እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሥነ-ልቦና አማካሪዎች የሚባሉ ባለሙያዎች በአደባባይ አይታወቁም ነበር። ሙያው ለማህበረሰብ አገልግሎት በሰፊው እየዋለ ሲመጣ የምክር አገልግሎት ፈልገው ወረፋ ከሚይዙት መካከል የሕይወት ጉዞ ውስጥ ጥያቄ የበዛባቸው ግለሰቦች ተጠቃሾች ናቸው።
አማካሪን ፍለጋ ወረፋ ከሚይዙት ጋር ለንጽጽር የማይቀርብ የኅብረተሰብ ክፍል ጉዳዩን ከራሱ ጋር ይከርምበታል ወይንም ባሉት ማህበራዊ መስተጋብሮች ውስጥ መፍትሔን ይፈልግላቸዋል። መንደርደሪያ ታሪካችን ውስጥ መነሻ የምናደርጋቸው ግለሰቦች ከእዚሁ ምድብ ሊመደቡ የሚችሉ ሆነው እናገኛቸዋል።
እነርሱም በሊስትሮ፤ መኪና በማጠብ፤ ሱቅ በደረቴ ሥራን በመሥራት እና በፓርኪንግ አገልግሎት የተሰማሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ወጣቶቹ በመደዳ ሆነው ሥራቸውን ሲሰሩ ከሁሉም ለየት ብሎ የሚወጣው ሊስትሮው ነው። አብዝተው ሊስትሮው ላይ ብዙ እንዲቀልዱበት የሚያደርጋቸው ለሕይወት ያለው እይታ ነው።
በተለይም ለሥራው ሕይወት። ሊስትሮው የግለሰቦችን ጫማ በሚጠርግበት ጊዜ የሚያያቸውን የጫማ ዓይነቶች በሙሉ በአጽንኦት የመመልከት ልምድ አለው። «ደግሞ እንዲህም ዓይነት ጫማ አለ?» ይላል፤ ይገረማልም።
«እንዴት እንዲህ አድርገው ሠሩት?» የሚለው ጥያቄ ቀጥሎ ያስከትላል፡፡ እያንዳንዱን ጫማ ተመልክቶ እንዴት ሊሠራ እንደቻለ ግንዛቤውን ወስዶ ስለ ነገው አሻግሮ እየተመለከተ አብረውት ላሉት ወጣቶች «ፍሬንዶች ሁላችንም እዚሁ አንቆይም፤ አንድ ቀን ዛሬ ካልንበት ደረጃ ከፍብለን በሌላ ደረጃ ላይ እንደርሳለን።
ነገርግን ለውጥ አይቀሬ ነውና እኛ አስበን ያልሠራነው ለውጥ እንዳያገኘን እኛ ዛሬ ተዘጋጅተን እንጠብቀው» ይላቸዋል። ብዙ ጊዜ እያሾፉ ይሰሙታል። አሻግሮ የሚያየው ትልቅ ሆኖባቸው፤ የእለት ጉርስ ለማግኘት የሚታገሉ መሆናቸውን የዘነጋም ሆኖ ይሰማቸዋል፡፡
እቅጩን ሲነግራቸው «ዛሬ ሊስትሮ ብሆንም አሻግሬ የማየው የጫማ ፋብሪካ ኖሮኝ ነው» ይላቸዋል። ንግግሩ ከአንደበቱ የማይጠፋ፤ የሚጠርጋቸውን ጫማዎች በጥንቃቄ በሚመለከትበት ጊዜ ለራሱ ደጋግሞ የሚናገረው ነው። የለውጥ አይቀሬነትን የተገነዘበ፤ አሻግሮ በማየት ውስጥ መፍትሔ እንዳለ የሚመለከት፤ መንገድ ዳር ጫማ እየጠረገ ዛሬ የሚኖር የነገ ባለፋብሪካ፡፡ ይህ ወጣት አሻግሮ ከማየት ባሻገር ያዩት ጋር ለመድረስ በሚረዳ ጉዞ ውስጥ መሆን ይገባል ከሚለው እምነቱ ተነስቶ ቀጣዩን ጉዞ ሲያስብ በጫማ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ግድ እንደሆነ አሰበ።
በመሆኑም ከአመታት በኋላ የጫማ ፋብሪካ ባለቤት የመሆን ጉዞውን በአካባቢው ባለ ጫማ ሰፊ ቤት ውስጥ በመቀጠር ጀመረ። ልክ መንገድ ዳር እንደነበሩት ጓደኞቹ በጫማ ሰፊው ቤት ላሉ ጓደኞቹም የሚነግራቸው ተመሳሳዩን ነበር።
ወዴት መድረስ እንዳለበት በግልጽ የተመለከተ ስለሆነ ያሰበበት ጋር ለመድረስ አንዳች ጥርጥር ወይንም ብዥታ የሌለው ሆኖ ራሱን ስለሚያገኝ ግርምትን ይፈጥርባቸዋል። ምክንያቱም በውስጡ ለራሱ የተቀበለው ስለሆነ። በሰዎች ላይ የሚደርስ ፈተና በሚደርስበት ጊዜ አሻግሮ የሚያየው ተስፋውን እጅግ አቅርቦ ይመለከትና ቀላል አድርጎ ያልፈዋል።
በድንግዝግዝ ጊዜ ከድንግዝግዝ መውጫ አቅምም ይሆነዋል። አንድ ቀን ጫማ በሚሠራበት ቤትውስጥ አብሮት ይሠራ የነበረው መኪና አጣቢው ጓደኛው መጣ። ዛሬም እያሾፈበት «ባለጫማ ፋብሪካው ጓደኛዬ» አለው።
የእርሱ ምላሽ «አቤት ወዳጄ ባለመኪና ፋብሪካው» የሚል ነበር። መኪና አጣቢውም ከጓደኛው አንደበት የሰማው አዎንታዊ ቃል ለአፍታም ቢሆን የቁምነገረኝነትን ስሜት ፈጠረለት። ዛሬ እየኖረበት ያለውን ድንግዝግዝ ሕይወት ተመልክቶ በጓደኛው አንደበት የተነገረው ፈጽሞ የማይሆን አድርጎ እንዲያስብ አደረገው።
የቤትኪራይ በወቅቱ መክፈል ሳይችል ቀርቶ ኑሮን በስቃይ እየመራ ከመሆኑ ሃቅ ጋር እና በሥራው ደስተኛ ያለመሆን የዘወትር ስሜቱ ጋር እንዲሁ ባዶ ተስፋ በጆሮው ዘልቆ የተሰማው መሰለው፡፡
መኪና አጣቢው እንዲህ አለ «ጓደኛዬ እባክህ ነገሮች ሁሉ ጭልምልም ብለውብኛል፤ ከእዚህ ሥራ እንዴት መውጣት እንዳለብኝ አላወኩም፤ ታውቃለህ ሁሉም ነገር ጨለማ መሆን ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ …. አቦ ሁሌም በራስ ነገርአስጨነኩህ» አለው።
አመጣጡ ብር ብድር ፍለጋ ነውና ጥያቄውን ጸጉሩን እያሻሸ አቀረበለት። ጓደኛውም ያለውን አበድሮ እንዲህ አለው፤ «ጓደኛዬ በምድር ላይ ስንኖር ትልቅ ነገርን አሻግረን በመመልከት፤ ያንን ለመፈጸም ዛሬ ላይ መድከም ባለብን ልክ ደክመን መገኘት እንጂ በድንግዝግዝ ውስጥ መኖር መፍትሔ አይደለም።
መፍትሔው ከድንግዝግዝ እንዴት መውጣት እንችላለን ነው፡፡» በማለት አበረታታው። የታክሲው ሰልፍ ላይ የተሰለፉት በራሳቸው የበዛ ድንግዝግዝ ውስጥ ሆነው ታክሲውን ይጠብቃሉ፤ ካሉበት ቦታ ወደሚፈልጉት ስፍራ የሚያደርሳቸውን። የሁለቱ ወጣቶች ንግግር ፍሬ ነገሩም በታክሲ ሰልፉ ውስጥ እንዲሁ ይገኛል፡፡
የታክሲው ሰልፍ ላይ የተሰለፉት
በምናባችን አንድ ታክሲ ሰልፍ ላይ ራሳችንን እንውሰድ። በአዲስ አበባ ለታክሲ በሚታየው ረጃጅም ሰልፍ ውስጥ ድንግዝግዝ ጉዞ ትምህርትን እንፈልግ። ከአሁን አሁን ታክሲ መጥቶ እኔ ወረፋ ጋር በደረሰ በሚል እሳቤ ትኩረታቸውን ቀጥሎ ወደሚመጣው ታክሲ ላይ ያደረጉ ተሰላፊዎች። ተረኛው ታክሲ መጥቶ መሳፈር እስኪጀምር ድረስ በሃሳብ ፈረስ ላይ ተሳፍሮ መሄድ። አንዳንዱ አይኑን ከሞባይሉ ላይ አድርጎ በሞባይል አድርጎ የዓለምን ፋይል ይጋራል።
የተወሰነ ሰው አጠገቡ ካለው ሰው ጋር ጨዋታ ብጤም ጀምሮ ይሆናል። ተራ አስከበሪው የሚሰጠው መመሪያም እንዲሁ ትኩረትን እየሳበ የሚሄድ መሆኑ እሙን ነው። ታክሲው እስኪመጣ ድረስ! በሕይወት ጉዞ ውስጥ የታክሲ ሰልፍ የሚመሳሰልበት መንገድ ድንግዝግዝ ጉዞን እንድናይ ያደርገናል። በሃሳብ ፈረስ ላይ ከተሳፈሩት ተረኛውን ታክሲ ጠባቂዎች መካከል ምናልባት በሕይወታቸው ምክንያት በድንግዝግዝ ውስጥ ሆነው የሚቸገሩ ሊኖሩ ይችላሉ። ነገሮች ወደየት አቅጣጫ እየሔዱ እንዳለ ለማወቅ ያልቻሉበት ድንግዝግዝ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሕይወት።
ነገሮች ባሰብነው አቅጣጫ መሄድ አቁመው በተቃራኒ በሚሆኑበት ጊዜ ከራሳችን ጋር ሙግት ውስጥ እስክንገባ ድረስ የሚያደርስ ሁኔታ ውስጥ ራሳችንን ልናገኝ እንችላለን። የእያንዳንዱ የታክሲ ተሰላፊ ድንግዝግዝ መነሻው ይለያይ ይሆናል።
ድንግዝግዝ ጉዞው በአንድ የተወሰነ ምክንያት የሚመጣ ሊሆን የሚችል ቢሆንም አንዳንዴ ግን ከአንድ በላይ በሆነ ምክንያት የተፈጠረ ሊሆንም ይችላል። የሥራ ቦታ ምቹነት መጥፋት የሥራ ጉዞችንን ድንግዝግዝ የሚያደርግ ሲሆን ይህን የአንድ መስመር ምክንያት ልንለው እንችላለን።
በሥራ ሕይወት በተጨማሪ በትዳር ሕይወታችን ውስጥ ነገሮች መስመራቸው ግልጽ ያልሆኑ ሆነው ሲሰሙን ደግሞ አቅጣጫው የበዛ ምናልባትም ከባድ የሆነ ድንግዝግዝ ሕይወት ውስጥ ራሳችንን እያገኘን ይሆናል።
እኒህ ሁሉ ግን ቀላል የሚባሉ ናቸው፡፡ ከሁሉም የሚከፋው ግን ከወቅታዊ አለመመቸት ባሻገር የሕይወት አቅጣጫን ከማጣት የሚመጣው ድንግዝግዝ ሕይወት ነው። እዚህ ጋር የታክሲውን ሰልፍ መልሰን እናስበው። የተሰለፈው ሰው ታክሲ ስለመምጣቱ እርግጠኝነት ባይኖረው እንዲሁ ተሰልፎ ይውላል? በፍጹም! ታክሲው የሆነ ሰዓት ላይ ሊደርሰኝ ይችላል ብሎ ማሰብ ባይችል ወረፋ የመያዝ ትርጉሙ ይገባዋል? አሁንም በፍጹም! ታክሲ ካገኘበት ቅጽበት አንስቶ መድረስ የሚፈልገው ቦታ እስኪደርስ ድረስ ያለው ጊዜን መገመት ባይችልስ መሰለፉ ትርጉም ይሰጠዋል? አሁንም ምላሹ በፍጹም ነው።
ምንም ትርጉም ስለማይሰጥ፡፡ አንዳንዴ ሥራ ኖሮን እየሠራን የሕይወት አቅጣጫ ልናጣ እንችላለን። ምናልባትም የሚከፈለን ደሞዝ አነስተኛ ሳይሆን፤ ምናልባትም የሥራ ቦታው ምቹ ከመሆን ጎድሎም ሳይሆን፤ ምናልባትም የትዳር ሕይወታችን ጤናማም ሆኖ ሌሎች የሚቀኑበትም ሆኖ ወዘተ። በቃ ሕይወት ድንግዝግዝ የምትልበት የሕይወታችንን አቅጣጫ በግልጽ ማስቀመጥ ተስኖን ውስጣችንን በብዙ ጥያቄ ውስጥ የምንሞላበት ወቅት ማለት ነው።
ይህ ዓይነት የድንግዝግዝ ጉዞ በስፋት በዕድሜያችን አጋማሽ ላይ የሚገጥመን ቀውስ አድርገንም ልንወስደው እንችላለን። በዚህ ዓይነት መንገድ የሚያልፉ ሰዎች ብዙ ናቸውና አንባቢው እንዲህ ባለመንገድ እያለፈ ከሆነ ለምን ለእኔ ብቻ ብሎ ከመጠየቅ ወደ መፍትሔው ይሄድ ዘንድ ይገባዋል። የዚህ ጽሑፍም አላማው ችግሩን ከማሳየት ባሻገር መፍትሔውን አብሮ መፈለግ ነውና የመፍትሔ ነጥቦቹን አንድን ነገር የማግኘት አስፈላጊነትን በማንሳት እንጀምር።
አንድን ነገር የማግኘት አስፈላጊነት
አንድን ነገር የማግኘት አስፈላጊነት እንደ ሰው ፍላጎታችን ብዙ ነው። ሁሉም ፍላጎታችንን በአንድ ጊዜ ማድረግ ደግሞ እንዳንችል በውስንነት ውስጥ እንኖራለን። «ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት» እንደሚባለው ሁሉን ያማረንን ለማግኘት ስንጥር ሁሉንም ልናጣ እንችላለን። ነገርግን ትኩረት ሊደረግ የሚገባው አንድ ነገር ግን ሊኖረን ግድ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ነገሮችን ሞክረን ይሆናል።
በእያንዳንዱ ሙከራ ውስጥ የምናገኘው ትምህርት መኖሩ የማይካድ ቢሆንም ልባችንን የሚያሳርፍ ምዕራፍ ላይ ሳንደርስ ዛሬም በሌላ ሙከራ ውስጥ ራሳችንን እንገኛለን። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች የሚያውቁን ብዙ በመሞከር ሊሆንም ይችላል። አንድን ማግኘት የሚገባንን ነገር ማግኘት ባለመቻላችን ምክንያት ግርታ ውስጥ ራሳችንን ደጋግሞ የመክተት አዙሪት።
በሙሉ ትኩረታችን የምንሠራው አንድ ሥራን በማግኘት ሂደት ውስጥ ካልሆንን ድንግዝግዝ መፈጠሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን ፈጥረው ያለፉ ሰዎች በተለያዩ የድንግዝግዝ መንገዶች ውስጥ ያለፉ ሰዎች እንደሆነ ከታሪካቸው እንማራለን። በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ ለዛሬ ምቾት የሚሰጥ አይሁን እንጂ ለነገ የሚሆን ስንቅ እየሰነቅን እንድንራመድ የሚያስችል ነው። ሙሉ ትኩረታችን የምንሰጠው ሥራ ላይ እስክንደርስ ድረስ ድንግዝግዙ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ዛሬ በምንም ሁኔታ ውስጥ እንገኝ አንድን ነገር የማግኘት አስፈላጊነትን ግን ችላ ልንለው አይደገባም። ከትናንት ብዙ መከራዎች ውስጥ ትምህርት እየወሰድን፤ ለነገ የሚሆን የተሻለ ስፍራ ላይ መድረስን ስናስብ አንድን ነገር ማግኘት ላይ ማተኮር አለብን።
የምናገኘው አንድ ነገር የምር ሆኖ እጃችን እስኪገባ ድረስ ፍለጋው መቀጠሉ እንዲሁ የሚጠበቅ ነው። የምንፈልገው አንድ ነገር ማለት ሕይወታችን ትኩረት ሰጥቶት የሚኖርለት ማለት ነው። አንዳንዴ ከብዙ ጊዜ በፊት ሞክረነው የነበረ ነገርግን የተውነው ነገር ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው ‘ለምን ተውኩት’ ብለን ራሳችንን በቁጭት እንድንጠይቅ ያደርገናል። ይህ ሁሉም ሰው ሊያልፍበት የሚችል በመሆኑ የአንባቢው ብቻ አይሆንም።
ምናልባት አንድን ነገር ፈልጎ የማግኘት ትኩረት ላይ ተገኝተን ቢሆን ኖሮ እንዳሳለፍነው የሚቆጨንን ነገር አናሳልፈው ይሆናል። ዛሬም በሕይወት መኖራችን ውስጥ ዛሬም ዕድል መኖሩን የሚያሳይ ነውና፤ የመፍትሄው መንገድ አሁንም አንድን ነገር ማግኘት ነው፤ እርሱም የሚያስደስተን ሆኖ የሚገኝ ጊዜያችንን ውድ የሚያደርግ፡፡
የሚያስደስተን አንድ ነገር
ሀብት ውስን የሰው ልጆች ፍላጎት ደግሞ ገደብየለሽ በሆነበት ምድር ውስጥ ስንሆን የምንፈልገውን ሁሉ ለማግኘት መሄድ ስህተት ላይ ይጥላል። ሥራን ስናስብ በየሰሞኑ ፍላጎታችን ተለያይቶ አንዱን ይዘን አንዱን ስንጥል ዘመናችንን እንዳንጭርስ ልንጠነቀቅም ይገባል።
የሚያስደስተን አንድ ነገር ደግሞም ሠርተን ወደ ውጤት የምንደርስበትን ለማወቅ ጊዜን መስጠት ብልህነት ነው፡፡ በኮሌጅ ቆይታ ህልም ያደረግነውን ሥራ ለመጨበጥ ነገሮች ቀላል ሳይሆኑ ሲቀሩ የተገኘውን ሁሉ በመሞከር ውስጥ ጊዜው ሊሄድ ይችላል። መፍትሔው ስንሰራው ደስታን የሚሰጠን መሥራት እንደሚገባን ሠርተን ወደ ውጤት ልንደርስ የምንችልበትን ሥራ ማወቅና መለየት ነው። ደስታን የሚሰጠንን ሥራ ጋር መድረስ ስንችል ጥንካሬያችን ብዙ ማድረግ ይችላል። ጥንካሬህን ለይቶ ማውጣት እያንዳንዱ ሰው ውስጥ ጥንካሬ አለ።
ጥንካሬውን ለማወቅ የሚያስፈልግም ጥንካሬም አለ። ጥንካሬን አለማወቅ የሕይወትን አቅጣጫ ድንግዝግዝ ውስጥ ከሚጨምሩት ነገሮች መካከል ዋናው ነው። መፍትሔው ደግሞ ጥንካሬን ማወቅ። ጥንካሬ ሌላ ጥንካሬን የሚወልድ ሆኖ ሥራ ላይ ሲውል ወደ ውጤት የሚያመራ ነው። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ጥንካሬ ከማየት ምናልባትም የሌሎችን ከድንግዝግዝ ወደ …! የማየት አቅም ሊኖረው ይችላል። በመሆኑም ሌሎች ስለጥንካሬያችን እንዲሁም ድክመታችን የሚነግሩንን በጥሞና ማድመጥ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡
በሕይወት ጉዞ ውስጥ በድንግዝግዝ እየተራመድክ እንደሆነ ካሰብክ ዛሬ ቆመህ ለራስህ ምላሽ ስጥ፤ ምላሹም ጥንካሬህን በማወቅ ውስጥ ይሁን። ሆነን ማለፍ የምንፈልገውን ማድረግ የምንችል መሆናችን የሚወሰነው በጥንካሬያችን ውስጥ ነው። አንድ ሰው ሁሉንም ነገሮች መሆን ባይችልም አንዳች በልዩነት ሊያደርገው የሚችለው ነገር መኖሩን ግን መረዳት አለበት።
በልዩነት ሊያደርገው የሚችለውን ከሌሎች ጋር በማቀናጀት ትርጉም ያለው ነገር መስራት የሚችልበት አቅም ውስጥ እንዲገኝ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ዛሬ ለውጥን በሕይወትህ እንዲሁም በሌሎች ላይ ለማድረግ ስትነሳ ልትሠራው የሚገባው ነገር የምትፈልገውን ማወቅ ብቻም ሳይሆን የምትፈልገውን ዳር ማድረስ የምትችልበት ጥንካሬህንም ማወቅ ነው።
ጥንካሬህን ለማወቅ የሚረዱ ፈተናዎችን በመውሰድ ልትሠራበት ይገባል። ከሁሉም በላይ ራስን በማዳመጥ በዙሪያችን ያሉትን በተደጋጋሚ የሚነግሩንን በመረዳት ጥንካሬያችንን መረዳት ወደ ምንችልበት ምዕራፍ ላይ እንደርሳለን።
እሴታችንን መለየት መቻል
እያንዳንዳችን እንዲኖረን የምንፈልገው እሴት አለ። ከትናንት ወደዛሬ የመጣ በውስጣችን እውቅና የሰጠነው እሴት አለ። ተቋማት ራእያቸውን ለማሳካት የሚረዳቸውን እሴት ዘርዝረው ያስቀምጣሉ። በግል ሕይወታችን ውስጥ የራሳችን ያልናቸውን እሴቶች እንዲሁ ሊዘረዘሩ የሚችሉ ናቸው።
ዝርዝሩን ቁጥር እየቀነስን ወደ ተወሰነ ቁጥር እንድርስ። ምናልባትም አምስት እሴቶችን ልናስቀመጥም እንሞክር። እኒህን እሴቶች ማዕከል እያደረግን ውሳኔዎችን በወሰንን ቁጥር በሕይወታችን ውስጥ ከራሳችን ጋር የታረቀ የተግባር እንቅስቃሴ ውስጥ መራመድን ይጠይቀናል። ከድንግዝግዝ ጉዞ መስመር ወዳለው ጉዞም ያመጣናል። ለተግባር እርምጃ ሁልጊዜ አቅም ይሆነናል።
የተግባር እርምጃን መራመድ
በሕይወታችን ውስጥ ውጤታማን ጉዞ ለማድረግ የተግባር እርምጃ ማድረግ በምንም የሚተካ አይሆንም። የተግባር እርምጃ አድካሚ ነው። አሻግረን ወዳየነው በምናደርገው እርምጃ ውስጥ ውጤታማ ለመሆን የሚረዳ ወሳኝ መሆኑ ግልጽ ነው።
የተግባር እርምጃችን ከእሴታችን፤ ከጥንካሬያችን እና ሠርተን ማለፍ በምንፈልገው ፍላጎት የተቃኘ ሲሆን ወደ መሆን እጅጉኑ ይጠጋል። የተግባር እርምጃ ሲታሰብ ሁሉንም ሰው የሚፈትነው የጥንካሬያችን ተቃራኒ የሆነው ድክመታችን ነው። ድክመታችን የተግባር እርምጃችንን የሚገታ እንዳይሆን የውስጣ ፍላጎታችን፤ ጥንካሬያችን፤ እሴታችን ወዘተ ጦርነቱን በአሸናፊነት እንድንወጣ ያግዙናል። ድንግዝግዝ ባለጉዞ ከሚራመዱ ብዙ ሰዎች ውስጥ ተነጥለህ ለመውጣት የምታጠፋው ጊዜ አይኑር። ጊዜው አሁን ነውና፤ አሁን ከራስህ ጋር ምከርበት። ከድንግዝግዝ ወደ …!!!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014