በአገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ሰሞኑን የእውቅና፤ ሽልማትና ማዕረግ የማልበስ ሥነሥርዓት አካሂዷል።
«እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም» በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተካሄደው ሥነሥርዓት ላይ በምርጥ አዋጊ፣ በምርጥ ተዋጊ በአሃድና በግለሰብ፣ በውጊያ ድጋፍና የውጊያ አገልግሎት ዘርፍ፣ በስታፍ፣ በዩኒትና በግለሰብ ደረጃ 151 ግለሰቦችና ቡድኖች ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። እኛም ከእነዚህ ተሸላሚዎች መካከል ጥቂቶቹን እናስተዋውቃችሁ።
አስር አለቃ አስቴር ገነነ፡- የ23ኛ አንበሳ ክፍለጦር የመገናኛ ባለሙያ ወጣት ሴት ወታደር ናት በዚህ ዕድሜዋም በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ የጀግና ሜዳሊያ ከተሸለሙ የበታች አመራሮች አንዷ ናት። አስር አለቃ አስቴር እንደገለፀችው የተሰለፈችበት የመገናኛ ሙያ በጦርነት ውስጥ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግና 24 ሰዓት የሚሠራበት ነው።
እረፍት የማይፈልግ፤ ስህተቱ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ነው። በዚህ መሠረት ይህን ኃላፊነት የተረከበችው አስር አለቃ አስቴር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ቀንና ሌሊት ሥራዋን በብቃት በመወጣቷ ሽልማቱ ሊሰጣት ችሏል። ክፍለጦሩ እልህ አስጨራሽ ጦርነቶችን ባካሄደባቸው ጊዜዎች ሁሉ በእሷ በኩል አንድም ጊዜ መገናኛ ተቋርጦ አያውቅም።
በ2007 ዓ.ም ወደ መከላከያ የተቀላቀለችው አስር አለቃ አስቴር፣ የሰሜን ዕዝ አባል ነበረች። በወቅቱም ዕዙ በአሸባሪው ሕወሓት ሲጠቃ የዚሁ አካል ነበረች።
ከዚያ በኋላ የዕዙ ሁሉም ክፍለጦሮች ካፈገፈጉ በኋላ ዳግም ጠላትን በመግጠም ድል ባስመዘገቡባቸው እና በኋላም በተለያዩ ግንባሮች በተደረጉ ውጊያዎች ሁሉ ተሳትፋለች። በዚህ ላቅ ያለ ድል እንዲመዘገብ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች። በአፋር ግንባር በነበረው ጦርነትም ከፍተኛ ተጋድሎ ሲደረግ አስር አለቃ አስቴርም ለ22 ቀናት ቀንና ሌሊት ከጠላት ጋር በመተናነቅ አኩሪ ድል እንዲመዘገብ የራሷን አስተዋጽኦ አበርክታለች።
ወታደር ፍፁም ኢረና፡- የ64ኛ ክፍለጦር ሦስተኛ ሬጅመንት የጋንታ አንድ አባል
ገና የ19 ዓመት ወጣት ነው። ወደ ውትድርና የገባበትም ዋነኛ ምክንያት የሰሜን ዕዝ መጠቃት ነው። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ሕወሓት የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ የፍፁም አባት ወታደር ኢረና ተካ የዚሁ ዕዝ አባል ነበሩ።
በዚህ ወቅት ታዲያ አባቱ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ባደረጉት ትቅንቅ ሕይወታቸው አልፏል። ይሁን እንጂ የፍፁም አባት ቢሰዉም ጓዶቻቸው ግን ትግላቸውን ከመቀጠል ወደኋላ አላሉም። የፍጹም አባት ልጃቸውን ያሳደጉት የአገር ፍቅር ስሜት እንዲኖረው አድርገው ነው። በሕፃንነቱ አልፎ አልፎ ወደቤት ሲመጡ ራሱን እያሻሹ ስለአገር ፍቅር እንደ ተረት ይነግሩታል።
አገር ከሌለ ማንም እንደማይኖር፣ የሰው ልጅ ክብሩ አገሩ እንደሆነ፣ እርሳቸውም በዚያ መልክ ከልጆቻቸው ርቀው የሚገኙት ለእነሱ ነፃነት እንደሆነ ያጫውቱታል። በዚህ መልክ ያደገው ፍፁም አባቱ በግፈኛው የሕወሓት ፅንፈኛ ኃይል ሲሰዋ ሲመለከት ይህን ኃይል መዋጋት እንዳለበት ወሰነ። አንድ ቀንም ተደብቆ በመሄድ በጦር ሰራዊት አባልነት ተመዘገበ።
ከዚያ በኋላ ስልጠናውን በሚገባ ያጠናቀቀው ወታደር ፍፁም፤ በዋለባቸው የጦር አውደ ውጊያዎች ሁሉ በአባቱ ላይ የደረሰውን ግፍ እያስታወሰ በጀግንነት ተዋግቷል። ወታደር ፍፁም ውጊያ የጀመረው ድሬዶቃ ላይ ነው።
ከዚያ የመጣውን ኃይል በያዘው መሣሪያ እያስቀረ ቁጭቱን ተወጥቷል። ከዚያ በኋላ ቡርቃ እና ካሳጊታ ላይም የጠላትን ኃይል ለመደምሰስ በተደረጉ ውጊያዎች ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ በጀግነት ተዋግቷል።
ወታደር ፍጹም ብሬን ተኳሽ ሲሆን፤ የጁንታውን ተሽከርካሪም በመምታት እና በማውደም ጀብድ ፈጽሟል። በዚህም የጀግና ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
ኮሎኔል አሰፋ አማረ፤ የ77ኛ ክፍለጦር አዛዥ
ኮሎኔል አሰፋ አሸባሪው ሕወሓት አጥብቆ ከሚያውቃቸውና ከሚፈራቸው የጦር መሪዎች አንዱ እንደሆኑ ጓዶቻቸው ይናገራሉ::
በዚህም የተነሳ በተለያዩ ወቅቶች እኚህን የጦር መሪ አንዴ ገድለናቸዋል፤ ሌላ ጊዜም ማርከናቸዋል በሚል ሲያስወሩና ደጋፊዎቻቸውን ሲያስፈነድቁ ሰንብተዋል:: እርሳቸው ግን ወሬውን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው በጀግንነት ማዋጋታቸውን ቀጥለዋል::
በሽልማቱ ላይ ኮሎኔል አሰፋ ፊታቸው ላይ ደስታም ኀዘንም ይነበባል:: አንዴ ፈገግ፤ ሌላ ጊዜ ቅጭም የሚለው ገፅታቸው በትውስታ ወደኋላ ከሚመልሳቸው ስሜት የመነጨ ሳይሆን አይቀርም::‹‹ይህ ሽልማት ውስጤን ያስከፋኛልም፤ ያስደስተኛልም::
በዛሬው ዕለት ለዚህ ሽልማት እንድበቃ ያደረጉኝ የተሰዉ ጓዶች አሉ:: ሽልማቱ ለእኔ ብቻ ሳይሆን የዛሬዋ ቀን እንድትመጣ ትልቅ መስዋትነት ለከፈሉ ጓዶች ጭምር ነው:: ሰሜን ዕዝ ሲጠቃ ችግር ከገጠማቸው አባላት አንዱ ነኝ::
በወቅቱም ከፍተኛ ፈተና ተጋፍጠናል:: ዛሬም እዚያ የነበሩ ችግሮችን አልፈን በሕይወት በመገኘታችን ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ» ይላሉ:: በዚህ ጦርነት በርካታ ፈተናዎችን ብንጋፈጥም እነዚያን ሁሉ ፈተናዎች አልፈን ዛሬ ላይ የጠላትን ኃይል ለማንበርከክ በመቻላችን ትልቅ ደስታ ይሰጠናል ብለዋል ኮሎኔል አሰፋ:: ኮሎኔል አሰፋ በካሳጊታ ውጊያ እርሳቸውም ቆስለው ነበር:: ከዚያ ሕክምና ካገኙ በኋላ ወደውጊያ ተመለሱ::
በዚህ ጦርነት እንደ አንድ የጦር መሪ በውጊያ ድል ከማስመዝገብ ባሻገር ብዙ አመራሮች እንዲበቁ በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት የተወጡ መሪ ናቸው:: ይህ ጦርነት ኢትዮጵያ የወደፊት የቁርጥ ቀን ልጆቿን ያገኘችበት እንደሆነም ይገልጻሉ::
ለሽልማት ያበቃቸውም እነዚህና ሌሎች የአመራር ብቃታቸው ጭምር ነው:: ከዞብል እስከ አማሮ፤ ከአማሮ እስከ አራ አልፎም እስከ አላሊ በተደረጉ ውጊያዎች ፈታኝ ጦርነቶችን የመሩ እና ጠንካራ የጦር መሪዎችንም ያፈሩ ናቸው::
የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች ከተቀመጡበት ሊነሱ፤ ከተኙበት ሊነቁና ሊያስቡበት ይገባል የሚሉት ኮሎኔል አሰፋ፤ ከዚህ በኋላ የማያርፉ ከሆነ ግን ነገሮች ከባድ እንደሚሆኑባቸው ይገልጻሉ::«እኛ በማንኛውም ወቅት ዝግጁዎች ነን::
የትግራይ ሕዝብ አደጋ እንዲደርስበት አንፈልግም:: ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ በቃኝ ብሎ ከመንግሥት ጎን ቢሰለፍ መልካም ነው» ብለዋል::
ሻምበል ጌትነት አስፋው፡- የ23ኛ ክፍለጦር የትራስፖርት ኃላፊ
ሻምበል ጌትነት በተለይ ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ሎጅስቲክ ሥራው ሳይቋረጥ ለሚመለከታቸው አካላት በወቅቱ እንዲደርስ በማድረግ ላበረከቱት ተግባር የዕለቱ ተሸላሚ ነበሩ። ሻምበል ጌትነት ከሎጅስቲክ ባሻገር ቁስለኞችን ግንባር ድረስ በመግባት ቶሎ በማንሳትና ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ ያበረከቱት አስተዋፅኦ የላቀ ነው፡
በተለይ የጠላት ኃይል ከአርድቦ ወደ ቡርቃ በከፈተው ጦርነት ጠላት ካሳጊታን ለመቁረጥ ያደረገው ጥቃት ድንገተኛ ስለነበር በወቅቱ የሎጅስቲክ ሥራው ፈጣን መሆን ነበረበት።
ይህንንም በብቃት በመወጣት የመካለከያ ሰራዊታችን መሣሪያ እንዲደርሰው በማድረግ ቶሎ ወደማጥቃት እንዲገባ በማድረግ በተወሰደው እርምጃ የወገን ጦር ከብዙ ትግል በኋላ ድል ማግኘት ችሏል። በዚህ እቅስቃሴ ውስጥ የሻምበል ጌትነት ሚና የጎላ ነበር።
ወታደር አስራት መሰለ፤ የ77ኛ ክፍለጦር አንደኛ ሬጅመንት አባል
አሸባሪው ሕወሓት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በፈፀመበት ወቅት ወታደር አስራት የምሥራቅ ዕዝ አባል ነበረች። ከዚያ የሰሜን ዕዝ ሲጠቃ ከምሥራቅ ዕዝ በፍጥነት በመወርወር አደጋ የተጋረጠባቸውን ጓዶች ለመታደግ ወደ ስፍራው ከተጓዙ የሰራዊት አባላት አንዷ ናት።
ከዚያም በደረሰችበት ስፍራ ከጠላት ጋር ፊትለፊት በመጋፈጥ በርካታ ጀብዶችን ፈጽማለች። ወታደር አስራት በወቅቱ እስከ መቀሌ ድረስ በነበረው ውጊያ ስትዋጋ የቆየች ሲሆን የስናይፐር ተኳሽም ነበረች።
በድሬሮቃ ግንባር የነበረውን ጠላት ለመደምሰስ በተደረገው ውጊያም ከፍተኛ ትንቅንቅ በማድረግ በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች። እሷ የነበረችበት ጋንታ መሪም ድንገት ሲቆስሉም ሬድዮ በመቀበል ያለውን ኃይል በመምራት ጠላት ጥቃት እንዳይፈፅም በማድረግ ከፍተኛ ጀብድ ፈጽማለች።
እርሷ አንድ ጊዜ ቆስላ ሕክምናዋን ካገኘች በኋላ ወዲያው ወደጦሩ በመመለስ አገሯን ለመታደግ ከፍተኛ አስዋፅኦ አበርክታለች።
ወርቁ ማሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 /2014