የትምህርት ጉዳይ ሲነሳ አንዳንድ መሠረተ ሀሳቦች የሚታለፉ አይደሉም። ሁሉም እኩል አወዛጋቢዎች ናቸው። ሁሉም እኩል ተነሽና ወዳቂ ናቸው። ካስፈለገም ሁሉም እኩል የፖለቲካ መሣሪያዎች ናቸው። ይህ ደግሞ ለ’ኛ አዲስ አይደለም። “የትምህርት ተደራሽነት”፣ “የትምህርት ጥራት”፣ “የትምህርት ፍትሀዊነት”፣ “አግባብነትና ጥራት»፣ «የመምህራን ልማት»፣ «የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ”፣ የሚሉትን፤ በ”አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ” ላይ ሲወርዱ የነበሩ በረከትና መርገምቶችን ወዘተርፈ ሁሉ እናብራራ፤ ብንል ምንም አይበቃንም። በመሆኑም፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን “ትኩረቴ ውስጥ አስገብቼዋለሁ” ሲል ለአደባባይ ውይይት ያበቃውን “የትምህርት ጥራት” ጉዳይ እንመለከታለን።
ባለፈው ማክሰኞ ባለስልጣኑ በዲሊኦፖል ሆቴል አንድ (ሌሎች መድረኮችንም አዘጋጅቷል) መድረክ አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፣ የመድረኩ አላማም ለትጉሀንና ምዘናን ላለፉ መምህራንና የትምህርት አስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም ሱፐርቫይዘሮች እውቅና እና ሰርተፊኬት መስጠት ሲሆን፤ በመድረኩም አጠቃላይ ሂደቱን (በተለይም ከ2010 እስከ 2014 ዓ.ም ያለውን) እና መሆን ያለበትን ያመላከተ ጥናታዊ ሰነድ ቀርቦ የጋለ ውይይት ተካሂዶበት ነበር። (ለጊዜው የእኛ ትኩረት ሰነዱ ላይ ብቻ ይሆናል።)
በመድረኩ ላይ ሰነዱ (“የመምህራንና የት/ቤት አመራር የሙያ ብቃት ምዘናን አስመልክቶ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተዘጋጅቶ የቀረበ ሰነድ” የሚል)ን ያቀረቡት በባለስልጣኑ የመምህራን ምዘና ቡድን መሪ አቶ ሰንደቁ ያዛቸው እንደተናገሩት ተቋማቸው፣ “ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካትና ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት አንደኛው ተግባር የሆነውን የመምህራንና የት/ቤት አመራር ሙያዊ ብቃትን ማረጋገጥ ወሳኝ [በመሆኑ ለዚሁ ተግባር] ትኩረት በመስጠት፤ እንዲሁም፣ ለነባርና ወደ ሙያው ለሚገቡ ጀማሪ መምህራንና የት/ቤት አመራር ከትምህርት ይዘትና ከማስተማሪያ ስነዘዴ አንጻር የጽሑፍ እንዲሁም ለነባር መምህራንና የት/ቤት አመራር የማህደረ ተግባር ምዘናዎችን በመስጠት ክፍተቶችን ማመላከት የሚያስች[ሉ] ተግባራት[ን] እያከናወነ ይገኛል።” ምዘናውም “የመምህራንና የት/ቤት አመራር ሙያ ፈቃድ ምዘና በሁሉም፣ ከአጸደ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ የመንግሥት፣ የግል እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሠሩ መምህራን፣ ር/መምህራንና ሱፐርቫይዘሮችን እንዲሁም በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩ መምህራን ላይ የሚተገበር ነው።”
“ሌሎችስ የሉም?” ለሚለው በቀረበው ጥናታዊ ሰነድ ላይ መኖራቸው የተመለከተ ሲሆን “ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በመመሪያው መሠረት ምዘናው በግል ት/ቤቶች መምህራንና የት/ቤት አመራሮች ላይም እንዲተገበር የተደረገ ሲሆን ይህም መምህራን የሙያ ብቃት ምዘና ለመመዘን የሚያስችለውን መስፈርት ለማሟላት ተነሳሽነት እንዲኖራቸው እያደረገ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። ለዚህም በተለይም ወደ ማህደረ ተግባር ምዘና ለመግባት ሂደቱን በአግባቡ ለመምራት እንዲቻል ታሳቢ በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ፤ የአዲስ አበባ ከተማ መምህራን ማኅበርና የግል ት/ቤቶች ማህበር ተወካዮች የተገኙበት መድረክ በማዘጋጀት ሁሉም የየድርሻቸውን መውሰድ እንዲችል የጋራ በማድረግ ምዘናውን ማካሄድ ተችሏል።” በሚል ሰፍሮ ይገኛል።
ምዘናው የመምህራንና የት/ቤት አመራሮች የሚያካሂዱትን፣ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴዎቻቸውን ከተዘጋጁት ስታንደርዶች አንጻር እንዲሆን ጉልህ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፤ ከተከናወኑት የምዘና ውጤቶች አንጻር ሲታይም የተመዛኞች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን ያቀረቡት አቶ ሰንደቁ ከ2005 እስከ 2014 ዓ.ም የተከናወነን የመምህራንና የት/ቤት አመራር የሙያ ብቃት ምዘና ውጤትንም ለመድረኩ አቅርበዋል። እኛም ለጋዜጣው ገፅ በሚያመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ከ2005 – 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ነባር መምህራን ሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና ውጤት በትምህርት ዓይነትና በጾታ (ሰንጠረዥ 1)፤ ከ2005 – 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ነባር መምህራን ሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና ውጤት በትምህርት ዓይነትና በጾታ (ሰንጠረዥ 2) የቀረቡ ሲሆን በሁለቱም ሰንጠረዦች የቀረቡትን “በአጠቃላይ 11ሺህ 106 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነባር መምህራን የተመዘኑ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 35% ተመዛኞች ማለፊያ ውጤቱን (62.5% እና በላይ) ማስመዝገብ የቻሉ ናቸው። አፋን ኦሮሞ፤ ኬሚስትሪ፤ ባዮሎጂ እና ሥነ-ዜጋ የትምህርት ዓይነቶች ከ50% በላይ የሚሆኑት ተመዛኞች በጽሑፍ ምዘናው ማለፊያ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን፤ በስነ ጥበብ የትምህርት ዓይነት ደግሞ ማለፊያ ውጤት ማስመዝገብ የቻለ ተመዛኝ እንደሌለ ያሳያል።” በማለት ተብራርቷል። (የላይኛዎቹ ሰንጠረዦች በግራፎችም የተደገፉ ናቸው።)
ሰነዱ (በ”ሰንጠረዥ 3”) “ምዘና ከተጀመረበት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የጽሑፍ ምዘና የወሰዱ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ነባር መምህራንን ውጤት በዓ.ም እና በጾታ” ያስቀመጠ ሲሆን፣ ጠቅላላ ለምዘና ከቀረቡት (11ሺህ 106 (49.5% ሴት)) ያለፉ (≥62.5 %) 3ሺህ 849 (61% ወንድ)፣ ከ˂ 62.5 % ያመጡ 7ሺህ 257 (57% ሴት) እንደሆኑ ገልጿል።
ከሰንጠረዡ ቀጥሎ በቀረበው ማብሪያ እንደሰፈረው ከሆነ “በዘጠኝ ዙር የጽሑፍ ምዘና ከወሰዱት 11ሺህ 106 የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ነባር መምህራን መካከል ያለው ፆታዊ ተሳትፎ ተመጣጣኝ መሆኑን፤ ከተመዘኑት 11ሺህ 106 መምህራን ውስጥ ለማህደረ ተግባር ምዘና ማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 3ሺህ 849 (35%) መሆናቸው፤ በየአመቱ ከሚካሄደው ምዘና እንደሚታየው ማለፊያ ውጤት የሚያስመዘግቡት መምህራን ቁጥር በአብዛኛው እየጨመረ የመሄድ ሁኔታን ያሳያል። ይህም የሙያ ብቃት ምዘናው መምህራን በሙያቸው የተሻለ/ብቁ ሆነው ለመገኘት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ያሳያል።”
“2ሺህ 879 መምህራን ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ከ2008 – 2013 ዓ.ም በ6 ዙር ተመርቀው ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት የጽሑፍ ምዘና ወስደዋል። ከእነዚህ ውስጥ ማለፊያ ውጤት (70% እና በላይ) ያስመዘገቡት ወይም ብቁ የሆኑት 206 (7%) ናቸው። ይህም በእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት ውጤቱ ዝቅተኛ ሆኖ ይታያል።” (ሰንጠረዥ 4. ከ2008ዓ.ም—2013 ዓ.ም የሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና የተመዘኑ የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማ ተመራቂ አዲስ መምህራን ውጤት በትምህርት ዓይነትና በጾታ) የተሰጠው፤ እንዲሁም “ሰንጠረዥ 5” ተመሳሳይ ውጤትን የሚያሳይ ሲሆን፤ ይህም ምናልባትም በየጊዜው ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው የመምህራኑ የምዘና ውጤት ግብረ መልስ ዩኒቨርሲቲው የሰልጣኝ መምህራኑ ውጤት እንዲሻሻል ተጠቅሞበታል የሚል እምነት አለን።” የሚለውን ማብራሪያም የዚሁ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ታስቦና ታልሞ እየተሠራ ያለ ሥራ ከመሆኑ አኳያ እዚህ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የሚገባው አይደለም።
በአራት ዙር 2805 የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ነባር መምህራን የጽሑፍ ምዘና የወሰዱ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1ሺህ 700 (61%) መምህራን ለማህደረ ተግባር ምዘና ማለፊያ ውጤት (62.5% እና በላይ) ያስመዘገቡ መሆናቸውን በሚያሳየን “ሰንጠረዥ 6” ስር “ከተካሄዱት የአራት ዙር ምዘናዎች የተመዛኞቹ ውጤት የዚህ አመቱ ውጤት ከባለፉት ሦስት ምዘናዎች ዝቅተኛ ሆኖ ይታያል። ለዚህም ምዘናው አገር አቀፍ በመሆኑ ሌሎች ውስንነቶች እንዳሉ ሆኖ የምዘናው ፕሮግራም መለዋወጥ ነበርና ይህ እንደ አንድ ምክንያት ይሆናል ብለን ወስደናል። የሚለውንም ስለ ምዘናውና ተመዛኞች አጠቃላይ ሁኔታ እንረዳ ዘንድ የሚያግዝ ነው።
በሦስት ዙር በተካሄደው ምዘና 166 የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች አመራሮች የጽሑፍ ምዘና የወሰዱ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥትና የግል 2ኛ/ደ/ት/ቤቶች 591 አመራሮች ውስጥ 28% ሲሆን፤ ከተመዘኑት 166 (23 ሴት) የት/ቤት አመራር ውስጥ ለማህደረ ተግባር ምዘና ማለፊያ ውጤት (62.5% እና በላይ) ያስመዘገቡት 79 (48%) – 74 ወንድ – ናቸው። (ሰንጠረዥ 7)
በአራት ዙር በተካሄደው ምዘና 546 የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች አመራሮች የጽሑፍ ምዘና የወሰዱ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥትና የግል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች አመራሮች ውስጥ 29.5% ነው። ከተመዘኑት 546 የት/ቤት አመራር ውስጥ ለማህደረ ተግባር ምዘና ማለፊያ ውጤት (62.5% እና በላይ) ያስመዘገቡት 139 (25.5%) ናቸው። (ሰንጠረዥ 8)
የመምህራንና የት/ቤት አመራር የማህደረ ተግባር ምዘናን በተመለከተ ራሱን የቻለ መስፈርት ያለው ሲሆን፣ እሱም “ወደ ማህደረ ተግባር ምዘና የሚገቡት በጹሑፍ ምዘና ከ100% ውጤታቸው 62.5% እና በላይ ያስመዘገቡ ሲሆኑ፤ ይህም ወደ 80% ሲለወጥ 50 ይሆናል። የማህደረ ተግባር ምዘና ከ20% የሚያዝ ሲሆን ይህም ውጤት ከ80% + 20% ≥ 70% የሚያስመዘግቡ የሙያ ብቃት ሰርተፊኬት ያገኛሉ።” የሚለው ነው።
ከ2010 ዓ.ም-2014 ዓ.ም በአራት ዙር 4ሺህ 983 (1621 ሴት) ነባር መምህራን የማህደረ ተግባር ምዘና የወሰዱ ሲሆን ይህም ቁጥር የጽሑፍ ምዘና ከተመዘኑት ውስጥ (28 %) ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በ2014 ዓ.ም ለማህደረ ተግባር ምዘና የተዘጋጁ 3ሺህ 870 (78%) መምህራን (2ሺህ 485 ወንድ) በጽሑፍና በማህደረ ተግባር ምዘና ድምር ውጤታቸው 70% እና በላይ ማስመዝገብ በመቻላቸው የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘት የቻሉ ናቸው። ይህም መምህራኑም ከጽሑፍ ምዘና ውጤታቸው ይልቅ በማህደረ ተግባር ምዘና ውጤታቸው የተሻለ ማስመዝገብ በመቻላቸው አብዛኛው መምህራን በድምር ውጤታቸው 70% እና በላይ እንዲያስመዘግቡ ያስቻላቸው መሆኑን ያሳያል። (ሰንጠረዥ 9)
ከ2010 ዓ.ም-2014 ዓ.ም የት/ቤት አመራር የማህደረ ተግባር ምዘና ውጤትን በተመለከተ በሰነዱ ሰንጠረዥ 10 ላይ የተቀመጠ ሲሆን ከ2010 ዓ.ም-2014 ዓ.ም በአራት ዙር 220 (22 ሴት) የት/ቤት አመራር የማህደረ ተግባር ምዘና የቀረቡ ሲሆን ይህም ቁጥር የጹሁፍ ምዘና ከተመዘኑት ውስጥ (31%) ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 190 (90% (17 ሴት)) የት/ቤት አመራር በጽሑፍና በማህደረ ተግባር ምዘና ድምር ውጤታቸው 70% እና በላይ ማስመዝገብ በመቻላቸው የብቃት ማረጋገጫ ስርትፍኬት ማግኘት የቻሉ” መሆናቸውንና ይህም እንደ መምህራኑ የት/ቤት አመራሩም ከጽሑፍ ምዘና ውጤታቸው ይልቅ በማህደረ ተግባር ምዘና ውጤታቸው የተሻለ ማስመዝገብ በመቻላቸው አብዛኛው የት/ቤት አመራር በድምር ውጤታቸው 70% እና በላይ እንዲያስመዘግቡ እያስቻላቸው መሆኑ ተመልክቷል።
በመጀመሪያ ደረጃ የመንግሥትና በግል ት/ቤቶች የተካሄደን የጽሑፍና የማህደረ ተግባር ምዘና ሲታይ፡-
- የጽሑፍ 1ሺህ 838 (68%) የመንግሥት እና 882 (32%) የግል ት/ቤቶች መምህራንና የት/ቤት አመራር በድምሩ 2ሺህ 720 (1565 ሴት) ተመዛኞች ምዘና የወሰዱ ሲሆን፤
- የጽሑፍ ምዘና ከተመዘኑት ውስጥ 692 (38%) የመንግሥት እና 366 (41%) የግል ት/ቤቶች መምህራንና የት/ቤት አመራር በድምሩ 1ሺህ 058 (39% (734 ሴት፤ 323 ወንድ)) ተመዛኞች ለማህደረ ተግባር ምዘና ብቁ በመሆን 62.5% እና በላይ ውጤት አስመዝግበዋል።
- የማህደረ ተግባር ምዘና ከተመዘኑት ውስጥ 622 (34%) የመንግሥት እና 275 (31%) የግል ት/ቤቶች መምህራንና የት/ቤት አመራር በድምሩ 897 (33% (265 ሴት) ተመዛኞች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘት ችለዋል። (ሰንጠረዥ 11)
“በ2013 ዓ.ም የጽሑፍና በ2014 የማህደረ ተግባር ምዘና የወሰዱ የመንግሥትና የግል የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ነባር መምህራንና የት/ቤት አመራር ውጤት”ን በተመለከተ ሰነዱ “የጽሑፍ 931 (72%) የመንግሥት እና 365 (28%) የግል ት/ቤቶች መምህራንና የት/ቤት አመራር በድምሩ 1296 (1094 ወንድ) ተመዛኞች ምዘና የወሰዱ ሲሆን፤ የጽሑፍ ምዘና ከተመዘኑት ውስጥ 542 (58%) የመንግሥት እና 242 (66%) የግል ት/ቤቶች መምህራንና የት/ቤት አመራር በድምሩ 782 (60% (108 ሴት)) ተመዛኞች ለማህደረ ተግባር ምዘና ብቁ በመሆን (62.5% እና በላይ) ውጤት አስመዝግበዋል። የማህደረ ተግባር ምዘና ከተመዘኑት ውስጥ 497 (53%) የመንግሥት እና 190 (52%) የግል ት/ቤቶች መምህራንና የት/ቤት አመራር በድምሩ 687 (53% (598 ወንድ)) ተመዛኞች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘት ችለዋል።” (ሰንጠረዥ 12) በማለት አስፍሯል።
ከ2004ዓ.ም – 2014 ዓ.ም የሙያ ብቃት ምዘና የወሰዱ አጠቃላይ መምህራንና የት/ቤት አመራሮችን አስመልክቶም በአቶ ሰንደቁ የቀረበው ሰነድ ሳይናገር ያለፈው ነገር የለም። እንደዚሁ ሰነድ (ሰንጠረዥ 13) ማብራሪያ “ምዘና ከተጀመረ ከ2005 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም 17ሺህ 849 (8ሺህ 190 ሴት) የመ/ደረጃ እና የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች መምህራን የሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና የወሰዱ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥትና የግል ት/ቤቶች መምህራን ውስጥ (64 %) ነው። የጽሑፍ ምዘና ከተመዘኑት 17ሺህ 849 መምህራን ውስጥ 5ሺህ 913 (33% (3ሺህ 969 ወንድ)) በጽሑፍ ምዘናው ማለፊያ ውጤት (62.5% እና በላይ) ማስመዝገብ የቻሉ ናቸው። እንዲሁም የጽሑፍ ምዘና ከተመዘኑት 17ሺህ 849 መምህራን ውስጥ 4ሺህ 534 (22% (1ሺህ 487 ሴት)) የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘት ችለዋል።”
ይህ ብቻ አይደለም። ሰነዱ በዚሁ በጠቀስነው ሰንጠረዥ “በአጠቃላይ 712 (586 ወንድ) የት/ቤት አመራር የሙያ ብቃት የጹሁፍ ምዘና የወሰዱ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥትና የግል ት/ቤቶች አመራሮች 29.1%፤ የጽሑፍ ምዘና ከተመዘኑት 712 የት/ቤት አመራር ውስጥ 218 (31%) በጽሑፍ ምዘናው ማለፊያ ውጤት (62.5% እና በላይ) ማስመዝገብ የቻሉ ናቸው። እንዲሁም የጽሑፍ ምዘና ከተመዘኑት 712 የት/ቤት አመራር ውስጥ ውስጥ 190 (27% (17 ሴት)) የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘት” የቻሉ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
“በአጠቃላይ በሰንጠረዡ እንደሚታየው የመምህራንም ሆነ የት/ቤት አመራር የሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና ውጤት የሚያሳየው ሌሎች ከምዘና መሣሪያውና በአተገባበሩ ላይ የመምህራኑ ሆነ የት/ቤት አመራር ምልከታ ላይ ያሉ እጥረቶች እንዳሉ ሆኖ በመምህራንና የት/ቤት አመራር ብቃት ላይ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ አመላካች ነው።” በሚለው በሰነዱ ማጠቃለያ ጽሑፋችንን እናጠቃልላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2014