በኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው የብሔራዊ ክለቦች ቦክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል፡፡
በዓለም የሴቶች ቦክስ ሻምፒዮናው ተሳታፊ የሚሆኑ የሴት ብሔራዊ ቡድን አባላትም ከዚህ ውድድር እንደሚመረጡ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ከፍተኛ ፉክክርና ፍልሚያ ከሚታይባቸው የአገር ውስጥ የቦክስ ውድድሮች መካከል የብሔራዊ ክለቦች ሻምፒዮና ዋነኛው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ውድድሮችም በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
ሻምፒዮናው አራት ዙሮች ያሉት ሲሆን፤ በተለያዩ ክልሎች በዙር ይካሄዳል፡፡ በተያዘው ዓመት የሻምፒዮናው ሁለተኛ ዙር ውድድር ዛሬ ከሰዓት በኋላ (ከ8 ሰዓት ጀምሮ) በትንሿ አዲስ አበባ ስታዲየም የሚጀመር ይሆናል፡፡
በውድድሩ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ክለቦች የሚካፈሉበት ሲሆን ሻምፒዮናው በሁለቱም ጾታዎች የቡጢ ተፋላሚዎችን ያፎካክራል፡፡ በዚህም በወንዶች 70 በሴቶች ደግሞ 28 በድምሩ 98 የቦክስ ስፖርት ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በሻምፒዮናው ተሳታፊ የሚሆኑ ስምንት ክለቦች ሲሆኑ በወንዶች፤ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ ጎንደር ከተማ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀላባ ከተማ ናቸው፡፡
በሴቶች ደግሞ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ጎንደር ከተማና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቦክሰኞቻቸውን የሚሳተፉ ክለቦች እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ ውድድሮቹ የሚካሄዱባቸው የተለያዩ ምድቦችም ተለይተዋል፡፡
በአዋቂና ታዳጊ ወንዶች በ48፣51፣54፣ 57፣60፣ 63.5፣ 67፣71፣75፣ 80፣ 86፣92 ኪሎ ግራም እንዲሁም ከ92 ኪሎ ግራም በላይ ናቸው፡፡ በአዋቂና ታዳጊ ሴቶች ምድብ ደግሞ በ48፣ 50፣ 52፣ 54፣ 57፣ 60፣ 63፣ 66፣ 70፣ 75 እና 81 ኪሎ ግራም በሆኑ ቦክሰኞች መካከል ፉክክሩ የሚደረግ መሆኑም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በዚህ ሻምፒዮና ተሳታፊ ከሚሆኑት መካከል በሴቶች የተሻለ ብቃት ያሳዩት በዓለም የሴቶች ቦክስ ሻምፒዮና አገራቸውን የሚወክሉ ይሆናል፡፡ ይኸውም በቱርክ ኢስታንቡል ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄድ የዓለም የሴቶች የቦክስ ሻምፒዮና ሲሆን፤ ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓም ይደረጋል፡፡ በመሆኑም በሻምፒዮናው የኢትዮጵያን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በብሔራዊ ቡድኑ የሚካተቱ ቦክሰኞች እንደ ብቃታቸው ሁኔታ ቁጥራቸው የሚወሰን ሲሆን፤ ያለ ማጣሪያ በቀጥታ በዓለም አቀፉ ውድድር ተሳታፊ እንደሚሆኑም በፌደሬሽኑ የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ገልጸዋል።
የ2014 ዓ.ም የብሔራዊ ቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና የመጀመሪያ ውድድር ከጥር 25 እስከ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተካሂዶ በሁለቱም ጾታዎች አዲስ አበባ ፖሊስ አሸናፊ መሆን መቻሉ ይታወቃል፡፡
ቀጣዩ የሶስተኛ ዙር ሻምፒዮናም በግንቦት/2014 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን፤ አራተኛው ዙርና የሻምፒዮናው ማጠቃለያ ውድድር ሰኔ/2014 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ ይደረጋል። በአራቱም ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦች ውጤት ተደምሮም የ2014 ዓም የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊው የሚታወቅ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ጠቁማል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 /2014