የተወለደው በኤርትራዋ መዲና አስመራ ከተማ ውስጥ ነው። ወቅቱም ጥቅምት 5/1983 ዓ.ም ነበር። ወጣት ድምጻዊ ነው። ድምጻዊ ብቻ ሳይሆን የግጥምና ዜማ ደራሲ ፤ ተዋናይ ፤ የፊልም ስኮር ባለሙያም ነው። በሕዝብ ዘንድ የሚታወቀው ‹‹ተሸንፌያለሁ›› በተሰኘው ሙዚቃው ሲሆን ይህ ሙዚቃው ከወጣ እስካሁን ከ19 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል። ከድምጻዊነቱ ባለፈ ባጋጠመው የኩላሊት ሥራ ማቆም ህመም እና ሕዝብ እሱን ለማሳየት ባደረገው መረባረብም ለአንድ ሰሞን የመገናኛ ብዙሃን ትኩረትም ሆኖ ነበር። የዛሬው እንግዳችን ወጣቱ ድምጻዊ ሙሉአለም ታከለ ነው፡፡
ሙሉአለም ትውልዱ አስመራ ይሁን እንጂ እድገቱ አዲስ አበባ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በሚገኘው ሕዝባዊ ሰራዊት ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ከፍተኛ 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። ያደገበት ቤተሰብ ጠንካራ ቤተሰባዊ እሴትን ያዳበረ እና እርስ በእርሱ እጅግ የተሳሰረ ቤተሰብ ነበር። ይህ ሁኔታም በኋላ ላይ በተግባር የታየ ነው። አስተዳደጉ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ነው። ትምህርቱን ይማራል ፤ ይጫወታል ፤ ይዘፍናል ፤ ወዘተ..። ነገር ግን ከልጅነቱ ከሙዚቃ ጋር ለየት ያለ ፍቅር ነበረው። ሙዚቃ ባለበት ሁሉ ሙሉአለም አለ። ይዘፍናል። እርግጥ ሙዚቃ የሙሉአለም ብቻ ዝንባሌ አልነበረም። አንዲት እህቱም የፌዴራል ማረሚያ ቤት የሙዚቃ ቡድን አባል ናት። ስለዚህም ሙዚቃ በቤተሰቡ ደም ስር ውስጥ ነበረች ማለት እንችላለን፡፡
ለሙዚቃ መጀመሩ አስተዋጽኦ ያደረገውም ወንደሙ ክራር ተጫዋች መሆኑ ነው። በወንድሙ ታጅቦ ማንጎራጎር የጀመረው ሙሉአለም ድምጹን እየተሞረደ ፤ የዜማ ግንዛቤው እየጨመረ ፤ የሙዚቃ ፍቅሩም እየጨመረ መጣ። ከዚያም ክበባትን ተቀላቅሎ መዝፈን ጀመረ። ረዘም ያለ ጊዜውን ያሳለፈው እና ብዙውን የሙዚቃ ልምድ የቀሰመውም እዚያ ነው። ወደ መድረክ ወጥቶ የዘፈነው ግን ሚዩዚክ ሜይደይ በፑሽኪን አዳራሽ ባዘጋጀው መርሀግብር ላይ ነበር። ሁኔታውን ሲያስታውሰው በጣም ይጨንቅ ነበር ይላል። አስጨናቂ ቢሆንም እንኳ ያ መድረክ ግን ሙዚቃ የሙሉአለም እጣ ፈንታ መሆኑ የተረጋገጠበት መድረክ ነበር፡፡
ከዚያም በኋላ ከወንድሜ ቀጥሎ በእኔ የሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጥሯል ከሚለው ከዝነኛው ሙዚቃ አቀናባሪ ጊልዶ ካሳ ጋር ተገናኘ። እስካሁን ከሰራቸው ሥራዎች አብዛኛው የተሰሩትም በጊልዶ አቀናባሪነት ነው። እዚያ ባለበት ወቅት ከሌላው ወጣት ድምጻዊ ማይኪ ሸዋ ጋር አልበም መስራት ጀምረው የነበረ ሲሆን ነገር ግን ያ የአልበም ሥራ ሲቋረጥ ከዚያው ላይ አንድ ነጠላ ዜማ ሰርተው ለቀቁ። ያ ዜማ ለሕዝብ የቀረበ የመጀመሪያ ሥራው ሲሆን ርእሱም ‹‹ናንዬ›› የሚል ነበር። ከሱ በመቀጠል ሕዝብ አይን ውስጥ የገባበት ‹‹ሀመልማሎ›› የተሰኘ ነጠላ ዜማው ቀጠለ። ሀመልማሎ ከ6 ዓመት በፊት ከወጣ በኋላ እስካሁን ወደ 7 ሚሊዮን ገደማ ጊዜ ታይቷል። ቀጠለና ሌላኛው ተወዳጅ የሆነ ሙዚቃ እኔ እሻልሻለሁን ለቀቀ። በመቀጠል ከትግርኛው ድምጻዊ ኤፍሬም አማረ ጋር በመሆን በጋራ የተጫወቱት ‹‹ተሸንፌያለሁ›› የተሰኘ ሙዚቃ የሙሉአለምን ዝና ሌላ ከፍታ ላይ ሰቀለው። ከዚያም ሌሎች ነጠላ ዜማዎችን ቀጥሎ 8 ነጠላ ዜማዎችን በጥቅል እስካሁን ሰርቷል፡፡
ሙሉአለም ከድምጻዊነት ባለፈ ዜማ እና ግጥም መድረስም ተሰጥኦው ነው። እሱ ከሰራቸው ግጥምና ዜማዎች መሀከል ለየኛ የሙዚቃ ቡድን ያዘጋጀው ፍቅር ይብዛ እና ለማን ብዬ ይጠቀሳሉ። ፍቅር ይብዛ ከወጣ በኋላ እስካሁን በዩቲዩብ ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን ለማን ብዬም የተመልካች መጠኑ ከ4 ሚሊዮን አልፏል። ሌሎችም ስራዎችን ለሌሎች ድምጻውያን ሰርቷል። በሌላ መልኩ የጊልዶ ካሳ ላገባ ነው ሙዚቃ ክሊፕ ላይ በትወና እንዲሁም ህዳር የተሰኘ ፊልም ላይ በትወና እና የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ በመጫወት ተሳትፏል፡፡
ሙሉአለም በድምጹ ከማዜም ባለፈ ማስታወቂያም ይሰራበታል። ለምሳሌ ያህል ብዙ ሙዚቃዎች በዩቲዩብ የሚያቀርበው ሆፕ ኢንተርቴይንመንት በመግቢያነት የሚጠቀመው እና ብዙዎች የሚያውቁት ድምጽ የሱ ሲሆን ከሆፕ በተጨመረ ሌላው ዝነኛ የፕሮዳክሽን ድርጅት ሞኢሳም በሚያቀርባቸው የኪነጥበብ ሥራዎች ላይ የሚጠቀመው የመግቢያ ድምጽም የሱ ነው፡፡
ሙሉአለም የሙዚቃ ሕይወቱ እያበበ በነበረበት ሰአት ሳይታሰብ የኩላሊት ሥራ ማቆም አጋጥሞት ነበር። ይህ አጋጣሚ ቀደም ብለን የገለጽነው የሙሉአለም እና ቤተሰቦች ጥብቅ ትስስር በተግባር የታየነበት ብሎም የወዳጆቹ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ በይፋ የተገለጠበት ነበር። ለወራት የኩላሊት እጥበት ካከናወነ በኋላ የኩላሊት ንቅለ ተከላው በውጭ አገር የሚካሄድ በመሆኑ ገንዘብ ማሰባሰብ አስፈለገ። በዚህን ጊዜም ወዳጆቹ እና የሙያ አጋሮቹ ተረባረቡ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን ሙሉአለምን ባስገረመ መልኩ ለመሉአለም እጁን በሰፊው ዘረጋ። ከዚያ ግን ዋናው ጉዳይ ቀጠለ። ኩላሊት መስጠት። ለዚህም የሙሉአለም ወንድሞችና እህቶች ይሄኔ ግዴታቸውን ሊወጡ ተነሱ። ምርመራ ተካሄደ። ውጤቱም ለሙሉአለም ኩላሊት መስጠት የምትችለው የሁለት ልጆች እናት የሆነችው እህቱ እንደሆነ አሳወቀ። ለወንድሟ ኩላሊቷን ለመለገስ አይኗን አላሸችም። እሷ ቁርጠኛ ብትሆንም ግን ህንዳውያኑ በቀላሉ እሺ አላሉም። ብዙዎች በገንዘብ ተታለው አልያም ተገድደው ኩላሊታቸውን ይሰጣሉና የሙሉአለም እህትም የዚያ ሰለባ አለመሆኗን ማረጋገጥ ነበረባቸው። እህቱ መሆኗን እና በገንዘብ ተታላም ሆነ በጉልበት ተገድዳ ሳይሆን በፍቅር ያረገችው መሆኗን እሷም መሰከረች እነሱም አረጋገጡ፡፡
ቀዶ ጥገናው ቀላል አልነበረም። አንድ ቅጽበት ላይ እንደውም የሙሉአለም ልብ መምታት አቆመች። ሀኪሞች ተራወጡ። ልብ ምቱን ለማስነሳት ያላቸው አማራጭ ኤሌክትሪክ ንዝረት ነውና እሱን ተጠቀሙ። ሊያመልጥ የነበረው ሙሉአለም ተመለሰ። ወንድምና እህት ከቀዶ ጥገናው ሲነቁ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው አንዳቸው የሌላቸውን ደህና መሆን ነበር። ሁለቱም ደህና ሆነው ህክምናቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ወደ አገራቸው ሲመለሱ ሙሉአለም ላገዘው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሙዚቃ አበረከተ። ሙዚቃውን እዚህ ቢዘፍነውም ነገር ግን ዜማውን የሰራው እዚያው ሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ ከቀዶ ጥገናው ከሶሰት ቀን በኋላ ነበር፡፡
ሙሉአለም አሁን ላይ “ራሴን እንደ አደራ አያለሁ” ይላል። ስለዚህም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርጋል። የራሱ ስቱዲዮ ሰርቶ ሙዚቃዎችን እና የፊልም ማጀቢያ ድምጾችን ይሰራል። አልበም በመስራት ላይም ይገኛል።
የእረፍት ቀኑን በምን እንደሚያሳልፍ ጠየቅነው። “ሙዚቃ እሰማለሁ እሰራለሁ ፤ ፊልም አያለሁ። ከዚያ ውጭ መጓዝም እወዳለሁ። ግን መጓዝ የምወደው ብቻዬን ነው። ምክንያቱም ከራሴ ጋር መነጋገር ስለምፈልግ ነው” አለን።
ባገኘው አጋጣሚ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ለመሳተፍ እንደሚጥርም ይናገራል። ለአንባቢዎቻችን መልእክት እንዲያስተላልፍ እድል ሰጠነው። እንዲህም አለን “ውስጣችን ያለውን መልካምነት እናውጣው። የኛን መልካምነት የሚፈልጉ ብዙ ናቸው”
እኛም በዚህ መልእክት የነበረንን አጭር ቆይታ አጠናቀቅን ፤ ቸር እንሰንብት!
(አቤል ገ/ኪዳን)