አርሲ ዞን ጭላሎ ወረዳ ቀበሌ 01 ማሪያም ሰፈር አካባቢ በመሮጥ ላይ የሚገኘው አትሌት የተጋደመ አስከሬን የያል። ኅዳር 14 ቀን 2004 ዓ.ም በዛ ቦታ ላይ የተገኘው አስከሬን መልኩን በውል ለመለየት የሚስቸግር ነበር። አስከሬኑ ትኩስ አይደለም። ጭንቅላቱ ተከስክሷል። አትሌቱ አልዘገየም፤ እንደተመለከተ ‹‹991›› ደውሎ ለአርሲ ዞን ፖሊስ ጣቢያ ስለጉዳዩ ጥቆማ ሰጠ።
የጣቢያ ኃላፊው መረጃውን ተቀብሎ የምርመራ ቡድን ይዞ ቦታው ላይ ሲገኝ፤ አስከሬኑ ተጋድሞ ነበር። ካኪ ሱሪ ሬንጀር ጃኬት እና የወታደር ጫማ አድርጎ የተንጋለለው አስከሬን ማን እንደሆነ በውል ለመለየት የሚያስቸግር ነበር። ጭንቅላቱ ከመከስከሱም በተጨማሪ ሆዱ ላይ ሶስት ቦታ በስለት ተወግቷል። አፍንጫው ላይ ደም የሚታይ ሲሆን፤ ወሬው የደረሳቸው የአካባቢው ሰዎች መሰባሰብ ሲጀምሩ ማንነቱ ታወቀ። የአካባቢው ነዋሪዎች ሰለሞን ተረፈ ነው እያሉ ማልቀስ ጀመሩ።
ሰለሞን ከአካባቢው ሰው ጋር በፍቅር እና በሰላም የሚኖር ተወዳጅ ሰው በመሆኑ ሁሉም ጩኸቱን አቀለጠ። መርማሪዎቹ በለቀስተኞቹ መካከል ሆነው በሚስጥር መረጃ ማሰባሰብ ጀመሩ። የአንዱ ሰው ለቅሶ ግን የተለየ ነበር። ትዳርም ሆነ እናት፣ አባት ወይም ወንድም እና እህት በቅርብ የሌለው መሆኑን በመግለፅ ሁሉም አምርሮ ሲያለቅስ እና እየተያየ ሲላቀስ ፤ አንድ ሰው ግን በጣም እየጮኸ ‹‹ተው እያልኩህ፤ አልሰማ አልከኝ፤ እምቢ አልከኝ። ወዳጄ ጓደኛዬ›› እያለ ሲንፈቀፈቅ በሚስጥር ምርመራ የሚያካሂዱ ፖሊሶች ቀልባቸውን ሳበው። ሁሉም እየተያዩ ወደ እርሱ ተመለከቱ።
ሃምሳ አለቃ ደረጄ ማልቀሱን አላቆመም ‹‹የኔ ታጋሽ፤ የኔ አስተዋይ እያለ›› የሚያወጣቸው ቃላት ሁሉም መርማሪዎች በአንክሮ እንዲከታተሉት አስገደዳቸው። ከመርማሪዎቹ አንዱ ተጠግቶ ሟች ሰለሞን ከሚያለቅሰው ሰው ጋር ያለውን ዝምድና በመጠየቅ የሃምሳ አለቃ ደረጄ እንደሚባል ስሙን መዝግቦ ያዘ። ሰውየው ያለው ግንኙነት ሲጣራ የሟች ሰለሞን የቅርብ ጓደኛ መሆኑ ተረጋገጠ። አስክሬኑ አሰላ ሆስፒታል ደርሶ ሲመረመር ደረቱም ላይ በስለት መወጋቱ ተጠቆመ።
የአርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ የምርመራ ቡድን ሞቶ ተገኝቷል ስለተባለው ሰለሞን መረጃ ማሰባሰብ ቀጠለ። ሟች ከዚህ በፊት እገድልሃለሁ እያለ ይዝትበት ነበረ በማለት በእነ ሃምሳ አለቃ ደረጄ የተጠቆመው ሰው ደምሴ ባንጃው ከነባለቤቱ በቁጥጥር ስር ዋለ። በዕለቱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቤቱ ሲበረበር የደም ነጠብጣብ ተገኘ። ከመርማሪዎቹ መካከል የተወሰኑት ወንጀለኛውን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል ፍንጭ እንዳገኙ በማመን ተደሰቱ። አንደኛዋ መርማሪ ግን መጀመሪያ የተጠረጠረውን እና አምርሮ ሲያለቅስ የታየውን የሃምሳ አለቃ ደረጄን ክፉኛ በመጠርጠሯ የነደምሴ መያዝ የምርመራውን አቅጣጫን እንዳያስት መስጋቷን በመግለፅ ይልቁኑ በተለየ መልኩ ሲያለቅስ የነበረው ጓደኛ የተባለው ሃምሳ አለቃው ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል አለች።
ምርመራው
ቡድኑ እያንዳንዱን መረጃ በጥንቃቄ በመያዝ መመርመሩን ቀጠለ። መርማሪዎቹ ዘመድ አለው ወይ በማለት ሲያጣሩ አንዲት ዘመዴ ናት የሚላት እና የሚረዳት ሴት እንዳለች አረጋገጡ። ወደ ሰለሞን ቤት በመሔድ በተለይ ቀረቤታ ያላቸው ጎረቤት የሆኑት እና አንዳንዴም የቤቱን ቁልፍ ሳይቀር የሚያስቀምጥባቸው አንዲት አሮጌት ቤት ሔዱ። ሴትየዋ በእርግጥም ሰለሞን አንዳንዴ ቤተሰብ ቢመጣ እንኳ ደጅ ሆኖ እንዳይጉላላ ‹‹እኔን ብሎ ለሚመጣ ሰው ቁልፍ ስጡልኝ›› ብሎ ቁልፍ እርሳቸው ጋር እንዳስቀመጠ ተናገሩ።
አሮጊቷ ከመሞቱ ከሁለት ቀን በፊት ሟች ሰለሞን ተረፈ ‹‹ደክሞኛል ገብቼ ልተኛ›› ብሏቸው እንደነበር ጠቁመው፤ ከዛ በኋላ ግን እንዳላዩት ተናገሩ። ጨዋ፣ ታዛዥ መሆኑን በመግለፅ እንባቸውን አፈሰሱ።
በእዛው ቤት ውስጥ መርማሪዎቹ አሮጊቷን ሲጠይቁ እየሰሙ የነበሩት አዛውንት በበኩላቸው፤ ደከመኝ ልተኛ ብሎ ከመግባቱ በፊት 11 ሰዓት አካባቢ ከአንዲት ሌላ ጊዜም ዘመዴ ናት ከሚላት ሴት ጋር አብሮ ሲሔድ እንዳዩት ተናገሩ።
ደምሴ ባንጃው
ደምሴ ባንጃው ‹‹እገድልሃለሁ›› እያለ ይዝት ነበር መባሉን ተከትሎ ከነሚስቱ በቁጥጥር ስር ሲውል፤ ፍፁም የተረጋጋ ነበር። ‹‹ገድለሃል›› ሲባል በልበ ሙሉነት በፍፁም እርሱ ሰለሞንን እንዳልገደለ ይናገር ነበር። ደጋግመህ ትዝትበት ነበር፤ ሲባልም በፍፁም ዝቶበት እንደማያውቅ ተናገረ።
በቤቱ በተካሔደ ምርመራ ልብሱ ላይ የደም ነጠብጣብ እንደተገኘ ሲነገረው ከመደንገጥ ይልቅ በጣም በመሳቅ ደሙም የሟች ሰለሞን ሳይሆን ቀን አንድ ከማያውቀው ሰው ጋር ተደባድቦ የዛ ሰው ደም መሆኑን ተናገረ። ሲደባደብ የተጋጋጠ እጁንም አሳየ። መርማሪዎቹ እርጋታው እና በፍፁም ለሚቀርብለት ጥያቄ ምላሽ አለማጣቱ፤ ድፍረቱን በማሰብ ‹‹ይሔ ሰው ነፍሰ በላ ወንጀለኛ ነው።›› ብለው ገመቱ።
ለመልቀቅ አልደፈሩም፤ ተጨማሪ መረጃ ይሰበሰባል በማለት እዛው ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ወሰኑ። ነገር ግን በሌላ በኩል ወንጀሉን ፈፅሞ ላይሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬም አድሮባቸው ነበር። ከአርሲ ሆስፒታል የተገኘውን የአስክሬን የምርመራ ውጤት እንዲሁም ሟቹ ከመሞቱ በፊት ባሉ ተከታታይ ቀናት የነበረው የስልክ ልውውጥ መረጃን በመያዝ የምርመራ ቡድኑ ሥራውን ማጠናከር ቀጠለ።
በሌላ አቅጣጫ ሌላ ምርመራ ያለፈውን መረጃ መሠረት በማድረግ ከለቅሶ ላይ የቅርብ ጓደኛ የተባለውን እና አምርሮ ሲያለቅስ የነበረውን ሃምሳ አለቃ ደረጄ ብርሃኑና ለመጨረሻ ጊዜ አብራ ታይታለች በሚል በአዛውንቱ የተጠቆመችው እና ዘመድ ነች የተባለችውን ጥሩነሽ ደስታን የአርሲ ዞን የምርመራ ቡድን በጥርጣሬ ይዞ ለመመርመር ወሰነ። ሁለቱም ሰዎች ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያው ተወሰዱ። ቅድሚያ ምርመራ የተደረገው የሃምሳ አለቃ ደረጄ ብርሃኑ ላይ ነበር።
ከሃምሳ አለቃ ደረጄ ለመጨረሻ ጊዜ መቼ እና የት እንተደተገናኙ ሲጠየቅ ሟች ሰለሞን ተረፈ እጅግ ጓደኛው መሆኑን እርሱ ሲታመም ሥራውን ሸፍኖ ይሠራለት እንደነበር እንዲሁም ሚስጥሩን በሙሉ እንደሚነግረው እና በተደጋጋሚ ደምሴ ባንጃው እገድልሃለሁ ብሎ ይዝትበት እንደነበረ ገለጸ። መርማሪዎቹ በድጋሚ መቼ እንደተገናኙ ሲጠይቁት በአካል ሳይሆን እርሱ ገጠር እናቱ ጋር ሆኖ ሰለሞን ከመሞቱ በፊት 12 ሰዓት ላይ ደውሎለት እንደነበር። ለሊትም 7 ሰዓት ላይ ሰለሞንን ደውሎ እንዳነጋገረው ገለጸ።
‹‹ለሊት ሰባት ሰዓት እንዴት አልተኛህም›› የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት እንደውም እናቱ ጋር እርጎ እየጠጣ እንደነበር እና እንቅልፍ ወስዶት እንዳልነበር ተናገረ። የስልክ ልውውጡ መረጃ ያለው መርማሪ ‹‹ለሊት ደውለህ ዕቃ ይዘህ ና›› ብለኸው ነበር። ለምን ማታ 12 ሰዓት ስትደውል ያንን ዕቃ ይዘህ ና ለምን አላልክም? ሲባል ‹‹በዛ ሰዓት ረስቼው ስለነበረ ነው›› የሚል ምላሽ ሰጠ።
የስልክ ጥሪው
ሟች ሰለሞን ደክሞት ስለነበር በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ሆኖ ለሊት 7 ሰዓት ስልኩ ጠራ። ስልኩን ሲያነሳ ጓደኛው ሃምሳ አለቃ ደረጄ ነበር። በስልኩ ውስጥ ‹‹ጥሩዬ ተዘረፈች ዕቃውን ይዘህ ና ድረስላት›› የሚል መልዕክት አስተላልፎ ስልኩ ተዘጋ። ሰለሞን ጊዜ አላጠፋም፤ ወዳጁ ጥሩዬ ሰው እንደሌለው ሰው እየተዘረፈች ነው ብሎ በማመን ልብሱን ለብሶ ተጣጣፊ ክላሹን ይዞ በር ከፍቶ ወደ ጥሩዬ ቤት ገሰገሰ። መንገድ ላይ ጥሩዬ እና ሃምሳ አለቃን ሲያገኝ መሳሪያውን ለሃምሳ አለቃው ሰጥቶ እሱ ዘራፊዎቹን በእጁ ሊፋለም ሲጣደፍ ጥሩነሽ ደስታ ኋላ ተከተለችው። አንዳች ከባድ ምት ከኋላው ጭንቅላቱ ላይ አረፈ። ሰለሞን አልቻለም ወደቀ። ጥሩነሽ ሆዱን ሶስት ጊዜ በስለት ወጋችው። ሆዱን ብቻ ሳይሆን በጭካኔ ደረቱ ላይም ስለቱን አሳረፈች።
ሁለቱ ነፍሰ በላዎች የወዳጃቸው እጅ ላይ እጃቸውን አሳረፉ። የሰለሞን ሕይወት ማለፉን ሲያውቁ ሃምሳ አለቃ ደረጄ ወደ እናቱ ቤት ሲሔድ ጥሩነሽ ወደ ቤቷ አቀናች። ግን ቀኑ ቀና አልሆነላትም። በአጋጣሚ በጠዋት ለሩጫ ልምምድ የወጣው አትሌት የሰለሞንን አስክሬን አግኝቶ ለፖሊስ ጠቆመ። የሰለሞን የጓደኛቸው የአስተዋዩ፣ ሰዎችን ሁሉ በፍቅር የሚቀርበው እና ከሁሉም ጋር በሰላም የሚኖረው ሰለሞን ሕይወቱ በገዛ እጃቸው አለፈ። ነገር ግን ይህንን ሁሉ መርማሪው ቡድን ሊያገኝበት የሚችልበት ዕድል ዝግ ነበር።
የጥሩነሽ ቃል
እንደ ሃምሳ አለቃ ደረጄ ሁሉ ጥሩነሽም በአርሲ ዞን መርማሪ ቡድን የተለያዩ ጥያቄዎች ይዥጎደጎዱላት ጀመር። መልሶቿ አጭር እና ድፍን ነበሩ። ከሰለሞን ጋር ከመሞቱ በፊት አብራ እንደነበረች ተናገረች። በመጨረሻ በደንብ የተጠራጠረው የምርመራ ቡድን የተናገረችው ሁሉ ውሸት መሆኑን በመግለፅ ሃምሳ አለቃ ደረጄ ሁሉንም እንደነገራቸው ሲገልፅላት ማልቀስ ጀመረች። ‹‹ያሳሳተኝ ራሱ ነው።›› አለች። ይሔኔ የምርመራ ቡድኑ አባላት በሙሉ የድል አድራጊነት ስሜት ተሰማቸው። ጥያቄያቸውን ሲቀጥሉ ጥሩነሽ ይህንን ድርጊት የፈፀሙት ሰለሞን በሚሊሻነት ጊዜው የተሰጠው ታጣፊ ክላሽን ለማግኘት ብቻ መሆኑን እና ሃምሳ አለቃ ደረጄ ክላሹን ሽጠን ብዙ ብር እናገኛለን በማለቱ ሰለሞንን እንደገደሉት አመነች። ብዙ ጊዜ ክላሹን ሽጥ ሲሉት እምቢ ስላላቸው እነርሱ ሽጠው ለመጠቀም በመፈለጋቸው ወንጀሉን ለመፈፀም መነሳታቸውንም በዝርዝር አስረዳች።
ውሳኔ…
ፖሊስ የምርመራ ስራውን አጠናቆ መረጃውን አደራጅቶ ለፍርድ ቤት አቀረበ። በእነ ሃምሳ አለቃ አቅጣጫ አሳችነት ዛቻ ይሰነዝር ነበር በመባል በጥርጣሬ ተይዞ የሰነበተው ደምሴ ባንጃው ከነባለቤቱ ድርጊቱን እንዳልፈፀመ ተረጋግጦ በነፃ ተሰናበቱ። ሃምሳ አለቃ ደረጄ ብርሃኑ እና ጥሩነሽ ደስታ ግን እያንዳንዳቸው የሃያ አምስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014