አምቡላንሱ በሚያሰማው ጩኸት መኪኖች መንገድ እንዲለቁለት እየጠየቀ በቻለው ፍጥነት እየከነፈ ነው። እያንዳንዱ ሴኮንድ በአምቡላንሱ ውስጥ ላለችው ከሞት ጋር ትግል ውስጥ ለገባችው ወጣት ትርጉም አለው። ሞትን ማስቀረት ወይንም ልጃቸውን ከማጣት ውጪ ሌላ አማራጭ የሌላቸው የቤተሰብ አባላት በተለያየ መንገድ የአምቡላንሱ መዳረሻ ወደሆነው ሆስፒታል እያመሩ ነው፤ ድንገተኛ አደጋ፤ በመከዳት ውስጥ የተወለደ፤ ከሞት ጋር ፊትለፊት ያገናኘ።
ወጣቷ ራሷን ስታ እንድትወድቅ ያደረጋት የመከዳት መዝገብ ፍንትው ሲል በእጇ የነበረው ሃብት ሁሉ ወደ ሌላ ሰው ዞሮ ያገኘችበት ቅጽበት። ነገሮች ያለቁ ሆነው በተሳለላት ጊዜ ህይወቷን ለማጥፋት የወሰደችው እርምጃ በቤተሰብ አባላት ጣልቃ ገብነት የተጨናገፈ ሆኖ ህይወት በማለሚያ ሙጣጭ ውስጥ ትገኛለች። አንዳች ተስፋ፤ ከአምቡላንሷ ጩኸትና ከሚረጨው እምባ ውስጥ።
በሌላው ጎራ ከወጣቷ ጀርባ ሲያደባ የነበረው በፍቅር ቃላት ቀርቦ በልቧ በር በኩል ሰተት ብሎ ገብቶ ያላትን ሲያራቁት፣ ሁሉ ነገሯን ለእርሱ ሰጥታ የተደላደለችበት ሰው። “ጨዋታው አለቀ/game over” በሚል በክፋት ጥግ አመታትን በወሰደበት ፕሮጀክት በድል መጠናቀቅ ምክንያት ሊጠጣው የቀረበው መጠጥ ጥንካሬውን ከፍ ያለ አድርጎታል። ተሸንፈው ሳሉ ራስን አሸናፊ አድርጎ የማቅረብ ውድቀት።
ጨዋታውን ፈጻሚ ግለሰብ የፖሊስ የምርመራ መዝገቦች ውስጥ የሚሰሙ ዘግናኝ ታሪኮች ጀርባ ያለው የጭካኔ ጥግ በወረሰው ማንነቱ ውስጥ ሆኖ ራሱ ፈጥሮ፤ ራሱ ተውኖ፤ ራሱን ተመልካች አድርጎ በሰራው ተውኔት ውስጥ ይገኛል። የሲኒማው አዳራሽ ወንበሮች በሙሉ በእርሱ መክዳትን ልብሱ ባደረገው ግለሰብ ተሞልተዋል። በስክሪን ላይ በሚታየው ፊልም ውስጥ ግን ንጹህ ልብ፤ የተከዳው ልብ፤ ህያውነት በሙላት የነበረበት ልብ፤ እንዴት ሲማረክ እንዴትም የራሱ ሲያደርግ እንዴትም ሲሰብረው እንዴትም ወደ ሞት እንዳደረሰው ይመለከታል፤ ጨዋታው አልቋልና “ተፈጸመ” እያለ ይመለከታል። በክፋት ጥግ በሰሩት የጭካኔ ተግባር ከመጸጸት ይልቅ፤ ክፋቱን መላልሶ እንደ ፊልም ተመልክቶ ራስን አሸናፊ አድርጎ ከማቅረብ በላይ ምን አይነት ውድቀት አንድ በህይወቱ ያለ ሰው ሊወድቅ ይችላል?
ልብስን አውልቆ ጥሎ ሌላኛውን ልብስ ለብሶ በአዲስ የፊልም ታሪክ፤ በአዲስ አቅርቦ የመግደል ታሪክ ውስጥ መሪ ተዋናይ አድርጎ ራስን ማቅረብ። ከተሳካ እስከ ጫፍ ድረስ መሄድ፤ ካልተሳካ በየመንገዱ ባለው ቅንጭብጫቢ ተደስቶ መራመድ። ህይወትን በማጨንገፍ ውስጥ ህይወትን ለመኖር በመሞከር ራስን አትራፊ መስሎ ማቅረብ።
ወደ ሞት ከሚደረግ ጉዞ ለመዘግየት የሚደረገው ግብግብ ቀጥሎ አምቡላንሷ ከሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ደረሰች። ተስፋን ሊመልሱ ነጩን ጋውን የለበሱ የህክምና ባለሙያዎቹ ያላቸውን ሊሰጡ ሩጫው ውስጥ ገቡ። ከቅርብ እርቀት ሲከተል የነበረው የሞት ኮቴ በህይወት ምስቅልቅል ውስጥ ባለች ነፍስ ውስጥ ሊነግስ እየፈጠነ ስለ ሰው ቃለመሃላ የፈጸሙት ስለ አንዳች መፍትሔ እየደከሙ ነው። ለሌሎች ለመኖር እጃቸውን አንስተው ቃል የገቡት ሐኪሞች በበዛው ትጋታቸው፤ በፈጣሪም ጣልቃ ገብነት የሞቱ ኮቴ ባለበት ቆመ። ደቂቃዎች እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር የሞት ኮቴው እየራቀም ሄደ፤ መዳረሻው መሸነፍ ሆነ። ወጣቷ ከአካላዊ ጉዳቷ ዳነች።
የወጣቷ አካላዊ መዳን የፈጠረው የቤተሰብ ፌሽታ ግን የተከዳውን ንጹህ ልብ በቀደመ ውበቱ ዳግም ማግኘት በሚያስችል ሁኔታ አልነበረም። እናትም አባትም ሌላውም ሁሉ በጥርጣሬ ቀለበት ውስጥ እየተቆጠረ የሚኖር አዲስ ህይወት በወጣቷ ልጃቸው ልብ ውስጥ እየተወለደ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ ወሰደባቸው። የመከዳት ውጤት ከራስ የህይወት መዝገብ ላይ ታትሞ ሲገኝ ይህ ሆነ። በየጓዳው ያለ ስብራት፤ በአግባቡ ባለመያዙ ምክንያት እያመረቀዘ ደጋግሞ የሚጎዳ፤ መከዳት!
በመከዳት ስሜት ውስጥ ያለፉ ሰዎች ስሜቱን በቃላት መግለጽ ሲቸገሩ ይስተዋላል። መከዳት ታላቅ የልብ ስብራትን ፈጥሮ የሚያልፍ መሆኑን ከተደረጉ በርካታ ጥናቶች እንረዳለን። በመከዳት ውስጥ ተስፋ ደብዝዞ፤ ከሰዎች ጋር የሚኖር የህይወት መስተጋብር ትርጉም ባለው ሁኔታ ተጎድቶ፤ ፍርሃት ነግሶ፤ ነጻነት ተገርስሶ ይታያል። አንዳች መፍትሔ እስካልተገኘ ድረስ። እነሆ “መከዳት ሲደርስብን” ብለን እንቀጥል።
መከዳት ሲደርስብን
መከዳትን ተከትሎ የሚመጣው የሥነ-ልቦና ቀውስ ቀላል አለመሆኑን ለመረዳት የግድ በህመሙ ውስጥ ማለፍን አይጠይቅም። መከዳትን ውስብስብ የሚያደርገው በአብዛኛው ሳይጠበቅ የሚደርስ፤ ካልተጠበቀ ሰው የሚመጣ በመሆኑ ነው። ሰው መከዳትን እያሰበ ግንኙነት ሊመሰረት አይችልምና። የትኛውም በመተማመን መንገድ ላይ ያለ ግንኙነት በሂደት ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላኛው ደረጃ በሚያድግበት ጊዜ ከመከዳት እየራቀ እየመጣ መሆኑን ውስጣችን ይቀበላል። በተቃራኒው መከዳት በሚሆንበት ጊዜ ጉዳቱ ቀላል የማይባል ሊሆን ይችላል። ልብን የሚሰብር ጉዳት፤ በወጌሻ ታክሞ ሊድን የማይችል ስብራት።
መከዳት በፍቅር ግንኙነት ውስጥ፤ መከዳት በቤተሰብ ውስጥ፤ መከዳት በንግድ ሥራ ውስጥ፤ መከዳት በፖለቲካ፤ መከዳት በሌሎችም ዘርፎች ውስጥ ሊፈጠር ይችላል። ‘እከሌ ሊከዳኝ ይችላል’ ብሎ አስቦ ግንኙነት ውስጥ መሆን ግንኙነቱ ማደግ በሚችልበት ደረጃ እንዳያድግ ማድረግ መሆኑ ግልጽ ነው። ነገርግን በህይወታቸው ውስጥ መከዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸው መከዳት ሲደርስብን እንዴት ማስተናገድ እንዳለብን ዛሬ ላይ ሆነን ከማሰብ ሊከለክለን አይችልም።
መከዳት ሲደርስ ራስን በመጣል፤ ራስን ለጉዳት በመዳረግ በሰፊው የምንመለከተው ምላሽ ነው። እንደ ግለሰብ የምንሰጠው ምላሽ ቤተሰባችንን እንዲሁም ሌሎች ለእኛ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰዎች አላስፈላጊ ዋጋ እንዲከፍሉ የሚያደርግም ሊሆን ይችላል። ከሁሉም በላይ ግን እነርሱንም በጥርጣሬ እንድናይ የምንገደድበት ሁኔታ የመፈጠሩ ሃቅ ጎልቶ የሚታይ ነው።
በችግር ጊዜ የቤተሰብ አባላት አብረው ከመቆም ይልቅ መራቅን ሲመርጡ፤ አሉልን ከጎናችን ናቸው ያልናቸው በቦታቸው ሳይገኙ ሲቀሩ፤ የሚፈጠረው ስሜት እንኳን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። በዚህ ስሜት ውስጥ የተገኙ ሰዎች ዋናው መከዳት ሲደርስባቸው እንዴት ሊቀበሉት እንደሚከብዳቸው ቢያስቡ ሊገርመን አይገባም። ይህም ሰዎች ምን ያህል እርስበእርሳችን ባለው ግንኙነታችን ውስጥ ህይወታችን የተሳሰረች መሆኑን እንድንረዳ ያደርገናል።
አንባቢው ምናልባት በህይወቱ ውስጥ የገጠመውን መከዳት እያሰበ እያነበበ ይሆናል። ምናልባትም በህይወቱ ቀጣይ ምእራፍ ሊያጋጥመው የሚችል ሆኖ ሊመጣም ይችላል። ምናልባትም በመከዳት ውስጥ ያለን የሚያውቀውን አንድ ሰው እያሰበም ይገኛል። ምናልባትም ራሱን ለመክዳትም እያዘጋጀ ወይንም በመክዳት ህይወት ውስጥ አልፎ ከህሊናው ጋር ጸብ ውስጥ የሚገኝ ሊሆን ይችላል።
በዋናነት መከዳት ሲደርስብን እንዴት በመከዳት ስሜት ሳንጎዳ የህይወታችንን አቅጣጫ ማስተካከል እንዳለብን ግንዛቤን የሚሰጡ ነጥቦችን በቀጣይ እናነሳለን። መከዳት ሲደርስ ፈራርሶ ከመቀመጥ ዛሬ ላይ ራስን ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑን ጸሐፊው ያምናል። በተቃራኒው ደግሞ መከዳት ሊደርስ ይችላል ብሎ የግንኙነትን እድገት መወሰን ውስጥ እንዳንገባ ማሰብም ተገቢ ሆኖ ይገኛል። ጠንካራን ግንኙነት እየፈጠሩ ነገርግን መከዳት ሲያጋጥም መልሶ በእግር እየሄዱ ህይወትን ለመቀጠል በሚረዳ ሚዛን ውስጥ። ከጥበብ በሚገኝ ሚዛን መካድን በመቀበል የመፍትሔውን ሃሳብ እናስቀምጥ።
ከመካድ መቀበል
መከዳት ሲያጋጥመን እውነታውን ለመካድ ከመሞከር መቀበል የተሻለው የመፍትሔ መንገድ መሆኑን የሚያስረዳ ነጥብ ነው። በህይወታችን ውስጥ እንዳይሆኑ የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉ። ምናልባትም ሰዎች እንዳያውቁብን የምንፈልጋቸው። ነገርግን ሁሉም በእኛ ቁጥጥር ውስጥ ያለ ባለመሆኑ፤ በተጨባጭ መከዳት በሚፈጠርበት ጊዜ ላለመቀበል ብዙ እርቀት ከመሄድ እውነታውን በቁመናው ልክ መቀበል ተገቢነት ይኖረዋል።
የከዳንን ሰው እኛም በተመሳሳይ መንገድ በመክዳት ሂደት ውስጥ ከመግባት እውነታውን ተቀብሎ የመፍትሄ መንገዶችን መፈለጉ በባለሙያዎች የሚሰጠው ቀዳሚ ምክር ነው። በህጻናት አስተዳደግ ውስጥ የመከዳት ትርጉም ቦታን ይዞ እናገኛለን፤ እንዴት የሚለውን ስናነሳ መከዳት በሰዎች ህይወት ውስጥ ተዋህዶ እንዴት ሊገኝ እንደሚችል እንድንረዳ ያደርገናል። መከዳትን ተቀብሎ ለመፍትሔው ከመስራት ይልቅ፤ አቅልሎ የማየት አስተሳሰብን እንድንፈጥር የሚያደርግ።
መከዳት ከመጠበቅ የሚወጣ በመሆኑ ህጻናት በተፈጥሯቸው ከቤተሰባቸው የሚጠብቁ ናቸው። ከቤተሰብ የሚጠብቁት ከመሰረታዊ ፍላጎታቸው ውጪ ፍቅርንና እንክብካቤን ተቀባይነትን ወዘተ የመሰሉ ቁሳዊ ከሆኑ ፍላጎቶች ውጭ የሆኑትንም ነው። ህጻናቱ እኒህን የሚጠብቁትን በሚያጡበት ጊዜ በውስጣቸው እያደገ የሚሔድ ቤተሰባቸውን ያለመቀበልና በስተመጨረሻ በቤተሰብ ውስጥ ጤናማ የመቀባበል ስሜት እንዳይኖር ያደርጋል። አለመቀባበሉ በሂደት አድጎ በአዋቂ እድሜ ውስጥም ሆነ በመከዳዳት ውስጥ ሊያልፉ ይችላሉ።
የመከዳት ስሜት አብሮን እያደገ የሚመጣ በሚሆንበት ጊዜ ችግሩን እንደ ችግር ሲያጋጥም ተቀብሎ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ‘መከዳትም ሆነ መክዳት ያለ ነው’ ብሎ ተቀብሎ ለተወሳሰበ ችግር ራስን ማጋለጫ ምክንያት ሊሆን ይችላል። መከዳትንም የምንቀበልበት መንገድ ወደ ተሻለ የህይወት አቅጣጫ የሚመራ ከመከዳት ወይንም መክዳት ህይወት መውጣት የሚያስችል ሳይሆን መከዳዳት እየሰፋ እንዲሔድ የሚያደርግ ይሆናል።
ከትናንት ከረጅሙ የአስተዳደግ ጉዞ ውስጥ የተፈጠረ መከዳዳትን አቅልሎ የሚያይ አተያይ ውስጥ ካለን እንዴት ልንወጣ እንደምንችል ስናስብ መፍትሔው በትናንትናችን ውስጥ የሆነውን መርምሮ መቀበል ሆኖ እናገኘዋለን። ስለሆነም መከዳት የህይወትን አቅጣጫ በተሳከረ መንገድ እንደሚመራ፤ መከዳት በአግባቡ ካልታከመ ጉዳቱ እየተባዛ እንደሚሔድ፤ መከዳዳት ህይወትን በሙላት ከመኖር የሚያግድ መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል።
ከትናንት ተጉዞ የመጣም ይሁን አዲስ የተከሰተ የመከዳትም ሆነ የመክዳት እውነት በህይወታችን ውስጥ ካለ ችግሩን እንደ ችግር መቀበል ችግሩን ክዶ ከመቀመጥ የተሻለ ነው። ላለመቀበል የምናደርገው ትግል በበሽታው ውስጥ አብረን እንድንቆይ ሊያደርግ ይችል ይሆናል እንጂ ወደ መፍትሔው ሊያደርሰን የሚችል ባለመሆኑ።
የስሜት ቀውስን ምላሽ መለማመድ
በመከዳት ውስጥ የሚፈጠረው የስሜት ቀውስን በየአይነቱ ለይቶ ስሜቱ ሲፈጠር ልንሰጥ የሚገባውን ግብረ-መልስ መለማመድ ሌላው የመፍትሔ መንገዱ ቁልፍ ነጥብ ነው። መከዳትን ተከትተሎ ንዴት፤ ቁጣ፤ ህመም፤ እፍረት ወዘተ የስሜት አይነቶች ይፈራረቃሉ። እያንዳንዱ የስሜት ቀውስ የራሱ የሆነ መገለጫና ባህሪ አለው። ለእያንዳንዱ የምንሰጠው ትርጉምና በሚሰማን ጊዜ ልናደርግ የምንፈልገውን ለይተን ማወቅ አለብን። ከልየታው በኋላ በእያንዳንዱ ስሜት ውስጥ ራሳችንን እየጨመርን በተጨባጭ ስሜቱ ሲፈራረቅብን ራሳችንን እንዴት እየገዛን ልናልፈው እንደሚገባ ትምህርት እንወስዳለን።
ለምሳሌ፣ በተፈጠረብን መከዳት ስሜት ውስጥ ሆነን መከዳታችንን የሚያውቁ ሰዎች በሚያገኙን ጊዜ እንዴት ምላሽ እንደምንሰጥ ማወቅ በተጨባጭ የእፍረት ስሜቱ ሲያጋጥመን ከምናደርገው ያልተዘጋጀንበት ምላሽ የተሻለ ነው። ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ተነጥቀው በሃዘን ላይ ሆነው ሌላ ሟችን በጋራ የሚያውቁትን ሰው ሲያገኙ ስለሟች እያነሱ ማውራት እንዲሁም አብረውም ማልቀስ ባህላችን ነው።
በሂደቱም ስሜትን መጋራትና መጽናናት ይሆናል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከምናልፍበት የመከዳት ስሜት አንጻር ከሰዎች ጋር ስንገናኝ የሚገጥመን የስሜት ጎርፍ አለ። ይህን የስሜት ጎርፍ እንዴት አድርገን ማስተናገድ እንደሚገባን አስቀድሞ ማወቁን ነው እያነሳን ያለው። ይህ ማለት ስላለንበት ስሜት ድብቅ እንሁን ማለት አይደለም፤ ማንን ስናገኝ ምን ሊሰማን ይችላል የሚለውን ካወቅን በኋላ ስሜታችንን በጤናማነት እንዴት መግራት እንዳለብን ማሰብ መቻል ነው። የከዳንን ሰው የቅርብ ቤተሰብ ስናገኝ እንዴት እንመለከታለን? ያንን ስሜት ዛሬ ላይ መለማመድ። የእኛን መጎዳት የማይፈልግ የልብ የምንለው ሰው ሲገጥመን ምን ሊሰማን ይችላል? አሁንም ያንን ስሜት ዛሬ ላይ መለማመድና ስሜቱ ሲገለጥ በአግባቡና ወደ ተሻለ መፍትሔ ሊያደርሰን መንገድ ውስጥ ማረቅ መቻል ማለት ነው።
ለእርዳታ መቅረብ
ሰው በመሆናችን ውስጥ ያለው አንዱ በረከት አንዳችን ለሌላችን ያለን ቦታ ነው። በህይወታችን ውስጥ ልዩ ቦታ የምንሰጣቸው ሰዎች አሉ። ቤተሰብ እና ጓደኞች ልዩን ቦታ ከሚይዙት መካከል ቀዳሚዎች ናቸው። በማንኛውም የስሜት መዋዠቅ ውስጥ ስንሆን እጅግ ቅርብ ከምንለው ሰው ጋር ካልሆነ በስተቀር ከሌሎች ሰዎች ልንርቅ እንችላለን። ከሁሉም ሰው መራቅ ደግሞ አደገኛ ነው። ያለንበትን የስሜት መዋዠቅ ተለማመድን ሰው ጠሊታ ሆነን ራሳችንን እንድናገኝ ሊያደርገን ይችላል። የቅርብ የምንለው ሰው ግን ስሜታችንን እንዲያውቅና ካለንበት ነገር ለመውጣት በምናደርገው ሂደት ውስጥ እንዲያግዘን ማድረግ አለብን። ይህ ራሳችንን ለሌሎች እርዳታ የማቅረብ ምእራፍ ነው።
የመከዳት ስሜት ወደ በቀል፤ የመከዳት ስሜት ራሳችንን ምሽግ ውስጥ እንድንደብቅ እንዲሁም ህይወትን በፍርሃት የምንከተል እንዳያደርገን ከፈለግን የመውጫ መንገዱ ላይ መግባትን ይፈልጋል። እርዳታ ለሚያደርጉልን ሰዎች ራሳችንን ማቅረብ ከመውጫ መንገዱ ላይ የሚገኝ አንዱ የመፍትሔ ሃሳብ ነው።
በቅርባችን ያሉ ሰዎች በምንሆነው ሁናቴ እንዲሁ ከሚጨነቁ እውነታውን ተረድተው በምክርም፤ በተግሳጽም እንዲሁም በእንክብካቤም እንዲረዱን ማድረግ አስፈላጊ ነው። ውድ የምንላቸው ሰዎች በተጨባጭ ውድ መሆናቸው የሚገባን እንዲህ ባለወቅት ነውና።
በምንፈልገው ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ
በፍቅር ግንኙነት ውስጥ የተፈጠረ መከዳት እምነትን መልሶ ሊቀጥል የሚችልበት መንገድ ላይ መግባት ስለመቻሉ በጥቅሉ መናገር ባይቻልም እድል ሊኖረው ይችል ይሆናል። በመከዳት ጊዜ ግን የምንፈልገው ነገር እስከምን ድረስ መሆኑን ግብ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዳን የምንለው ሰው የከዳን በምን ምክንያት ነው ብለን በእርሱ ጫማ ሆነን በእውነተኛ ይቅርታ ከተመለሰ አብረን ህይወትን ለመቀጠል ወይንም መለየታችን እርግጥ ሆኖ የራሳችንን አቅጣጫ ለማስተካከል ብሎ ትኩረት መደረግ የሚገባውን ነገር መለየት ያስፈልጋል።
ትኩረት ያደረግነው ላይ ለመድረስ የሚወስደው ጊዜ መኖሩ እሙን ነው። በጊዜ ውስጥ የሚሰራውን ስራ ማወቅም እንዲሁ ተገቢነት አለው። ልብ አንጠልጣይ ፊልም በማየት ራሳችንን ለአፍታም ቢሆን በመርሳት ከአዲሱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለመግባባት ማድረግ ብቻም ሳይሆን ተጨማሪ ልማዶችን ወደ ህይወታችን በመጨመር ትኩረት ያደረግነው እንዲሳካ ማድረግ ያስፈልገናል። በጸሎት፤ በቅዱሳት መጽሐፍት ንባብ፤ አዳዲስ ልማዶችን (ሆቢዎችን) በመተግበር ወዘተ ውስጥ ትኩረት ወዳደረግነው የመፍትሔ አቅጣጫ ላይ መድረስ እንችላለን።
ማጠቃለያችን መከዳት የሚያመጣውን አሉታዊ ተጽእኖ እንዴት ተቋቁመን የህይወታችንን አቅጣጫ አስተካክለን መራመድ እንደምንችል እንድናስብ። ወጣቷን ለማዳን የተደረገው እርብርብ አካላዊውን ችግር ለመፍታት የቻለ ቢሆንም ከውስጥ የሚወጣው የመከዳት መራር ስሜት ግን በጥንቃቄ መታከምን ይፈልጋል። በተለይም የጉዳዩ ባለቤት ችግሩን በመቀበል፤ የስሜት መዋዠቆቹን በመለማመድ፤ እርዳታ ሊያደርጉለት ከሚገቡ አካላት እርዳታን በመቀበል እና ትኩረት መደረግ ባለበት ላይ ትኩረት በማድረግ ስለ ሰዎች መልካም ሆኖ መኖር!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014