ኮስታሪካ ለምታዘጋጀው የ2022 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ነገ የጋና አቻውን አዲስ አበባ ላይ ያስተናግዳል፡፡
ስኬታማ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙት የሉሲዎቹ ተተኪዎች በዓለም ዋንጫው አፍሪካን ከሚወክሉት ሁለት ቡድኖች መካከል አንዱ ለመሆን በሚገባ ዝግጅት ማድረጋቸውን የቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ሃይለገብርኤል አስታውቀዋል፡፡
የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚቆጣጠረው ፊፋ ከሚመራቸው የዓለም ዋንጫ ውድድሮች መካከል እአአ ከ2002 ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ የሚደረገው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ውድድር ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ በኮስታሪካ አዘጋጅነት ይካሄዳል፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ 16 ቡድኖችን በማሳተፍ በሚደረገው በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተካፋይ ለመሆን የሚያስችለውን የመጨረሻ የማጣሪያ ውድድር ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ አፍሪካን የሚወክሉ ሁለት አገራትን ለመለየት በሚያስችለው የመጨረሻው የደርሶ መልስ ጨዋታ አራት አገራት ብቻ ቀርተዋል፡፡
ዛሬ እና ነገ በሚደረጉት ጨዋታዎችም ሴኔጋል ናይጄሪያን ስታስተናግድ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በ10 ሰዓት ከጋና ጋር ትጫወታለች፡፡ የሩዋንዳ፣ ቦትስዋና እና ታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድኖችን በመርታት ከመጨረሻው ምዕራፍ የደረሰውና የሴካፋ አሸናፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እጅግ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በቀሪው 180 ደቂቃ ፍልሚያም በተለመደው አሸናፊነት የዓለም ዋንጫ ትኬቱን ለመቁረጥም በሚገባ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ዋና አሰልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል አስታውቀዋል፡፡ አሰልጣኙ ከጨዋታው አስቀድመው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት
መግለጫ 24 ተጫዋቾችን በመያዝ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስል የረጅም ጊዜ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህም ተጫዋቾቹ ላይ ከፍተኛ ተነሳሽነትና ዝግጁነት መፈጠሩን አሰልጣኙ አረጋግጠዋል፡፡ በተጫዋቾች በኩል መልካም የሚባል ተነሳሽነት ቢኖርም ቁልፍ ተጫዋቾችን ጨምሮ አራት የቡድኑ አባላት ጉዳት ላይ መሆናቸውንም አሰልጣኙ አስታውቀዋል፡፡
ጉዳት የገጠማቸው ተጫዋቾችም የቡድኑ ወሳኝ ግብ አስቆጣሪ ረድኤት አስረሳኸኝ፣ ቱሪስት ለማ፣ ገነት ኃይሉ እና ማዕድን ሳህሉ ሲሆኑ፤ በነገው ጨዋታ ለመሰለፍ የጤንነት ሁኔታቸው ማረጋገጫ ከህክምና ባለሙያዎች እየጠበቁም ይገኛሉ፡፡ የተጋጣሚያቸውን የጋና ብሄራዊ ቡድንን በሚመለከትም፤ ከዚህ ቀደም ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በተንቀሳቃሽ ምስል ከተጫዋቾቹ ጋር በመመልከት ዕቅድ ማውጣታቸውን አሰልጣኝ ፍሬው ጠቁመዋል፡፡
የተጋጣሚያቸውን ጠንካራና ደካማ ጎን ለይቶ በማውጣት በእግር ኳስ የማይደፈር ነገር እንደሌለ ለተጫዋቾቹ እንዳስረዱም አብራርተዋል፡፡ በተጠናቀቀው የካቲት ወር 2014 ዓም የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ለ27 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ወደ ዝግጅት የገባው የአሰልጣኝ ፍሬው ስብስብ ለረጅም ጊዜ በ35 እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳዎች ላይ ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል።
በእነዚህ ጊዜያትም ከልምምድ ባለፈ ከሌሎች አገራት ቡድኖች ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሳካለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ቡድኑ በቅርበት ሊያገኛቸው ከሚችላቸው የምስራቅ አፍሪካ ቡድኖች ጋር እንዲጫወት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ ከዚህ ቀደም በውድድር ያገኛቸው ቡድኖች በመሆናቸው ወደ ሌላ አማራጭ ማማተር የግድ እንደነበርም የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡
ከሰሜን አፍሪካ ቡድኖች መካከል ከሞሮኮ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ መግባባት ላይ ቢደረስም፤ በእነርሱ በኩል የተያዘው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ጨዋታ በምታደርግበት ዕለት በመሆኑ ሊሰረዝ ችሏል፡፡ በመሆኑም ቡድኑ ከ20ዓመት በታች የወንድ ቡድኖች ጋር ጨዋታ በማድረግ ሲዘጋጅ መቆየቱ ታውቋል፡፡
ነገ በሚደረገው ወሳኝ ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡ በካፍ በተቀመጠው የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል መሰረት 25 ከመቶ ተመልካቾችን አበበ ቢቂላ ስቴድየም ተገኝተው ፍልሚያውን መከታተል ስለሚችሉ በስፍራው ተገኝተው ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ በስታዲየም መገኘት ያልቻሉ ደጋፊዎች ደግሞ በፌዴሬሽኑ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ በቀጥታ ስርጭት ማየት እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡
ቡድኑን በመምራት ስኬታማ ጊዜ በማሳለፍ ላይ የሚገኘው አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ተጨማሪ ሁለት ዓመታትን በዋና አሰልጣኝነት እንዲቀጥል ከፌዴሬሽኑ ጋር መስማማቱንም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ በውሉ የአሰልጣኙ ደመወዝ ማሻሻያ ተደርጎበት የተጣራ 50ሺ ብር የሚያገኙ ሲሆን፤ ውድድር በማይኖር ጊዜም ከቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር በመሆን በተለያዩ የእግር ኳስ ልማት ስራዎች እንደሚሳተፉም ታውቋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 /2014