ልጆች የዛሬ ሁለት ሳምንት የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ከዲላ ዩኒቨርሲቲና ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ከየካቲት 12 እስከ 16/2014 አመተ ምህረት በደማቋና አረንጓዴዋ፣ በጌዴኦ ዞን ስር በምትገኘው ዲላ ከተማ ደማቅ የንባብ ሳምንት መድረክ ተዘጋጅቶ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደ ተሳተፈበት ነግሬአችሁ ነበር። አዎ፣ ብዙ ልጆች እንደየፍላጎታቸው በመጻሕፍት አውደ ርእዩም ሆነ አጠቃላይ የንባብ ባህልን ለማጠናከር የተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ተሳትፈዋል፤ ይህንንም ነግሬአችኋለሁ።
ዛሬ ደግሞ የምነግራችሁ በእለቱ ከንባብ ባህል ጋር በተያያዘ እቦታው ላይ ተገኝተው ሲያነቡ፣ ሲገዙና ሲጎበኙ ያገኘናቸውን የዲላ ልጆች አነጋግሬ የሰጡኝን አስተያየት እኔም መልሼ ለእናንተ እነግራችኋለሁ።
ልጆቹ ተማሪዎች ናቸው። የሚማሩትም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ነው። ሁሉም እድሜያቸው ተቀራራቢ ነው። ፍላጎታቸውም የተቀራረበ ሲሆን እንቅስቃሴያቸውም አንድ ላይ ነው። በመሆኑም በቀላሉ አንድ ላይ አግኝቼ ላነጋግራቸው ቻልኩ።
ባለፈው እንደነገርኳችሁ በመጀመሪያ ያናጋገርኳት የኮሚዩኒቲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችውን ኤደን ቢልቢልሳን ነበር። የ13 አመቷና የ7ኛ ክፍሏ ተማሪዋ ኤደን እንደነገረችኝና እኔም እንደ ነገርኳችሁ ከሆነ ንባብ በጣም ትወዳለች። ቤተሰቦቿም ያነባሉ። ስለዚህ ንባብ ለእሷ አዲስ ነገር አይደለም። የዛሬው እንግዳችንስ ምን ይላል? የሚለውን ደግሞ አብረን እንመለከታለን።
የዛሬው እንግዳችን ከእነ ኤደን ጋር ተሰባስቦ በማንበብ ላይ የነበረውና በጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአንደኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሙሉቀን ገዛኸኝ ነው። ሙሉቀን ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሲያነብ አገኘሁት። እንደ ጓደኞቹ ሁሉ የያዘው መጽሐፍ ከፍ ያለ ሲሆን በመጽሐፉ ላይ ያረፈው የፊደል አቀማመጥም መጠኑ ከፍ ከፍ ያለ ነው። ለማንበብ አያስቸግርም። በመሆኑም ተማሪ ሙሉቀን ሳይጨናነቅ ነበር የሚያነበው። መቅረፀ ድምፄን ይዤ ተጠጋሁት። ላነጋግረው እንደ ፈለኩ ገብቶታል መሰለኝ በፈገግታ ተመለከተኝ። መነጋገር ጀመርን። በምንነጋገርበት ጊዜ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? አዎ፣ ስለ ንባብ የሚከተለውን ነበር ያለኝ።
እድሜዬ ዘጠኝ አመት ነው። ፀሐይ ጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአንደኛ ክፍል ተማሪ ነኝ። ወደ እዚህ የመጣሁት እንድመጣና እየሆነ ያለውን እንድመለከት ተጠርቼ ነው። የተጠራሁት ደግሞ በትምህርት ቤቴ በኩል ነው። ሂዱ፣ ብዙ ነገር ትማራላችሁ ተብለን ነው የመጣነው። ሁሉም ነገር በጣም ደስ ይላል። ያምራል። ማንበብ በጣም ደስ ስለሚል ማንበብ በጣም እወዳለሁ። ለጓደኞቼም ይሄንኑ ነው የምነግራቸው፤ “ማንበብ ጥሩ ነው፣ ደስ ይላል” ብዬ ነው የምንግራቸው። እንዲያነቡ ነው የምመክራቸው። መጻሕፍትን አንብቡ ነው የምላቸው።
ሌላው እዛው የሚያነቡት ልጆች ጋር በመሆን ሲያነብ ያገኘሁትና ያነጋገርኩት ተማሪ ሙሉቀን ወርጌ ነው። ሙሉ ቀንም ልክ እንደ ጓደኞቹ፣ እንደ ሞክሼው ሙሉቀን ገዛኸኝ ንቅት ያለ ነው። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መጽሐፍ ማንበብ መቻሉ ደስ ያለው ይመስላል። ላነጋግረው እንደፈለኩ ገብቶታል። እንደውም ጓደኛው ሙሉቀንን ሳናግር ጣልቃ እየገባ መልስ ሊሰጠኝ ይፈልግ ሁሉ ነበር። እሱስ ምን ያለኝ ይመስላችኋል? አዎ፣ ሙሉቀን ወርጌም የሚከተለውን ነበር ያለኝ።
እድሜዬ 10 ነው። በዳዊት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነኝ። ወደ እዚህ የመጣሁት እህቴ (ወይንሸት ወርጌ) ነግራኝ ነው። እሷ እዚህ መጥታ ነበር። ልማር ነው የመጣሁት። ላጠና ነው የመጣሁት። በጣም ደስ ይላል። ነገም ቢኖር ጥሩ ነው። እኔ አንባቢ መሆን ነው የምፈልገው። ለጓደኞቼ የምመክራቸው ሁሉም እንዲያነቡ ነው። አንብቡ ነው የምላቸው።
ልጆች፣ የዛሬ እንግዶቻችን ስለ ንባብና እውቀት ምን እንዳሉ በጽሑፍ አማካኝነት ሰማችኋቸው አይደል፤ አዎ፣ በጥቅሉ ማንበብ ደስ የሚል ተግባርና የእውቀት ምንጭ መሆኑን ነው የነገሩን። እናንተም በእነሱ ሀሳብ እንደምትስማሙ እርግጠኛ ነኝ። ትስማማላችሁ አይደል፣ በጣም ጥሩ። ለዚህ እኮ ነው ባለፈው ጊዜ “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!!!” በሚለው ላይ በደንብ የተነጋገርነውና የተስማማነው።
በሉ እንግዲህ ልጆች፣ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ በዲላ ከተማ “መጻሕፍት ለእውቀት ገበታ፤ መዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ለዘመን ትውስታ።” በሚል መሪ ቃል ባካሄደው “የወጣት ተኮር ንባብ እና የምርምር ንቅናቄ መድረክ” ሳምንት ላይ በቦታው ተገኝቼ ያነጋገርኳቸውን ልጆች ነበር ያስተዋወኳችህ። ሳምንት ደግሞ በሌላ ርእስ እንገናኛለን። እስከዛው ሰላም ሁኑ ልጆች፤ መልካም የትምህርት ሳምንት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2014