ዛሬ የአንጋፋውን የታሪክ ጸሐፊ የሕይወት ጉዞና አበርክቶ ታሪክ በጥቂቱ ልንመለከት ነው። በጋዜጠኝነት፣ በዲፕሎማትነትና በተለይ በታሪክ ጸሐፊነት ዘመን የማይሽራቸው አስተዋፅዖዎችን ያበረከቱት የአንጋፋው ባለሙያ፣ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ታሪካቸው እጅግ ሰፊ ቢሆንም ካልተዘመረላቸው የአገር ባለውለታዎች አንዱ በመሆናቸው አበርክቷቸውን አጠር አድርገን እንመለከታለን።
ዘውዴ ረታ የተወለደው ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ነው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን (ከ1933-1945 ዓ.ም) በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በ17 ዓመቱ ‹‹እኔና ክፋቴ›› የተሰኘውን የመጀመሪያ የትያትር ስራውን አዘጋጀ። በመቀጠልም (በ1945 ዓ.ም እና በ1946 ዓ.ም) ‹‹ፍቅር ክፉ ችግር››፣ ‹‹የገዛ ስራዬ›› እና ‹‹እንግዳ ሰው የቡልጋው›› የተባሉ ሌሎች የትያትር ስራዎችን ጽፏል።
እነዚህ አራት የትያትር ስራዎቹ በአፃፃፍ ጥበባቸውና በይዘታቸው በወቅቱ ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተቀባይነት አግኝተው ነበር። ከዚያም በወቅቱ የማስታወቂያ መስሪያ ቤቱን ይመሩ ለነበሩት ለአቶ መኮንን ሀብተወልድ ሬዲዮ ላይ ለመስራት ያለውን ፍላጎት እንዲታወቅለትና ዕንዲታይለት ማመልከቻ ፃፈ። በ1945 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ገብቶ መስራትም ጀመረ።
ሬዲዮ ላይ እየሰራ በነበረበት ወቅት ቋሚ የቤተ መንግሥት ዘጋቢ እንደሚያስፈልግ በመታመኑ ዘውዴ በአቶ መኮንን ሐብተወልድ ተመረጠ። ስራውም በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በየዕለቱ የሚከናወኑ ስራዎችን እየተከታተሉ ለራዲዮ ዜና ማቅረብ ነበር። ይህ ተግባሩም በንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ለመታወቅና ወደ እርሳቸው ለመቅረብም እድል ፈጠረለት።
ንጉሠ ነገሥቱ የወጣቱ ዘውዴን ስራዎች ሲያዳምጡ ዘውዴ የተሻለ ትምህርት ቢያገኝ ከዚህ የበለጠ መስራት እንደሚችል አመኑ። ዘውዴም ወደ ውጭ አገር ሄዶ የጋዜጠኝነት ለማጥናት ቀደም ብሎ ጥያቄ አቅርቦ ስለነበር ንጉሠ ነገሥቱ ለዘውዴ ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ሰጡ።
በዚህም ምክንያትም እስከ 1948 ዓ.ም ድረስ በጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት የሬዲዮ ዜና አቅራቢና የቤተ መንግሥት ዜና ዘጋቢ ሆኖ የቆየው ዘውዴ፣ በ20 ዓመቱ ወደ ፓሪስ፣ ፈረንሳይ በማቅናት ለአራት ዓመታት ከግማሽ ያህል (ከ1948 እስከ 1952 ዓ.ም) በፓሪስ የጋዜጠኝነት ከፍተኛ ትምህርት ቤት (Ecole Supérieure de Journalisme de Paris)›› የጋዜጠኝነት ሙያን አጥንቶ በዲፕሎማ ተመረቀ።
ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰም ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› ጋዜጣና የ‹‹መነን›› መጽሔት ዳይሬክተር (1952 ዓ.ም – 1954 ዓ.ም)፣ የኢትዮጵያ ራዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት ዳይሬክተር (1954 ዓ.ም – 1955 ዓ.ም)፣ የቀድሞው ‹‹የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ›› (የአሁኑ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) ዋና ዳይሬክተር (1955 ዓ.ም – 1958 ዓ.ም)፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር (1958 ዓ.ም – 1960 ዓ.ም)፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ (1960 ዓ.ም – 1962 ዓ.ም) እንዲሁም ከ1956 ዓ.ም እስከ 1962 ዓ.ም የፓን አፍሪካ ዜና ኤጀንሲ (Pan-Africa News Agency) ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ሠርቷል።
በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ በነበረባቸው ዓመታትም በውጭ አገር የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ሙያው ኢትዮጵያ ውስጥ መሻሻል እንዲያሳይ የበኩሉን አስተዋፅዖ አበርክቷል።
በ1962 ዓ.ም ደግሞ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተዛወረ በኋላ እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ በፓሪስ፣ ፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስለር፣ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር እንዲሁም በኢጣሊያና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አምባሳደር ሆኖ አገልግሏል።
ንጉሠ ነገሥቱ በሄዱባቸው አገራት ሁሉ ተከትሎ በመሄድ ስለ በርካታ ጉዳዮች ልምድ መቅሰም ችሏል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ መኮንን ሀብተወልድም ዘውዴን እንደልጃቸው ይቆጥሩትና ያቀርቡት ስለነበር ወደ ንጉሣዊው መንግሥት በእጅጉ ጠጋ ብሎ ብዙ ነገሮችን የመመልከትና የማወቅ እድል አግኝቷል።
ዘውዴ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ሰዎች ብቻ የሚያውቋቸውን ምስጢራዊ ጉዳዮችንም ማወቅ ችሏል። የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ከወደቀ በኋላ በነበረው ወታደራዊው የደርግ አስተዳደር ወደ ውጭ ተሰዶ ሮም፣ ኢጣሊያ በሚገኘው በዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ (International Fund for Agricultural Development – IFAD) ውስጥ ለ13 ዓመታት ያህል የፕሮቶኮልና የመንግሥታት ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ሰርቷል።
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት በቅርበት የመከታተልና የማወቅ እድል የነበራቸው አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከትምህርታቸው፣ ከስራቸውና ከሕይወት ተሞክሯቸው በመነሳት በ1992 ዓ.ም ‹‹የኤርትራ ጉዳይ››፣ በ1997 ዓ.ም ‹‹ተፈሪ መኮንን›› እንዲሁም በ2005 ዓ.ም ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት›› የተሰኙ ዳጎስ ያሉና ከፍተኛ ተነባቢነትን ማትረፍ የቻሉ የታሪክ መጽሐፍትን ለአንባቢ አድርሰዋል። አምባሳደር ዘውዴ አንድ ቀን መጽሐፍ እጽፋለሁ የሚል ምኞትና ኅልም እንደነበራቸው ተናግረው ነበር።
ስለጉዳዩም በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ‹‹ … መጽሐፍ እፅፋለሁ የሚል ትልቅ ምኞት ነበረኝ። ፈረንሳይ አገር በምማርበት ወቅት ‹ጋዜጠኛ ሆኖ ያሳለፈ ሰው ብዙ ያየው፣ የሰማውና ያሳለፈው ነገር ስለሚኖረው መጽሐፍ መፃፍ ይችላል› ሲሉ እሰማ ነበር። የእኔ መምህራን የነበሩት ሰዎች መጽሐፍትን ጽፈው ተመለከትኩ …›› ብለው ነበር። በ1992 ዓ.ም የታተመው ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› መጽሐፋቸው ከኢትዮጵያ አልፎ በኤርትራውያንም ጭምር ዘንድ በእጅጉ የሚፈለግ መጽሐፍ ሆኖ ነበር። ለበርካታ ጊዜያትም ታትሟል።
መጽሐፉ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳዮች በበርካታ ማስረጃዎች የታገዙ ማብራሪያዎችን ይዟል፤መጽሐፉ ከኢትዮጵያ ባሻገር በኤርትራውያንም ዘንድ ተነባቢ መሆን ችሏል። የኤርትራን ጉዳይ የተመለከተው ይህ መጽሐፋቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘበው በዶክተር ኃይሉ ሀብቱ አማካኝነት ‹‹The Eritrean Question›› በሚል ተተርጉሞ ለሕትመት ዝግጁ መሆኑም ይነገራል። አምባሳደር ዘውዴ ረታ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› ስለተሰኘው መጽሐፋቸው በአንድ ወቅት ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር።
‹‹ … በኤርትራ ጉዳይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ እውቀትና መረጃ የነበራቸው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሐብተወልድ ስለኤርትራ ጉዳይ ያስጠኑኝ ታሪክ በጣም ብዙ ነው። ከዚህም በተጨማሪም ቢትወደድ አስፍሓንም አውቃቸው ነበር።
እርሳቸው ደግሞ የኤርትራ ዋና አስተዳዳሪ (Chief Executive)ና በኤርትራም በጣም የታወቁ ሰው ስለነበሩ ብዙ መረጃዎችን ነግረውኛል። ‹ዘውዴ! አንተ ትፅፋለህ ብዬ አምናለሁ፤አማርኛህንም እወደዋለሁ … ስለፌዴሬሽኑ አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልፁ መረጃዎችን ሰጥቼሃለሁ …›› ብለው በራሳቸው ጽሑፍ የተፃፉ ብዙ መረጃዎችን ሰጥተውኛል።
ይህን ሁሉ መረጃ ከሰበሰብኩ በኋላ ስለፌዴሬሽኑ አጠቃላይ ሁኔታ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ የሚጠቅም ነው ብዬ በማሰብ መጽሐፉን ለመጻፍ ተነሳሁ … እኔ ቀደም ሲል ‹ታሪክ ብጽፍም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት ታሪክ ብቻ ነው የምጽፈው› ብዬ አስቤ የነበረ ቢሆንም ስለኤርትራ ጉዳይ ያስተማሩኝና መረጃ የሰጡኝ ሰዎች ‹ለኤርትራ ጉዳይ የተደረገው ሙግት በጣም ብዙ ስለሆነ የኤርትራን ጉዳይ ነጥለህ አውጣና ለብቻው ጻፈው› በማለት ነገሩኝ … እንደነገሩኝም የኤርትራ ጉዳይ ራሱን የቻለ ታሪክ/መጽሐፍ ወጣው›› ከዚህ በተጨማሪም መጽሐፉ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረውን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጉዳይ ብቻ እንጂ ኤርትራና ኤርትራውያን አሁን ስላሉበት ሁኔታ የሚመለከት እንዳልሆነ አምባሳደር ዘውዴ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ጠቁመዋል።
አምባሳደር ዘውዴ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› ከሚለው መጽሐፋቸው በመቀጠል የፃፉት ‹‹ተፈሪ መኮንን›› የሚለውን መጽሐፍ ነው። ይህን መጽሐፍ ለመፃፍ ምክንያታቸው ምን እንደነበር ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል። ‹‹ … እኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያቀድኩት ስለ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ለመፃፍ ነበር። ስለኤርትራ ጉዳይ የሚያብራራውን መጽሐፍ ጽፌ ከጨረስኩ በኋላ ስለ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ለመፃፍ ስዘጋጅ ሌላ ነገር ተፈጠረ።
ሕዝቡ ስለቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት ታሪክ በትክክል መረዳት የሚችለው ‹ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ማን ናቸው? በምን አኳኋን ነጉሠ ነገሥት ለመሆን በቁ?› የሚለውን ጉዳይ በሚገባ ማወቅና መረዳት ሲችልና ከተወለዱበት እስከነገሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን የጀርባ ታሪክ መታወቅ ስላለበት ታሪካቸውን ለመፃፍ ተነሳሁ።
በርካታ ጥናቶችን ሳደርግ ቆይቼ መጽሐፉን መጻፍ ቻልኩ። እኔም እንደአቅሜ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ውስጥ ቦታ ከነበራቸው ሰዎች መካከል አንዱ ስለነበርኩ ነገሮችን በቅርበት የመከታተል እድል ነበረኝ።›› መጽሐፉ ከተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) ታሪክ (ከ1884-1922 ዓ.ም) ባሻገር በጊዜው የነበረችውን ኢትዮጵያንና ቤተ-መንግሥታዊ ፖለቲካዋን የሚያስቃኝ፤ ሲሆን ታሪኩ የቀረበበት የትረካ ስልትም ማራኪና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆን ችሏል።
የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ሦስተኛውና በ2005 ዓ.ም የታተመው ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት›› መጽሐፍ ከ1923 ዓ.ም እስከ 1948 ዓ.ም ድረስ የነበረውን የንጉሠ ነገሥት መንግሥት አስተዳደር በስፋት የሚቃኝ ነው። መጽሐፉን ለመፃፍ የሚያስችሉ ጥናቶችን ያካሄዱት ከብዙ ዓመታት በፊት እንደነበርና መጽሐፉ የስድስት ዓመታት ዝግጅትን እንደፈጀ አምባሳደር ዘውዴ ተናግረዋል።
ምንም እንኳ የዚህ መጽሐፍ ርዕስ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር ቢገናኝም የመጽሐፉ ሰፊ ይዘት ግን በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው። መጽሐፉ ከልብ ወለድና ከአፈ ታሪክ ነፃ ስለመሆኑ በመግቢያው ላይ የጠቀሱት አምባሳደር ዘውዴ፣ ‹‹ስራ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ የቆየሁባቸው የሥራ ቦታዎች የታሪክ ቦታዎች ነበሩ።
ጠይቆ ለመረዳትም ሆነ ለማዳመጥም ብዙ እድሎችን አግኝቻለሁ። ከብዙ ታላላቅ ሰዎችና እኔም ፈልጌ ያገኘኋቸውን መረጃዎች አጠናቅሬ ነው የፃፍኩት። የመረጃዎቹ ምንጮች ብዙ ናቸው›› ብለዋል። የመጽሐፋቸውን የተለየ ፋይዳም እንዲህ በማለት ገልጸውታል። ‹‹ … እንግዲህ ማንም ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ኢትዮጵያ የነፃነት ችግር ያጋጠማት በሁለት ኮሎኒያሊስት በሆኑ አገሮች ነው።
የመጀመሪያው የፋሽስቱ የሙሶሊኒ የግፍ ወረራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ነፃ አውጪዎች ነን ብለው በመጡት ወዳጆቻችን በምንላቸው በእንግሊዞች ወታደራዊ የሞግዚት አስተዳደር የተፈጸመብን በደል ነው። ከእነዚህ ከሁለቱም ኮሎኒያሊስቶች የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስመለስ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የደረሰበት መከራና ፈተና በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
ይህን ሁሉ በተለይ አዲሱ ትውልድ እንዲያውቀው ስለሚያስፈልግ፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ታሪኩ በተቻለ መጠን ተዘርዝሮ ቀርቦለታል።›› አምባሳደር ዘውዴ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ቅርበት እንደነበራቸው የሚያውቁ የታሪክ ምሁራንም ስለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት የሚያብራራ የታሪክ መጽሐፍ እንዲጽፉ እስከመጠየቅ ደርሰዋል።
ለአብነት ያህልም አንጋፋው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደአረጋይ ‹‹… ዘውዴ! ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ከሆነው ትውልድ መካከል እንደ አንተ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት አመራር በቅርብ የማየትና የመረዳት ዕድል ያገኘ ብዙ ሰው የለም። ቀጥሎ ደግሞ ያየውንና የተረዳውን፣ ጣዕም ባለው ጽሑፍ አብራርቶ ለመግለጽ ተሰጥኦ ያለው እንደ አንተ የመሰለ ጸሐፊ ብዙ የለም።
ስለዚህ በእኔ አመለካከት ሁለት የተጣመሩ ዕድሎች በአንተ እጅ ተይዘው ይገኛሉ። እነዚህም ታሪኩን የማወቅና የጽሕፈት ችሎታህ ናቸው። ስለዚህ እኔ አጥብቄ አደራ የምልህ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ጉዳይ አንተ ዕድል አጋጥሞህ ያየኸውንና ከአዋቂዎች ዘንድ ቀርበህ ያጠናኸውን እውነተኛውን ታሪክ ገልጠህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጻፍለት።
ለዚህ ሕዝብ ከአንተ በኩል ከዚህ የበለጠ የምታደርግለት ሊኖር አይችልም። አንተም አስበህ የጀመርከውን ለመፈጸም እግዚአብሔር ይርዳህ። … እኛም ወዳጆችህ፣ ዕድሜና ጤና አግኝተን የምትደክምበትን ለማንበብ ያብቃን…›› በማለት ጥያቄም ልመናም ጭምር አቅርበውላቸው ነበር። ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት›› መጽሐፍ በ2005 ዓ.ም ታትሞ የነፕሮፌሰር መርዕድ ጥያቄም ምላሽ ለማግኘት በቃ። ሞት ቀደማቸው እንጂ አምባሳደር ዘውዴ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት›› መጽሐፍን ሁለተኛ ክፍል እያዘጋጁ ነበር።
‹‹ይህ የመጨረሻዬ አይደለም። ቀጣይ ክፍል አለው፤ጀምሬዋለሁ። በመጀመሪያው መጽሐፍ ውስጥ የተዳሰሱት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት ናቸው … የሚቀጥለው መጽሐፍ ከ1948 ዓ.ም በኋላ ያለው ታሪክ ይቀርብበታል›› በማለት ተናግረው ነበር።
የአምባሳደር ዘውዴን መጻሕፍት ያነበቡ አንጋፋ ምሁራንም ስለመጽሐፎቻቸው ፋይዳ፣ ስለአፃፃፋቸው ስልትና ስለማስረጃዎቹ ጥንካሬ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ‹‹ … አምባሳደር ዘውዴ ረታ ለአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት በነበረው ቀረቤታና በተለይም ለኤርትራ ጉዳይ የታሪኩን ሁለት ዓበይት ተዋንያን፣ ማለትም የአክሊሉ ሐብተወልድንና የኣስፍሓ ወልደሚካኤልን አመኔታ በማግኘቱ አያሌ ብርቅ የሆኑ ሰነዶች ለጥናቱ ድምቀትና ጥልቀት ሊሰጡት ችለዋል። በዚህም አማካኝነት በትውልዶች መካከል ተፈጥሮ የቆየውን የእውቀትና የልምድ ክፍተት ለመድፈን ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል።
አምባሳደር ዘውዴ ከፍተኛ የታሪክ ስልጠና ሳያገኝ የተካነበትን የጋዜጠኝነት ሙያ በመመርኮዝ ታሪካዊ ሁኔታዎችን ተረድቶ በሚጥም ቋንቋ ትልቅ ገፀበረከት ስላቀረበልን እናመሰግነዋለን።›› ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹‹ … አምባሳደር ዘውዴ ረታ ያሳተሙት ‹የኤርትራ ጉዳይ› የተባለው መጽሐፍ በኛ የታሪክ ተመራማሪዎችና መምህራን በኩል እስካሁን ሙሉ በሙሉ ያላየናቸውንና ያልደረስንባቸውን ቀጥተኛ መረጃዎች ለብዙ ዓመታት በክብር ጠብቀው በማጥናትና በማመሳከር አዲስ የተጣራ ዘገባ ስላቀረቡልን ደራሲውን በሕዝብ ፊት እናመሰግናለን።›› ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት የታሪክ ፀሐፊ፣ አርታኢና ሃያሲ አቶ ብርሃኑ ደቦጭ አምባሳደር ዘውዴ «ተገቢውን ምንጭ በመጠቀም ሕዝባዊ ታሪክ የሚጽፉና በሥራዎቻቸው ወደፊትም ምሳሌ የሚሆኑ ባለሙያ» ሲሉ ገልፀዋቸዋል።
አቶ ብርሃኑ «የኤርትራ ጉዳይ» የተሰኘው የአምባሳደር ዘውዴ መጽሐፍ በኢትዮጵያና ኤርትራ የፖለቲካ ታሪክ ጉልህ ጠቀሜታ ካላቸው የታሪክ መዛግብት መካከል አንዱ መሆኑንም መስክረዋል።
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በፀባያቸውም ትሁት፤ ‹‹ይህን ሠርቻለሁ›› ብለው ‹‹ልታይ፣ ልታይ›› የማይሉ ሰው እንደነበሩ የሪያውቋቸው ወዳጆቻቸው ይናገራሉ። በጋዜጠኝነት፣ በዲፕሎማትነትና በታሪክ ጸሐፊነት ላበረከቷቸው አስተዋፅዖዎች የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
የምኒልክ የመኮንን ደረጃና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አዛዥ መኮንን ኒሻን ሽልማትን ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት፤ ከ22 የአፍሪካ፣ አውሮፓና እስያ አገራት ደግሞ የታላቅ መኮንን ደረጃ ኒሻን ሽልማቶችን ተሸልመዋል።
የ2006 ‹‹የበጐ ሰው ሽልማት›› ተሸላሚም ነበሩ። ከሕልፈታቸው ቀደም ብሎ በነበሩት ጥቂት ዓመታት በውጭ አገራት በመዘዋወር ስለመጽሐፎቻቸውና ስለታሪክ ማብራሪያ በሰጡባቸው ጊዜያትም ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የ2007 ዓ.ም የ‹‹ንባብ ለሕይወት›› የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ እና የኪነጥበባት ዝግጅት የወርቅ ብዕር ተሸላሚም ሆነዋል። አምባሳደር ዘውዴ ረታ በ1959 ዓ.ም ከወይዘሮ ገሊላ ተፈራ ጋር ጋብቻ መስርተው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።
ለ‹‹ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት›› መጽሐፍ ሁለተኛ ክፍል ግብዓት የሚሆኑ ተጨማሪ ሰነዶችን ለማጥናት ወደ እንግሊዝ በሄዱበት አጋጣሚ መስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ለንደን ከተማ ውስጥ በድንገት አርፈዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 /2014