ታሪኩ የሆነው ከዓመታት በፊት ነበር። ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መግቢያ ውጤት እንደ ዲቪ ሎተሪ በሚቆጠርበት ጊዜ። ባለታሪኩ ተማሪ መዘጋጀት ባለበት ደረጃ የተዘጋጀ እንደሆነ ስለቆጠረ ውጤቱን በጉጉት ነበር የጠበቀው። የአስራ ሁለት አመታቱን ጉዞ ውጤት። በወቅቱ ውጤት የሚገለጸው በት/ትቤቱ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ነበር።
ለዲግሪና ለዲፕሎማ ያለፉ ተማሪዎች በውጤታቸው ቅደም ተከተል ይጻፋሉ። ባለታሪኩ ተማሪ ውጤቱን ሊመለከት በጉጉት ወደ ትምህርት ቤቱ አቅንቶ በተማሪዎች የውጤት መግለጫ ሰሌዳ ላይ አይኑን ተክሏል። ከተዘረዘሩት ተማሪዎች ዝርዝር ውስጥ የእርሱን ስም በአይኑ ፈለገ፤ ደጋግሞ ፈለገ፤ በትኩረት ፈለገ፤ ነገር ግን ስሙ የለም። ለአመታት የደረጃ ተማሪ ሆኖ የመጣው ተማሪ የሚያየውን ማመን አቃተው። የሕይወቱ ፍጻሜ አድርጎም ቆጠረ። ደጋግሞ ዝርዝሩንም ተመለከተ በዝርዝሩ ውስጥ የእርሱ ስም የለም፤ የዓለም ፍጻሜ ሆኖ ተሰማው። አሳዛኙ ታሪክ ተማሪው እራሱን ለማጥፋት መፍጠኑ ነበር።
በእውነት የሆነ ታሪክ። ቤተሰቦቹ የደስታውን ቀን እየጠበቁ ሳለ የልጃቸውን ራስን ማጥፋት ሃቅ ተጋፈጡት። ታላቅ ዱብ እዳ።
ትልቅን ነገር ተስፋ አድርጎ፤ ተስፋ ያደረጉትን ባጡ ጊዜ ለውሳኔ በመፍጠን ውስጥ የሚያጋጥም ጥፋት። አሳዛኙ ነገር ተማሪው በከፍተኛ ውጤት ለዲግሪ ያለፈ መሆኑና የተማሪዎች ዝርዝር ሲጻፍ የተዘለለ መሆኑ ነበር።
ትምህርት ቤቱ አስተካክሎ ውጤቱን ቢጽፍም ተማሪው ግን እስከ ወዲያኛው አሸልቦ ነበር። ላይመለስ እስከ ወዲያኛው። የፈተናው ውጤት የፈጠረበት የችኮላ ውሳኔ። ይህን ታሪክ እንደ መነሻ እንድናነሳ ያደረገን ከሰሞኑ የተማሪዎች የፈተና ውጤት ዙሪያ ላይ እየተደረገ ያለው ሰፊ ውይይት ነው። ከየአቅጣጫው የተቃውሞ ድምጽና የማሳሰቢያ መልእክት እየተላለፈ ነው።
በብዙ ያልተጠበቀ ስለሆነ መነጋገሪያነቱ የሰፋም ሆኗል። የፈተናው ውጤትን መቀበል የቸገራቸው ምክንያቱን እያስረዱ የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን በሰፊው ገልጸዋል። የፈተናው ውጤት! በምናባችን በአንድ የማዋለጃ ክፍል ውስጥ እንግባ።
እናት ልጇን ልትታቀፍ እያማጠች ነው። ቤተሰብ ደግሞ ከውጭ ሆኖ በተፈቀደለት ቦታ ላይ የምጡን ውጤት ይጠብቃል። በተስፋና በስጋት መካከል ሆነው የሚቆጥሩ አስጨናቂ ደቂቃዎች። ምክንያቱም ምጥ ትርጉሙ ብዙ ስለሆነ። ከምጥ በኋላ እናት በደስታ ልጆቿን ትታቀፍ ይሆናል ወይንም ልጇን ልታጣ።
የከፋ ከሆነ የራሷንም ሕይወት ልታጣ ትችላለች፤ ምክንያቱም ጉዳዩ ምጥ ስለሆነ። ለሰዓታት ስታምጥ የነበረች እናት ልጅ ታቅፋ ለማየት ሲጠብቅ የነበረ ሰው ከሚጠብቀው ውጭ ሌላውን መቀበል እጅግ ይከብደዋል።
ለእናትም ከምጧ የተነሳ የጠበቀችውን ማቀፍ ካልቻለች የልብ ስብራት ይሆንባታል። የከፋ የልብ ስብራት። የፈተናው ውጤት ይዞት የሚመጣው የከፋ የልብ ስብራት። የጠበቀውን በማጣቱ ሕይወቱን ያጣውን የማትሪክ ውጤት ጠባቂውን ተማሪ እና ከረጀም ሰዓታት ምጥ በኋላ የጠበቀችውን ማቀፍ ያልቻለች እናት ቦታ ላይ ሆነን ራሳችንን እንፈልግ። በሕይወት ጉዞ ውስጥ በሚደርሱ ክስተቶች የሕይወት አቅጣጫ መልኩን ሲቀይር ልናገኝ እንችላለን።
ትላንት ውስጥ የተቀመጠው ያልጠበቅነው ነገር ዛሬ ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ ነገን ባልተጠበቀ አቅጣጫ ሊመራው ይችላል። ምናልባት አንባቢው በአንድ ወቅት እንዲህ በመሰል ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ሊሆንም ይችላል። ወይንም ዛሬ እያለፈ የሚገኝ። የዚህ ጽሁፍም አላማ የፈተናው ውጤትን ተንተርሶ ከሚመጣ የሕይወት አቅጣጫ መዛባት ራሳችንን እንድንጠብቅ ነው።
እንዲህ በመሰለ ወቅት የአስተሳሰብ ቅኝታችን ምን ይምሰል? ሁኔታውን እንዴት ወደ ተሻለ የሕይወት አቅጣጫ ማስፈንጠሪያ እንጠቀምበት? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክራለን።
በተጨባጭ ጠንካራ ፈተና በሚገጥመን ጊዜ ወይንም የፈተናው ውጤት ያልጠበቅነው ሆኖ የሕይወት በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ አቅጣጫችንን በሚያዛባ ጊዜ ልናደርጋቸው የሚገቡ ነጥቦችን ቀጥሎ እናነሳለን።
1. ዝግጁ መሆን
አንዳንዱ ነገር በእቅድና በስራ የሚመጣ ነው። አንዳንዱ ነገር ሳይታቀድ ድንገት የሚሆን እና መሰረታዊ በሚባል ደረጃ የሕይወታችንን አቅጣጫ የሚቀየርም ነው። በሕይወት ላይ ያልተጠበቀ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ አስቀድሞ ዝግጅት የሚያደርግ ሰው ምን ያህሉ ይሆን? ሰዎች በሰዎች የሚጎዱበት ዋናው ምክንያት የማይጠብቁ በመሆኑ ነው።
የሚጠብቁ ቢሆን አይጎዱም፤ ያልጠበቁት በሚሆንበት ሁኔታ ግን ለጉዳት ይዳረጋሉ። በኮቪድ ወቅት የነበረው አስቸጋሪ ነገር በሽታው ብቻ አልነበረም፤ በሽታውን ተከትሎ የመጡ ያልተጠበቁ ነገሮችም ይገኙበታል። አርሶ አደሩ ወደ እርሻው ስፍራ ሲሄድ ግብ የሚያደርገው ያቀደውን ምርት ከማሳው ላይ መሰብሰብ ነው።
ተማሪው ከትምህርት ቤት ሲሄድ ወደ ቤቱም ሲመለስ፤ ከመጽሐፍት ጋር ጊዜን ሲያሳልፍ ያለመውን ውጤት የራሱ ለማድረግ ነው። ነገር ግን በተጨባጭ የታሰበው ሳይሆን ሲቀር ሕይወት ላይ ጥሎ የሚያልፈው ጠባሳ ከባድ ይሆናል። አንዳንዴም በመነሻችን ላይ እንዳገኘነው ታሪክ እስከ ወዲያኛው የሕይወትን በር መዝጋት ይሆናል።
በመሆኑም በሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰው አንድ ቀን በእኔ ሕይወት ውስጥ ቢደርስ ምን አደርጋለሁ ብሎ ራስን እየጠየቁ መኖር እጅግ ማትረፍ ነው። ዛሬ መልካሙን ለመያዝ ፍጠን፤ ነገር ግን ሕይወት ባልተጠበቀው አቅጣጫ መንገድን ሰርታ ብትጠብቀህ ወደ መልካሙ አቅጣጫ ሕይወትን ለመውሰድ አንድ እርምጃ ወደ መፍትሔው ለመቅረብ እንድትችል ያልተጠበቀው ቢሆን የሚል ዝግጁነት ይኑርህ።
መልካሙን ወይንም ምርጡን መጠበቅ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን በተቃራኒው አስከፊው ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ ዝግጁ መሆን ይገባሃል። ‘የምበላው አጣ ይሆን?’ ብለህ አስበህ በማታውቅበት ወቅት ወይንም ጓዳህ ተትረፍርፎ ባለበት ወቅት ሕይወት በተቃራኒው አቅጣጫ ሄዳ የምትገኝበት ጊዜ መጎዳት እንዳይሆን ሁሌም ለማንኛውም ነገር ዝግጁ መሆን አትራፊነት ነው።
2. ስሜትን መቆጣጠር መቻል
በሕይወታችን ውስጥ ባልተጠበቀው ሰዓት ከፍተኛ የሆነ የስሜት ስብራትና የስሜት ውድቀት ይገጥመናል። ለጥቂት ጊዜ ይህን የስሜት ቀውስ በመግታት ራስን ወደ መስመር ለመውሰድ ስሜትን መቆጣጠር መቻል እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ሰዎች መርዶ በሚረዱበት ጊዜ ወይንም በጣም የሚቀርቡትን ሰው ሲያጡ የሚሰማቸው የስሜት መዋዠቅ ከፍተኛ ነው።
ከፍተኛ የስሜት መዋዠቅ ውስጥ የሚከተውን መረጃ አንድ ሰው መኪና እያሽከረከረ እያለ ቢሰማ ምን ሊያደርግ ይችላል? የደም ግፊት በሽታ ያለበት ሰው ቢሆን ድንጋጤው በጤናው ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ምን ሊሆን ይችላል? ወዘተ ብለን ብናስብ ስሜትን በተቻለው አቅም ሁሉ በመቆጣጠር ያንን ቅጽበት በማሳለፍ ውስጥ የሕይወትን አቅጣጫ መበላሸት መጠበቅ ይቻላል። ሰዎች በስሜት ግልፍተኝነት ምክንያት በእጃቸው ያላሰቡትን ወንጀል ሰርተው በጸጸት ጊዜያችውን ይጨርሳሉ።
እንዲህ ካለው ሁኔታ መማር ያለብን ስሜት መቆጣጠር መቻልና ነገሮችን ግራና ቀኙን ለማሰብ ጊዜ መውሰድ ያለውን ፋይዳ ነው። ያልጠበቀውን ውጤት የተመለከተ ተማሪ፤ ባሏን ባልጠበቀችው ስፍራ ያገኘች ሚስት፤ በድንገተኛ ቸነፈር የለፋበትን ምርቱን በቅጽበት ያጣ አርሶ አደር እውነታውን ባወቁ ጊዜ የሚወስዱት እርምጃ የከፋው እንዳይሆን ስሜትን መቆጣጠር መቻል ታላቅ ምክር ነው።
3. የተግባር እርምጃ መውሰድ
የተግባር እርምጃን የማይጠይቅ ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር ክፉም ሆነ መልካም የተግባር እርምጃን ይፈልጋል። በሕይወታችን ውስጥ የተፈጠረ ቀውስ ቢኖር ቀውሱ ከተፈጠረ በኋላ ራስን በማረጋጋት ‘ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢነት ይኖረዋል። ከጥያቄው መለስ መደረግ ያለበትን ነገሮች ለማድረግ ጊዜን መጠቀም እንዲሁ እጅግ ወሳኝ ነው።
የቅርባችን ሰው አደጋ ደርሶበት እጅግ ስሜታዊ ልንሆን በሚያስችለን ሁኔታ ውስጥ ሳለን ስሜታችንን አዳምጠን እንደ ስሜታችን ከመሆን፤ አደጋ ውስጥ ያለውን ሰው ልንረዳው በምንችለው መንገድ ለመረዳት ብንጥር የተሻለ ነው። በሕይወት ውስጥ በእኛ ቁጥጥር ውስጥ ያሉ እና ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ያሉ ነገሮች አሉ። በተቻለው መጠን በእኛ ቁጥጥር ውስጥ የሆነው ነገር እንዳይበላሽ በሃላፊነት ስሜት ነገሮችን ማድረግ መቻላችን ብልህነት ነው።
እንዲህ ባለጊዜ የተግባር ሰው መሆን ጠቃሚ ነው። በነገሮች ተደናግጦ ያለውን ተስፋ ለማጨለም ከመፍጠን ባለው ቀዳዳ ሁሉ አንዳች ፍሬያማ የተግባር እርምጃን በመራመድ ማድረግ የሚገባውን ለማድረግ መጣር ይገባል። አንዳንዴ ጉዳዩ ከቁጥጥራችን ውጭ መሆኑን እያወቅን እንኳን ማድረግ የምንችለውን በማድረግ ውስጥ የምንወስደው ትምህርት አለ። የፈተናው ውጤት ይዞት የመጣውን ቀውስ የምናልፍበት የተግባር እርምጃ።
4. ከሌሎች እገዛን መጠየቅ
አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ከእኛ አቅም በላይ የሚሆን ነገር መኖሩ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እንዲህ ባለ ወቅት የቤተሰብ አባላት፤ ጓደኞች፤ የሥራ ባልደረቦች ወዘተ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው። የማህበራዊ ሕይወት መስተጋብራችን በተለየ ሁኔታ ጥቅሙ የሚገባን እንዲህ ባለ ወቅትም ነው።
አብረን ስንኖር አንዳችን ለሌላችን ገንዘብ መሆናችንን የምንረዳበትን ወቅት በሕይወታችን ውስጥ እናገኝ ይሆናል። ዛሬ በአጠገባችን ያለ ሰው ምንም እያደረገ የማይመስለን ቢሆን እንኳን አንድ ቀን በሕይወታችን ውስጥ ትርጉም ያለው ነገር ሊያደርግ ይችላል። ሰዎችን ለመርዳትም መፍጠን ያለብን እነርሱ ላይ የደረሰው እኛም ሰው በመሆናችን አንድ ቀን ሊያገኘን የሚችልበት እድል ሊኖር ስለሚችል ነው።
እኛ እነርሱ በሚያልፉበት ቦታ ውስጥ ብናልፍ ሊሰማን የሚችለውን በማሰብ እነርሱ እያለፉ ካለበት መማር ይኖርብናል። የተግባር እርምጃችን ከሌሎች እገዛ ጋር ተዳምሮ ሕይወታችንን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ካልተጠበቀ ገጽታ እጅግ ወዳላስበነው ስፍራ ሊያወጣው ይችላል።
በሕይወት ጉዞ ውስጥ የሰዎችን ትርጉም ተረድተን ለሰዎች ያለንን አመለካከት መቀየር እስኪያስችል ድረስ የሚሆንን ግንዛቤን ፈጥሮልንም ሊያልፍ ይችላል። አንባቢ ሆይ እጅግ ከባድ በሆነ ፈተና ወይንም የሕይወት ቀውስ ውስጥ ስታልፍ ዛሬ አጠገብህ ያለው ሰው ምንዛሬው እንዲሁ በብር የሚተመን የማይሆን ሊሆን ይችላልና ለሰው ልጅ ዋጋን ስጥ። ዋጋ ያለው ነገር ዋጋው ትርጉም በሚኖርበት ጊዜ ትርጉሙ ይታያልና።
5. ትምህርት መውሰድ መቻል
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚያልፍን አንድን ሰው እየወሰደው ስላለው የሕይወት ትምህርት እያሰበ ላይሆን ይችላል። እውነታው ግን ለነገ ትልቅ አስቸጋሪ ሁኔታ ዛሬ ላይ ትምህርት እየወሰደ መሆኑ ነው። ሕይወት እጅግ ከባድ በሆነችባቸው ወቅቶች የሚገኘው ትምህርት ከሌሎች ቦታዎች ከሚገኘው ትምህርት የተለየ እና ልዩም ነው።
ከመደበኛ ትምህርት ውስጥ እውቀት የሚገኝ ሲሆን በፈተና ውስጥ በማለፍ ደግሞ ጥበብን የራስ ማድረግ ይቻላል። እውቀትም ሆነ ጥበብ በስፍራቸው በሕይወት ውስጥ ያላቸው ትርጉም ከፍተኛ ነው። የሚወሰደው ትምህርት የትኩረት አቅጣጫችንን እንድንፈትሽ እንዲሁም ቅድሚያ የምንሰጠውን ነገር ለይተን እንድናውቅ ያደርገናል። በዚህ ዘመን ብዙ ነገሮች በሞባይላችን አድርገው እኛ ጎዳ ይደርሳሉ።
የትኛውንም ድንበር አልፈው እስከ መኝታ ክፍላችን ድረስ ይዘልቃሉ። በሕይወታችን አጥር የሚባል ነገር እንዳይኖር ሆኖ በብዙ አቅጣጫ የተበታተነውን ነገራችንን እንድናውቅ ሊያደርገን ይችላል። ትምህርት መውሰድ መቻላችን አእምሮችንን በቁጥሮች ከመሙላት ባሻገር የሕይወትን መስመር በሚገባ ለመቅረጽ የሚረዳን ነው።
ተጋላጭ የሆንባቸውን ነገሮች ለይቶ ለማወቅና ተገቢውን ማስተካከያ ለማድረግ የሚረዳም ነው። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች፤ ሚዲያው፤ በሥራ ቦታችን ያለው ከባቢ ሁኔታ ወዘተ በሕይወታችን ውስጥ ተጋላጭ የሆንበትን ነገር ጎጂና ጠቃሚ አድርጎ ሊገጥመን ይችላል።
እንደ ግለሰብ ጎጂና ጠቃሚውን መርምሮ አካሄዳችንን ለማስተካከል እንጠቀምበታለን፤ የሚረዳ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። 6. ነገ እንዳይደገም ምን ማድረግ እንደሚቻል ማሰብ መቻል ትላንት ካለፍንበት መንገድ ውስጥ የምንወስደው ትምህርት ለነገ ትምህርት የሚሰጥ ነው ስንል ነገ ተመሳሳይ ነገር ቢገጥመን በተሻለ ሁኔታ እናልፈዋለን ማለት ነው።
ተመሳሳይ አይነት ያልተጠበቀ ነገር ምናልባትም መልኩ ቀይሮ ቢመጣ ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ጠቃሚ የሚሆነውም ለዚሁ ነው። አንድ ድንጋይ አንድን ሰው ደጋግሞ ከመታው ድንጋዩ እራሱ ሰውዬው ነው እንደሚባለው ሕይወታችንን በማይሆን አቅጣጫ ውስጥ ይዘውን የሚሄዱ ነገሮች በእኛ ቁጥጥር ውስጥ ያሉ ከሆነ ደጋግመው እንዳይመጡ ምን ማድረግ እንዳለብን ማሰብ ተገቢነት ይኖረዋል።
የፈተናው ውጤት ስሜታዊ አድርጎን በመንገዳችን ላይ ተጽእኖውን ከፍተኛ አድርጎት ከነበረ ለነገ ተመሳሳዩ እንዳይደገም ዝግጁ ማድረጉ የሚጠበቅ ነው። በሰዎች ደጋግመው የተጎዱ ሰዎች ራሳቸውን ከሰው በመራቅ ለራሳቸው በሰሩት ዓለም ውስጥ ተደብቀው ይኖራሉ።
ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ነው ባንልም ከተጎዳንባቸው ሰዎች የምንወስደው ትምህርት ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ትርጉሙን እንድናስተካከል የሚረዳ ይሆናል። ዛሬ ያለፍንበት ነገ እንዳይደገም የምናሳልፈው ውሳኔ በመሰረታዊ ደረጃ አካሄዳችንን ለውጥ የሚያመጣና ሰዎች ስለ እኛ ብዙ እንዲወያዩ ሊያደርጋቸው ይችላል። ትላንት በፈለጉን ቦታ ላይ ሊያጡንም ይችላሉ።
በራሳችን ደሴት ውስጥ ራሳችንን አጥረን በተሳሳት መፍትሄ ውስጥ እንድንገኝ ሊያደርገንም ይችላል። ጽንፍ የወጣን ውሳኔ በሕይወታችን ላይ አሳልፈን እንዳንገኝ ነገስ ምን ማድረግ እችላለሁን በሚዛናዊነት መመልከት አስፈላጊ የሚሆነው ለእዚህ ነው።
አንባቢ ሆይ ከታሪካችን የምንረዳው በፈተና ውስጥ ማለፍ ለሰው ልጅ የተሰጠ መሆኑን ነው። ፈተናውን ፈርቶ መቀመጥ ሳይሆን ፈተናውን ተጋፍጦ ወደ ውጤት መድረስ የሚቻል። የፈተናው ውጤት ያሰብነው ቢሆን ቤታችንን ፈጥነን በምስጋና እንደምንሞላው፤ ውጤቱ በተቃራኒው ከሆነ ደግሞ የሃዘን ድባብ።
ዛሬ ባልጠበቅነው አቅጣጫ የተገለጠው የፈተናችን ውጤት በሕይወታችን ውስጥ ጎድቶን እንዳያልፍ ምን ማድረግ እንዳለብን በአስተዋይነት እንመርምር። ሁሌም ዝግጁ መሆንን፤ ስሜትን መቆጣጠር መቻልን፤ የተግባር እርምጃ መውሰድን፤ ከሌሎች እገዛን መጠየቅን፤ ከሆነው ትምህርት መውሰድ መቻልን እና በቁጥጥራችን ውስጥ ያለ ከሆነ ነገ ዳግም እንዳይደገም የሚጠበቅብንን መወጣትን ተመለከትን። መልካም የፈተና ውጤት!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014