በዘንድሮው ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የህፃናት አስተዋፅኦ ጎልቶ ታይቷል። ህፃናቱ በተለይ የልደት በዓላቸውን ወጪ ጭምር በመተው ቦንድ እንዲገዛላቸው በማድረግና የልደት በዓል ስጦታቸውንና የኬካቸውን ወጪ ጨክነው ለግድቡ በማበርከት የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።
ህፃን ክርስቲያን ሰለሞን አዲስ አበባ በሚገኘው ይርጋለም አካዳሚ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ናት። ‹‹የህዳሴ ግድብ ለእኔ መብራት የሚሰጠኝ ነው›› ትላለች። የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መብራት እንዲያመነጭ ታዲያ ጠንክራ እየተማረች እንደምትገኝና ለግድቡም የራሷን አስተዋጽኦ እያበረከተች እንደምትገኝ ትገልፃለች። ከእናቷ ተቀብላ ያጠራቀመቸውን ገንዘብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳበረከተችም ትናገራለች። በእርሷ እድሜ ያሉ ህፃናትም ወላጆቻውን ጠይቀው ገንዘብ በማጠራቀም ለገድቡ ግንባታ ያበርክቱም ትላለች።
ህፃን ምዕራፍ ወልደሩፋኤል በቅዱስ ማርቆስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ‹‹የህዳሴ ግድብ ለእኔ የህልውናዬ መሰረት ነው›› ይላል። የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ያለመብራት ቁጭ ብለው እራት የሚበሉትንና የሚያጠኑትን ህፃናት ወደ ብርሃን እንደሚያመጣቸውና በቴክኖሎጂም ጭምር ታግዘው እንዲኖሩ እንደሚያስችላቸው ይገልፃል።
ከወላጆቹ ተቀብሎ ገንዘብ በማጠራቀምና ቦንድ በመግዛት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ይናገራል። በትምህር ቤት በሚዘጋጁ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍና ቅስቀሳ በማድረግ ድጋፍ እያደረገ እንዳለም ይገልፃል። በቀጣይም ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልና ሌሎች ህፃናትም ለግድቡ ድጋፍ እንዲያደርጉ ቅስቀሳ እንደሚያደርግ ይጠቁማል።
በአርዲ ዩዝ አካዳሚ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ህፃን ዮሚዩ ሰለሞን በበኩሉ ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለእኔ የመብራት ምንጭ›› ነው ይላል። ልክ እንደ ህፃን ክርስቲያንና ህፃን ምእራፍ ሁሉ ከወላጆቹ ገንዘብ በመጠየቅና በማጠራቀም ለግድቡ ግንባታ እያበረከተ እንደሚገኝ ይገልፃል።
ሌሎች በእርሱ እድሜ ክልል የሚገኙ ህፃናትም ወላጆቻቸውን በመጠየቅና ቦንድ እንዲገዙላቸው በማድረግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም መልእክቱን ያስተላልፋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር እንደሚሉት ባለፉት ስድስትና ሰባት አመታት ህፃናት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ይህ ስራ በክልሎችም ሰፍቶ እየተከናወነ ይገኛል። የ11ኛ አመት የግድቡ በዓልም ‹‹ግድባችን የአንድነታችን ብርሃን ነው›› በሚል መሪ ቃልም በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና በመላው ኢትዮጵያ ሲከበር ሰንብቷል።
በህፃናት ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም ህፃናት የነገ አገር ተረካቢ በመሆናቸውና ወላጆቻቸው አሻራቸውን ያሳረፉበትን ግድብ ተረክበው ወደፊት እንዲያስቀጥሉ ነው። በተለይ ህፃናት ለግድቡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ እንዲኖራቸውም ስለሚያስፈልግ በግድቡ ዙሪያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ውይይት እንዲያደርጉ፣ በትምህርት ቤት እንዲከራከሩ፣ ግጥም እንዲያቀርቡና የመሳሰሉትን እንዲያደርጉ የሚያስችሉ መድረኮች እየተዘጋጁ ይገኛሉ። በቀጣይም ይኸው መድረክ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በህፃናት መካከል የሥዕል፣ፊልም፣ ግጥምና ሌሎችም ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ከዚህ ባለፈ በዘንድሮው በጀት አመት በተለየ መልኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ ህፃናትና ታዳጊዎች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በርካታ ድጋፎችን አድርገዋል። የልደታቸውን ወጪ፣ ቤተሰቦቻቸው ቦንድ እንዲገዙላቸው በማድረግ ድጋፋቸውን አሳይተዋል። አሁን ደግሞ በቦንድ ሳምንት በአገር አቀፍ ደረጃ በየትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በቦንድ ግዢ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በዚህም በርካታ ገንዘብ መሰብሰብ ተችሏል። በቀጣይም ‹‹አሻራዬን አኑሪያለሁ›› የሚል የደረት ፒን ሁሉም ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲገዙና ለልጆቻቸው ስጦታ እንዲሰጡ የማድረግ ፕሮግራም ይካሄዳል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም