18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሰርቢያ ቤልግሬድ ከተማ አስተናጋጅነት ከነገ በስቲያ ይጀመራል።
ለተከታታይ ሦስት ቀናት የዓለማችንን ከዋክብት አትሌቶች በመካከለኛና አጭር ርቀት ውድድሮች እንዲሁም የሜዳ ተግባራት ውድድሮች በሚያፋልመው በዚህ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለድል የሚጠበቁ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ምሽት በቤልቪው ሆቴል አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።
ኢትዮጵያ ለ17ኛ ጊዜ በምትሳተፍበት የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ወደ ቤልግሬድ የሚያቀናው ልዑካን ቡድን በተደረገለት የሽኝት መርሐግብር ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መሥፍን ቸርነት ተገኝተው ቡድኑን በማበረታታት መልካም ውጤት እንዲገጥመው ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የሥራ አስፈፃሚና የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሽኝት መርሐግብሩ የተገኙ ሲሆን ኮማንደር ደራርቱ ቱሉና አምባሳደር መሥፍን ቸርነት በየተራ ባደረጉት ንግግር ለልዑካን ቡድኑ አባላት የሥራ መመሪያና የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሰልጣኞችና የአትሌቶች ተወካዮችም ስለ ዝግጅታቸው አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ የሰንደቅ ዓላማ ርክክብም ተደርጎላቸዋል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቻምፒዮናው በሁለቱም ጾታ በሦስት የተለያዩ ርቀቶች(በ8መቶ ሜትር፣ 1500 ሜትርና 3ሺ ሜትር) ይሳተፋሉ።
በ8መቶ ሜትር ሴቶች ባለፈው አመት በዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈችው አትሌት ሃብታም አለሙ በዚህ የዓለም ቻምፒዮና በቀጥታ የመሳተፍ ዕድል ያገኘች ሲሆን፣ በዘንድሮው አመት ተመሳሳይ የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች አስደናቂ ፉክክር እያደረጉ የሚገኙት ፍሬወይኒ ኃይሉና ትእግስት ግርማ በተመሳሳይ ርቀት ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው።
በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት ግን ከስኬታማው አትሌት መሐመድ አማን ወዲህ ኢትዮጵያን በርቀቱ የሚወክል አትሌት አልተገኘም።
በወንዶች 1500 ሜትር ግን ሁለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቻምፒዮናው ተሳታፊ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው ውጤት ታስመዘግብበታለች ተብሎ ከሚጠበቁ ርቀቶች አንዱ ነው።
በዚህ ርቀት የቀድሞው የርቀቱ የዓለም ባለክብረወሰን የነበረው አትሌት ሳሙኤል ተፈራና ታደሰ ለሚ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ይሆናል። በተመሳሳይ ርቀት በሴቶች ባለፈው አመት የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች አጠቃላይ አሸናፊ የሆነችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በቀጥታ ተሳታፊ መሆኗን አረጋግጣለች።
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የአምስት ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ጉዳፍ ባለፉት አምስት ሳምንታት ባደረገቻቸው የተለያዩ የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ከማሸነፏም በላይ ፈጣን ሰዓቶችን ማስመዝገብ ችላለች። የርቀቱ የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት መሆኗም በቤልግሬዱ ቻምፒዮና ለወርቅ ሜዳሊያ እንድትጠበቅ አድርጓታል።
ጉዳፍ አስደናቂ ብቃት ባሳየችባቸው ያለፉት ሳምንታት ውድድሮች ድል ባይቀናቸውም ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ተከታትለው ውድድራቸውን ሲጨርሱ የነበሩት አክሱማይት አምባዬና ሂሩት መሸሻ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በዚህ ቻምፒዮና ምናልባትም ሦስቱንም ሜዳሊያዎች ጠራርጋ እንደምትወስድ ተስፋ የተደረገበት ርቀት የወንዶች ሦስት ሺ ሜትር ነው። በዚህ ርቀት የቶኪዮ ኦሊምፒክ የአስር ሺ ሜትር ቻምፒዮኑ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ባለፈው አመት የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች አጠቃላይ አሸናፊ በመሆኑ በቤልግሬዱ ቻምፒዮና በቀጥታ የመሳተፍ ዕድል አግኝቷል።
ከሰለሞን በተጨማሪ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ለሜቻ ግርማ እንዲሁም በድንቅ ብቃት ላይ የሚገኘውና የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የዓለም ክብረወሰንን የጨበጠው በሪሁ አረጋዊ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ሰለሞን ባረጋና ለሜቻ ግርማ ባለፉት አምስት ሳምንታት በቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች አስደናቂ ፉክክር ያሳዩ አትሌቶች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ሁለት ውድድሮችን ለሜቻ በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ ሰለሞን አንዱን ውድድር ማሸነፉ አይዘነጋም።
በተመሳሳይ ርቀት በሴቶች ለምለም ኃይሉ በባለፈው አመት ስኬቷ ቀጥታ ተሳታፊ ስትሆን አስደናቂ ብቃት ላይ የሚገኙት ዳዊት ስዩምና እጅጋየሁ ታዬ ኢትዮጵያን ወክለው ተጨማሪ ሜዳሊያዎች እንደሚያስመዘግቡ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 /2014