• ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣዩን ምርጫ አስመልክቶ ማሳሰቢያ ሰጡ
አዲስ አበባ፡- በፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም በተናጥል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ስርዓት የቃል ኪዳን ሰነድ በ107 ፓርቲዎች ተፈረመ።
ኢህአዴግን በመወከል ፊርማቸውን ያኖሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ በስነስርዓቱ ላይ ለኢህአዴግ አባላት፣ ለመገናኛ ብዙሃን፣ ለፓርቲዎችና ለመላው ኢትዮጵያውያን ቀጣዩን ምርጫ አስመልክቶ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። መጪው ብሔራዊ እና አካባቢያዊ ምርጫ ነፃ እና ፍትሐዊ እንዲሆን በሚደረገው ዝግጅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ተሳትፎና ሚና ማጎልበትን ዓላማ በመያዝ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት የተዘጋጀው የቃል ኪዳን ሰነድ ትናንት በምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት በሂልተን ሆቴል ኢህአዴግን ጨምሮ 107 ፓርቲዎች ፈርመውታል።
ሰነዱ 20 አንቀፆችን የያዘ ሲሆን፤ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በማናቸውም መልኩ ከሚገለፁ የሐይል አሠራሮች፣ ከሁከትና ከአመፅ ድርጊቶች የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው አስቀ ምጧል። ሐይል የመጠቀም ስልጣን የመንግሥት ብቻ መሆኑንና ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አመራር፣ አባል ወይም ደጋፊ በምንም ሁኔታ ህግን በማስፈፀም ተግባር ውስጥ ከራስ ወይም ከሦስተኛ ወገን ጋር በሚኖረው ግንኙነት የራሱን ጥቅም በፍትህ ስም ለማስፈፀም እንደማይችልም ሰነዱ ያመለክታል። ሰነዱ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ሂደት የሌሎች አካላትን መብት ስለማስከበር፣ የስብሰባዎች ህዝባዊ ሰልፎችና የሌሎች ሁኔታዎችን አፈፃፀም ያካተተ ሲሆን፤ ፓርቲዎቹ ይህ ሰነድ በነፃ ፈቃዳቸው የተዘጋጀ መሆኑን አምነውበት በተወካዮቻቸው አማካኝነት ፊርማቸውን አኑረዋል።
የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርን በመወከል ሰነዱን የፈረሙት አቶ ሃሰን አብዱላሂ በሰጡት አስተያየት ሰነዱ የህግ የበላይነትን ለማስፈን፣ የመቻቻል ባህልን ለማዳበር፣ ለውጡን ለማስቀጠል እንደሚረዳና የሚታየውን ያለመረጋጋት ለመፍታት እንደሚያግዝ አመልክተው ተግባራዊ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። አርበኞች ግንቦት ሰባትን የወከሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ሰነዱ የሰላም በመሆኑ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶችን እንደሚቀበል አስታውሰው፤ ህዝቡ ያሉትን አማራጮች በማንኛውም ቦታ ማሰማት እንዲችል ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። አያይዘውም ፓርቲያቸው በሙሉ ልቡ የቃል ኪዳኑን ሰነዱን እንደሚቀበልና ለአባላቶቹም ስልጠና እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክን የወከሉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ሰነዱ ካለፉት ጊዜያት የተለየ በመሆኑ ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም ፓርቲዎች ይተገብሩታል ብለው በማመን መፈረማቸውን ጠቁመዋል። ነገር ግን በፓርቲዎች መካከል ያልተመጣጠነ የፋይናንስ አቅም በመኖሩ ይህን አስመልክቶም መላ ሊደረግለት እንደሚገባ አመልክተዋል። አረናን የወከሉት አቶ አብረሃ ደስታ፤ ፓርቲያቸው ሰነዱን መሰረት አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ተናግረው የህጉ አተገባበር በሁሉም ክልል አንድ ዓይነት መሆን እንዳለበት፤ ፉክክሩም ሰላማዊ እንዲሆን እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።
የአማራ ብሔራዊ ፓርቲ (አብን)ን የወከሉት አቶ በለጠ ሞላ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ህገ መንግሥቱን ጨምሮ የማይቀበላቸው ህጎች ቢኖሩም፤ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ እንታገላለን በማለት ሰነዱን መፈረማቸውን ገልጸዋል። ኦነግን የወከሉት አቶ ቀጀላ ረጋሳ የቃልኪዳን ሰነዱን ለማክበር ፈቃደኛ ሆነው መፈረማቸውን አረጋግጠው፤ ለተቀራራቢ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ‹‹ተቀራርበን እንሥራ›› የሚል ጥሪ አቅርበዋል።
በፊርማው ሥነስርዓት ላይ ተገኝተው የኢትዮጵያ ህዝች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢህአዴግ) በመወከል ፊርማቸውን ያኖሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ፤ ኢህአዴግ የቃል ኪዳን ሰነዱን ሙሉ ለሙሉ ያመነበት መሆኑን ገልጸው የኢህአዴግ ፍላጎት ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ማምጣት እንጂ ለዘመናት ሥልጣን ላይ መቀመጥ አለመሆኑን እያንዳንዱ አባል ሊገነዘብ እንደሚገባ፤ ‹‹ቃልኪዳኑን ከፈረሙት ፓርቲዎች መካከልም አንዱ ቢያሸንፍ ኢህአዴግ ተፎካካሪ ሆኖ የመቀጠል ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
የኢህአዴግ አባላት በሙሉ «በእናንተ፣ ቀበሌ ወረዳም ሆነ ክልል የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሰው ሃሳቡን ለማራመድ፤ ከደጋፊዎቹ ጋር ለመወያየት ሲፈልግ ከቻላችሁ መደገፍ ካልሆነም አለማደናቀፍ ከእናንተ ይጠበቃል›› ብለዋል። የመንግሥት የፀጥታ አካላት የሆኑት የፖሊስም ሆነ የመከላከያ አባላት የማንም ፓርቲ ተወካይ ሳይሆኑ ማንኛውም ፓርቲ በሄደበት ክልልም ሆነ ወረዳ ካለምንም ችግር ሃሳቡን በነፃነት እንዲያራምድ ጥበቃ ከማድረግ ውጪ ‹‹የመንግሥት ልዩ ጠበቆች ነን›› በሚል ማንኛውንም ሥራ መሥራት እንደሌለባቸው በማስታወስ፤ ለህግ ብቻ እንዲታገለግሉ አደራ አዘል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
በመንግሥት እና በህዝብ ገንዘብ የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም መድረክ የሚያራምዱትን ሃሳብ ከኢህአዴግ እኩል ማስተናገድ የሞያ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ግዴታ መሆኑን አውቀው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አደራ በማለት መገናኛ ብዙሃኑ ኢትዮጵያውያኑን ለሚያባሉ ቦታ እንደሌላቸው ሁሉ፤ ይህችን አገር ለሚያገለግሉ እኩል ዕደል በመስጠት «የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን» ሊሆኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የቤት ሥራቸውን በአግባቡ ባለመሥራታቸው ሁሉም ፖለቲከኛ መምሰሉን ያስታወሱት ዶክተር አብይ፤ መምህሩም የማስተማር ሥራውን እንዲሠራ፤ ገበሬውም እርሻውን ፖለቲከኛውም በሙያው ሐላፊነቱን በመወጣት፤ አገሪቷን ወደ ኋላ ከሚመልሳት ተግባር ራሱን እንዲጠብቅና ለጋራ ዕድገት እንዲተጋ አደራ ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋት 6/2011
በምህረት ሞገስ