አርቲስት ሙሉቀን መለሰ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አይረሴ ዜማዎችን አኑሯል። እሱ ከሙዚቃው ዓለም ከወጣ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም አሁንም ይደመጣል። ስለዚህ አርቲስት ጥቂት ልንላችሁ ወደደን። ለእዚህ ደግሞ በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር በ1973 ከተጻፈ ጽሁፍ የተወሰነውን ቀንጭበን ይዘናል።
ሙሉቀን መለሰ አጠር ፣ ወፈር ያለ፣ በጣም ቀይ የሆነ የሃያ ስምንት ዓመት ጐረምሳ ነው። ለሁለት ሰዓት ይህል ሲያነጋግረን እንደገመትኩት ሙሉቀን ሃሳቡን በቀጥታ የሚናገር ሰው ነው። ማለቴ፣ “እንዲህ ያልኩ እንደሆነ እንደዚህ ተብሎ ሊተረጐምብኝ ይችላል” የሚል ሥጋት የለበትም።
“ሙሉቀን ብለው ስም ያወጡልህ ለምንድነው?” አልነው።
“እህቴ ነች ያወጣችልኝ። እናቴ ‘ሙሉሰው’ ነው የምትለኝ። ከኔ በፊት አስወርዷት ነበር። ደሞ ታላላቆቼ አራቱም ሲወለዱ ምጥ ይበዛባት ነበር። እኔ ስወለድ ግን ይህ ችግር አልነበረም። ለዚህ ነው ‘ሙሉሰው’ ያለችኝ። ‘ስማቸው’ ይለኛል አባቴ። የመሬት ሙግት ነበረበት። ጠላቶች ነበሩት። እነሱን ስማቸው ማለቱ ነው።”
ሙሉቀን መለሰ በጐጃም ክፍለ ሀገር አነደድ ወረዳ ውስጥ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ.ም ተወለደ። አሥር ዓመት ሲሆነው እናቱ ስለሞቱ፣ አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ አጐቱ እንዲማር ብለው አመጡት። ኰልፌ ሰፈር ጳውሎስ ትምህርት ቤት ገባ። ግን ብዙ አልተማረም። ያጐቱ ሚስት ይጠሉት ስለነበረ ብስጭት በዛበት። እንግዲህ ኰልፌ አንድ የጡረታ ቤት ነበረ። ባንድ ጐኑ የልጆች ማሳደጊያ ነበረው። የሚረዱ አሉ ሲባል ሰምቶ ሙሉቀን ሄዶ ጠየቀ። ተቀበሉት።
“የበላይ አስተዳዳሪዋ ይወዱኝ ነበር። ‘ኤልቪስ’ ነበር የሚሉኝ። በሁለት ወር እንደዚህ ልብስ ይዘውልኝ ይመጡ ነበር። ውጭ አገር ልኬ አስተምርሃለሁ ብለውኝም ነበር። ይንከባከቡኝ ነበር። እወዳቸው ነበር። ውለታቸው በጣም ትዝ ይለኛል።”
እዚያው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተከፈተ። አቶ ተፈራ አቡነ ወልድ ነበሩ አስተማሪው።
ሙሉቀን ስድስት ወር ያህል እንደተማረ እህቱ ስለታመመች ወደ አገር ቤት ሄደ። ያን ጊዜ ነው አዲስ አበባ ውስጥ አክስት እንዳሉት ያወቀው። እሳቸው ይዘውት መጡና ከሳቸው ጋር መኖር ጀመረ። ቤታቸው የካ ሚካኤል ነው። እንግዲህ ሙሉቀን ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤቱ አልተመለሰም።
አክስቱ የወታደር ሚስት ናቸው፣ ጠላም ይነግዳሉ። ኑሮአቸው ጐስቋላ ነው። ልጁ አልተመቸውም። አንድ ቀን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ሄደ። ሊቀጠር። አልተቀበሉትም። ግን በእርዳታ መልክ ሻይ የማፍላት ሥራ ሰጡት።
“ምድጃዋ የኤሌክትሪክ ነበረች። ባንድ ቀን ውስጥ ሶስት ጊዜ ኮረንቲ ያዘኝ” አለ። ስድስት ወር ያህል ከሰራ በኋላ ትቶት ወጣ። ጥቂት ወራት ተንከራተተ።
ከአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወረድ ብሎ አንድ ሻይ ቤት ነበረ። የሻይ ቤቱ ባለቤት ሙሉቀንን ይወደዋል፤ ይረዳዋል። ሀርሞኒካ የሚጫወት ጓደኛ አለው ሙሉቀን። ሻይ ቤቱ ቁጭ ይሉና ጓደኛው ሀርሞኒካውን ይጫወታል። ሙሉቀን ይዘፍናል።
አንድ ቀን ሙሉቀንና ጓደኞቹ አብረው ሲጫወቱ ያመሹና ወደ ሶስት ሰዓት ላይ አንዱን ጓደኛቸውን ለመሸኘት ይነሳሉ። ደጃች ውቤ ሰፈር ሲደርሱ የውቤ በርሃ ልዩ ልዩ ቀለማት መብራቶች በርተው ሙሉቀንን በጣም ያስደንቁታል። አንዱ ቤትማ ከሌሎቹም የበለጠ አሸብርቋል። ጓደኛሞቹ ይኸ ቤት ምንድነው ብለው ሲጠያይቁ፣ ይኸማ ‘ፈጣን ኦኬስትራ’ የሚጫወትበት ‘ፓትሪስ ሉሙምባ ናይት ክለብ’ ነው ይሏቸዋል።
ፊት ለፊቱ ካለው ሱቅ ሄደው፣
“ባለቤቱ ማነው የዚህ ናይት ክለብ?” ብለው ጠየቁ።
“ወይዘሮ አሰገደች አላምረው ናቸው” አለ ባለሱቁ።
“ሥራ ይሰጡኝ ይሆን ወይ?” ብሎ ጠየቀ ሙሉቀን።
“ፃፍና ጠይቃቸው” አለው ባለሱቁ ወረቀትና እስክሪፕቶ እየሰጠው።
እዚያው ቆሞ ደብዳቤውን ፃፈ። ጓደኛሞቹ ከፍርሃት ጋር እየታገሉ ከዚያ ከአስደናቂ ቤት ገቡ። ሙሉቀን ደብዳቤውን ለኦርኬስትራው መሪ ሰጠው።
አነበበውና ሳቀበት።
“ምንድነው እሱ?” አሉ ወይዘሮ አሰገደች ከወዲያ ቁጭ ብለው።
ሰውየው ነገራቸው። ደብዳቤውን ተቀብለው አነበቡ።
“ፈትነው። ካለፈ ጥሩ … አለዚያም ሌላ ሥራ እሰጠዋለሁ” አሉ። የልጅ መልኩና ጎስቋላ ሁኔታው ኀዘኔታቸውን ቀስቅሶ ሳይሆን አይቀርም።
ያን ጊዜ ሙሉቀን እንደ ጥላሁን ገሰሰና እንደ ዓለማየሁ እሸቴ እያደረገ ይዘፍን ነበር። ባዶ እግሩንና በቁምጣ ሱሪ መድረኩ ላይ ወጣና ‘ለውነት እሞታለሁ፣ አልሳሳም ለነብሴ’ን እና ‘እንክርዳድ’ን ዘፈነ።
የናይት ክለቡ ሴቶች (በጣም ብዙ ናቸው) ዘፈኑን ወደዱለትና ያን ጊዜውኑ አንድ አራት መቶ ብር የሚሆን አዋጡለት።
“በበነጋታው ካኪ ልብስ ተገዛልኝ፤ ሱፍ ልብስ ተለካሁ። ቢትልስ ጫማ አደረኩ … እግሬን ታጥቤ!” አለ።
እዚያው ክፍል ተሰጠው። ምግብም ከዚያው ነው። የዘፈን ሥራ ጀመረ።