገራዊ ምርት የመጠቀም ባህል ፋይዳው እጅግ ብዙ ነውና እዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበትና ምርቶቹን ማበረታታት እንደሚገባ ባሙያዎች ይገልፃሉ። ዲዛይነር ሄለን አየለ በፋሽን ኢንዱስትሪው ገብታ መስራት ከጀመረች ከ3 ዓመት በላይ ይሆናታል። እንደ ዲዛይነርዋ ዋንኛ ትኩረትዋ አገራዊ ምርቶችን በአገር ውስጥ ተሰርቶ በሚቀርቡ ጨርቆች ሰርቶ ወደ ገበያ ማቅረብ ቢሆንም ማህበረሰቡ ከባህላዊ አልባሳት ውጪ ያሉ አልባሳት በአገር ውስጥ ከሚዘጋጀው ይልቅ ከውጭ የሚመጣውን ይመርጣል፡፡
ዲዛይነር ሄለን፤የማህበረሰቡ ምርጫ የውጭ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት ያገር ውስጡ ጥራት የለውም ብሎ በመደምደሙ መሆኑን ትናገራለች። ነገር ግን በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ከውጭ ከሚገቡት በተሻለ መልኩ ጥራትና ያማረ ዲዛይን ቢቀርቡም ማህበረሰቡ እምነቱ ላይ ጠንካራ ሥራ አለመሰራቱ ምርጫው የውጭ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የክሬቲቭ ሃብ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጁ አቶ ተመስገን ፍስሀ አገር በቀል የሆኑ የፋሽን ኢንዱስትሪዎች ለማበረታታት አገራዊ ምርት የማሳደግ ሥራን መስራትና ህብረተሰቡ በአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀም መገፋፋት ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ። በተለይ የአገር ውስጥ አዳዲስ የዲዛይን ፈጠራዎች በፋሽን ዲዛይነሮች ኢንዲመነጭና የፈጠራ ክህሎታቸው እንዲያድግ ለማድረግ እዚሁ የተመረቱ ምርቶች ማህበረሰቡ መጠቀሙ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
የአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልማድ ቢጠነክር በአልባሳቱ ባህል እራስን ከማንፀባረቅ ባለፈ ገና ጅምር የሆኑ የፋሽን ኢንዱስትሪዎችን ለማነቃቃትና ሰፊ የሆነ የሥራ እድል ለመፍጠር ጥሩ መንገድ ነው እንደ አቶ ተመስገን። በአገር ደረጃ አንድ ሰሞን ላይ በስፋት እየተሰራበት ቆይቶ መልሶ የሚደበዝዘው አገራዊ ምርት የመጠቀም ባህል የማስተዋወቅና የማበረታታት ተግባር በተከታታይነት ስላልተሰራበት የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻለም የምትለው ዲዛይነር ሜላት ለኢንዱስትሪው እድገት ሥራው ተጠናክሮ መሰራት ይኖርበታል፡፡
በፋሽን ኢንዱስትሪው ተሳታፊ የሆኑ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸው በተጠቃሚው ዘንድ ተፈላጊና ተቀባይነት ማግኘቱ ለተቋማቱ ህልውና ወሳኙ ጉዳይ ነው። የሚያመርቱት ምርት ተጠቃሚው ጋር ደርሶ የሚያወጡትን ወጪ ሊሸፍኑ የሚችሉበት ገቢ ማግኘት ይኖርባቸዋል። አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡት አልባሳት ወይ ሌላ ፋሽን ተኮር ቁስ ተጠቃሚው ሲሸምት ገቢያቸው አስተማማኝ በሆነ መልክ ይጨምራል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የህዝብ ቁጥር የያዘች አገር እንደመሆንዋ በፋሽን ኢንዱስትሪ የሚመረቱ አገራዊ ምርቶች በአገር ውስጥ በስፋት መጠቀም ቢቻል አገራዊ ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል። በተለይም እንደ አገር ፋሽንን ለማሳደግ ከሚሰሩ ሥራዎች ውስጥ ህዝቡ በአገሩ ምርት እንዲጠቀም የማበረታታትና የማስተዋወቅ ሥራ ሊሰራ ይገባል። ከውጭ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ፈሶባቸው የሚገቡ የፋሽን ምርቶች በአገር ውስጥ ቢሸፈን የውጭ ምንዛሪን ማዳን ያስችላል።
ህብረተሰቡ አገራዊ ምርት መጠቀም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ እንዲያውቅ ከማድረግ ጎን ለጎን የምርቶቹን ጥራት መጠበቅም ሌላኛው ጉዳይ መሆኑ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። በፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ምርት ተወዳዳሪ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ነጥቦች ምርቱ ለአይን የሚስብ መሆኑ፣ ሲጠቀሙበት የሚሰጠው ምቾት፣ የሚሰራበት ቁስ (ማቴሪያል) ጥራትና መሰል ጉዳዮች በትኩረት ማየትና የምርት ሂደት ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።
የፋሽን ምርት ወደ ገበያ ሲቀርብ አልያም ለሽያጭ የሚቀርብበት መንገድ ምቹ ማድረግና አገራዊ ምርት ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ማድረግ ወሳኙ ነጥብ ነው። አገራዊ ምርት መጠቀም ለአገር ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር በትኩረት ሊሰራበት ይገባል የዛሬው መልዕክታችን ነው።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2014