᎐ልዑኩ የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ቅሪተ አካልም ሀገሩ ላይ በክብር ለማሳረፍ ጥረት ይደረጋል
የአፄ ቴዎድሮስ ሹሩባን (ቁንዳላ) ከ150 ዓመታት በኋላ ወደ ሀገር ቤት ለማስመለስ የፊታችን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም አንድ ልዑክ ወደ ለንደን እንደሚያቀና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኽኝ አባተ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገለጹ።
አቶ ገዛኽኝ እንደተናገሩት ፤በእንግሊዝ በሚገኘው የብሔራዊ ጦር ሙዝየም በይዞታው ስር የቆየውን የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ለመመለስ ተስማምቷል።
በመሆኑም በባህልና ቱሪዝም ሚስቴር ዶክተር ሂሩት የሚመራ አራት የቡድን አባላት ያለው ልዑክ ወደ ለንደን የሚጓዝ ሲሆን፤ ልዑኩ የአፄ ቴዎድሮስን ቁንድላ ከማስመለሱ ባሻገር ሌሎች ተግባሮችም እንዳሉት ተገልጿል።
እንደ ሃላፊው ማብራሪያ ፤በመቅደላ ጦርነት ወቅቱ በእንግሊዝ ጦር ተዘርፈው የሄዱትን የአጼ ቴውድሮስ አክሊል፣ መጽሀፍት፣ ጽላቶች ና በርካታ ቅርሶች በእንግሊዝ ሀገር ይገኛሉ ።ልኡኩ እነዚህ ቅርሶችን ማስመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
አቶ ገዛህኝ አክለው በጦርነቱ ወቅት ወደ እንግሊዝ የተወሰዱትን የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልኡል አለማየሁ ቴዎድሮስ ቅሪተ አጽምን ለማስመለስ የሚደረግ ጥረት የውይይቱ አካል እንደሚሆን አመላክተዋል።
የአባታቸው ሹሩባም የልኡል አለማየውን ትክክለኛውን ቅሪተ አካል ለማግኘት የዲኤን ኤ ምርመራ ለማድረግ አጋዥ እንደሚሆን አቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል ። ልኡል አለማየሁ በፈረንጆቹ ሚያዝያ 23 ቀን 1861 የተወለደ ሲሆን በ18 አመቱ ነበር ህዳር 14 ቀን 1879 ዓ.ም ነበር ህይወቱ ያለፈው።
ዳንኤል ዘነበ