ምዕራባውያን የብዙ ሙያዎችና ተሰጥኦዎች ባለቤት የሆነን ግለሰብ ለመግለፅ ‹‹A Jack of All Trades›› የሚል አገላለፅ ይጠቀማሉ። ‹‹ለዚህ አገላለፅ ተገቢ (እውነተኛ ምሳሌ) የሆነ ኢትዮጵያዊ ማነው?›› ተብሎ ቢጠየቅ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ አንዱና ዋነኛው ስለመሆናቸው ብዙም ክርክር የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።
ስመጥር አዝማሪ፣ ባለቅኔ፣ ቀራፂ፣ ሰዓሊ፣ ነጋዴ፣ መኪና አሽከርካሪ፣ መካኒክ፣ ፖለቲከኛ፣ ፎቶ አንሺ … የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፤ የበርካታ ሙያዎችና ተሰጥኦዎች ባለቤት ሆነው ሳለ የአበርክቷቸውን ያህል ግን ታዋቂነትና ውለታ አላገኙም። ብዙ ነገር የተነፈጋቸው ሰው ናቸው።
ነጋድራስ ተሰማ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ጉቤ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለተየስ ሐብቱ ሐምሌ 20 ቀን 1869 ዓ.ም ምንጃር ውስጥ ቀርሾ አጥር በተባለ ስፍራ ተወለዱ። አባታቸው አቶ እሸቴ ጉቤ በመሰንቆ ተጫዋችነታቸው ተወዳጅነትን ያተረፉ አዝማሪና የራስ መኮንን ባለሟል ነበሩ። ራስ መኮንን ወደ ሐረር በዘመቱበት ወቅት እርሳቸውን ተከትለው ወደሐረር የዘመቱት አቶ እሸቴ፤ ኑሯቸውን በዚያው በሐረር አድርገው ሳለ ሕይወታቸው አለፈ።
የአባቱን ማረፍ ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ታዳጊው ተሰማ፣ ገና በልጅነታቸው በስዕል ችሎታቸው ተደናቂ መሆን ቻሉ። ለሙዚቃም የተለየ ፍቅር ነበራቸው። ይህ የሙዚቃ ፍቅር ያደረባቸው ከአባታቸው ወርሰውት ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል። በችሎታውም በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩ የአውሮፓውያንን ጭምር ቀልብ ለመግዛት ብዙም አልተቸገረም።
ሙሴ አርኖልድ ሆልስ የተባለ ጀርመናዊ በአዲስ አበባ የነበረውን ቆይታ ጨርሶ ወደ አገሩ ለመመለስ ለስንብት ወደ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘንድ ሲቀርብ ለንጉሠ ነገሥቱ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው። ሦስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ወደ ጀርመን ወስዶ በማስተማር ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሳቸው እንደሚፈልግ ተናገረ። ንጉሠ ነገሥቱም ተሰማን በጥሩ ሰዓሊነቱና ቀራፂነቱ ያመሰግኑት ነበርና ‹‹ያ ተሰማ እሸቴ እጁ ብልህ ስለሆነ መኪና መንዳትና መጠገን እንዲማር እርሱም ይሂድ›› ብለው ከሦስቱ ወጣቶች መካከል አንዱ ተሰማ እሸቴ እንዲሆኑ ፈቀዱ። ወደ ጀርመን ሄደውም ለሁለት ዓመታት ያህል የአውቶሞቢልን አሠራር (መኪና መንዳትና መጠገን) አጥንተው ተመለሱ።
በጀርመን ቆይታቸው በንጉሠ ነገሥቱ ከተፈቀደላቸው ትምህርት በተጨማሪ በራሳቸው ተነሳሽነት ‹‹ሂስ ማስተር ቮይስ›› ከሚባለው ኩባንያ ጋር በመዋዋል 17 የዘለሰኛና የመዲና ዘፈኖቻቸውን በሸክላ ላይ አስቀርፀዋል። ይህም ሙዚቃን በሸክላ ላይ ያስቀረጹ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንዲሆኑ አስቻላቸው። ሁለቱ ሙዚቃዎቻቸው በግዕዝ ቋንቋ የተሰሩ ነበሩ። በሙዚቃ ሥራዎቻቸው ግጥሞች ላይ ያነሷቸው ጉዳዮች ሰውየው በወቅቱ የነበራቸው የዕይታ አድማስ ሰፊ እንደነበር የሚያመለክቱ ናቸው።
በግጥሞቻቸው ላይም በጊዜው በኢትዮጵያ ስለነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ በድፍረት አመልክተዋል። እቴጌ ጣይቱንና የወቅቱን ታላላቅ መኳንንት ጭምር ወቅሰዋል፤አስጠንቅቀዋል፤መክረዋል። ሥራዎቻቸውን ላስቀረፁበትም 17ሺ የጀርመን ማርክ ተከፍሏቸዋል።
ከዚያ በፊት ዘፈኖችና የአዝማሪዎች ሥራዎች የሚደመጡት በግራማ ፎን ነበር። ሌሎች ዘፋኞች ዘፈኖቻቸውን በዲስክ ማስቀረፅ እስከቻሉበት እስከ 1925 ዓ.ም. ድረስ ለ20 ዓመታት ያህል በአዲስ አበባና በሌሎች ትልልቅ የኢትዮጵያ ከተሞች ይደመጡ የነበሩት የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሥራዎች ብቻ እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል።
ከጀርመን እንደተመለሱም የቤተ-መንግሥት መኪናዎች ኃላፊ ሆኑ። ኢትዮጵያውያን የመኪና አሽከርካሪዎችንም አሰለጠኑ። በዚህ ሙያቸውም ከፍተኛ ተወዳጅነትንም አተረፉ። ባሳዩት የስራ ትጋት የአዲስ አበባ ፍል ውሀ ድርጅትን እንዲመሩ ተሾሙ። የራስ ካሣን እህት ወይዘሮ ፀሐይወርቅ አንዳርጌን አገቡ። ከወይዘሮ ፀሐይወርቅ ጋር የነበራቸው ትዳር ሊሰምር ባለመቻሉ ወይዘሮ ሙላቷ ገብረሥላሴን አገቡ። ከትዳራቸውም ሰባት ልጆችን አፍርተዋል።
ከልጆቻቸው መካከል አንዱ ‹‹የአፍሪካ እግር ኳስ አባት›› በመባል የሚታወቁት ታዋቂው የስፖርት ሰው አቶ ይደነቃቸው ተሰማ ናቸው። ልጆቻቸውንም ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ አድርገዋል። ቁጥራቸው በርከት ያሉ ታክሲዎችን ከውጭ በማስመጣትና የሕዝብ ትራንስፖርት በማቋቋም በርካታ ኢትዮጵያውያን ሹፌሮችን አሰልጥነዋል።
ነጋድራስ ተስማ እሸቴ ከሙዚቃ ችሎታቸው በተጨማሪ በግጥም ችሎታቸውም እጅግ የተደነቁ ነበሩ። ብዙዎቹ ግጥሞቻቸው የሰምና ወርቅ ፍችዎች ያሏቸው፣ የሚያስተላልፉት መልዕክት ጠንካራ እና በአፃፃፍ ቴክኒካቸው የተዋጠላቸው ናቸው። በወቅታዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የተመሠረቱም ሲሆኑ፤ የተችነት ባህርይም ይንፀባረቅባቸዋል። ቀጥለው የተጠቀሱት ሶስት ምሣሌዎች የነጋድራስ ተሰማን የግጥም ርዕሰ-ጉዳዮችና የግጥሞቹን ደረጃዎች ሊያመለክቱ ይችላሉ።
‹‹ የአገሬ ወንዞች መጥኔውን ይስጣችሁ፣
ክረምት ሲመጣ እየጨነቃችሁ፣
ዋጋ አትቀበሉ አስታዋሽ የላችሁ፣
ከአዳም ጀምሮ እስከአሁን እድሜያችሁ፣
ሰውንም ከብቱንም እቃ እንዳጋዛችሁ፣
የማትታመኑ በዋል ፈሰስ ናችሁ፣
ለውቅያኖስ ዓሣ እያስረከባችሁ፣
አንድ እንኳ አታመጡ ወዲህ መልሳችሁ።
***
አገሬ ታውቂያለሽ እንደምንወድሽ፣
በታመምሽ ጊዜ ተዘግቶ ጆሮሽ፣
በነፃነት ፀጋ እስክትፈወሽ፣
በአራቱ ማዕዘን ዓለም ሲጠራሽ፣
ያምላክ ውለታ ምነው ማጥፋትሽ፣
አትናገሪም ወይ ተሰማ ብለሽ?
***
የወዲያ ሰዎች ክፋታቸው፣
ሬሳ አጋድመው መብላታቸው፣
የሸዋ ሰው መልካም፣
ወዳጁን ሳይቀብር አይበላም። ››
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥታት ሲኖሩ በበርካታ ሙያዎቻው የሚታወቁትን ያህል በቀልድ አዋቂነታቸውም የተደነቁ ነበሩ። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን በቅርብ እናውቃለን የሚሉ ወገኖች ከወቅታዊ ሁኔታ በመነሳት የሚያመነጯቸው ቀልዶች ከአለቃ ገብረሃና ቀልዶች ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ሲናገሩ ይስተዋላል። ነጋድራስ ተሰማ በሕይወት ዘመናቸው ከቀለዷቸው አሽሙሮች መካከል ሁለቱን ቀጥሎ እንመልከታቸውና ምላተ-ጉድለታቸውን እንመርምር።
ሀ) ነጋድራስ ተሰማ በአንድ ወቅት ከመኳንንቱ ጋር ቁጭ ብለው ሲጫወቱ «አሁን ሁላችሁም በሆዳችሁ የምታስቡትን አውቃለሁ» በማለት ተናገሩ። መኳንንቱም ‹‹አያውቁም›› ሲሉ ተከራከሯቸው። ከመኳንንቱ አንዱ «አያውቁም» ብለው በመቶ ብር ተወራረዷቸው። እርሳቸውም «ሁላችሁም ለንጉሡ ነው የምታስቡት። በሆዳችሁ ያለው ይህ ነው» ብለው ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ደፍሮ ‹‹አይደለም›› ብሎ የሚከራከር በመጥፋቱ ውርርዱን ረቱ።
ለ) በአንድ ወቅት ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ ባሉበት የኢላማ ተኩስ ሲደረግ እልፍኝ አስከልካዩ በመጀመሪያ ጥይት ተኩሶ ዒላማውን መታ። በዚህ ጊዜ ነጋድራስ ተሰማ ቀስ ብለው «ባንዴ ቡን አደረጋት!» ሲሉ ተናገሩ። የእልፍኝ አስከልካዩ በፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ዓመታት ባንዳ ስለነበር ያንን በአሽሙር ለመንካት ሲሉ የተናገሩት ጣምራ ትርጉም ያለው ንግግር ነበር።
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በኢትዮጵያ ባልተለመደ መልኩ ሃሳብን በነፃ መግለፅና መንግሥታትንና መሪዎችን በመተቸት ባህርያቸው ነበር።
‹‹ ባለስልጣኖቹ እስኪ አስቡበት፣
መናገራችሁን እንዳትተውት።›› ብለው የገጠሙት የዚሁ ማሳያ ነው።
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በልጅ ኢያሱ ዘመን ጉልህ ፖለቲካዊ ተሣትፎ ነበራቸው። ለልጅ ኢያሱም የተለየ አክብሮት ነበራቸው። በልጅ ኢያሱ የአስተዳደር ዘመንም ሰይድ ባዝራ ከተባለ ግለሰብ ጋር በመሆን ከብት ወደ ውጭ አገራት ይልኩና ወደአገር ውስጥ ደግሞ ፈቃድ ጠይቀው የጦር መሳሪያ ያስመጡ ነበር።
አብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የመሐል አገሩ መኳንንት ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን ለማውረድ በተሰለፈ ጊዜ ሁሉ ነጋድራስ ተሰማ ግን የልጅ ኢያሱ ታማኝ ባለሟል ሆነው እስከ መጨረሻው ድረስ ዘልቀዋል። ልጅ ኢያሱ ከዙፋን ሲወርዱም የልጅ ኢያሱ ወዳጆችና ደጋፊዎች ለግዞትና ለእንግልት ተዳረጉ። ነጋድራስ ተሰማም ጅማ ውስጥ በግዞት ተቀምጠው ቆዩ። ከልጆቻቸው መካከል አራቱ የተወለዱት በግዞት ላይ ሳሉ ነው። ነጋድራስ ተሰማ በአባ ጅፋር ግቢ ለሰባት ዓመታት ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
‹‹ አታበሉኝም ወይ ከጮማው ቆርጣችሁ፣
አታጠጡኝም ወይ ከጥሩ ጠጃችሁ፣
ሰባት ዓመት ሙሉ ተለፋሁላችሁ።›› ብለው ስሜታቸውን ገለፁ።
ከግዞት በተጨማሪም ብዙ ንብረቶቻቸው ተወርሰውባቸው ነበር። ሳይወረስ የቀረው አዲስ አበባ ከተማ ራስ መኮንን ድልድይ (ፒያሳ አካባቢ) የሚገኘው ቤታቸው ብቻ ነበር። በጉምሩክ መሥሪያ ቤትና በአንድ ግሪካዊ ነጋዴ ቤት ያስቀመጡት 300ሺ ብር የሚያወጣ ጠበንጃና ጥይትም ሳይመለስላቸው ቀረ።
የማይጨው ዘመቻ እንደተጀመረ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ዘመቻው ከማምራታቸው በፊት የልጅ ኢያሱ ደጋፊዎች ዝም ብለው አይቀመጡም ብለው በማሰብ ከአዲስ አበባ ያርቋቸው ጀመር። ነጋድራስ ተሰማም በነጋድራስነት ሹመት ሰበብ ወደ ወላይታ ግዛት እንዲርቁ ተደረገ። በዚህ ወቅትም፣ የጠላት ወረራ የፈጠረው የብጥብጥ ስሜት በግዛቱ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳያስነሳ የፀጥታ ኃይል አቋቁመው ሕግና ሥርዓት እንዲጠበቅ አድርገዋል።
የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተጣሉ ሰዎችን ሰብስቦ አክብሮት መለገስ ጀምሮ ስለነበር ነጋድራስ ተሰማም የተወረሰው ቤታቸው ተመለሰላቸው። ቤታቸውን አከራዩት። ይሁን እንጂ ቤታቸውን የተከራዩት ጣሊያኖች ለነጮች እንጂ ለጥቁሮች ቦታ ስላልነበራቸው ነጋድራስ ተሰማ ከዕለታት አንድ ቀን ምግብ ለመብላት ወደአከራዩት የራሳቸው ቤት ሲገቡ በጥቁርነታቸው መገለል ደረሰባቸው። ቀደም ሲል ወደ ወላይታ እንዲርቁ መደረጋቸውና አሁን ደግሞ በጥቁርነታቸው ምክንያት የደረሰባቸው አድልኦ ያበሳጫቸው ነጋድራስ ተሰማ እንዲህ ብለው ተቀኙ።
‹‹ ታሪኬ ብዙ ተሰማ እሸቴ፣
ተደብቄያለሁ በገዛ ቤቴ።››
ወደ ፋሺስት አስተዳደር አለቃው ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ሄደው ‹‹ልናሰለጥናችሁ መጣን ብላችሁ የዘር ልዩነት ልትመሠርቱና ከሰው በታች ልታደርጉን ነው?›› ብለው ጠየቋቸው። ግራዚያኒም ‹‹አዝናለሁ፤ ከሙሶሊኒ የመጣ ትዕዛዝ ነው›› ብለው መልሰውላቸዋል። ነጋድራስ ተሰማ በነገር የሚሸነቁጡት ምዕራባውያንንም ጭምር ነበርና
‹‹ የሰላም አለቆች እንግሊዝ ፈረንሳይ፣
እግዜር እንዳይገድለኝ የእናንተን ጉድ ሳላይ ›› በማለት እንግሊዝና ፈረንሳይ በወቅቱ በኢትዮጰያ ላይ ይሸርቡት የነበረውን ሴራ ጠቁመዋል።
ፋሺስት ኢጣሊያ ተሸንፎ ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ ሲገቡ ነጋድራስ ተሰማ ‹‹ከፋሺስት ኢጣሊያ ጋር ተባብረው መሥራታቸውን እናውቃለን›› የሚሉ ከሳሾች በዙና ወሊሶ አካባቢ ለስድስት ዓመታት በግዞት እንዲቆዩ ተደረገ። ይሁን እንጂ ፋሺስት ኢጣሊያ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱት አርበኞች ከነራስ አበበ አረጋይ ጋር እንዲያስታርቁት ሽምግልና ልኳቸው ነበር። ነገር ግን አርበኛውን የሚጠቅምና ጠላትን የሚጐዳ ድርድር አድርገው መመለሳቸው ስለታወቀ ለተወሰነ ጊዜ ችግር አጋጥሟቸው ነበር። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ፋሺስት ኢጣሊያንን የሚቃወሙና የሚተቹ ብዙ ግጥሞችን ገጥመዋል።
‹‹ እገበያ መሀል ፈስ እያንዛረጡ፣
አውራ ጐዳና ላይ ዳቦ እየገመጡ፣
ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ትምባሆ እየጠጡ፣
እንዲህ ነው ወይ ጣልያን አልጋ ላይ ሲወጡ ›› ብለው ነበር።
የጣሊያንን ክፋትና አደገኛነት ለኅብረተሰቡ ለማሳወቅና በጀግንነት እንዲመክተው ለማድረግም ይህን ብለዋል።
‹‹ እናንት ገበሬዎች በፊት ተማከሩ
አረማሞ እንክርዳድ ሲናር እንዳትዘሩ
ገና በሽፍኑ ፍሬ ሳያፈራ ጨፍጭፎ ቆራርጦ
መጣል ነው ለአሞራ።
ይህን የመጥፎ ዘር የባህር ማሽላ
ነቃቅሎ ማጥፋት ነው መቼም አይበላ።››
ከግዞት እንደተፈቱም የሻሸመኔ የእንጨት ፋብሪካና የቲማቲም ድልህ ፋብሪካ ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ። በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሸንኮራ አገዳ መትከል የጀመሩት እርሳቸው ነበሩ። አገራቸው በግብርና ዘርፍ ታዋቂ እንድትሆንና የውጭ አገራት ጎብኚዎችን ዓይን እንድትስብም ጥረት ያደርጉ ነበር። በሶደሬ፣ በወንጂ፣ በወሊሶ ፍልውሃና በቦኮ እንፋሎት ላይ ያከናወኗቸው ተግባራት ለዚህ ምስክሮች ናቸው። በቱሪዝም ረገድ ለአገራቸው የነበራቸውን ስሜትም በዚህ ስንኝ ገልጸውታል።
‹‹ ከዓባይ ኢንዱስትሪ ከአዶላም ከወርቁ፣
ከዋቢ ሸበሌም አትክልቶች ሲፀድቁ፣
የዓለም ቱሪስቶች እኛን እንዲያደንቁ፣
ደስም እንዲላቸው ሲመጡ ከሩቁ።
ይህ ነው የኔ ምኞት ጥንትም ሆነ ዛሬ፣
እንዲህ ሆና እንዳያት ኢትዮጵያ አገሬ።››
የኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል አጥብቀው ይጥሩ እንደነበር የሚነገርላቸው ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፣ በየጊዜው አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ እርሻና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ለንጉሠ ነገሥቱ ሃሳብ እያቀረቡ የውሀ ግድቦችና ሰፋፊ እርሻዎች እንዲሠሩ አድርገዋል። በፍል ውሃ ድርጅት ዳይሬክተርነትና በፖስታ ሚኒስትርነትም አገልግለዋል። የሕዝብን መንፈስ የሚያዳክሙ ነገሮችን በፅኑ ይቃወሙ ስለነበር ከልክ ያለፈ የመጠጥ፣ የትምባሆና የጫት ተጠቃሚነት አመል እንዲጠፋ በምሳሌነትም ሆነ በምክር ከፍ ያለ ትግል አድርገዋል። የእርሳቸውም አመጋገባቸውና የመጠጥ አወሳሰዳቸው በጥብቅ ፕሮግራምና ስርዓት ይከናወን እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል።
ከመንግሥታዊ አገልግሎታቸው በተጨማሪም፣ በተለያዩ ጊዜያት ከግሪካውያን ጋር በመሆን የሸክላ ጣሪያ በማምረትና በእርሻ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል። ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አዲስ አበባ ከተማ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ አለቃ ነገደ እስራኤል የተባሉ መምህር ቀጥረው ከመንደሩ ለተውጣጡ ልጆች ነፃ የአማርኛ ትምህርት እንዲሰጥ አድርገዋል።
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ‹‹ነጋድራስ ተሰማ የአማርኛን ውበትና ውስጠ ምስጢር በተሰጥኦ የተካኑ፣ የቋንቋውን ብልት ተንትነው የበለቱ፣ ሰዋሰውስ ሸዋ ሰው የሚያሰኙ ነበሩ›› በማለት አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል። የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አደርኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛና አረብኛ ቋንቋዎችን ይናገሩ ነበር።
የአየር ኃይል አብራሪ የነበረው ልጃቸው መቶ አለቃ ኤልያስ ተሰማ በአውሮፕላን አደጋ መሞቱን ሰምተው ደንግጠው ሲታከሙ ቆዩ። በአንጎላቸው ውስጥ ደም በመፍሰሱና የልሳን ማዕከላቸው በመጎዳቱ የመናገር ችሎታቸው ቀንሶ ለአምስት ዓመታት በሕክምና ላይ ከቆዩ በኋላ ጥቅምት 3 ቀን 1957 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 /2014