
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ከሁለት ዓመታት በኋላ ቻይና ትልቅ በተባለችው ከተማ ላይ ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች።
የቻይና የጤና ኃላፊዎች ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ በነዋሪው ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ እስከሚያደርጉ ድረስ ሻንግሃይ ከተማ በሁለት ዙር ለዘጠኝ ቀናት የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባታል።
የቻይና ምጣኔ ሃብት ማዕከል ከሆኑት ከተሞች አንዷ የሆነችው ሻንግሃይ ባለፉት 30 ቀናት የኮቪድ-19 ስርጭት ታይቶባታል።
ምንም እንኳን በሌሎች አገራት አንጻር በከተማዋ የታየው የኮቪድ-19 ስርጭት ይህ ነው የሚባል ባይሆንም የቻይና ባለሥልጣናት ግን ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድን መርጠዋል።
ባለሥልጣናት በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት የ25 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችውን ከተማ ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት ሲያቅማሙ ነበር።
ነገር ግን ባለፈው ቅዳሜ ሻንግሃይ ከወረርሽኙ የመጀመሪያ ቀናት በኋላ በአንድ ቀን ውስጥ ትልቁ ነው የተባለውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ካስመዘገበች በኋላ ባለሥልጣናቱ በፍጥነት እንቅስቃሴ ወደ መግታት እርምጃ ለመግባት ተገድደዋል።
የእንቅስቃሴ ገደቡ በሁለት ዙሮች የሚካሄድ ሲሆን የከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል ለሁለት ሳምንታት ያክል ዝግ ሆኖ ይቆያል። ምዕራባዊው ክፍል ደግሞ በመቀጠል ለአምስት ቀናት በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ እንደሚያልፍ የቻይና የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ይህንን ተከትሎ በከተማዋ የሕዝብ ትራንስፖርት ሙሉ በሙሉ እንደሚቆም ያስታወቁ ሲሆን፤ ትልልቅ
ድርጅቶችና ፋብሪካዎች ሥራቸውን ማቆም አልያም ከቤት መስራት መጀመርን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው ተብሏል።
የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ ዊቻት በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ባስተላለፈው መልዕክት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ለመከላከል ሲባል ሕዝቡ መመሪያዎቹን በአግባቡ እንዲረዳና እንዲተባበር ጠይቋል።
በቻይና በተደረጉ ሌሎች የእንቅስቃሴ ገደቦች በርካታ ከተሞችና ግዛቶች የተዘጉ ሲሆን ነዋሪዎች ግን በአካባቢ የተገደበ እንቅስቃሴ ማድረግ ይችሉ ነበር።
ነገር ግን ሻንግሃይ በጣም ከፍተኛ ሕዝብ የሚኖርባት ከመሆኗ አንጻር መሰል የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለባት ትልቋ ከተማ ሆናለች።
የቻይና የንግድ ማዕከል የሆነችው ሻንግሃይ አንዳንዶች በአገሪቱ ትልቋ ከተማ ነች ይሏታል።
እስካሁን በነበሩ አካሄዶች የቻይና ባለሥልጣናት በተለይ የከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል የንግድ ማዕከል ከመሆኑ አንጻር ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ በሚል እንቅስቃሴዎችን መገደብ የሚለውን ሀሳብ ገሸሽ ማድረግ መርጠው ቆይተዋል።
የእንቅስቃሴ ገደቡን ተከትሎ የሻንግሃይ ነዋሪዎች አስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን አንዳንድ ነገሮች ለመግዛት ሲሯሯጡ ተስተውለዋል። በርካቶች በሱፐር ማርኬቶችና ሱቆች በር ላይ ተሰልፈው ተራቸውን ሲጠብቁ ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የከተማዋ የባቡር አገልግሎትም ቢሆን ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎቱ የሚቋረጥ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎችም በከፍተኛ ቁጥር ወጥተው የኮቪድ-19 ምርመራ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 /2014