ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት ጥሩ ነው? መቼም አዎ እንደምትሉኝ እገምታለሁ። ምክንያቱም እናንተ ጎበዞች ናችሁ። በዚያ ላይ ደግሞ ዛሬ የተማራችሁትን ዛሬውኑ አጠናቃችሁ ፤ የቤት ሥራችሁን ጨርሳችሁ ቤተሰብ እያገዛችሁ እንደሆነም አስባለሁ። ምክንያቱም እለተ ሰንበት የእናንተ የእረፍት ቀን ነው። ስለዚህም በዚህ ጊዜ ከማጥናት ባለፈ ቤተሰብን ማገዝ ይገባችኋል። ከዚያ የተረፈ ሰዓት ካላችሁ ደግሞ ጨዋታ መጫወት መልካም እንደሆነ ታውቃላችሁ። ለዛሬ አስደናቂና አስተማሪ ተረት በዚህ ለእናንተ ባዘጋጀነው አምዳችን ይዘንላችሁ ቀርበናል። ታሪኩ በጥንቸልና ኤሊ መካከል የተደረገ ነው።
ከዕለታት በአንድ ቀን አንድ ኩሩ እና ፈጣኑ ጥንቸል በመንገድ ላይ እየተንቀሳቀሰ እያለ ዓይኑ አንድ ነገር ላይ አረፈ። ይህም የኤሊዋ አረማመድ ሲሆን፤ እጅግ አስገርሞት ነበር። በሁኔታዋ ስለተደመመም ወደእርሷ ቀረበ። በዘገምተኝነቷና የእግሮቿ ርዝመት ማሾፍ ጀመረም። ምክንያቱም ይህንን አይነት አፈጣጠር አይቶ አያውቅም። እናም በፍጥነቱና በሩጫ ችሎታው ስለሚተማመን እኔና አንቺ በሩጫ ብንወዳደር ሰፊ ሰዓት ሰጥቼሽ አሸንፍሻለሁ ሲልም ቀለደባት። እርሷም ‹‹እኩል ብንጀምርም አታሸንፈኝም›› አለችው።
ጥንቸሉ በማሸነፉ እርግጠኛ በመሆኑ እያፌዘባት ‹‹እንሞካከራ›› ሲል ጠየቃት። እርሷም ‹‹እሺ እንጀምር›› አለችው። ሩጫው ከመጀመሩ በፊት ግን ሁለቱም ቀበሮው ግብ ላይ ምልክት እንድትሆን ቁራ ደግሞ እንደ ዳኛ ሆኖ እንዲፈርድ ተስማሙ። የውድድሩ ሰዓት ሲደርስም በውድድሩ መጀመሪያ ላይ ጥንቸል እና ኤሊ በአንድ ጊዜ ወጡ። ኤሊዋ ሳትቆም ገሰገሰች ፣ ግን በዝግታ ነበር ሩጫዋን የቀጠለችው ። ጥንቸሉ ደግሞ በጣም ፈጣን ስለነበር ቀድሟት ረጅሙን ርቀት ሸፈነ። ገና ነች ብሎም ለራሱ ረፍት ሰጠ። የዚያን ጊዜ ድብን ያለ እንቅልፍ ወሰደው። ኤሊዋ ቀስ ብትልም እስክታልፈው ድረስ አልተነሳም።
እንደውም ከእንቅልፉ የተነሳው መጨረሻው ላይ ደርሳ ሲጨበጨብላትና አሸንፈሻል ተብላ ሜዳሊያው ሲሰጣት ነው። በዚህ ጊዜ እጅጉን ተናደደ። ሊሆን እንደማይችልም እየጮኸ ተናገረ። ሆኖም የሰማው አልነበረም። ስለዚህም ያሲያዘው ነገር ተበላበት። ጉራ ብቻ የትም እንደማያደርስ ተነግሮት መተረቻ ሆኖም ቀረ።
እናም ልጆች ግባችንን ማሳካት የምንችለው ከሠራንና ካለማቋረጥ ከለፋን ብቻ እንደሆነ ከዚህ ታሪክ እንረዳለን። በተፈጥሮ መቀለድም እንደማይገባ የጥንቸሉ ተግባር በትክክል ያስረዳናል። ሰው በተሰጠው ጸጋና ተፈጥሮ ልክ መሥራትና ለመለወጥ ፍላጎት ካለው የማይተገብረው ነገር አይኖርም። ሁልጊዜም አሸናፊ ይሆናል። ስለዚህ ጠንክሮ መሥራት፣ ጽናት እና ጥረት ወደ ግባችን ያደርሱናል። ሌሎች እንዳይበልጡንም እንሆናለን። በትንሽ በትንሹ ቢሆንም ተስፋ ካልቆረጥን ስኬታችንን የሚነጥቀን አይኖርም።
በተጨማሪም እብሪተኝነት፣ የፅናት እጦት እና በራስ መተማመንን ከመጠን በላይ ማድረግ ብዙ መልካም ዕድሎችን ያስመልጠናል። ስለሆነም ልጆች ልክን ቀድሞ ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ አለባችሁ። ለምሳሌ፣ በትምህርትቤት አንደኛ መውጣት ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም። ብዙ ልፋትና ሥራን ይጠይቃል። በዚያው ልክ ደግሞ ማንም አይበልጠኝም ብሎ መኩራራትም ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም ከእኛ እኩል የሚለፋ ተማሪ እኛን ሊቀድመን ይችላል።
ስለሆነም መበላለጥና ስኬት ላይ መድረስ የሚመጣው ጠንክሮ በማንበብ፤ እብሪተኛ ባለመሆንና ከሰዎች ጋር አብሮ በመሥራት ነው። ስለዚህም እናንተም ይህንን በማድረግ ውጤታችሁን በእየለቱ መገንባት አለባችሁ እያልን ለዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነውን ጉዳይ አበቃን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው