በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት የጎላ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሴቶች 1500 ሜትር ኢትዮጵያውያን ፍጹም የበላይነት አላቸው።
ባለፉት አምስት ቻምፒዮናዎችም በዚህ ርቀት አሸናፊ መሆን የቻሉት ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ለዚህም እኤአ በ2012፣ 2018 ገንዘቤ ዲባባ፣ በ2010 ቃልኪዳን ገዛኸኝ፣በ2008 ገለቴ ቡርቃ ውድድሩን ማሸነፋቸው ይጠቀሳል። በ2016 ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፋን ሃሰን እንዲሁም ለስዊድን የምትሮጠው አበባ አረጋዊ በ2014 ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ለ18ኛ ጊዜ ትናንት በሰርቢያ ቤልግሬድ መካሄድ በጀመረው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮናም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በርቀቱ ይህን የበላይነት ለማስጠበቅ ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።
ለዚህም የወቅቱ የቤት ውስጥ ኮከብ የሆነችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ለወርቅ ሜዳሊያው እጩ ሆናለች። የሃያ አምስት ዓመቷ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ በገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የቆየውን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ባለፈው ታህሳስ 3:53:09 በሆነ ሰአት ፈረንሳይ ሌቪን ላይ የግሏ ማድረጓ በዛሬው ፉክክር ለድል እንድትጠበቅ አድርጓታል።
ጉዳፍ ባለፉት አስራ ሶስት ወራት ያሳየችው አስደናቂና ወጥ አቋም ዛሬ ለድል ቢያሳጫት አስገራሚ አይሆንም። በተለይም የዓለም ክብረወሰኑን ካሻሻለች ከሳምንት በኋላ ቶረን ላይ የርቀቱን ሁለተኛ ፈጣን ሰአት በ3:54:77 ማስመዝገቧ ምን ያህል የብቃቷ ጥግ ላይ እንደምትገኝ አመላክቷል። ከሁለት ሳምንት በፊትም ማድሪድ ላይ 3:57:38 መሮጥ መቻሏ የሚታወስ ሲሆን በ2022 ርቀቱን ከአራት ደቂቃ በታች ማጠናቀቅ የቻለች ብቸኛዋ የዓለማችን አትሌት ናት።
ይህም በዛሬው ፉክክር በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የመጀመሪያዋን የወርቅ ሜዳሊያ የተለየ ችግር ካልገጠማት በቀር ለማሳካት እንደማትቸገር የሚያረጋግጥ ሆኗል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በቤት ውስጥ ውድድሮች በተለያዩ ርቀቶች ያደረገቻቸውን ዘጠኝ ውድድሮች ማሸነፍ የቻለችው ጉዳፍ በቤት ውስጥ ውድድሮች ሽንፈት የገጠማት እኤአ በ2019 ታህሳስ ወር ነው፤ ይህም ማድሪድ ላይ በ3ሺ ሜትር ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ነው።
ከዚህ ውጪ ጉዳፍ በተለይም በ1500 ሜትር በቤት ውስጥም ይሁን ከቤት ውጪ ውድድሮች እስከ 2019 የዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ድረስ ሽንፈት ገጥሟት አያውቅም።
ጉዳፍ በዋናው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዶሃ ላይ ሲፈን ሃሰንን እንዲሁም ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን ተከትላ በሶስተኛነት ነበር ያጠናቀቀችው። በሶስት ታላላቅ ውድድሮች በተለያዩ ርቀቶች የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀችው ጉዳፍ ዛሬ ወደ ወርቅ ሜዳሊያ የምትሸጋገርበት ቀን እንደሚሆን ይጠበቃል።
እኤአ በ2016 የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በ1500 ሜትር፣ በ2019 የዶሃ የዓለም ቻምፒዮና በ5ሺ ሜትር እንዲሁም ባለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ በተመሳሳይ ርቀት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች። በቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ግን ይህ ታሪክ እንደሚቀየር ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል።
በዛሬው ምሽት ወሳኝ የፍጻሜ ፍልሚያ ከጉዳፍ ቀጥላ ሁለተኛውን ፈጣን ሰአት የያዘችው አትሌት ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አክሱማይት አምባዬ ናት።
አክሱማይት በጀርመን ካርልሹ 4:02:12 በሆነ ሰአት ርቀቱን ማሸነፏ የሚታወቅ ሲሆን በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎችም ልምድ አካብታለች። እኤአ በ2014 አበባ አረጋዊ ባሸነፈችበት ቻምፒዮና አክሱማይት የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወስ ሲሆን በ2016 ሲፈን ሃሰን ባሸነፈችበት ቻምፒዮና ዳዊት ስዩምና ጉዳፍ ጸጋይን ተከትላ አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች።
ጉዳፍ አስደናቂ ብቃት ባሳየችባቸው ያለፉት ሳምንታት ውድድሮች ድል ባይቀናቸውም ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ተከታትለው ውድድራቸውን ሲጨርሱ የነበሩት አክሱማይት አምባዬና ሂሩት መሸሻ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አትሌት ሂሩት መሸሻ የ2019 መላ አፍሪካ ጨዋታዎች የ800 ሜትር አሸናፊ መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን አክሱማይት በጀርመን ካርልሹ ባሸነፈችበት ውድድር 4፡02፡22 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 /2014