የምናብ ታሪካችን ወደ ችሎት ይወስደናል:: ለመጀመሪያ ጊዜ በፍርድ ቤት ችሎት ለመገኘት የተገኙ እናትን በችሎት የተነገረ አስተያየትን:: እኒህ እናት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ስለ ብዙ ጉዳይ የሆነን ሰፊ ሰልፍ ተመልክተዋል:: ቀበሌ ሄደው ከሸማቾች ለመግዛት ተሰልፈዋል:: ዳቦ ለመግዛት ተሰልፈዋል:: አውቶብስ ወረፋ ለመያዝ ተሰልፈዋል:: ዛሬ ደግሞ ፍርድ ቤት መጥተው በሰው ጋጋታ ውስጥ ናቸው:: ፍርድ ቤትም የሰው ጋጋታ ይኖራል ብለው ፈጽሙውኑ አልጠበቁም:: የፍርድ ቤቱ መዝገብ ክፍል እጅግ ብዙ በሆነ መዝገብ ተሞልቶ ሲመለከቱ ግርምትን ፈጥሮባቸዋል:: በየችሎቱ ስማቸው እየተጠራ ለመግባት ጥሪ የሚጠብቁትን የሰዎችን ትርምስምስ ተመልክተው እርሳቸውን ለፍርድ ቤት በር የዳረጋቸውን ጎረቤታቸውን “ምን አደርኩህ ልጄ?” አሉት:: እርሳቸው የሚያውቁት እንደ ባህላችን በሽማግሌ ችግርን እየፈቱ በይቅርታም ሁሉም አሸናፊ እየሆኑ የሄዱበትን አግባብ ነው::
እማማ ከችሎት ያስገኛቸው ሁለት ተከራዮቻቸው እርስ በእርስ ተጣልተው አከራዮን እናት ምስክር ሆነው መጠራታቸው ነው:: እማማ በትርምሱ ውስጥ ሆነው ንግግራቸውን በመቀጠል “ልጆቼ እዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ ከመግባት ምናለ በጓዳችን መክረን ችግራችንን ብንፈታ? እዚህ እንግልት ውስጥ በመግባት ጊዜያችሁን ገንዘባችሁን ለምን ታጠፋላችሁ? በመነጋገር ችግራችንን ፈተን በይቅርታ ብናልፈው አይሻልም?” አሉ:: ከሳሽ ተከራይም ለምስክርነት የጠራቸውን አከራዩን “እማማ በይቅርታ ችግሩን መፍታት ያሉት እንኳን ይቅር፤ ይቅርታ እያልን አንተም ተው አንተም ተው በሚል ነገሮች እየተባባሰባቸው ሄዱ እንጂ መፍትሔ አላመጣም:: ያለኝ አማራጭ በህግ ፊት መፋረድ ነው::” አላቸው::
እማማም “ይቅርታው እንኳን ይቅር” የሚለውን አገላለጽ መላልሰው እያሰቡ ብዙ በሃሳብ ሄዱ:: በይቅርታ በሕይወት ዘመናቸው ያለፉትን ትልልቅ ጥፋት እያሰቡ ከራሳቸው ጋር አወሩ:: ደም የተቃቡ ሰዎች እንኳን ነገራቸውን በሽማግሌ እግር ስር አስቀምጠው ችግርን እየፈቱ በኖሩበት ዘመን ውስጥ እንዲህ ቀላል ጉዳዮች ወደ አደባባይ ደርሰው ወረፋ ሲይዙም አስገረማቸው:: ይቅርታ ሲቀር አብሮ መኖር የማይቻልበት እርስ በእርስ በጎሪጥ እየተያዩ መመላለስን የሚያመጣ አንዱ አሸናፊ ለመሆን ሌላውም ላለመሸነፍ ሁሉም ተሸናፊ ሆኖ እንደሚኖር በመረዳት ከራሳቸው ጋር መከሩ::
ችሎቱ ድረሱ ባላቸው ሰዓት ቢደርሱም ችሎቱ በሰዓቱ ሊጠራቸው ባለመቻሉ የመድኃኒት ሰዓት ደረሰባቸው:: አዛውንቷ አከራይ ለጡረታቸው ብለው የሰሯቸውን የሰርቪስ ክፍል ቤትን በማከራየት ገቢ ያገኛሉ:: የተከራዮቻቸው ጸብ ወደ ችሎት አምጥቷቸው የመድኃኒት ሰዓታቸውን አዛባባቸው:: ይህም ችሎቱ የማይመዘግበው ወጪያቸው ነበሩ:: የችሎቱ ሰዓት ደርሶም ተጠሩ:: የምስክር ቃልም መሰማት ጀመረ እማማም ወደ ዳኛው እየተመለከቱ “ልጄ እኔ ምስክር ሆኜ የመጣሁት ያየሁትን ለመመስከር ነው:: እርሱንም አደርጋለሁ:: ነገር ግን የእናንተንም ሰዓት ላለመሻመት ሁሉንም ነገር ሰዎች እዚህ ይዘው ሲመጡ ለምን ትቀበላላችሁ? አንዳንዱን በአካባቢ ሽማግሌዎች በወጋችን ለምን አንፈታውም? አሁን እኔም የመድኃኒት ሰዓቴ ደርሶ እዚህ መምጣቴ አግባብ ነው? እንዴት ሰው ተነጋግሮ ይቅርታ በመጠያየቅ ውስጥ ያለውን ግሩም መፍትሔ ትቶ ይጠላለፋል?” አሉ:: የችሎቱ ዳኛም የችሎት ስርዓትን አላከበሩም ብሎ ከዚህ በላይ እንዳይናገሩ አስቆማቸው::
እማማም ዳግመኛ “እግሬን አላነሳም” እያሉ ከራሳቸው ጋር እያወሩ ምስክርነታቸውን አሰምተው ተመለሱ:: ሁለቱም ተከራዮች ወደ ሰፈር ሲመለሱ እማማን ማንገላታታቸው ያስቆጫቸው በመሆኑ እማማን ሽማግሌ አድርገው ነገራቸውን ለመፍታት ተስማሙ:: እማማ በሽምግልናቸው ካሳ ቢበይኑ ለመካካስ፤ ይቅርታም በቦታው ስራውን እንዲሰራም ተስማሙ:: እንደ እማማ አይነት የሚገስጽ ኖሩ ችግሮችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መፍታት ቢቻል ምንኛ መልካም በሆነ ነበር:: አለመግባባትን በመቀነስ፤ ሲፈጠርም በአነስተኛ ዋጋ ለመፍታት በመስራት::
አለመግባባት
የሰዎች ልጅ በረጅም ታሪኩ ውስጥ ግጭት በጉልህ የሚታይ ነው:: የሰው ልጅ ከግጭት ተፋቶ መኖር የማይችል ነው ብለን መደምደም እስክንችል ድረስ የሚያደርስ የግጭት ታሪክ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጉልህ ይገኛል:: ሰው አጠገቡ ካለው ሰው ጋር የመወዳጀትም ሆነ የመጋጨትን ጊዜዎችን ሊያሳልፍ ይችላል፤ ደግሞም ነው:: አለመግባባት አድጎ ወደ ግጭት ሲያመራም ኪሳራው ይከተላል:: ኪሳራውም በቀላሉ የሚከፈል ወይንም ፈጽሞውኑ የማይከፈል ሆኖም ያልፋል:: የሰው ልጅ ሕይወት ፈጽሞውኑ የማይከፈል ኪሳራ ውስጥ ተመድቦ እናገኘዋለን::
ግጭት ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ እየቀጠፈ ባለበት በዚህ ጊዜ ስለግጭት ማስረዳት አንባቢውን ማሰልቸት ሊሆን ይችላል:: የግጭት መነሻ የሚሆንን አለመግባባትን ወደ መግባባት ለመቀየር ሊሰራ የሚገባው ስራ ካልተሰራ አለመግባባት ግጭትን እያበዛ የሚቀጥል መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው::
አለመግባባት በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችል ሲሆን ዋናው ጉዳይ ግን አለመግባባት እንዳይፈጠር ለማድረግ መሞከር፤ ከተሞከረም ፍሬያማ በሆነ በአነስተኛ ዋጋ ሊፈታ የሚችልበትን መንገድ መፈለግ ነው:: አለመግባባት ወደ ውጤት እንዳይመጣ የሚያደርገው ኢፍትሃዊነት ዋናው ጉዳይ ነው:: አንድ አካል እኔ ብቻ የፈለኩትን ላድርግ አንተ ግን ፍላጎትህን አምቀህ ኑር ቢል ይህ ኢፍትሃዊነትን አለመግባባትን፤ አለመግባባትም ግጭትን ይፈጥራል::
ከትላንት ታሪካችን እንደ አገር መማር እንዳንችል በአብዛኛው አንዱ የሌላኛውን ጥፋት ለማሳየት የሚሄደውን ያህል ራሱ ምን ያህል ለችግር አስተዋጽኦ እንዳደረገ መመልከት አለመቻሉ ነው:: እያንዳንዱ ሰው የሚፈጥረውን ኢፍትሃዊነት ወደ ጎን አድርጎ ሌሎች የሚፈጥሩትን ኢፍትሃዊነት የምናጎላ ከሆነ ወደ መፍትሔ መድረስ ሳንችል ቀርተን በአለመግባባትና በግጭት አዙሪት እንከርማለን:: የመፍትሔ መንገዱ ብዙ ቢሆንም በዚህ ጽሁፍ የፍላጎት ልዩነትን ማጥበብንና የይቅርታን በር እንደ መፍትሔ እናነሳቸዋለን::
የፍላጎቶች ልዩነት
በአካባቢያችን ያሉ ልጆችን ስንመለከት ከምንረዳቸው ነገሮች መካከል አንዱ እርስ በእርስ የሚኖራቸው ግጭት የሚነሳበት ዋና ምክንያት ይገኛል:: ልጆች አብረው ሲሆኑ ሲጫወቱ፣ ሲያጠኑ ወይንም ሲመገቡ በአጠቃላይ በሰላም ቆይተው በቅጽበት ድብልቅልቅ ያለ ጸብ ውስጥ ገብተው ልናገኛቸው እንችላለን:: ቅድም ደማቅ በሆነ ጨዋታ ውስጥ የነበሩት ልጆች እንዴት በቅጽበት ጩኸት ወደ በረከተበት ጸብ ሊያመሩ ቻሉ ብለን ብንጠይቅ ምላሹ ከመካከላቸው አንዱ ኢፍትሃዊነት የገጠመው መሆኑን እንረዳለን:: ልጆቹ በተስማሙበት ህግ መሰረት ጨዋታው ሳይሄድ ሲቀር፤ አንዱ ልጅ የእርሱን ድርሻ የተነጠቀ ሲመስለው ወዘተ ግጭት ይፈጠራል:: የቅድሙ ፍቅር በቅጽበት ወደ ጸብ ይቀየራል::
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ኢፍትሃዊነትን መቀበል የማይችል በመሆኑ የፍላጎቶች ልዩነት መኖሩ የሚያመጣው አለመግባባት በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: መፍትሄው ፍትሃዊነትን በማስፈን ፍላጎትን ማቀራረብ እንጂ አስቀድሞ የሆነውን በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ አይደለም:: ህጻናት ለመቀበል የሚቸግራቸውን ኢፍትሃዊነት አዋቂ ሰው በተለይም የእውቀት ነጻነት የመረጃ ፍሰት ከፍተኛ በመሆነበት ዘመን ሊቀበል የሚችልበት እድሉ አነስተኛ ነው:: በመሆኑም አለመግባባትን እየፈታን ሰላማዊ ህይወትን በግላችን፣ በቤታችን፣ በሥራቦታ ወዘተ መኖርን ስናስብ ልናስብ የሚገባው እውነት ፍላጎቶቹን የማቀራረብን ጥቅም ነው::
የዛሬ 28 አመት በሩዋንዳ ውስጥ በእያንዳንዱ ቀን ከአስር ሺ በላይ ሰዎች ይጨፈጨፉ ነበር:: ብሔርን ማእከል አድርጎ የተነሳው ግጭት ለሦስት ወራት ያህል ቀጥሎ ከአንድ ሚሊዮን የማያንሱ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ ምድሪቱ በደም ጎርፍ ተመታ ነበር:: ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች እንደ አንዱ ከሞት ጋር ፊት ለፊት እንደተገናኘ ሰው ሆነን ራሳችንን ስንመለከት ለሰላም የሚሰጥ ዋጋ ያለውን ቦታ እንረዳለን:: በጭንቅ ሰዓት የሰላም ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑን እንገነዘባለን:: ሰውን በግፍ ከመጨፍጨፍ መለስ በጥሞና ፍላጎቶችን ማቀራረብ ላይ መስራት ቅድሚያ ቢሰጠው ኖሮ በታሪክ ውስጥ አንካሳ ታሪክን ጥሎ ማለፍ ባልሆነ ነበር::
በመግቢያችን ላይ ያነሳነው የፍርድ ቤቶች መኖር ለሰላም ያላቸው አስተዋጽኦ ቀላል ባይሆንም ፍትህን ለማግኘት ውድ በሆነበት ሁኔታ፤ የፍትህ ስርዓቱም አሸናፊና ተሸናፊ ብሎ በሁለት ጎራ ከፍሎ መዝገቡ በሚዘጋበት ሁኔታ፤ ፍላጎትን አቀራርቦ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መንገድ ላይ መገኘትን አዳጋች ሊያደርገው ይችላል:: የፍላጎቶች ልዩነት በሰፋ ቁጥር ግጭት አይቀሬ መሆኑን ስንረዳ አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ የማሰብን የወርቃማውን ህግ መሰረታዊነት እንረዳለን::
አንዳችን በሌላችን ጫማ
“ጎረቤቴ የሚለቀው ፍሳሽ ለጤናዬ እክል ሆነብኝ”፤ “ጎረቤቴ የሚሰማው ድምጽ ሰላም ነሳኝ”፣ “ከጎረቤቴ የሚመጣው ጭስ አላስተኛ አለኝ” ወዘተ ብለው ሰዎች ፍትህን ፍለጋ ወደሚመለከተው አካል ከመሄዳቸው በፊት በሌላኛው ጫማ ውስጥ ቢኬድ ጥሩ ይሆን ነበር::
አንዳችን በሌላችን ጫማ ሆነን ማሰብ በተሳነን ጊዜ ተጎድቼያለሁ የሚለው ሰው አለኝ በሚለው መንገድ ፍትህን ይፈልጋል ወይንም የሚፈልገውን ለማድረግ ጥረት ያደርጋል:: አንዳችን በሌላችን ጫማ ሆነን ስንገኝ የሰላም አየር አካባቢያችንን ይከበዋል:: በተፈጥሮ እናት ለልጆቾ አንዳች ጥቅምን ፈልጋ ብዙ እርቀት ትሄዳለች:: ሰው ሁሉ ይህን እርስ በእርሱ ማድረግ ባይችል እንኳን በሞራል ህግ ለእኔ እንዲሆን የምፈልገውን ለሌላው፤ በእኔ ላይ እንዲሆን የማልፈልገውን በሌላው ላይ ወዘተ ብለን ማሰብ ይኖርብናል::
ዋልት ዴዝኒ “አንድን ነገር ለመጀመር ዋናው ነገር ማውራትን አቁሞ የተግባር እርምጃን ማድረግ ነው” እንደሚለው አንዳችን በሌላችን ጫማን ለመተግበር የሚፈልገው የተግባር እርምጃን ብቻ ነው:: ግጭትን ለመፍታት በመሄድ ውስጥ አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ መሆናችን ጥቅሙ ለሁሉም ነው:: ይህም ሁሉ ሆኖ በሰዎች መካከል በተለያየ ምክንያት ግጭት ሊፈጠር ይችላል:: በተለይ ከእኛ የሚጠበቀውን ተወጥተን ነገር ግን አይቀሬ የሆነ ግጭት ውስጥ ስንገባ መፍትሔው አንዳችን በሌላችን ላይ ቢላ መሳል ሳይሆን ተነጋግሮ በይቅርታ ፋይሉን መዝጋት ነው::
ይቅርታ አይቅር ብለን የምናነሳው ነጥብም የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ የሆነበት ምክንያት በይቅርታ ውስጥ ያለውን መንፈሳዊም ሆነ ሥነ-ልቦናዊ ጥቅምን በማሰብ ነው:: ለእኛ እንዲሆን የምንፈልገው ስለሆነ:: የሰው ልጅ የጋራ ኑሮ ያለ ይቅርታ ትርጉም ሊኖረው ስለማይችል፤ ይቅርታ አይቅር ብለን ንባባችንን እንቀጥል::
ይቅርታ አይቅር
ኔልሰን ማንዴላ የሕይወት ታላቁ ክብር “ፈጽሞ አለመውደቅ ሳይሆን በወደቅን ቁጥር መነሳት መቻል ነው” ማለቱ ከመውደቅ መነሳት ዋና በመሆኑ ነው:: ይቅርታ ደግሞ ከውድቀት የመነሻ አንዱ ነገር ነው:: ሩዋንዳን ያለፉት 28 አመታት የሚሊዮን ዜጎቿን ሕይወት የቀጠፈውን ታሪክ በየአመቱ እያስታወሰች ምን ሆነን ነበር ትላለች:: ምን ሆነን ነበር የሚለው ጥያቄ ያኔ የመጀመሪያው ቢላ ከሚሳልበት ቅጽበት በፊት ቢሆን ኖሮ ምንኛ ጥሩ በሆነ ነበር:: የሆነው ከሆነ በኋላ ግን ችግሩን በይቅርታ ለመፍታት የሄደችበት መንገድ አስተማሪ ነው::
በደቡብ አፍሪካም ታሪክ ውስጥ ለይቅርታ የተሰጠው ቦታ አስተማሪነቱ ብዙ ነው:: የከበደውን ቁስል ግን በይቅርታ በማለፍ አዲስን ምእራፍ በስምምነት የመክፈት ምእራፍ:: ይቅርታ ያለውን ትልቅ ቦታ የምንረዳው የግድ ጉዳዩ በአገር አቀፍ ደረጃ ባለ ጉዳይ ስለሆነ አይደለም:: ዛሬ ብዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር ያለንን ሰላም መሆን መርምረን የይቅርታ ጉዞችንን መፈተሽ ይኖርብናል:: በመነጋገር እና ትላንትናን በእውነተኛ ይቅርታ በመዝጋት ወደ ውጤት ነገሮችን ማምጣት ይቻላል:: ይቅርታ አይቅርም የምንለው ለዚህ ነው::
የይቅርታ በቦታው መገኘት እረፍቱ ለበዳይም ለተበዳይም መሆኑን ስንረዳ የሕይወታችን መገለጫ እናደርገዋለን:: በዳይ ጥፋቱን እንዲረዳ የሚያደርገው፤ ተበዳይም በሞራል ልእልና ውስጥ ገብቶ ነገሮን ትቶ የሰላምን ኑሮ እንዲኖር የሚረዳው ነው:: ግጭት የማይኖርበትን ጊዜ ምድር ላይ ከማለም ግጭት እንዳይፈጠርና ከተፈጠረም እንዴት ሊፈታ እንደሚገባ ማሰቡ የተሻለው ነው:: የተሻለውን መንገድ በእርግጥም የተሻለ መሆኑን የሚያስረዳው የይቅርታ አቅም ነው::
መጽሐፍ ቅዱስ ለይቅርታ የሚሰጠውን ቦታ ከፍ አድርጎ ማስቀመጡን የምንረዳው ተበዳይ ወደ በደለው ሰው ሄዶ ይቅርታን እንዲያደርግ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው:: በዳይ ወደ ተበዳይ ወይንስ ተበዳይ ወደ በዳይ የሚለውን አንባቢ በጥንቃቄ እንዲያስተውል እጠይቃለሁ:: ምላሹ ተበዳይ ወደ በዳይ የሚል ነው:: በዳይ ወደ ተበዳይ መጥቶ የሚጠይቀውን ይቅርታ ሁላችንም የምናውቀው ቢሆንም በተቃራኒው ሲሆን ግን ግርታን የሚፈጥር ሊሆን ይችላል:: ይህ የሚያሳየው ለይቅርታ ሊሰጥ የሚገባው ቦታ ከፍተኛ መሆኑን ነው::
እያንዳንዳችን ለይቅርታ ያለንን ቦታ እንፈትሽ? በትዳር ሕይወታችን ውስጥ ይቅርታ ምን ያህል እየተጠቀምንበት ነው? በሥራ ቦታስ? በምንሳተፍበት የትኛውም አይነት ማህበራዊ መስተጋብርስ? ምናልባትም ከራሳችንስ ጋርስ? አንዳንዴ ግጭቱ ከራሳችን ጋር ይሆንና ለራሳችን ይቅርታን ማድረግ ተስኖን ራሳችንን ለመቅጣት የምንሄድበት መንገድ አለ:: ራሳችንን በመጣል የምንሄድበት መንገድ ራስን የመቅጫ መንገድ ሆኖ ሊታይ ይችላል::
ይቅርታ አይቅር ብለን ከራሳችን ተነስተን ወደ ውጭ ወጥተን ስንሄድ የምናየው የሰላም አየር ያልተለመደ ሆኖ እናገኘዋለን:: በሰላም ውስጥ፤ ነገሮች መስመር በያዙበት ሁኔታ ያልተፈታ ችግር በግጭት ውስጥ ሊፈታ የመቻል እድሉ አነስተኛ ነው:: ስለሆነም በጭንቅ ውስጥ ላለሽ አገሬ ይቅርታ አይቅር እላለሁ:: ለአንባቢው ለአንዱ ሰው:: ደግሞሙ ለሁሉም:: ፍላጎትን በማቀራረብ፣ አንዱ በአንዱ ጫማ ውስጥ በመሆን ይቅርታን ይዘን ወደ በደለን በመሄድ::
ይህ በሆነ ጊዜ ጎልማሶቹ ስራቸው ላይ የሚያተኩሩ፤ አዛውንቷን ለሽምግልና እንጂ ለማንገላታት ምክንያት የማይሆን፤ ታማሚዎች በአግባቡ አስታማሚ የሚያገኙ መድኃኒታቸውን በጊዜ የሚወስዱበት፤ ልጆች በሰላም ተጫውተው በሰላም ተጋጭተውና ታርቀው ተፈጥሮ ስራዋን በአግባቡ የምትሰራበት ይሆናል:: ይህ እንዲሆን ጣታችንን ወደ ሌላው ከመቀሰር ወደራሳችን አድርገን ይቅርታ አይቅር ብለን እንነሳ:: ታሪካችን ሁሉ እንዲህ እየሆነ ሌላ ምን ልንል እንችላለን::
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014