የዓድዋ ድል መታሰቢያ በመላ ኢትዮጵያ ተከብሯል
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በተገኙበት ፸፪ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ቅዳሜ የካቲት ፳፫ ቀን ፷ ዓ.ም በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ ውሏል።
የዛሬ ፸፪ ዓመት በዓድዋ የተፈጸመውን ታላቅ ድል ምክንያት በማድረግ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ስለበዓሉ ክብር ከጧቱ ፲፪ ሰዓት ከ፵፭ ደቂቃ ላይ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተገኝተው አስቀድሰዋል።
ለበዓሉ ከብር በተደረገው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋው ወሰን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ተገኝተዋል።
የቅዳሴውን ሥነ ሥርዓት የመሩት ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እንደራሴና የሐረር ጠቅላይ ግዛት ሊቀ ጳጳስ ናቸው። ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል የቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ተፈጽሞ ታቦቱ ወጥቶ ዑደት የተደረገው ልዑላን መሳፍንቱ ክቡራን ሚኒስትሮች ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ከፍተኛ የጦርና የፖሊስ መኰንኖች እንዲሁም በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ በተገኘበት ነው። በሥነ ሥርዓቱ ፍጻሜ ላይ ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የበዓሉን ታሪክ በመግለጥ ጸሎተ ቡራኬ ሰጥተው አሳርገዋል። የዛሬ ፸፪ ዓመት በ፲፷፹፰ ዓ/ም አድዋ ላይ ኢትዮጵያ
በጣሊያን ላይ ያገኘቻቸውን ታላቅ ዝነኛ ድል ቅዳሜ የካቲት ፳፫ ቀን ፷ ዓ.ም በመላ ኢትዮጵያ መከበሩን የሚያበሥሩ ፳፩ ጊዜ የመድፍ ጥይቶች ከጧቱ ፲፪ ሰዓት ተተኩሷል።
በነፃነቱ የሚኮራው ፸፪ኛው የዓድዋ ድል ዓውደ ዓመት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያከበረው ሲሆን ፤በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ለበዓሉ ማዝከሪያና ማስታወሻ በተዘጋጀው ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ላይ በዓሉ ታጅቦ አምሮ ደምቆ ተገኝቷል።
(የካቲት 27 1960 ዓ.ም ) አብዮታዊ ሠራዊት በሶማሊያ ላይ ባገኘው ድልአጠቃላይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ሕዝብ ደስታውን ገለጠ
በምሥራቅ ጦር ግንባር የተሰለፈው የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሠራዊት የጅጅጋን ከተማና ካራማራን ከሞቃዲሾ አድኃሪ የጦር ኃይል በማስለቀቅ በጠላት ላይ ድልን በመቀዳጀቱ የአዲስ አበባ የከተማ ነዋሪዎች ማኅበር የተሰማውን አብዮታዊ ደስታ በመግለጽ በየጠረፉ ለሚገኘው መደበኛና ሚሊሺያ ሠራዊት ትናንት መልዕክት አስተላልፏል።
የአዲስ አበባ ሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክት ‹‹ዛሬ አብዮታዊት ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተባብረው ቢነሱባትም ፤በአንተ መደበኛውና ሚሊሺያው ሠራዊት ክንድ እየተደመሰሱ ኢትዮጵያ በመቃብራቸው ላይ እንደምትመሠረት አንጠራጠርም።
ከአብዮት አደባባይ ተነስተህ ትናንት ኢትዮጵያን ማነው የሚደፍራት? በማለት ያለህን የወኔ ስሜት በሠልፍ ትዕይንት ስታሳይ በየመንገዱ ተሰልፎ ፤ ‹‹በቃ ! በቃ! አብዮታዊት ኢትዮጵያ አትደፈርም ›› በማለት አበባ እየበተነ እልልታውን እያቀለጠና በደስታ ስሜት እያነባ ሆ ብሎ የሸኘህ የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ በድል አድራጊነትህ የደስታ ስሜቱን አቅፎ ሊገልጸው ባይችልም ፤በርቀት ልትሰማው በምትችል እልልታ ገልጦታል።
‹‹አሁንም የአዲስ አበባ ሰፊ ሕዝብ ትናንት አብሮህ እንደነበረ ሁሉ ፤ዛሬም ከጦር ሜዳ አልተለየህም ።የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ የእናት አገር ጥሪ በዓል በማዘጋጀት የስንቅ ድጋፍ በማድረግ ከጎንህ ሲቆም አርሰህ ዘርተህ የሄድከውንም ሰብል እንዳይበላሽ በወቅቱ ከሥፍራው በመገኘት አጭዶ በመሰብሰብ ቤተሰብህን እየረዳ ነው። ድሬዳዋ (ኢ.ዜ.አ.) በምሥራቅ ጦር ግንባር የዘመተው መደበኛው መለዮ ለባሽ ፤ሚሊሺያው ሠራዊትና አባላት ጦረኛው የአድኃሪው የሶማሌ ገዥ መደቦች ወራሪ ወታደሮች በማንበርከክና ቅስም በመስበር ፍጹም ስትራቴጂካዊ የሆነውን የካራማራ ኮረብታና የጅጅጋን ከተማ በማስለቀቁ የተሰማውን ደስታ በመግለጽ የድሬዳዋ ከተማና የአካባቢው ሕዝብ ከትናንት በስቲያ ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል።
በከተማው ውስጥ በሚገኘው የኮካኮላ ፋብሪካ አጠገብ በሚገኘው አደባባይ ላይ በተደረገው በዚሁ የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ የ፳፫ ቀበሌ የሴቶችና የወጣቶች የገበሬዎች ማኅበራት አባሎች የመንግሥት ሠራተኞች የማምረቻና ሰበነክ ወዛደሮች የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት አንቂ ጓዶችና ወታደራዊ ካድሬዎች የፖሊስ አባሎች መምህራን ተማሪዎች በጠቅላላው ቁጥሩ ከ፺፭ ሺ የማያንስ ሕዝብ ተካፋይ ሆኗል።
ከጦር ሜዳ ትግሉ ጀርባ በደጀንነት ተሠልፎ ዘማቹ ሠራዊት አብዮታዊውን ጦርነት በአሸናፊነት እንዲወጣ የሞራል የስንቅ እርዳታ የሚያደርገው ይኸው የከተማውና የአካባቢው ሕዝብ በየማኅበሩና በየሙያ ዓርማ ሥር ተሰልፎ ደስታውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በተጓዘበት ወቅት ‹‹አሻግሮ ገዳይ በረሃ ያለውን ጠላቱን ዛሬ አመድ አረገው›› በማለት ወኔን የሚቀሰቅሱ መዝሙሮች ሽለላና ፉከራዎች አሰምቷል።
(የካቲት 29 ቀን 1970 ዓ.ም ) የሴቶች በዓል የአብዮታችን ዓለም አቀፋዊ መልኩ መዳበሩን ይገልጣል (ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ፤በመላው ዓለም ላይ በየሥፍራው ከበዝባዥ መደቦች ጋር የሚታገሉትን ሴቶች ትግል ከትግላችን ጋር ለማቀነባበርና የአብዮታችንም ዓለም አቀፋዊ መልኩ እየዳበረ መራመድን በተጨማሪ ለመግለጽ ያስችለናል ሲሉ ጓድ ሻለቃ እንዳለ ተሰማ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ቋሚ ኰሚቴ አባልና የደርጉ ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ትናንት አስገነዘቡ። ጓድ ሻለቃ እንዳለ ተሰማ ይህንን ያስገነዘቡት ፤በዛሬው ዕለት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ሴቶች ያላቸውን የሙያ ችሎታ የሚያስረዳ በብሔራዊ ቲያትር የተዘጋጀውን የሙያ ኤግዚቢሽን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባሰሙት ንግግር ነው።
ይኸው በአዲስ አበባ ከተማ በየቀበሌው የሚገኙት ሴቶች በየማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅቶች የሚሠሩት ሴት ወዝ አደሮች እንዲሁም የልዩ ልዩ የሶሻሊስት አገሮች በመተባበር ሴቶች በሙያ ችሎታና በምርት ኃይል በኩል የኅብረተሰቡ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን የሚያስረዱ ቁሳቁሶች ፤የእጅ ሥራ ውጤቶች ፤ፎቶግራፎችና ቅርጻ ቅርጾች የሚገኙበት ኤግዚቢሽን በተከፈተበት ወቅት ጓድ ሻምበል ካሣዬ አራጋው የሸዋ ክፍለ ሀገር ቋሚ የደርግ አባል ሚኒስትሮች ጓድ ዶክተር ዓለሙ አበበ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ማኅበር አጠቃላይ ምክር ቤት ቋሚ ኰሚቴ አባሎችና የከፍተኛና የቀበሌ ማኅበራት መሪዎች ተገኝተዋል።
በከፍተኛ ድምቀት በአብዮት አደባባይ በሚከበረው በዚሁ በዓል ላይ ለመገኘት ከኢትዮጵያውያን ሴቶች ጎን በመሰለፍ የትግል አንድነታቸውን ለማረጋገጥ ከልዩ ልዩ የሶሻሊስት አገሮች የመጡት ልዑካን በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል። (የካቲት 29 ቀን 1970 ዓ.ም )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2014