ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ። ባለፈው ሳምንት ወደ ዲላ በመሄድ ከእነ ተማሪ በረከት ማስረሻ፣ አቤኔዘር ፀጋዬና ጓደኞቻቸው ጋር መገናኘትና እነሱን ከእናንተ ጋር ማስተዋወቅ ስለነበረብኝ፣ ወደ እዛ በመሄዴ ምክንያት ሳንገናኝ ቀረን አይደል? ምንም ችግር የለም። ዛሬ ከዲላ ልጆች ጋር ያደረኩትን ቆይታና ያደረግነውን ጭውውት በተመለከተ፣ ያው እንደ ተለመደውና በተለመደው ልክ አጠር ያለች ታሪክ አቀርብላችኋለሁ። ትከታተሉኛላችሁ አይደል ልጆች፣ በጣም ጥሩ።
ልጆች ዲላ ከተማ የት እንደሚገኝ ታውቃላችሁ? ጥሩ። ባጭሩ ስለ ዲላ ከተማ የሚከተለውን የተጠና መረጃ እንዳለ ላስነብባችሁ:-
ዲላ ከባህር ወለል በላይ በ1ሺህ 570 ሜትር ወይም 5ሺህ 150 ጫማ ከፍታ ላይ የምትገኝ፣ የብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያዋ፣ የበርካታ ባንኮች፣ የዘመናዊ ዲጂታል ቴሌፎን፣ የፖስታ አገልግሎት እና የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ፤ ከአዲስ አበባ ኬንያ በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ያለች፤ በኢትዮጵያ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ የጌዴኦ ዞን ዋናና ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት የንግድ ከተማ ናት። ዲላ ከአዲስ አበባ በ365 ኪ.ሜ እና ከሃዋሳ 90 ኪ.ሜ በአ.አ ሞያሌ ዋና የንግድ መስመር ላይ የምትገኝ፤ የመቶ ሺዎች መኖሪያና የአንድ ግዙፍ (ዲላ) ዩኒቨርሲቲ ባለቤትም ነች።
አሁን ስለዲላ ከተማ ምጥን መረጃ አገኛችሁ አይደል ልጆች፣ በጣም ጥሩ። ቀጥሎ ከዲላ ልጆች ጋር ወደ አደረኩት ቆይታ ልመልሳችሁ። በመጀመሪያ ስለትምህርት ቤቱ ልንገራችሁ።
ትምህርት ቤቱ ቆፌ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ይባላል። ከቆፌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ ቃለአብ አለማየሁ በከተማ ደረጃ በተካሄደ የጥያቄና መልስ ውድድር 1ኛ የወጣው ይህንን ት/ቤት ወክሎ በመወዳደር ነው) ጋር በጉርብትና ይገናኛል።
በ1943 ዓ.ም የተመሰረተው አንጋፋው ቆፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት
ቤት ከ”ዜሮ ክፍል” (በአሁኑ ዘመን ዘመናዊ መጠሪያው ሙአለ ሕፃናት (ኪንደርጋርተን/ኬጂ) እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ የሚዘልቅ ትምህርት ቤት ሲሆን በጌዴኦ ዞን፣ ዲላ ከተማ መሀል የሚገኝ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ነው።
በትምህርት ቤቱ ውስጥ በርካታ አይን የሚገቡና ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅሙ ጉዳዮች አሉ (በሌላ ጊዜ እነግራችኋለሁ) ለዛሬ ግን የመረጥኩላችሁ ከ”ዜሮ ክፍል” ተማሪዎች ጋር ያደረኩትን ደስ የሚል ጭውውት ነው።
ይህ ሙአለ ሕፃናት (የዜሮ ክፍል ተማሪዎች የሚማሩበት ግቢ) እራሱን የቻለ ግቢ ሲሆን በዋናው የትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ወደ እዛ ልሄድ የቻልኩት የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው “የወጣት ተኮር ንባብ እና የምርምር ንቅናቄ መድረክ” ላይ ለመገኘት ነው። ፕሮግራሙ የንባብ ባህላችንን የማሳደግ አላማን የያዘ በመሆኑ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በደማቅ ሁኔታ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤ ከትምህርት ተቋማቱም አንዱ ቆፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር። (ፕሮግራሙ አቤት ደስ ሲል ልጆች፤ የንባብ፣ የሥነጽሑፍ፣ የጥያቄና መልስ …. ሁሉ ዝግጅቶች ነበሩበት። እናንተስ በየትምህርት ቤታችሁ እንደ እነዚህ አይነት ዝግጅቶችን ታደርጋላችሁ? በጣም ጥሩ። በርቱ።)
በዚህ አጋጣሚ ነው እንግዲህ ከእነ ተማሪ በረከት ጋር የተገናኘነውና ስለ ትምህርት የሆድ የሆዳችንን የተጨዋወትነው።
እንዳጫወትኳቸውና እንደ ነገሩኝ ከሆነ እነ አቤኔዘር ትምህርት በጣም ይወዳሉ። መውደድ ብቻ እንዳይመስላችሁ፣ መምህራኖቻቸው ሲያስተምተሩ ሁሉ በጣም ነው የሚያዳምጡት፤ የሚሰጠውን ትምህርት በሚገባ ይከታተላሉ። የቤት ስራ ሳይሰሩ በፍፁም ወደ ትምህርት ቤት አይመጡም። ሲጠየቁ ይመልሳሉ። ያልገባቸውን ይጠይቃሉ። ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ደግሞ ማጥናት ስራቸው ነው፤ በጣምም ያስደስታቸዋል። መጫወት ካለባቸውም ይጫወታሉ። ቤተሰብን መርዳት ካለባቸውም ያግዛሉ፤ ይላላካሉ። አቤት እርስ በርሳቸው ሲዋደዱ ደግሞ፤ ያገኘኋቸው በቡድን ሲጫወቱ ነበርና ፍቅራቸውንና ጓደኝነታቸውን በቀላሉ ነው ያወኩት። ገና ሲታዩ እንደሚዋደዱ ያስታውቃሉ። ልክ እናንተ እርስ በርሳችሁ እንደምትዋደዱት ማለት ነው።
ልጆች ምን ልበላችሁ፣ እነዚህን የስምንትና የአስር አመት ልጆች አግኝቼ ሳዋራቸው ምን እንደ ተሰማኝ ታውቃላችሁ? አዎ፣ የተሰማኝ አንድ ትልቅ ጉዳይ ሲሆን፤ እሱም “ፓፓፓ … ኢትዮጵያ ወደ ፊት ምርጥ ምርጥ፣ ስሟን በአለም ደረጃ የሚያስጠሩ፣ የተማሩና የተመራመሩ ልጆች አሏት ….” የሚል ነበር።
ለካ እኔ ብዙ ጊዜ ወደ ክፍለ ሀገር ስለማልሄድ የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋዎች በየአካባቢውና በየትምህርት ቤቶቹ የሚገኙ አይመስለኝም ነበር፤ ለካ ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገርና በየአካባቢው ልክ እንደ እናንተ ምርጥ ምርጥ ልጆች ያሏት አገር ነች። በእውነት በጣም ደስ ይላል። በጣም!!! “ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!!!” ሲሉ አይገባኝም ነበር እኮ። እንዴ “ኧረ ለዘለአለም አለሙ ትኑር!!!” በተለይ የዲላንም ሆነ አካባቢዋን አረንጓዴነት ብታዩት “አቤት ኢትዮጵያ ውበቷ፣ ደም ግባቷ ….” እንደምትሉ አልጠራጠርም።
ልጆች ከዚህ በኋላማ እዚህ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያም እየሄድኩ ከጎበዝ ጎበዝ ልጆች ጋር አስተዋውቃችኋለሁ። እንደዛ ባደርግ ጥሩ ነው አይደል ልጆች፤ በጣም ጥሩ። በቃ፣ አደርጋለሁ። ልምን መሰላችሁ ይህንን የማደርገው፤ ልክ እንደ እናንተ በጣም ጎበዝ የሆኑ ብዙ ልጆች ስላሉ እኮ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014