የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከወራት በፊት በመካከለኛና ምስራቅ አፍሪካ (ሴካፋ) ዋንጫ አስደናቂ ጉዞ አድርጎ የውድድሩ አስተናጋጅና ጠንካራ ስብስብ ያላትን ዩጋንዳን በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት አሸንፎ ቻምፒዮን መሆኑ አይዘነጋም። ይህም በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው አህጉር አቀፍ የዋንጫ ስኬት በመሆኑ ቡድኑን ታሪካዊ አድርጎታል።
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ምናልባትም በቅርቡ ዋናውን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እንደሚተኩ የሚጠበቁት የሉሲዎቹ ተተኪዎች ከሴካፋው ታሪካዊ ድል በኋላ ለዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በአስደናቂና ስኬታማ ግስጋሴ መቀጠል አልተሳናቸውም። በድል ላይ ድል እየደረቡ አራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ወደ ኮስታሪካ ለማቅናት ከጫፍ ደርሰዋል። ሆኖም የመጨረሻውና አምስተኛው ፈታኝ የማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ እንደ አመጣጣቸው ሳያምር ቀርቷል። ይህን የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ ከጋና አቻቸው ጋር ትናንት በአበበ ቢቂላ ስቴድየም ያደረጉት የሉሲዎቹ ተተኪዎች በሜዳና በደጋፊያቸው ፊት በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባስተናገዱት ሶስት ግብ በመረታት ደምድመዋል። ይህም እኤአ በ2001 የአርጀንቲና የዓለም ወጣቶች ዋንጫ ከተሳተፈው የወንዶች ወጣት ብሔራዊ ቡድን በኋላ በዓለም ዋንጫ የሚሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመሆን ተስፋውን አመንምኖታል።
በማጣሪያ ውድድሩ ሰባት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆና በመምራት ላይ የምትገኘዋን ረድኤት አስረሳኸኝን የመሳሰሉ ወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ባልተሰለፉበት ጨዋታ የሉሲዎቹ ተተኪዎች በሜዳቸው ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው ለጋና አቻቸው እጅ ለመስጠት እንዲገደዱ አድርጓቸዋል።
የሉሲዎቹ ተተኪዎች ትናንት በሜዳቸው በሰፊ የግብ ልዩነት መረታታቸው የመልሱን ጨዋታ ውጤት ከሜዳቸው ውጪ ቀልብሰው የሞተ የሚመስለውን የዓለም ዋንጫ ተስፋ ነብስ ይዘሩበታል ብሎ መገመት ከባድ ቢሆንም እግር ኳስ በተአምራት የተሞላ ስፖርት ነውና የትናንቱን ሽንፈት ወደ ኋላ ትቶ በመልሱ ጨዋታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው። ከምንም ተነስተው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት የሉሲዎቹ ተተኪዎችም ምስጋና ሊቸራቸውና ሊበረታቱ እንደሚገባ ብዙዎች ይስማማሉ።
የአሰልጣኝ ፍሬው ሃይለገብርኤል የወጣቶች ስብስብ የሁለተኛና ሶስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ሩዋንዳንና ቦትስዋናን በሰፊ የግብ ልዩነት ጭምር በደርሶ መልስ ማሸነፍ መቻሉ የሚታወስ ሲሆን፣ አራተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውንም ኤርትራን በመርታት እንዲሁም ከብሩንዲ ጋር በጠባብ ልዩነት በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ከተቀላቀለው የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ተፋልሟል። በታንዛኒያው አማን ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታም ታንዛኒያ በቅጣት ምት ባስቆጠረችው ግብ ነጥብ አስመዝግባ ስትወጣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞው ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥር ጨዋታውን ማጠናቀቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የመልሱን ጨዋታ በሜዳው ሁለት ለዜሮ በማሸነፍ ለመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ሊበቃ ችሏል።
ከሉሲዎቹ ተተኪዎች ጋር አስደናቂ የስኬት ጉዞ እያደረገ የሚገኘው አሰልጣኝ ፍሬው ሃይለገብርኤል ከትናንቱ ጨዋታ አስቀድሞ ከቡድኑ ጋር እንዲቆይ የተሰጠው ተጨማሪ የሁለት ዓመት ኮንትራትም እየተገነባ ለሚገኘው ቡድን ወደ ፊት በተሻለ ደረጃ ጠንክሮ እንዲወጣ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።
በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ-19 ምክንያት ለመራዘም ከተገደዱ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የዓለም ከ20ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ከወራት በኋላ በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። የዓለም እግር ኳስን በበላይነት የሚመራው ፊፋ ተተኪ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚታዩበትና እንደ ወንዶቹ ያላደገውን የሴቶች እግር ኳስ ወደ ሌላ ደረጃ ያሸጋግራሉ በሚል እምነት ይህንን ውድድር ያዘጋጃል። 16 ቡድኖች የሚፋለሙበትን ይህንን ውድድር የምታስተናግደው ኮስታሪካ ከፓናማ ጋር በጥምረት መሰናዶውን ብትጀምርም እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ብቻዋን ዝግጅቷን በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች። በዚህ ውድድር ተሳታፊ ለመሆንም የተለያዩ አገራት ብሄራዊ ቡድኖቻቸው በየአህጉራቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ስር የማጣሪያ ውድድራቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንም በዓለም ዋንጫው አፍሪካን የሚወክሉ ቡድኖችን ለመምረጥ የሚያስችለውን የማጣሪያ ውድድር እያከናወነ ሲሆን፤ 56ቱ አባል አገራት 40ዎቹ የወጣት ሴት ቡድናቸውን በማጣሪያው እያሳተፉ ይገኛሉ። አምስት ዙሮች ባሉት በዚህ ማጣሪያ በደርሶ መልስ ጨዋታዎች አሸንፈው ለመጨረሻው ዙር ያለፉ ሁለት ቡድኖች አፍሪካን ወክለው በኮስታሪካው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም