–“አግላይነት፣ የፖለቲካ ጽንፈኝነትና መገፋፋት የፖለቲካ ችግሮቻችን ናቸው”
አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት መጨመር ይህንን ተከትሎ የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርት እጥረት ማጋጠሙ የከተማዋ ነዋሪዎች በአግባቡ ሊያስተናግዱ አቅም የሚያንሳቸው የጤና ተቋማት እንዲሁም አገልግሎት መስጫዎች ችግር ሕብረተሰቡን እያማረረ ለብዙ ሮሮና መከራ እየዳረገም ይገኛል።
ይህንን ተከትሎም በተለያዩ ሁኔታዎች እንደ ማሕበራዊ ሚዲያና ሌሎችንም በመጠቀም ሕዝቡ ብሶቱን ሲገልጽም ቆይቷል። ከመጋቢት 2 ቀን እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤውን ማካሄዱን ተከትሎም እንደ ከተማ እንዲሁም እንደ አገር ሕዝቡን ምሬት ላይ የጣሉና የሚስተዋሉ መቀረፍ ያለባቸውን ለውጡም እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን አንስቶ ተወያይቶ በጉዳዮቹ ላይም የመፍቻ አቅጣጫን አስቀምጦ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
ይህንን ተከትሎም እንደ አገር ሕዝቡ ምን ምሬት አለበት? ከብልጽግና ፓርቲስ የሚጠብቀው ምንድን ነው? የሚለውን ለመለየት ብሎም በጉባኤው የተቀመጠውን አቅጣጫ ወደ ሕዝቡ ለማውረድና ሕዝቡ ጋር ያለውን ስሜት ለማዳመጥ ያለመ በከተማ ደረጃ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ካቢኔዎቹን በመመደብና ሕዝቡ ከብልጽግና ምን ይፈልጋል? አሁን ያለበት ሁኔታ ምን መልክ አለው? የሚለውን በአግባቡ ለመመርመር ትልቅ ሕዝባዊ ጉባኤን አካሂዷል። በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ አደም ፋራህ በተገኙበት በተካሄደው መድረክ ላይ ሕዝቡ አሉብኝ ያላቸውን ብሶቶች፣ የወደፊት ተስፋና ስጋቱን እንዲህ ገልጿል።
የከተማዋን ሴቶች በመወከል በመድረኩ ላይ የተገኙት ወይዘሮ እንዳሉት እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ፖለቲካ ስለአንተ እኔ አውቅልሃለሁ የሚል ነበር ፤አሁን ግን ብልጽግና ሕዝቡ ከእኔ ምን ይፈልጋል? እኔን መርጦኛልና በምን መልኩ ላስተዳድረው? የሚለውን ለማወቅ ወደ ሕዝብ ወርዶ ማወያየቱ ትልቅ ነገር በመሆኑ ልትመሰገኑ ይገባችኋል።
አሁን ላይ አገር እየተተራመሰ ያለው ተምረናል፣ አውቀናል የእናንተንም ችግር እናውቅላችኋለን በሚሉ ነው ፤ በዚህ ላይ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። አሁን ላይ ከተማ አስተደዳሩ በተለይም የእኛን የድሆቹን ልጆች በትምህርት ቤት ምገባ እየመገበልን እኛ ደግሞ የልጆቻችንን ምግብ እንድናዘጋጅ እድል ሰጥቶናል ትልቅ ነገር ነው ፤ ነገር ግን ቀጣይነት እንዲኖረው ምን እየተሰራ ነው የሚለው ነገር በግልጽ ቢነገር፤ ሲሉ ጠይቀዋል። በሌላ በኩል አዲስ አበባ ከተማ ላይ መንግሥት ፍቃድ ሰጥቶት የዜጎችን ጉልበት የሚበዘብዝ ኤጀንሲ የሚባል ተቋም አለ ፤ እናንተ ፍቃድ ሰጥታችሁ እኛን እየጎዳችሁን ነው።
መንግሥት በቀጥታ ሥራ ፈላጊውን መቀጠር ለምን አቃተው? የጥቂቶች መበልጸጊያ እንዲሆን በማሰብ ብቻ የተሰራ ነው በመሆኑም ሊታይ ይገባል። እስከ አሁን የመጣችሁበት መንገድ ብልሹ አሰራርን የካበ ያንቆለጳጰሰ ነበር፤ ይህንን ማድረጋችሁ ደግሞ እንደዚህ ዋጋ አስከፍሏችኋል ፤ አሁንም ቢሆን አጥፊዎችንና ብልሹ አሰራርን በመዋጋት በኩል መንግሥት ከፍተኛ የሆነ ትዕግስት እያሳየ ችግሮቹም ስር እየሰደዱና እየገነገኑ የመጡበት ሁኔታ ነው ያለው በመሆኑም ለብልሹ አሰራር የምንሰጠው ምላሽ ፈጣንና የማያዳግም ሊሆን ይገባል። እንደ ሴቶች ተወካይዋ ገለጻ ብልጽግና ትልቅ ራዕይ ያለው ፓርቲ ነው፤ ነገር ግን ከታች ሆኖ የሚያስፈጽምለት አላገኘም።
ክፍለ ከተማና ወረዳ ሌላ መንግሥት ነው ያለው ፤ መብራት ሃይልና ውሃና ፍሳሽም እንደዛው ራሳቸውን መንግሥት አድርገው የተቀመጡ አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው ፤ በጠቅላላው በአገራችን ያለው የመንግሥት ብዛቱ ስፍር ቁጥር የለውም ይህ ሊታይ ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ክብርት ከንቲባ እንደተሾሙ ሰሞን በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች ላይ ድንገተኛ ጉብኝት እያደረጉ የሕዝቡን ሁኔታ ፤አገልግሎት አሰጣጡን ያዩ ነበር፤ ይህ ጥሩ ቢሆንም ከሰሞነኛ ሁኔታ አላለፈም፤ በመሆኑም በወረቀት የሚመጣሎትን ሪፖርት አምነው አይቀመጡ በወረቀት እየሄደ ያለ ሪፖርት አገር የሚያፈርስ የነዋሪውን ነባራዊ ሁኔታና ችግሮቹን የማያሳይ ነው።
በመሆኑም እንደ ቀድሞው አልፎ አልፎም ቢሆን ሥራዎችን በተለይም አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ወርዳችሁ እዩ። ብሔርና ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ በሁለት ቢላ የሚበላ አመራራችሁን ፈትሹ ያሉት አስተያየት ሰጪዋ ይህንን ማድረግ ካልቻላችሁ ግን ከዚህ በላይ ዋጋ ልትከፍሉ ትችላላችሁ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ከፍተኛ የሆነ ችግር ላይ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በኑሮ ወድነት እየተፈተነ ነው በተለይም አሁን መሰረታዊ የሚባሉትን የፍጆታ እቃዎች እንኳን በአግባቡ ከሙስና በጸዳ ሁኔታ የሚያቀርብለት አጥቶ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል። ይህ በቶሎ አልባት ካላገኘ ለመንግሥት ለድርጅቱም ጠንቅ ይሆናል ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶችን በመወከል የተናገሩት ሰውም እንዳሉት ሕዝቡ ብዙ ሰቆቃ ያለበት ነው ይህንን ደግሞ አታውቁትም ለማለት እቸገራለሁ የቁስሉንም አይነቶች ዳሳችኋላል ግን ምን ያህል ነው የሚለው አሁንም አጠያያቂ ነው። አሁን ከእናንተ የሚጠበቀው ብዙ ማውራት ሳይሆን ጥቂት በመስራት የሕዝቡን ቁስል ማከም ነው።
አሁን ላይ የከተማው ነዋሪ ችግሮች ተደራራቢና ትልቅ በመሆናቸው የቱ ተፈቶ የቱ እንደሚቀር እራሱ አስጨናቂ መሆኑንም ተናግረዋል። በተለይም የከተማው ነዋሪ እህል አጥቶ እንደሚራበው ሁሉ በሰላም ወጥቶ የመግባቱ ነገር እጅግ አሳሳቢ ረሃብ ሆኖበታል፤ ክብርት ከንቲባ እርስዎ ከሚያስተዳድሯቸው የቢሮዎ ሰራተኞች ጀምሮ የመንግሥት ሰራተኛው በሙሉ በመሀል ከተማ የመኖር እድል አላገኘም። ከከተማው ወጥቶ ነው የሚኖረው፤ ይህ ደግሞ የትራንስፖርት ችግር ከፍተኛ በመሆኑ ከቤቱ ሌሊት መውጣት ማታም አምሽቶ መግባት ግድ እያለው ነው።
በዚህ ውስጥ ደግሞ ሌሊት ወጥቶ ለመስራትም አመሽቶ ወደቤቱ ለመግባትም የከተማዋ ሰላም አስተማማኝ አይደለም ሰቀቀኑ ገድሎታል በማለት ገልጸዋል። የሰላሙ ጉዳይ አሳሳቢ ነው ያሉት ተወካዩ አሁን ላይ ሰዎች ለዘመናት የኖሩበትን ቤት ራሱ አምጡ የእኔ ነው በማለት ሰላም የሚታወክበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ ዛሬ ላይ በእጃችን ያሳደግናቸው ልጆች ሳይቀሩ ከሰውነት ወደአውሬነት ተቀይረዋል።
ይህንንስ ውጥረት መቼና እንዴት ነው የምትፈቱት? ይህንን ችግር ለመፍታት ከተነሳችሁ እኛስ እንደ ሕዝብ ምንድን ነው ማገዝ ያለብን የሚል ጥያቄ አዘል ሃሳብ አቅርበዋል። ኑሮው እንድ እሳት እያንገበገበው ያለው የከተማ ነዋሪ ምንም እንኳን የሸገር ዳቦም የሚያስፈልገው ቢሆንም ዳቦ ለመግዛት አምሽቶ ለመግባት ሰርቶ ለመብላት ልጆቹን ለማሳደግና ለማስተማር ሰላም በእጅጉ እንደሚያስፈልገው መገንዘብ አለባችሁ ብለዋል።
አሁን ላይ እንደ ሰው አቅዶ የሚኖር ቤት የሚሰራ ሌላም ሌላም ነገር የሚያደርግ የከተማ ነዋሪ የለም ፤ ከዛ ይልቅ በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነው ያለው በመሆኑም የጀመራችሁትን ሕዝብ የማዳመጥ ሁኔታ ቀጥሉበት። ግን ደግሞ ሰምቶ ዝም ማለት ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃም ወስዳችሁ ማሳየት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹነቱ በአሁኑ ወቅት ሥርዓት መንግሥት ጠል የሆነ ሕዝብ አፍርቷል በተለይም በተቋማት በኩል ጉዳይ ይዞ መሄድ ካለ ደላላ (ጉዳይ አስፈጻሚ) የሚሳካ አይደለም፤ የማይታሰብ እስከመሆን ደርሷል። በተለይም አገልግሎት አሰጣሰጥ ላይ እየታየ ያለው ችግር ሌቦችን የሚያበራክት ሕዝብ በአገሩ ላይ እንደ ባይተዋር እንዲሆን ብሎም መንግሥት ላይ እንዲያምጽና ታዛዥ እንዳይሆን የሚያደርግ በመሆኑ እንደ ከተማ አስተዳደርም ሆነ እንደ አገር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታችሁ መስራት ይገባችኋል የሚል ሃሳብም አንስተዋል።
ብልጽግና ከላይ ያለው አመራሩ ጥሩ ነው ቁርጠኛም ይመስላል፤ ነገር ግን ሕብረተሰቡን በእለት ተዕለት እንቅስቃሴው የሚያገኙት የታችኞቹ አመራሮች እውነት ብልጽግና ናቸው ወይ? የብልጽግና ዓላማስ ገብቷቸዋል ወይ? ወይስ እንደሚባለው በተረኝነት ስሌት ውስጥ እየዋኙ ነው ሕዝብን የሚያስለቅሱት የሚለው ሊታይልን ይገባል፤ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ እነሱን የሚታገስ ለእነሱ ጉቦ እየሰጠ ጉዳይ የሚያስፈጽም በጠቅላላው እነሱን ደጅ ለመጥናት ዝግጁነት ያለው የከተማ ነዋሪ የለም። ይህ አልሆነም ማለት ደግሞ በእናንተ ወንበር ላይም ችግር ማስከተሉ አይቀርምና በተቻለ ፍጥነት እነዚህን ሕዝብ የሚያስለቅሱ የበታች ሹማምንቶቻችሁን እዩልን በማለትም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
በጠቅላላው በውይይት መድረኩ ላይ የታደሙ ነዋሪዎች ሰላም ለማስፈንና ጸጥታን ለማስከበር ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲሰራ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱ የሚታዩ ብልሽቶችን ለማስተካከል አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ጠይቀዋል። ሥራ አጥነትን፣ የኑሮ ውድነትና ግሽበትን ለመቀነስ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው ተወያዮቹ ጠይቀዋል።
በርካታ እናቶች ወደ ጤና መድህን እንዲገቡ ቢደረግም በሚገባው ልክ እየተጠቀሙ ባለመሆናቸው መፍትሄ እንዲሰጥም በውይይቱ ላይ አንስተዋል። የጎዳና ተዳዳሪዎች ጉዳይ ትኩረት ይፈልጋል፣ የቤት ኪራይ ዋጋ መናርም መታየት አለበት ብለዋል ነዋሪዎቹ። በሥራ ላይ ያለው ሰንደቅ ዓላማም ወደቀድሞው እንዲመለስና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግርም እንዲስተካከል በውይይቱ ተጠይቋል።
በሕብረተሰቡ መካከል የተፈጠሩ አለመተማመኖችን ለማረምም ከሃይማኖት ተቋማትና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር መስራት ይገባል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ አንድነትን፣ መተባበርንና መተጋገዝን የማይፈልጉ አካላትን ለማጋለጥ ከመንግሥት ጋር እንደሚሰለፉም ቃል ገብተዋል። የቀደመው አይነት ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን በአንድ አካባቢ ሰዎች የመያዝ አባዜ ሊታረሙ የሚገባቸው ናቸው ብለው ካነሷቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተሰጡት ሃሳቦች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያም እንደ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ በርካታ ተግባራት ቢኖሩም አሁንም ነዋሪውን እርክተነዋል የሚል እምነት የለንም።
ይህንንም ስላወቅን ነው እንመካከር ማለታችን ብለዋል። በተለይም በቂ ጊዜ አልተሰጠንም ጥያቄያችን አልተመለሰም የእኛ ፍላጎት አልተከበረም የሚሉ እንደ ከተማም እንደ አገርም ብዙ ድምጾች አሉ። ይህንን ህመም ለመላቀቅ ደግሞ አካታችነት ትልቁ መፈትሔ ነው ብሎ ብልጽግና ያምናል።
ሁሉም ካልተሳተፈበትና ለሁላችንም የምትበጅ አገር ካልገነባን ሁላችንም ማስተናገድ የሚችል የፖለቲካ ሥርዓት ካልኖረ ሁላችንም ነን ችግር ውስጥ የምንገባው ብለዋል። እንደ ከንቲባዋ ገለጻ ሥርዓቱ ሁላችንንም የሚያስተናገድ ሁላችንንም ደግሞ የሚያሳትፍ ሊሆን ይገባል፤ ይህንን ማድረግ ደግሞ ግድ ነው። ምክንያቱም ይህንን ማድረግ ካልቻልን ማንም ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም።
በአንድ አገር እየኖርን ደግሞ ገለልተኛ ተደርጎ ቁጭ ብለህ ተመልከት የሚባል ሊኖር አይገባም። የኔ የኔ ለኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ልንዋጋው ሁሉንም አስተሳሰቦች ወደመካከል ልናመጣው ይገባል፤ ለኔም ለእሱም ለሌላውም በጠቅላላው ደግሞ ለሁላችንም የሚል አስተሳሰብን መገንባት ያስፈልጋል ካሉ በኋላ በብሔርና በሃይማኖት በመገፋፋት ፖለቲካ የትም ልንደርስ አንችልም ይህ መቀረፍ ያለበት ከመሆኑም በላይ ወንድማማችነትን የትብብር መንፈስን እህትማማችነትን ማስፈን ያስፈልጋል ብለዋል።
በጠቅላላው አግላይነት የፖለቲካ ጽንፈኝነት መገፋፋት የፖለቲካ ችግሮቻችን ናቸው ፤ እነዚህን ስብራቶች ደግሞ በዚህ መሰል መድረክ ተነጋግረን ካልፈታን እያነከስን የምንሄደው ጉዞ የት ድረስ ነው የሚያደርሰን ወደብልጽግናችን አገርን ወደመገንባት ወይስ ወዴት በመሆኑም ያሉብንን የፖለቲካ ስብራቶች በአካታችነት በሚዛናዊነት በመተሳሰብ የፖለቲካ ባህል መተካት ያስፈልጋል ብለዋል ወይዘሮ አዳነች።
ሁሉንም የማሕበረሰብ ክፍል ቀርበን ልናዳምጠው ይገባል ያልነው ብዙ የሚነግረን ነገር እንዳለ ስለምናውቅ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች በ 121 ወረዳዎችና በ11 ክፍለ ከተሞች በተካሄደው መድረክ ሁላችንም የየድርሻችንን ወስደን ጥያቄዎችን በሚገባቸው ቅደም ተከተል እየፈታን የምንዘልቅ ይሆናል ብለዋል።
ትርክቶች፣ ሰንደቅ ዓላማና መሠል አጀንዳዎች በአገር አቀፍ ምክክሩ ላይ አጀንዳ ተደርገው ተይዘዋል ያሉት ከንቲባዋ በዚያም መፍትሔ ያገኛሉ ብለን እናምናለን ሲሉ ገልጸዋል። የተነሱ ችግሮችና ጥያቄዎች በአንድ ጀንበር ላይፈቱ ቢችሉም ደረጃ በደረጃ መፍትሄ ይሰጣቸዋል፣ አንዳንዱን በአፋጣኝ ስር የሰደደው ደግሞ በሂደት እንደሚቀረፍም አመላክተዋል። የመንግሥት ሠራተኞች በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል ይገባቸዋል ያሉት ከንቲባዋ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያገለግል፣ ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚያጸና አንድነት እንደሚገነባም ቃል ገብተዋል።
የፖለቲካ ስብራቶች እንዲጠገኑ ሕብረተሰቡን ያማከለ ሥራ እንደሚሠራ የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፤ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ዘላቂ ሰላም ማስፈን ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ትግበራው ሕብረተሰቡን ያማከለ ይሆናልም ብለዋል። አብሮ የመኖር እሴትን ለማጎልበት የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን በመጠቆምም፤ የዜሮ ድምር የፖለቲካ ችግሩ ተጽእኖ መፍጠሩንም ተናግረዋል። አግላይነት፣ በብሔርና በፖለቲካ አመለካከት መገፋፋት የፖለቲካ ጉዞው ችግር ናቸው።
የኑሮ ውድነትና ግሽበትን ለመቆጣጠር ይሠራል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ችግሩን ለመቅረፍ አቅርቦትን ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግና በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተሞክሮው እንዲሰፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል። የንግድ ሚዛኑን የሚያዛቡ ነጋዴዎችን በማረም የንግድ ሥርዓቱን ለማስተካከል ቁጥጥር ይደረጋል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሽቱን ለማረምም መንግሥት ይሰራል።
ቤተ እምነቶች፣ ልሂቃን፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ጋዜጠኞች፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች ከችግሮቹ ለመውጣት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል። የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው አመራሮችን ማጥራት፣ የተቋማትን አሰራር መፈተሽ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ሌብነትን መታገል ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የተመለከቱ ጥያቄዎችና ሌሎችንም ከሕዝቡ ጋር ተቀራርበን እየመከርን በጋራ እያረምን የምንሄደው የቤት ሥራችን ይሆናል ብለዋል።
አግላይነትን በማስወገድ፣ ልዩነትን ማጥበብ እና ሕዝባዊ አንድነታችንን በማጠናከር በጊዜ ሂደት ሕዝባችንን በማሣተፍ ፈተናዎቻችንን በመሻገር ላጋጠሙን ችግሮችም መፍትሄ እየሰጠን የምንሄድ ይሆናል ያሉት አቶ አደም ከሕዝብ የሚሰበሰቡ ጥያቄዎችን ወደ ዕቅድ በመለወጥ በሂደት ለተነሱ ጉዳዮች ተመጣጣኝ ምላሽ እየሰጠን እንሄዳለን ለስኬታማነቱም ሕዝባችን በሁሉም ረገድ ሊያግዘን ይገባል ብለዋል።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 /2014