አዲስ አበባ፡- ሁሉም የአበባ እርሻ ልማቶች ዝቅተኛውን መስፈርት (የነሐስ ደረጃ) የማያሟሉ መሆናቸውን የአካባቢ፣ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ሆልቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር በበኩሉ በመስፈርቱ ዙሪያ ውይይት ያልተደረገበትና የመረጃ አሰባሰቡም ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት በመሆኑ ውጤቱ ተቀባይነት የለውም ሲል ገለጸ። ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት መስሪያ ቤታቸው የአበባ እርሻ ልማቶች ያሉባቸውን ችግሮች ለመለየት ባደረገው ቁጥጥርና ምልከታ የአበባ እርሻዎቹ ዝቅተኛውን መመዘኛ መስፈርት የማያሟሉና ያሉበት ሁኔታም እጅግ አሳሳቢ ሆኖ አግኝተውታል። በአካባቢ ህግ አተገባበር ላይ የታዩት ዘርፈ ብዙ ችግሮችም የማህበረሰቡ ጤና ላይ ስጋትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የአበባ እርሻ ልማቶቹ የአየር ንብረት መዛባት በማያስከትልና የሰዎችን ጤና በማይጎዳ መልኩ ሥራቸውን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው የእስከአሁኑ የአሠራር ሂደት ግን በአፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ መሆኑን አሳስበዋል። የአበባ እርሻ ልማቶቹ በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣አካባቢያዊ ተፅዕኖ በቀነሰ መልኩ ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ምክትል ኮሚሽነሯ ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በያዝነው ዓመት በ70 የአበባ እርሻ ልማቶች ላይ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ሠርቶ ሁሉም መመዘኛ መስፈርቱን ማሟላት አለመቻላቸውን ጠቅሰው፤ይህም አካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖውን ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
«የምርት ጥራቱን አሳድጎ ዘርፉን ተወዳዳሪ ከማድረግ አንጻር ብዙ መሥራት ይገባዋል» ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ የአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ተፅዕኖን በመከላከል በኩል የአበባ እርሻዎቹ የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላት አለባቸው፡፡ አንድ የአበባ እርሻ ልማት ማሟላት ያለበት ዝቅተኛው 13 መስፈርቶች ቢሆኑም በአንዱም ላይ ተሟልቶ አለመቅረቡ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከፍ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በአበባ እርሻ ልማቶቹ ይታያሉ የተባሉ ዋና ዋና ችግሮች አካባቢያዊ ኃላፊነት መዘንጋት፣ በእቅድ ላይ ያልተመሰረተ የመሬት አጠቃቀም፣ የአካባቢያዊ መረጃ አያያዝና አጠቃቀም ትኩረት ማነስ ፣ህጋዊ ስርዓት አለማሟላትና በየደረጃው የቁርጠኝነት ማነስ እና ሌሎችም ናቸው።
እስከአሁን መስፈርቱን ባላሟሉ የእርሻ ልማቶች ላይ የተወሰደ ዕርምጃ ባይኖርም ካሁን በኋላ ህጋዊነትን ተከትለው በማይሠሩ የአበባ እርሻ ልማቶች ላይ አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡ በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ሆልቲ ካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር የስልጠና ቡድን መሪ አቶ ሚኪያስ በቀለ የኮሚሽኑን ሃሳብ እንደማይስማሙበት ተናግረዋል። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ኮሚሽኑ መመዘኛ መስፈርቶችን ሲያወጣ የአበባ እርሻ አምራችና ላኪዎችን ያላሳተፈ እና የሃሳብ ስምምነት ላይ ያልተደረገበት በመሆኑ ነው። አሁን የሚቀርበውን አስተያየት መቀበል ከባድ መሆኑን
ገልጸዋል። በመሆኑም መስፈርቶቹን በድጋሚ መፈተሽ ይገባል ብለዋል፡፡ አቶ ሚኪያስ እንዳሉት የተቀመጡትን መመዘኛ መስፈርቶች የአበባ እርሻ ልማቶቹ ሊያምኑበት ይገባል፡፡ በምልከታ ወቅትም ኮሚሽኑ መረጃ ይሰበስብበት የነበረበት መንገድ የአበባ እርሻ ልማቶቹ ያልተስማሙባቸው እንደነበሩም ይገልጻሉ፡፡ «ሆኖም ግን ሁሉም የአበባ እርሻ ልማቶች መለከያ መስፈርቶቹን ያሟላሉ ለማለት አያስደፍርም» ያሉት አቶ ሚኪያስ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ዘርፉን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
ተገኝ ብሩ