ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት የሚገኝባት አገር ናት። ይህ ቁጥር ታዲያ አንድም እንደ መልካም እድል ሁለትም እንደ ስጋት ይቆጠራል። በርካታ ቁጥር ያለው ትኩስ ሃይል ወደ ሥራ ቢሰማራ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚያሳድግ በመሆኑ እንደመልካም አጋጣሚ ሊቆጠር ይችላል። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ለዚህ ትኩስ ሃይል በበቂ ሁኔታ የሥራ እድል መፍጠር ካልቻለ መልሶ ስጋት የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው።
መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር በርካታ ጥረቶችን ቢያደርግም የሚጠበቀውን ያህል አመርቂ ውጤት አላመጣም። የወጣቱ ተደጋጋሚ የሥራ እድል ጥያቄም በቂ ምላሽ ባለማግኘቱ ወደ ተቃውሞ ተሸጋግሮ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት የመንግሥት ለውጥ አስከትሏል።
ባለፉት አራት ዓመታት የለውጡ መንግሥት በብዙ መናወጥ ውስጥ ሆኖ ለወጣቱ የሥራ እድል ለመፍጠር መጠነኛ ጥረቶችን ቢያደርግም ጀመረው እንጂ ገና ብዙ ይቀረዋል። በተለይ ደግሞ ወጣቱ የራሱን ሥራ እንዲፈጥር ማበረታቻዎችንና ድጋፎችን ከማድረግ አኳያ የጀመራቸውን እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የብዙዎች አስተያየት ነው። በዋናነት ደግሞ መንግሥት ለሥራ ፈጠራ አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት እንደሚገባው በዚህ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ይጎተጉታሉ።
አቶ መቅደላ መኩሪያ በቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ የማርኬቲንግ መምህርና በኢምፓክት የኢንተርፕረነርሺፕ ፕሮግራም የቢዝነስና የፋይናንስ አማካሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ሥራ ፈጠራን ማበረታታትና ማስፋት የሚቻለው በትምህርት ፕሮግራሞች፣ በተለያዩ የሚዲያ ዝግጅቶችና መድረኮች ላይ በማካተትና ዓላማ አድርጎ በመስራት ነው።
የሥራ ፈጠራን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ አካቶ ማስተማር ሳይሆን ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ልጆች እንዴት ሥራን መፍጠር እንደሚችሉ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል።
የትምህርት ሥርዓቱ፣ የሚዘጋጁ የሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና የጋዜጣ ፕሮግራሞች ችግር ላይ ብቻ አተኩረው መፍትሄ የማያሳዩ ከሆነ አሁን የሚታዩ የስራ አጥ ችግሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ። የትምህርት ተቋማትም የተማሪዎችን ክሂሎት ማዳበር ላይ ብቻ እንጂ ክሂሎታቸውን መመንዘር የሚያስቻለቸው ብቃት እንዲኖራቸው እየሰሩ አይደሉም።
ከዚህ አንፃር በተለይ ሥራ አጥነትን ለመቀነስና ከተቀጣሪነት አባዜ ለመላቀቅ ችግሮችን ከመስበክ ይልቅ ችግሮችን በማሳየት መፍትሄ ማምጣት የሚችል አእምሮ ላይ መሥራትና መኮትኮት ያስፈልጋል። ሚዲያዎችም በሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል። ተቋማትም ማሕበረሰቡ ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ወጣቶችም ከተቀጣሪነት አስተሳሰብ ወጥተው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ሥራን የመስራት ባህልና ሥራን ማክበር ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። ይህም ለመስራት ካሰቡት ጋር የተገናኘ ተቋም ላይ ሄደው በነፃ ማገልገልን ይጨምራል። ከዚህ በተቃራኒ እጎዳለሁ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ሥራ መፍጠር አይችሉም።
ሥራ ለመፍጠርና አዲስ መንገድ ለማምጣት ጊዜያቸውን በሥራ ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል። ለሚያመጡት ሃሳብ ሌሎች የተሻለ መንገድ አላቸውና ከእነሱ ምን እማራለሁ ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል። አለማወቃቸውን ሲያውቁም ነው ወጣቶች የተሻለ ቦታ መምጣት የሚችሉት።
እንደአማካሪው ገለፃ ሥራ ለመፍጠር በአብዛኛው የተመቹ ፖሊሲዎች አሉ። ሥራውን ማስቀጠል ላይ ፖሊሲዎቹ ምን ያህል ያግዛሉ የሚለውን ግን መፈተሽ ያስፈልጋል። ንግድ ፍቃድ ማውጣት ቀላል ቢሆንም ንግዱን ማሻገርና ማስኬድ ሲፈለግ ግን በርካታ እንቅፋቶች አሉ። በዚህ ረገድም ብዙ መሥራት ያስፈልጋል።
በእያንዳንዱ የሥራ ፈጠራ ዘርፎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የምክክር መድረኮችን በየጊዜው ማዘጋጀት ያስፈልጋል። አልፎ አልፎ በተቋማት ደረጃ ነጋዴንና የንግድ መፍትሄ ሃሳብ ይዘው የመጡ ተቋማትን በጅምላ የማየት ችግሮች ይታያሉ። እንዲህ አይነቱ አመለካከት ካለ ደግሞ ጎታች በመሆኑ ማስቀረት ይገባል።
ሌሎች አገራት የሥራ ፈጠራን ማሳደግ የቻሉት የንግድና አዳዲስ ሃሳቦችን ወደ ገበያ መምጫ መንገዶችን ስላቀለሉና የማዝለቂያ መንገዶችንም በማመቻቸታቸው ነው። ከዚህ አኳያ በነዚህ ነገሮች ላይ መስራት ያስፈልጋል። ይህ ሲባል ግን የመንግሥት ተቋማት ግዴታ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ሁሉም በዚህ ዘርፍ ላይ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተለይም የፋይናነስ፣ ሎጀስቲክስና የተለያዩ የንግድ ተቋማት የየራሳቸውን ሚና መጫወት አለባቸው።
በብሩማይንድስ አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ለማወርቅ ዴክሲሶ እንደሚሉት ድርጅቱ የፕሮጀክቶችን መነሻ ዳሰሳዎችን፣ የአጋማሽና መጨረሻ ምዘናዎችን እንዲሁም የማማከር ሥራዎችንና ሥልጠናዎችን ይሰጣል። የቢዝነስ ልማት አገልግሎትና ሥራ ፈጠራ ላይም ትኩረት አድርጎ ይንቀሳቀሳል።
ድርጅቱ ከተመሰረተ ወዲህ በየወሩ ‹‹ልዩ ምልከታ›› በሚል የሥራ እድል ፈጠራና የወጣቶች ሥራ ፈጣሪነትን ለማሻሻልና ለማስፋፋት ብሎም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ ያካሂዳል። በዚህ ወርም የመንግሥት አካላት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮችና የግል ተቋማት ተቀናጅተው የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እንዲቻል የምክክር መድረክ አካሂዷል።
እንደ አስተባባሪው ገለፃ በመጀመሪያው የውይይት መድረክ በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የፖሊሲ ማእቀፍ ክፍተት እንዳለ ለማወቅ ተችሏል። በዚህ ዙሪያ በመንግሥት፣ የግል ተቋማትና ድርጅቶች መካከል ተቀናጅቶ ያለመስራት ችግሮችም እንደሚታዩ ተረጋግጧል። ሆኖም በዚህ መድረክ እነዚህ ተቋማት በሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ተቀናጅተው የሚሰሩበትና ለፖሊሲ ግብአትነት የሚውሉ ነጥቦች ተገኝተውበታል።
የሥራ እድል ፈጠራ ጉዳይ ብሩማይንድስን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የሚመለከት በመሆኑ በሁለተኛው የውይይት መድረክ የበለጠ ግብአት ተሰብስቧል። ይህም ግብዓት የንግድ ፈጠራ የፖሊሲ ማእቀፍ እንዲኖረው አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በላፈ በመድረኩ የተሳተፉ ሥራ ፈጣሪዎችና ሥራ ለመፍጠር በዝግጅት ላይ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሥራ እድል ፈጠራን በምን መልኩ ማስኬድ እንደሚቻል ግብዓት አግኝተውበታል።
በዚህ የውይይት መድረክ የተሳተፉት በተለያዩ ፕሮጀክቶች ታቅፈው ሥልጠና የሚወስዱ ወጣቶች ሲሆኑ በቀጣይ በሚዘጋጁ ተመሳሳይ መድረኮች ለሌሎች ወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ በድርጅቱ በኩል እቅድ ተይዟል።
በኢትዮጵያ ትልቅ የሥራ እድል ፈጠራ አቅም ቢኖርም በዚህ ልክ የሥራ እድል ፈጠራው አላደገም። ለዚህም የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖር፣ መሬት የማሕበራዊና ፖለቲካዊ ተፅእኖ ያለው መሆንና ሌሎችም በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ከዚህ አንፃር የአሁኑን ጨምሮ በቀጣይ በሚካሄዱ ተመሳሳይ መድረኮች ከአካዳሚክና የምርምር ተቋማት፣ ከፖሊሲ አውጪዎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሃሳብ በመውሰድና ይህንኑ በማቀናጀት እሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ መድረስ ያስችላል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ መርጋ በበኩላቸው እንደሚገልጹት ተቋሙ በአዲሱ የመንግሥት አደረጃጀት ከአነስተኛና መካከለኛ ልማት ኤጀንሲ ወደ ኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ተቀይሯል። የዚህ ተቋም ዋነኛ ዓላማም ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ኢትዮጵያ በቀጣዩ አስር ዓመት የአምራች ኢንዱስትሪ ሽግግር ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ማገዝ ነው።
ከዚህ አኳያም ተቋሙ በተለይ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በአስተሳሰብና አመለካከት መለወጥ ላይ ይሰራል። ለሥራ አድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፤ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ይቀርፃል። ለአምራች ኢንዱስትሪውም የፋይናንስ፣ የመሬት፣ የማምረቻ ሼዶች አቅርቦትና ቴክኒካል ድጋፎችን ያደርጋል። ከኤክስፖርት ገበያው ጋር በተያያዘም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ወጣቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ይሰራል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የአገሪቱ አብዛኛው ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተንጠለጠለ እንደመሆኑ እስካሁን ባለው ሂደት በአገር አቀፍ ደረጃ 22ሺህ 800 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ ክልሎች ተፈጥረዋል።
በእነዚህም ከ600 ሺህ በላይ የሥራ አድሎች ተፈጥረዋል። ተጨማሪ አዳዲስ ኢንትርፕራይዞችም እየተፈጠሩ ይገኛሉ። ወደ ኤሜሪካና አውሮፓ ምርቶቻቸውን የሚልኩ ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር ተችሏል። በተለይ በኮቪድ ጊዜ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎችን፣ የእጅ መታጠቢያዎችንና ሳኒታይዘሮችን በማምረት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
በተመሳሳይ በጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ ምርትና በተቀነባበሩ የግብርና ምርቶችም ከፍተኛ እድገቶች ታይተዋል። ይሁንና አገሪቱ ካላት አጠቃላይ አቅምና የሕዝብ ብዛት አንፃር አስካሁን ያለው አድገት በጣም አነስተኛ ነው። ይህንኑ ሁኔታ ለመቀየርም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደረጃ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ይህም ኢንተርፕራይዞችን ያበረታታል፤ ምቹ ሁኔታም ይፈጥራል። አላሰራ ያሉ ውጣ ውረዶችን፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግሮችን በፍታት ረገድ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ሰፊ ወጣት (ከአጠቃላይ ሕዝቡ 70 በመቶ) የሰው ሀብት ያላት አገር እንደመሆኗ ይህ ትልቅ ገበያ በመሆኑ ሀብቱን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት በመሆኑ ይህን ሀብት በስፋት ለመጠቀም ወጣቶችን ከዚህ ሀብት ጋር በሕግ ማእቀፍ ማስተሳሰር ያስፈልጋል። ይህም ከውጭ አገር የሚገቡ በርካታ ምርቶችን ማስቀረት ያስችላል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት ቀደም ሲል የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በ1994 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ነበር። ሆኖም የወቅቱ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ፖሊሲው መሻሻል ስላለበት በአሁኑ ጊዜ ወቅቱን በሚመጥን መልኩ እየተሻሻለ ይገኛል።
መንግሥትም በራሱ ተነሳሽነት ባደረገው ልዩ ውሳኔ የወታደር የደምብ ልብሶች፣ የተማሪ የደምብ ልብሶችና ጫማዎች፣ የፖሊስና የልዩ ሃይል ደምብ ልብሶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ተደርጓል። መንግሥት የአገር ውስጥ ምርትን ወደ መጠቀም እያዘነበለ በመሆኑና ይህም በቀጣይ እየተጠናከረ ሲሄድ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2014