የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ለጉብኝት ፓሪስ በነበሩበት ወቅት ለመፍረስ አደጋ የተጋለጠውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለመታደግ የገቡላቸውን ቃል አክብረው መጋቢት ሶስት ቀን 2011ዓ.ም ቅርሱ በሚገኝበት ቦታ ተገኝተው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በከፍተኛ የሥራ አመራሮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የአካባቢው ነዋሪም በደማቅ ሥነሥርዓት ነበር አክብሮቱን የገለጸላቸው።ለክብራቸውም ዘጠኝ ጊዜ መድፍ ተተኩሶላቸዋል።ካባም ተደርቦላቸዋል።በዚህ ሁኔታ ነበር ጉዳት የደረሰበትን ቅርስን ተዘዋውረው የጎበኙት።
የማክሮን በስፍራው መገኘት የላሊበላና የአካባቢውንም ነዋሪ ያነቃቃ ነበር።ብዙዎቹ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን በመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ ነበር።ማክሮን በስፍራው ተገኝተው ቅርሱን መጎብኘታቸው ድጋፉን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ይታመናል። ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በጉብኝታቸው ቅርሱን ለመታደግ የፈረንሳይ መንግሥት የገንዘብና የባለሙያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በንግግራቸው አረጋግጠዋል። በስፍራው መገኘታቸው እንዳስደ ሰታቸውና አድናቆታቸውንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ማክሮን በቅርሱ መደመማቸውንና ለጥገናው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ቃል መግባታቸውን እንደገለጹላቸውም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያን መልስ ማምሻውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደ የስምምነት ፊርማ ስነስርዓት ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በተለያዩ መስኮ ች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውንአረጋግጠዋል። ሁለቱ መሪዎች በተወካዮቻቸው በተፈራረሙት ፊርማ ፈረንሳይ የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት ቅርስን የሙያና የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች።
በተጨማሪም በኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ ሃይል አቅም ግንባታ በተለይም በባህርና በአየር ሃይል ድጋፏን ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል። መሪዎቹ በሰጡት የጋራ መግለጫ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ከ1ኛው ገጽ የዞረ ተናግረዋል።በኢትዮጵያ መንግስት የተደረገላቸውን የስራ ጉብኝት ግብዣ ተቀብለው በመምጣታቸው ለማክሮን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በፈረንሳይ በነበራቸው ጉብኝት ወቅት የተደረሰውን ስምምነት ለመተግበር በሚቻልበት ሁኔታ መምከራቸውንም ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ማክሮንም ኢትዮጵያ ወደቀድሞ ገናናነቷ ለመመለስ የምታደርገውን ጥረት ፈረንሳይ የምትደግፍ መሆኗን እና አገራቸው ለኢትዮጵያ የገንዘብ ብድርና ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።የፈረንሳይ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚሰሩ መሆናቸውንና በአሁኑ ጉብኝታቸውም ባለሀብቶችን ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና ፈረንሳይ በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስርም እየጎለበተ መምጣቱን ኢዜአ ከፈረንሳይ ኤምባሲ የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ ገልጿል።
እንደ ዘገባው ፈረንሳይ የትራንስፖርት ቁሳቁስና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ትልካለች። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሶስት ሺህ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ 30 የፈረንሳይ ኩባንያዎች አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአምስት ወራት በፊት በአውሮፓ በተለያዩ አገሮች ጉብኝት ሲያደርጉ ከጎበኟት አገር መካከል ፈረንሳይ አንዷ ስትሆን ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወቃል።
ከነዚህም መካከል በዓለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች፣ በጸረ ሽብር፣ በአየር ንብረት ለውጥና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ)ጋር በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። ፈረንሳይ በኢትየጵያ የሚገኘው ኤምባሲዋን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለማደስ የሚያስችል የገንዘብና የባለሙያ እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ሌላው ከስምምነት ከደረሱባቸው ነጥቦች እንደሆኑም የኢዜአ ዘገባ አስታውሷል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር