እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? በጣም ጥሩ። ሳምንት ከዲላ ልጆች ጋር አስተዋውቄያችሁ ነበር፤ አስታወሳችሁ አይደል? በጣም ጥሩ። ዛሬም ወደ እዛው ልወስዳችሁ ነውና በንባብ አማካኝነት ከዲላና ከማስተዋውቃችሁ ልጆች ጋር በሚገባ ለመተዋወቅ ተዘጋጁ። ተዘጋጃችሁ፣ ጎበዞች።
ባለፈው እንደነገርኳችሁ፣ የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ የዘንድሮውን የንባብ ሳምንት በደማቅ፣ አረንጓዴና ሞቃታማዋ ዲላ ከተማ አክብሯል። በዝግጅቱም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን የዲላ ልጆችም ከተሳታፊዎቹ አንዱ ክፍል ነበሩ። ልጆች በፎቶው ላይ እንደ’ምትመለከቷቸው፤ ልጆቹ ተመስጠው ነው የሚያነቡት። ልክ እንደ እናንተ ማለት ነው። ሲፈልጉ ወንበር ላይ ሆነው፤ ሲፈልጉ ደግሞ ኤጀንሲው ባዘጋጀላቸው ምቹ ምንጣፍ ላይ ሆነው።
ልጆች ባለፈው እንደነገራችሁኝ ከሆነ እኮ እናንተም ልክ እንደምትመለከቷቸው የዲላ ልጆች ስታነቡ በፀጥታና በጥሞና ነው አይደል? አዎ እንደዛ ነው የነገራችሁኝ። እኔም በነገራችሁኝ መሰረት ነው እኮ ለሰው ሁሉ በጣም በፀጥታና በፅሞና እንደ’ምታነቡ እያወራሁ ያለ ሁት።
ልጆች እኔ እናንተ የነገራችሁኝን ሁሉ አምኜ ስለምቀበልና ተቀብዬም ለሰው ስለማወራ አደራ እንዳትዋሹ እሺ ልጆች፤ አዎ ውሸት በፍፁም ክልክል ነው። መጥፎም ነው። ደሞም እኮ ውሸታምን ሰው ማንም አይወደውም እኮ፤ እናንተ ውሸታም ሰው ትወዳላችሁ፣ አትወድዱም አይደል? አዎ፣ ውሸታምን ማንም አይወደውም፣ ማንም አያምነውም፣ ማንም አያከብረውም፣ ማንም ጓደኛ አያደርገውም። ስለዚህ ውሸታም መሆን መጠፎ ነው፣ እሺ ልጆች? አሁን መልሼ ወደ ዲላ ልጆች ልውሰዳችሁ።
ልጆች የመጻሕፍት አውደ ርእይ የተካሄደበት ቦታ (መሀል ከተማው ላይ በሚገኝ የሚያምር አደባባይ ላይ ነው የተካሄደው) ላይ ሲያነቡ የምትመለከቷቸው የዲላ ልጆች ናቸው። የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ ወደ ዲላ ይዟቸው ከሄዳቸውና ለልጆች ካቀረባቸው መጻሕፍት መካከል እነዚህ ልጆቹ ይዘው ሲያነቧቸው የምታዩዋቸው ይገኙባቸዋል። ብታዩዋቸው፣ መጻሕፍቱ በውስጣቸው ደስ የሚሉ ጥሩ ጥሩ ታሪኮችን ይዘዋል።
ታሪኮቹን በሚገባ የሚገልፁ ሥዕሎችም አሏቸው። ጽሑፉ የቀረበባቸው ፊዳላት ደግሞ ከፍ ከፍ ያሉ ስለሆኑ እንደምታዩዋቸው ልጆቹ ምንም ሳይጨናነቁ ነው የሚያነቧቸው። እናትስ? የምታነቧቸው መጻሕፍት እንደነዚህ ናቸው አይደል? በጣም ጥሩ ልጆች። ምን ጊዜም ተጨናንቃችሁ እንዳታነቡ እሺ ልጆች። አዋ፣ ንባብ ተጨናንቆ አይነበብም።
ንባብ የሚነበበው ዘና ብሎና ሙሉ ትኩረትን የሚነበበው ጉዳይ ላይ አድርጎ ነው። ልክ አይደለሁም እንዴ ልጆች፤ አዎ፣ በፍፁም ተጨናንቃችሁ አታንብቡ፣ አታጥኑም። እንደዛ ካደረጋችሁ ተሳስታችኋል። መጽሐፍ ሲገዛላችሁም ፊደላቱ ከፍ ከፍ ያሉ መሆን እንዳለባቸው ለወላጆቻችሁ ንገሩ። ለነገሩ እነሱም በሚገባ ስለሚያውቁ ችግር የለም።
በንባብ ላይ የሚገኙትን ልጆቹን የዲላ ልጆች ጠጋ ብዬ ፎቶ ሳነሳቸው በዛውም አነጋግሬያቸው ነበር። “ማንበብ ትወዳላችሁ እንዴ ልጆች፣ ምን ምን ጥቅሞች እንዳሉትስ ታውቃላችሁ እንዴ?” ብዬ ጠይቄአቸውም ነበር። ሁሉም መልስ ሊሰጡኝ ተሽቀዳደሙ። አቤት ደስ ሲሉ። ከዛ እኔ ደግሞ ከሁሉም በፊት እጇን ላወጣችውና የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ተማሪ ለሆነችው ለቢቢሳ አቤቤ እድሉን ሰጠኋት። አቤት እንዴት አድርጋ እንደ መለሰችልኝ እኮ ልጆች፤ ምን እንዳለችኝ ታውቃላችሁ? የተወሰነውን ብቻ ነው የምነግራችሁ። እንደዚህ ነበር ያለችኝ።
“እንዴ መጽሐፍ የማይወድ አለ እንዴ፣ እንዴ ማንበብ እማይወድ አለ እንዴ? ሁላችንም እንወዳለን። እኔ በበኩሌ መጽሐፍ ማንበብ ደስ ይለኛል። በጣም ነው የምወደው። አባቴም እናቴም ማንበብ ይወዳሉ። ቲቸርም እኮ ያነቡልናል። እኛም እኮ ላይብረሪ እየገባን እናነባለን።” አለችኝ። ከዛ ደግሞ “ጥቅሙንስ ትነግሪኛለሽህ?” ብዬ እንደገና አስታወስኳት። “አዎ” አለችኝና የሚከተለውን መለሰችልኝ።
በንግግር መጀመሪያ ላይ “እንዴ …” ማለት የምትወደውና ፈጣኗ ተማሪ ቢቢሳ “እንዴ፣ በጣም ጥቅም አለው እንጂ፤ በጣም አለው። የአማርኛ መምህራችን እኮ ሁል ጊዜ ማንበብ ብዙ ጥቅም እንዳለው ይነግሩናል። እኔ እናቴም አባቴም ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሌ ሲያወሩ እሰማለሁ። እኔም አውቃለሁ።” ካለችኝ በኋላ “ሰው ካላነበበ እንዴት እውቀት ሊያገኝ ይችላል?” ብላኝም ወደ ንባቧ ተመለሰች።
ልጆች የ…………. መልስ ደስ አይልም፡፡ ጎበዝ አይደለም? አዎ ………… በጣም ጎበዝ ነው። በተለይ ወደ ፊት በጣም በማንበብ ብዙ እውቀት ማግኘት እንደሚፈልግ የነገረኝንማ ብነግራችሁ፣ ኦኦኦ …. በጣም ነው የምታደንቁት። ደግሞም በጣም ሊደነቅ የሚገባው ልጅ ነው እኮ፤ አይደለም እንዴ ልጆች? አዎ፣ በጣም ጎበዝ ነው። ለነገሩ የዲላ ልጆች እኮ ልክ እንደ እናንተ ጎበዞች ናቸው እኮ። በጣም ጎበዞች።
በሉ እንግዲህ ልጆች፣ ከሌሎቹ ጋር ያደረኩትን ውይይት ደግሞ ሌላ ጊዜ ይዥላችሁ እመጣለሁ። እሺ ልጆች፣ እስከዛው ደህና ሁኑ ልጆች ደህ………. ኦአ አንድ ነገር ሳልነግራችሁ፤ በስነ ስርዓቱ ላይ ዋናው መልእክት ምን እንደነበር ሳልነግራችሁ፤ አዎ፣ ዋናው መልእክት “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!!!” የሚል ነበር። ዋው፣ ደስ አይልም፣ በጣም ደስ ይላል። አዎ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋልና ሁላችንም እናንብብ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2014