ሻሸመኔ ላይ ሰው ገድለው በመስቀል በአስከፊ ግድያ ወንጀል የተከሰሱ ወጣቶች ላይ ሊመሰክር የነበረው ሰው ደብዛው ጠፍቶብኛል ሲል የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።
በሻሸመኔ ከተማ ነሐሴ ስድስት ቀን 2010 ዓ.ም አንድን ወጣት ቦንብ ይዟል በሚል ገድለው የዘቅዝቁ ወጣቶች መኖራቸው ይታወሳል። በዚህ በአሰቃቂ ግድያ ወንጀል ከተከሰሱ ስድስት ሰዎች መካከል ሁለቱ የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው እና የተቀሩት አራት ተጠርጣሪዎቸ ደግሞ ምስክሩ ደብዛው በመጥፋቱ በነጻ መለቀቃቸውን የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ ምክትል አቃቢ ህግ አቶ አሽማው ሰይፉ ገልጸዋል።
ተከሳኞች የምስክሩን ደብዛ አጥፍተዋል የሚል ግምት እንዳለ የገለጹት አቶ አሽማው፤ ምስክሩ ባስመዘገበው ስልክ ቁጥርም ሆነ በአድራሻው ተፈልጎ እስከአሁን ሊገኝ አለመቻሉን ተናግረዋል።
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ጨመሮ በግለሶችና በተቋማት የሚገኙ የምስል እና ድምጽ
ማስረጃዎች እንደምስክርነት ለምን ጥቅም ላይ አልዋሉም የሚል ጥያቄ ከአዲስ ዘመን የቀረበላቸው አቶ አሽማው፤ የምስልና ድምጽ ማስረጃዎቹ ከፖሊስና ከተለያዩ አካላት ለፍርድ ቤቱ መቅረባቸውን ተናግረዋል። ይሁንና ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ቅንብረ የተደረገበት ስለመሆኑ እና ስላለመሆኑ ማረጋገጫ ባለማግኘቱ ማስረጃው ፍርድቤቱን ሊያሳምን አልቻለም።
እንደ አቶ አሽማው ከሆነ፤ አራቱ ተከሳሾች በነጻ ቢለቀቁም የሰው ምስክሩ በተገኘ ሰዓት ክሱ መጀመሩ አይቀርም። በፍርድ ሂደቱ ላይ የአራቱ ሰዎቸ በነጻ መለቀቅ በአቃቤ ህግ በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ ይግባኝ ተጠይቄ ውሳኔ እየተጠበቀ ይገኛል።
በጌትነት ተስፋማርያም