አሁን ላይ የሚስተዋለው የኑሮ ውድነት በአመዛኙ ሰው ሰራሽ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለዚህም የንግዱ ዘርፍ በብልሹ አሰራር የተተበተበና ሥር የሰደደ አደገኛ የኢኮኖሚ ሴራ የሚተወንበት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል ።
በደሃ ሸማች ጉሮሮ ላይ ቆመው መክበር የሚፈልጉ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች በእሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ጭካኔ በተሞላበት ስግብግብነት ምርት ደብቀው በሚፈጥሩት ትርምስ ሸማቹን ግራ ሲያጋቡና ሲያስጨንቁ መመልከት የተለመደ ሆኗል።
እርግጥ ነው በአገሪቱ ያለው የንግድ ስርዓት በዕውቀትና በስርዓት የሚመራ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ በንግዱ ዘርፍ በየጊዜው በርካታ ችግሮች ሲፈጠሩ ይስተዋላል። የችግሩ ተጋላጮችም በዋናነት ሸማቾች ቢሆኑም ጤናማ የንግድ ስርዓትን ተከትለው በሚነግዱት ላይም ይታያል። ከእነዚህ መካከልም በከተማዋ የሚገኙ ነጋዴ ሴቶች ይጠቀሳሉ። ሴቶች በአመዛኙ በህግ አግባብ የሚሰሩና ጤናማ የንግድ ስርዓትን የሚከተሉ ስለመሆናቸው ይነገራል።
በንግድ ሂደት ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ሴቶች ታድያ በዘርፉ በርካታ ተግዳሮቶች ሲገጥማቸው ይታያል። እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍም የሚመለከታቸው አካላት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ነው።
ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አንዱ ሲሆን፤ ሴቶች ሁለንተናዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ ከመስራት ባለፈ በተለይም በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተው ያሉ ሴቶችን በመደገፍ እየሰራ ስለመሆኑ በአዲስ አበባ ሴቶች ህጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አራጋው ይናገራሉ።
በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴ ሴቶችን ለማገዝና ለመደገፍ ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል ከንግዱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ለአብነትም የገቢዎች ቢሮ፣ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንና ሌሎችም ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት በተገኙበት ነጋዴ ሴቶች ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች ዳሰሳዊ ጥናት ማድረግ አንዱ ነው።
በጥናቱም ችግሮቹን መለየት እንደቻሉና በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር ባላቸው አጋርነት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠትና ስትራቴጂያዊ ለውጦችን ለማምጣት እየሠሩ ይገኛሉ።
ቢሮው በዝቅተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ የንግድ ዘርፍ ውስጥ ተሰማርተው ከሚነግዱ ሴቶች ጋር በጋራ በመሆን ነጋዴ ሴቶች በንግዱ ዘርፍ የሚያጋጥማቸውን የአሰራር፣ የመመሪያ፣ የአፈጻጸምና ሌሎች ችግሮችን በመለየት መፍትሔ የማፈላለግ ሥራ ይሠራል ያሉት ኃላፊዋ፤ ሴቶች እንደማንኛውም በንግዱ ዘርፍ እንደተሰማሩ አካላት ከብልሹ አሰራርና ከሌብነት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች ወንድ ነጋዴዎች ከሚገጥማቸው ችግር በበለጠ ሴቶች ላይ ይበረታል። ለዚህም ሴቶች በርካታ ማህበራዊ ጫናዎች ያሉባቸው የስርዓተ ጾታ መዛባቱ በምክንያትነት ይጠቀሳል።
ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ሴቶችን መደገፍ ውጤታማ ማድረግ አገርን ማሳደግ በመሆኑ በተለይም ግንዛቤ የሌላቸው ሴቶች ላይ መብቶቻቸውን ከማክበር አንጻር የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ሴቶች መብቶቻቸው እንዲከበር ይደረጋል። የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የበላይነት ዛሬም ለውጦች እየታዩ እንደሆነ ያነሱት ኃላፊዋ፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ከጥቃቅን ንግድ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ንግድ ሴቶች እንዲሰማሩ፤ በማህበራት ነጋዴ ሴቶች ተደራጅተው መብቶቻቸውን እንዲያስከብሩና በርካታ ሴቶች ወደ ንግዱ እንዲገቡ ተደርጓል። በአብዛኛው ንግድ ተብሎ ሲታሰብ በአቋራጭ መክበርና የማጭበርበር በመሆኑ ብዙ ጊዜ ወንዶች ተሳታፊ ሲሆኑ ይታያል።
ነገር ግን ሴቶች በአቋራጭ የሚኬድበትን መንገድ የማይደፍሩና ወደ ኋላ የሚሉ በመሆናቸው ምክንያት በንግዱ ዘርፍም የተሰማሩ ሴቶች የሚገጥማቸው ችግር ስለመኖሩም አስረድተዋል።
ከአሰራር ጀምሮ በትናንሽና በጉሊት ንግድ የሚተዳደሩ ነጋዴ ሴቶች የሚገጥማቸውን መሰል ችግሮች ለመፍታትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ገና ብዙ የሚቀር ሥራ ስለመኖሩም ኃላፊዋ አንስተዋል። ሁሉም ሰው ከለፋና በህግ አግባብ ከሰራ የልፋቱን ማግኘት እንደሚችል በመግለጽ ሴቶች ንግዱን ማሳለጥ አይችሉም።
ወንዶች ቢሆኑ ንግድን ማቀላጠፍ ይችላሉ የሚል የተዛባ አመለካከት ስለመኖሩ ጠቁመው እንዲህ አይነት አመለካከቶችም ሴቶች በንግዱ ዘርፍ ስኬታማ እንዳይሆኑ ከማድረግ ባለፈ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያደርስ መሆኑን በመግለጽ በአሁኑ ወቅት ሴቶች ወደ ንግድ ተሳትፎ መምጣታቸው ትልቅ ነገር ቢሆንም መንግሥት በተለያዩ የሥራ ዕድሎች ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አመላክተዋል። በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ካሉት ግብር ከፋዮች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሴት ግብር ከፋዮች በመሆናቸው እነዚህ ሴት ግብር ከፋዮች ላይ መስራት ለገቢ ዕድገት ወሳኝ ነው የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሴቶችና ህጻናት ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ወይንሸት ጸጋዬ ናቸው።
በተለይም ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ በአገልግሎት አሰጣጥና ብልሹ አሰራሮችን ከመታገል አንጻር ከሴቶች ጋር መሥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውና ሚናቸው የጎላ በመሆኑ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከዋናው ቢሮ በተጨማሪ በስሩ 16 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹም ለሴቶች ብቻ የሚሆኑ የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ሴቶች ላይ በመሥራት ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል አምኖ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት ።
በቀጣይ ከሚዘጋጁ ፕሮግራሞችም በሚገኘው ግብዓት ከሴት ግብር ከፋዮች ጋር የሚሰራው ሥራ በተለይም በገቢ አሰባሰቡ ላይ የጎላ ሚና የሚጫወት ይሆናል ብለዋል።
በንግዱ ዘርፍ በተሰማሩ ሴቶች ላይ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። በተለይም ከመረጃ ጋር ተያይዞ ሰፊ ክተት አለ ይላሉ። ለአብነትም ነጋዴ ሴቶች ለታክስ ስርዓቱ ያላቸው ግንዛቤ እጅግ በጣም አናሳ ሲሆን በዚህም ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣሉ።
ለአብነትም ምን ያህል ግብር እንዳለባቸው፣ መቼ መክፈል እንዳለባቸውና የት ሄደው መክፈል እንደሚገባቸው አለማወቅ ማለት ጊዜው አልፎ ለቅጣትና ለወለድ ይዳረጋሉ። በግብር አከፋፈልና አወሳሰን ስርዓቱም ቢሆን ችግር ካለ መብቶቻቸውን የት ሄደው መጠየቅ እንዳለባቸውና
እስከምን ድረስ ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚገባቸው አጠቃላይ በተቋሙ ውስጥ ስላለው አሰራር የታክስ ህጎችና ደንቦች አዋጆችና መመሪያዎች ላይም ሴቶች ያላቸው ግንዛቤ እጅግ አናሳ ነው።
በመሆኑም ይህን ችግር ለይቶ ኃላፊነት በመውሰድ ቢሮው የራሱን ድርሻ ለመወጣት የተለያዩ የስልጠና እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀት ያለበት መሆኑን ጠቁመው ሴቶችም ወደ ንግድ ስርዓቱ ሲገቡና በንግድ ስርዓቱ ውስጥ ባሉበት ሂደት የራሳቸውን አቅም መገንባት ያለባቸው መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ መብትና ግዴታን ለማወቅ መረጃ ማግኘት አስፈላጊ እንደሆነና ይህንንም ለማረጋገጥ የላቀ አገልግሎት በመስጠት የተመቻቸ የሥራ አካባቢ መፍጠር ይገባልም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው፤ ሴቶች በንግዱ ዘርፍ የሚጋጥሟቸው ችግሮች ምን እንደሆኑና መፍትሔዎቻቸው ምን መሆን እንዳለበት፤ እንዲሁም መንግሥት ለሴቶች ያደረገው ድጋፍ ምን ያህል ነው በሚል በንግዱ ዘርፍ በተሰማሩ ሴቶች ላይ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ ለማውጣት መድረክ አዘጋጅተው እንደሚወያዩ ይገልጻሉ። ከትንሽ ተነስታ ትልቅ ደረጃ የሚደርሱ በርካታ ነጋዴ ሴቶች በመኖራቸው እነዚህን ሴቶች በማገዝ በመደገፍ ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ሴቶች በሚመሩት የንግድ ሥራ ለአገር ኢኮኖሚ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የጎላ ድርሻ አላቸው።
ስለዚህ ሴት ነጋዴዎችን የማበረታታት ሥራ በስፋት መሥራት ያስፈልጋል። በመሆኑም መንግሥት የማበረታታቱን ሥራ ሲጨምር አገር ጥሩ ደረጃ ላይ ትደርሳለች፡ በተለይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በጋራ መሥራት በርካታ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል በማለት ለአብነትም ከገቢዎችና ጉምሩክ ንግድ ቢሮ ከመሳሰሉት ጋር በመስራት ሴቶች ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ያስችላል።
ከአስመጪው ጀምሮ ታች እስካሉት ጉልት ነጋዴዎች ድረስ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በንግዱ የተሳተፉ ሴቶችን በማገዝ አገርን ማልማት ይቻላል ብለዋል። እንደ ነጋዴ ማህበር የንግዱ ማህበረሰብና መንግሥትን በማገናኘት ከታች የሚመጡትን ጥያቄዎች ወደ ላይ ከላይ የሚመጡትንም ወደ ታች በማውረድ እንዲተገበር ማስቻልና ማስታረቅ የማህበሩ ዋና ሥራ መሆኑን በመግለጽ፤ ከመንግሥት በኩል ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን እየተሰራ ነው።
ከዚህ ቀደም በንግዱ ዘርፍ ይታዩ የነበሩ በርካታና ሰፋፊ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የንግዱ ማህበረሰብና መንግሥት ተቀራርበው ለውጦች እየመጡ ያለ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ፤ ይህም የሆነው በርካታ ሴት አመራሮች ወደ ኃላፊነት ቦታ በመምጣታቸው እንደሆነ አመላክተዋል።
ወደፊት መምጣት እየቻሉ ወደ ኋላ የሚቀሩ ሴቶችን በመደገፍ በማበረታታት ወደፊት መምጣት እንዲችሉ ማህበሩ እየሰራ ሲሆን በተለይም የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶችና መነሻ ምክንያታቸውን በማዳመጥ መፍትሔ ማምጣት እንዲቻልም ችግሮቹን ለሚመለከተው አካል የማቅረብ ሥራዎች እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።
ይሁን እንጂ በርካታ ሥራ መሥራት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም በኢንተርፕራይዝ ደረጃ የሚሰሩ ሴት ነጋዴዎች ከመንግሥት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት መንግሥት የራሱ የሆነ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ሲሆን በግል ተነሳስተው የሚሰሩ ሴቶች ደግሞ በማህበሩ ስር ሆነው ማህበሩ መብታቸውን የማስጠበቅና ግዴታቸውን የማስቻል ሥራ እየሠራ ይገኛል። ‹‹ሴቶች በተፈጥሯቸው ታማኝና ጠንቃቃ በመሆናቸው እምነት ከተሰጣቸው ታማኞች ናቸው።
በመሆኑም ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ህጋዊ ሆነው መስራት ይፈልጋሉ›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ህጋዊ ሆነው ሲሰሩ ደግሞ ህገወጥ የሆኑ ነጋዴዎች ተመሳሳይ ዕቃ በራቸው ላይ አድርገው በመሸጣቸው ተጎጂ መሆናቸውን ጠቁመው ህገወጥ ነጋዴዎች በህግ አግባብ እንዲሄዱ የሚያስችል አመራር ያስፈልጋል ስለዚህ በህገወጥ መንገድ የሚገዳደራቸውን ህገወጥ ነጋዴ መንግሥት በህግ አግባብ ሊያስተካክል ይገባል። ከመንግሥት በተጨማሪም ማህበሩ ህጋዊ ሆነው መስራት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 /2014