ሚዲያዎች ተፅእኖ ፈጣሪነታቸውን በመጠቀም እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ከመቀነስ አንፃር ያለባቸውን ሀላፊነት መወጣት አለባቸው ሲሉ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ ተናገሩ፡፡
አቶ ምትኩ ይህንን ያሉት ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ‹‹የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚድያ ተቋማት ሚና›› በሚል ርአስ እየተካሄደ ያለውን የስልጠናና የውይይት መድረክ በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡
እንደ አቶ ምትኩ ገለፃ ህግን የሚያከብር ትውልድ በመፍጠርና ሚዲያዎች ያላቸውን ተፅእኖ በመጠቀም እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ከመቀነስ አንፃር ያላቸውን ሀላፊነት መወጣት አለባቸውም ብለዋል፡፡
ሚዲያ አራተኛ መንግስት ነው ያሉት አቶ ምትኩ ህብረተሰብን በማስተማር በመምከርና መንግስትን በመደገፍ ህዝብን ከማስተማር አንፃር የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን ቁጥር መቀነስ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል፡፡
የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ትምህርትና የግንዛቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዮሃንስ ለማ በበኩላቸው የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የትራፊክ አደጋን ከመከላከል አንፃር በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸውን ነገሮች ትኩረት በመስጠት ከትምህርት ሚኒስቴርና ጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ዮሃንስ አጠቃላይ በትምህርት ስርአት ውስጥ የትራፊክ ትምህርቶችን ለማካተት ስራዎችን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየተሰሩ ነው፡፡ ከጎልማሶች ትምህርት ጋርም በተያያዘ ክበባትን በማጠናከር በፕላዝማ የተለያዩ አደጋዎችን የሚያሳዩ ማስታወቂያዎችን በማሳየት ረገድም ስራዎች እየተሰሩ ነው ተብሏል፡፡
የውይይትና ስልጠና መድረኩ እስከ ነገ ድረስ ይቆያል፡፡
በዳግማዊት ግርማ