ከአራት ሳምንታት በፊት በተጠናቀቀው የካሜሩን 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቻምፒዮን ከመሆኗ ባሻገር በውድድሩ በርካታ ያልተጠበቁ ክስተቶችና ሊነገርላቸው የሚገቡ ታሪኮችና ኮከቦችን ማየት ተችሏል። ባለፉት ሦስት ሳምንታት የስፖርት ማህደር አምዳችንም በአፍሪካ ዋንጫው ኮከብ ተጫዋችና ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው ያጠናቀቁትን ሴኔጋላውያኑን ኮከቦች ሳዲዮ ማኔና ኤድዋርድ ሜንዲን ለመዳሰስ ሞክረናል።
ባለፈው ሳምንት ግን ከጥቁር ሕዝቦች መታሰቢያ ወር ጋር በተያያዘ ሌላ ዘገባ ይዘን መውጣት ስለነበረብን በአፍሪካ ዋንጫው ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀውን ካሜሮናዊ ኮከብ ቪንሰንት አቡበከርን ማቅረብ አልቻልንም። በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ግን ወደ አፍሪካ ዋንጫው መለስ ብለን በበርካታ የግንባር ግቦቹ የእግር ኳስ አፍቃሪውን ያስደመመው ኮከብ የእግር ኳስ ሕይወት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ለሚገኙ ወጣትና ታዳጊ የእግር ኳስ ተስፈኞች ትምህርት ይሆናልና እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
በዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ጨምሮ በርካታ ግቦችን በግንባር በማስቆጠርና አደገኛ ሙከራዎችን ከማድረግ ባሻገር በትክለ ሰውነቱ ግዝፈት ብዙዎች የሚያስታውሱት ካሜሮናዊው አጥቂ ቪንሰንት ፓት አቡበከር ነው። 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርባት ያውንዴ ከተማ ሞናንቴሌ በተባለች ትንሽ መንደር የተወለደው አቡበከር የተወለደው እኤአ በ1992 ነው።
በሕይወት ዘመኑ ወላጅ እናቱን አጥብቆ እንደሚወድ የሚነገርለት ይህ ካሜሮናዊ ግዙፍ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች፣ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰው ከምንም ተነስቶ ነው። በድህነት ወለል ውስጥ ከሚኖሩ የመንደሩ ነዋሪዎች የአቡበከር ቤተሰብ አንዱ ነው። አስከፊ ድህነትና በለጋ እድሜው የተጋፈጠው ችግር ግን እግር ኳስን ለወደፊት የተሻለ ሕይወት ተስፋ አድርጎ ጊዜያዊ ችግሮቹን ጠንክሮ ከመታገል አላቆመውም። በረሀማ በሆኑት የያውንዴ ሜዳዎች እግር ኳስን በመጫወት የእግር ኳስ የተጫዋችነት ህልሙን ለማሳካት ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር መነሻውን አደረገ።
ዕድሜው በክለብ ደረጃ ለመጫወት ሲበቃም የትውልድ አገሩ ክለብ በሆነው ኮተን ስፖርት የወጣቶች ክለብ ለሶስት አመታት ያህል ተጫውቷል፤ በዚህ ቡድን ቆይታውም ባሳየው አስደናቂ ብቃት የተነሳ ለካሜሮን ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሩን መለያ በመልበስ ገና በወጣትነት ዕድሜው ካሜሩንን ማገልገል ችሏል።
ከ17 አመት በፊትም በኮተን ስፖርት የወጣት ቡድን ድንቅ ብቃት ማሳየቱን ተከትሎ አስራ ስድስት ጊዜ የካሜሮን ፕሪምየር ዲቪዥን ቻምፒዮን ወደ ሆነው የኮተን ስፖርት ዋናው ቡድን ሊያድግ ችሏል። በተደጋጋሚ ለክለቡ ግቦችን በማስቆጠር ስኬታማ ጊዜን በሁለት አመት የክለቡ ቆይታው ማሳየትም ቻለ። ከነዚህ አመታት በኋላ ወደ ፈረንሳይ በማቅናትም በሊግ ዋን ተሳታፊ በሆነው ቫሌንሺየስ ቡድንን በመቀላቀል የእግር ኳስ ህይወቱን ቀጠለ።
በመቀጠልም ሎረንቴ በተባለው ሌላኛው የፈረንሳይ ሊግ ዋን ክለብ የመጫወት እድል አገኘ። በሁለቱ የፈረንሳይ ክለቦች በቆየባቸው ስድስት አመታትም ወደ 26 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የግብ ማሽን መሆኑን አስመሰከረ።
በፈረንሳይ የነበረውን ቆይታ ደምድሞ ወደ ፖርቹጋሉ ሀያል ክለብ ፖርቶ በማምራት አምስት አመት በመቆየት በድምሩ 36 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በሁለት አጋጣሚዎች ለቱርኩ ቤሽክታሽ በሱፐር ሊጋው በሁለት አጋጣሚዎች ተመልሶ በመጫወት 27 ግቦችን አስቆጥሯል። ከተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት ጀምሮ ወደ ሳውዲው ክለብ አልናስር በመዘዋወርም እየተጫወተ ይገኛል።
ከትንሿ የድሆች መንደር መነሻውን ያደረገው ይህ ግዙፍ ግብ አዳኝ ወደ ሳኡዲው ክለብ በ6 ሚሊዮን ዮሮ ለሶስት አመት ኮንትራት ነው ለመጫወት የተስማማው። ግብ አነፍናፊነቱ፣ ቦታ አያያዙ እና ግብ የሚያስቆጥርበት መንገድ የተለየ እንደሆነ የሚነገርለት አቡበከር፣ በዘጠና ደቂቃ የሜዳ ላይ ቆይታው 0.5 ግብ የማስቆጠር አቅም እንዳለውም ይነገራል።
በአልናስር የዘንድሮው የውድድር አመትም ስድስት ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል። በጠቅላላው ከ20 በላይ ግቦችንም በዚሁ ክለቡ እየተጫወተ ከመረብ አሳርፏል። በአገሩ ካሜሩን በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለአገሩ ከምድብ ማጣሪያ ጀምሮ አስገራሚ ግቦችን በማስቆጠር ታሪክ ሰርቷል። ካሜሩን ለዋንጫ ማለፍ ባትችልም በደረጃ ጨዋታው ከቡርኪናፋሶ ጋር በተገናኘችበት አጋጣሚ ከ73ተኛ ደቂቃ በኋላ ተቀይሮ በመግባት የሰራው ታሪክ የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ታሪክ ሆኖ ይታወሳል። በዚያ የደረጃ ጨዋታ ካሜሩን ሶስት ለባዶ በሆነ ውጤት ስትመራ ብትቆይም፣ አቡበከር በመጨረሻ ደቂቃዎች ተቀይሮ በመግባት ሁለት አስደናቂ ግቦችን አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ አቻ አሸጋግሮ አዘጋጇ አገር በሜዳና በደጋፊዋ ፊት ባዶ እጇን እንዳትቀር የነሀስ ተሸላሚ አድርጓታል።
አቡበከር በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ 8 ግቦችን አስቆጥሮ በአንድ አፍሪካ ዋንጫ በርካታ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ስሙን በወርቅ ቀለም አጽፏል። ካስቆጠራቸው ግቦች ባሻገር ዘንድሮ ለአገሩ እና ለክለቡ 8 ግብ የሆኑ ኳሶችን ለጓደኞቹ አቀብሏል። አንድ ሜትር ከ84 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው እና ከሰሞኑ ዕድሜውን 30 ያደረሰው አቡበከር በሳኡዲ አረቢያው ክለብ አልናስር ያለው ኮንትራት በቀጣይ አመት ሲጠናቀቅ 9 ሚሊዮን ዩሮ ያወጣል ተብሎ ዋጋ ተቆርጦለታል።
እጅግ የሚወዳትና በልጅነት ሕይወቱ አስከፊ የድህነት አመታት ከጎኑ ሆና የደገፈችውን ወላጅ እናቱን ማዎቢያል አሊስን ከሁለት አመት በፊት በሞት ከተነጠቀ በኋላ “አለም ጨልማብኛለች” ብሎ የሚያምነው አቡበከር፣ ከአንድ መቶ ስልሳ በላይ ግቦችን በህይወት ዘመኑ አስቆጥሯልም። ከድህነት ወለል በታች ካሉ ቤተሰቦች የተገኘ በመሆኑ ሁሌም መርዳት የሚያስደስተው ይህ ተጫዋች የሜዳ ላይ ወኔው ታታሪነቱ እና አቅሙ በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን መማረክ ችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014