ለሰው ልጆች ፍቅር ለሰው ልጆች ሰላም
ለሰው ልጆች ፍቅር ለሰው ልጆች ሰላም
ለሰው ልጆች በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ
ሕፃናት እንዲያድጉ በንፁሕ አዕምሮ
ነፃ ሕሊናቸው ጎልብቶና ዳብሮ
ወጣት ሽማግሌ የሰው ዘር ሁሉ
ሰላም ለዓለማችን ይላሉ በሙሉ።
ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ትምህርታችሁን በደንብ እየጎበዛችሁ ነው አይደለ፤ ጎበዞች ሁኑ እሺ። ለዛሬ በጣም ጎበዝ ሠዓሊ የሆነችውን አርሴማ ጌትነትን ላስተዋውቃችሁ። አርሴማ ስምንት ዓመቷ ሲሆን መፃፍ ከቻለችበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ሥዕሎችን መሳል እንደጀመረች ትናገራለች። የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው አርሴማ ሥዕል አስተማሪዎቿ የሳሉትን ከመድገም አንስቶ የተለያዩ ሥዕሎችን በራሷ መንገድ እየሳለች የምታስቀምጥ ሲሆን በሥዕሎቿ ሀሳቧ ውስጥ ያለውን በሙሉ ለመግለፅ እንደምትሞክር ትናገራለች። በትምህርቷ በጣም ጎበዝ ልጅ የሆነችው ተማሪ አርሴማ እሷ ሰላም ያለበት ቦታ በመኖሯ ትምህርቷን በደንብ መማር፣ ሥዕለ መሳል እንደፈለገች መጫወት መቻሏ ቢያስደስታትም ሌሎች ጦርነት አካባቢ ያሉ ልጆች ግን ይህን እድል ያለማግኘታቸው እንደሚያሳዝናት ተናገራለች።
“እኛ ልጆች ሰላም ያስፈልገናል። እኛ የምንኖርበት ቦታ ሰላም ቢሆንም ጦርነት አካባቢ ያሉ ልጆች እየራባቸው፤ እየሞቱ ያሉ ልጆች በሰላም እንዲኖሩ ትልልቅ ሰዎች እባካችሁ መጣላት ተዉ፤ ሰላም ይሁን” ትላለች።
በቴሌቪዥን የሚታዩት ነገሮች ሁሉ እንደሚያስጨንቋት የምትናገረው አርሴማ በእሷ አንደበት ይህን ያህል መናገርዋ ቢያሳዝንም “እባካችሁ የፈጠርናቸውን ልጆች ዓለማቸውን አናጨልምባቸው፤ በቃ በሉና ሰላም ይሁን” ትላለች።
የሰላም ዋጋውን የሚረዳው ጦርነት ውስጥ ያለፈ ነውና ዋጋው ምን ያህል ውድ እንደሆነ ተረድተን ከጠፋው ጥፋት በላይ ሌላ እንዳይጨመር ዛሬ ላይ ልናቆም ይገባል በሚል የሕፃን አርሴማን ሀሳብ ተጋርቼ አበቃሁ።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም