«የመጀመሪያው እንጂ ሌሎቹ ዋና ቀዶ ህክምና አይደሉም፤በሆስፒታሉ የማይገኙ መድሃኒቶችን እንድንገዛም ህጉ አይፈቅድም» ሆስፒታሉ
አዲስ አበባ:- በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ለመውለድ የገባችው ባለቤታቸው ሶስት ጊዜ ቀዶ ህክምና ቢደረግላትም እንዳልተሻላት እና እስከአሁን ድረስ ለመድሃኒት ግዢ ከ25ሺ ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸው አግባብ አለመሆኑን አቶ ተስፋዬ ደስታ ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ በበኩሉ ሶስት ጊዜ ቀዶ ህክምና አለመካሄዱን እና የመድሃኒት ወጪውም በሆስፒታሉ የማይገኙ መድሃ ኒቶችን የተመለከተ መሆኑን ገልጿል። አቶ ተስፋዬ ደስታ ታህሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ነበር ለመውለድ የተቃረበች ባለቤታቸውን ይዘው በሆስፒታሉ የተገኙት። ባለቤታቸው ወይዘሮ አየለች ድጉማ በቀዶ ህክምና ስድስተኛ ልጃቸውን በሰላም ከተገላገሉ በኋላ ታህሳስ አራት ቀን ወደ ቤታቸው መሄዳቸውን አስታውሰዋል።
የባለቤታቸው የሆድ መጠን ሊቀንስ ባለመቻሉ ተመልሰው ወደሆስፒታሉ ሲሄዱ ኢንፌክሽን መፈጠሩ ተነግሯቸዋል። የማጠብ ስራ ከተከናወነ በኋላ ለተከታታተይ ሁለት ጊዜ ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸዋል። ከሶስት ወራት በኋላም ከፍተኛ የህመም ስሜት እያሰቃያቸው መሆኑን አስታውሰዋል። «ይዤ የመጣሁት ጤነኛ ሰው ነው፤ እባካችሁ ባለቤቴን አድኑልኝ እያልኩ ዶክተሮቹን ብጠይቅም ሰሚ አላገኘሁም» የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣የስድስት ልጆች አባት ሆነውሳለ ሙሉ ጊዜያቸውን ሆስፒታል ውስጥ ለማሳለፍ መገደዳቸው ተጨማሪ ጉዳት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ስህተቱ በሆስፒታሉ የተፈጸመ በመሆኑ የህክምናውን ወጪ መሸፈን ሲገባው እስከአሁን ድረስ ከ25ሺ ብር በላይ ለመድሃኒት ግዢ እንዲያወጡ መገደዳቸው አግባብ አለመሆኑንም ተናግረዋል። ስድስተኛ ልጃቸውን ለመሳም የጓጉት ወይዘሮ አየለች ድጉማ በሰላም ቢገላገሉም በሆስፒታሉ የተሰጣቸው ህክምና ለከፋ ስቃይ እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡ ሶስት ወራት ሙሉ አልጋ ላይ በመተኛታቸው አቅማቸው መዳከሙን እና አሁንም በከፍተኛ ህመም ውስጥ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ልጃቸውን በአግባቡ ለማጥባት እንደተቸገሩ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸው እንደማያውቅ የተናገሩት ወይዘሮ አየለች፤ በአሁኑ ወቅት ምግብ በአግባቡ መመገብ እንደማይችሉ እና ከፍተኛ ትኩሳት እንዳለባቸው አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት የደም ማቅጠኛ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጾላቸው «ተኝ ተው ይታከማሉ ወይንስ ቤትዎ ሄደው ህክምና ይሰጥዎት?» የሚል ምርጫ ቢቀርብላቸውም የከፋ ችግር እንዳይደርስባቸው በመፍራት በሆስፒታሉ ቆይተው ህክምናውን ለመከታ ታል መገደዳቸውን ተናግረዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የማህጸንና ጽንስ ህክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ታደሰ ኡርጌ እንደገለጹት፤ታካሚዋ በቀዶ ህክምና ከወለዱ በኋላ ኢንፌክሽን አጋጥሟቸዋል። ኢንፌክሽን በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል። በመሆኑም ቁስሉን የማጠብ እና የማከም ስራ በማስፈለጉ ሁለት ጊዜ አነስተኛ የቀዶ ህክምና /ማይነር ኦፕራሲዮን/ ተደርጎ የታካሚዋ ሆድ ላይ ያለው የተጎዳ አካል ተነስቶ ሌላ ስፌት ተሰርቷል። በመሆኑም ሶስት ጊዜ ቀዶ ህክምና ተደርጓል ማለት እንደማይቻል አስታውሰዋል።
እንደ ዶክተር ታደሰ ማብራሪያ፤ የታካሚዋ ቁስል ሰፊ በመሆኑ በፍጥነት ኢንፌክሽኑ ሊቀንስ አልቻለም። በመሆኑም የሆስፒታሉ ህክምና ባለሙያዎች ተገቢውን ህክምና እየሰጧቸው ነው። በመድሃኒት ግዢ በኩል የቀረበው ጥያቄ ከሆስፒታሉ አሰራር ውጪ ነው። ምክንያቱም በመንግስት ሆስፒታሎች አሰራር በህክምና የታዘዘ መድሃኒት በግቢው የመድሃኒት መደብር ከተገኘ በነጻ መውሰድ ይቻላል። ለታካሚዋ የታዘዙት አንዳንድ መድሃኒቶች ግን በሆስፒታሉ የመድኃኒት መደብር ባለመገኘታቸው በእራሳቸው ወጪ ገዝ ተው ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው አስረድ ተዋል።
ዶክተር ታደሰ ስለቀጣዩ ህክምና እንዳ ስረዱት፤ እስከአሁን እንደተደረገው ሁሉ አሁንም ለታካሚዋ አስፈላጊው ህክምና እየሰጠ ይገኛል። አሁን ያለው ከፍተኛ ትኩሳትም ብዙ ጊዜ ከመተኛት ጋር ተያይዞ የመጣ የደም መጓጎል በመሆኑ ከችግሩ ጋር የተያያዘ ህክምና እየተሰጠ ነው። ከታካሚዋ ቆይታ አንጻር አሁንም በሆስፒታሉ የማይገኙ መድኃኒቶች ሊታዘዙ የሚችሉበት እድል መኖሩ እንደማይቀርም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ምክትል ፐሬዚዳንት ዶክተር ብርሀኑ ነጋ እንዳሉት፤ በጤና ሚኒስትር የህግ ጉዳይች ዳይሬክቶሬት ስር በተገልጋዮች ዘንድ የሚቀርቡ የህክምና ቅሬታዎችን የሚያይ የፌዴራል ስነ ምግባር ኮሚቴ አለ። ኮሚቴው ቅሬታውን ተቀብሎ ጉዳዩን ለሚያጣራ አካል ያስተላልፋል። በመሆኑም የታካሚዋን ቅሬታ ከሆስፒታሉም አልፎ በጤና ሚኒስቴር ደረጃ መቅረብ የሚያስችል አሰራር አለ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011
በጌትነት ተስፋማርያም