ባለጉዳዮች የካቲት 11 ቀን 2005 ዓ.ም የሰነድ መለያ ቁጥር 81163 አምስት ዳኞች በተሰየሙት ችሎት አመልካች አቶ ሲሳይ ረታ ጠበቃ አቶ መዝገቡ ወልዴ ከችሎቱ ፊት ቀርበዋል፡፡
ተጠሪው ደግሞ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት ሲሆን፤ ነገረ ፈጁን አቶ ሙሉጌታን ይዞ ቀርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም መዝገቡን መርምሮ ተከታዩን ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ጉዳዩም የመጋዘን ኪራይ ውል ጋር ተያይዞ የቀረበ ሃሳብ ላይ ያጠነጥናል፡፡
ፍርድ ጉዳዩ የመጋዘን ኪራይ ውል ጋር ተያይዞ የቀረበ ክርክርን የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመልካች ላይ ባቀረበው ክስ መነሻነት ነው፡፡
የክሱ ይዘት ባጭሩ የተጠሪ ንብረት የሆነውና በጎንደር ከተማ ቀበሌ 01 ውስጥ የሚገኘው መጋዘን አመልካች ከመጋቢት 1 ቀን 1997 ዓ.ም እስከ የካቲት 30 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ በወር ብር 5 ሺህ 109 ነጥብ 45 ኪራይ እየከፈለ ሲጠቀም የቆየ መሆኑን ጠቅሶ የኪራይ ውሉ ከሚያበቃበት መጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ አመልካች የመጋዘኑን ወርሃዊ ኪራይ ክፍያ ብር 13ሺህ 800 እየከፈለ ውሉ በዚህ መልኩ ተሻሽሎ እንዲቀጥል ወይም በዚህ መልኩ ተስማምቶ ለመቀጠል ካልፈለገ ደግሞ መጋዘኑን እንዲያስረክብ በተለያዩ ደብዳቤዎች ማስጠንቀቂያ ቢጻፍለትም እምቢተኛ ሆኗል ይላል፡፡
በተጨማሪ ከእኛ ፈቃድ ውጪ የቀድሞውን የመጋዘኑን የኪራይ መጠን በባንክ ሂሣባችን እያስገባ በመጋዘኑ መጠቀም የቀጠለ በመሆኑ የመጋዘኑን ኪራይ ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ ያለውን የ18 ወራት ኪራይ ክፍያ በ13ሺህ 800 ታስቦና ካለእኛ ፈቃድ የከፈለው ተቀንሶለት በአጠቃላይ ብር 156ሺ429 እንዲከፍልና እንዲሁም ከመስከረም 1 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ መጋዝኑን እስኪያስረክብ ድረስ ያለውን ብር 13ሺ800 ወርሃዊ ኪራይ ክፍያ ታስቦ ከወለድ ጋር ይከፈላቸው ዘንድ ዳኝነት የጠየቀበት ሂደት ነው፡፡
አመልካችም ቀርቦ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና በፍሬ ጉዳዩ ላይም ወርሃዊ የመጋዘኑን ኪራይ ክፍያ በተመለከተ በብር 13ሺ800 እንዲከፍል የሚያስገድደው የውልም ሆነ የሕግ ግዴታ አለመኖሩን በመከራከር መልስ ሰጥቷል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ከመረመረ በኋላ የቀድሞው የኪራይ ውል ጊዜ ከማለቁ በፊት ተጠሪ ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ የመጋዘኑ ወርሃዊ ኪራይ መጠን ብር 13ሺ800 መሆኑን ጠቅሶ በተለያዩ ጽሑፎች ለአመልካች በመግለጽና በዚሁ መልኩ ውሉ ተሻሽሎ እንዲቀጥል አልያም በዚህ የማይስማማ ከሆነ ደግሞ መጋዘኑን እንዲያስረክብ በተገለፀለት መሠረት አመልካች ቀርቦ ካለመዋዋሉም ባሻገር የቀድሞ ኪራይ ውል ጊዜ ከተጠናቀቀም በኋላ መጋዘኑን ሳያስረክብ ይዞ መጠቀሙን መቀጠሉ በተጠሪ የቀረበለትን ድርድር ወይም አዲሱን ወርሃዊ የኪራይ መጠን በዝምታ የተቀበለ መሆኑን ስለሚያሳይ ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም እስከ የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ያለው ወርሃዊ ክፍያ በብር 13ሺህ 800 ታስቦና የተከፈለው ተቀንሶለት ብር 387ሺህ 990 ለተጠሪ ከፍሎ መጋዝኖቹንም እንዲያስረክብ ሲል ወስኗል፡፡ አመልካች በዚህ ውሳኔ ባለመስማማት ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅሬታውን ያቀረበ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በፍትሐ ብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ 337 መሠረት ቅሬታውን ሰርዞታል፡፡
አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይህንኑ በመቃወም ሲሆን፤ አመልካች ሰኔ 25 ቀን 2004 ዓ.ም ጽፎ ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ማመልከቻ ይዘትም እንዲህ ይብራራል፡፡ አመልካች የመጋዘኑን ኪራይ በተመለከተ በወር ብር 13ሺህ 800 ለመክፈል በየትኛውም መልኩ የተስማማሁት ውል ሳይኖር እና እንዲሁም አዲሱን የኪራይ መጠን እንደማልቀበል በግልጽ ለተጠሪ ምላሽ በመስጠትና ይልቁንም በመጀመሪያ የኪራይ መጠን መቀጠል እንደምፈልግ ሐሳቤን በመግለጽ አሳውቄ እያለሁ አዲሱን ዋጋ በዝምታ ተቀብሎታል በማለት የተሰጠው ውሣኔ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1684 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ በመሆኑ ውሣኔው ታርሞ በተዋዋልኩት ውል መሠረትና በቀድሞው የኪራይ መጠን እንዲከፍል ውሣኔ ይሰጥለት ዘንድ ጠይቋል፡፡
አቤቱታው ተመርምሮ አመልካች አዲሱን የመጋዘን ኪራይ ዋጋ በዝምታ በመቀበል ተስማምቶበታል ተብሎ በአዲሱ የኪራይ ዋጋ ስሌት መሠረት የኪራይ ገንዘቡን እንዲከፍል የመወሰኑን አግባብነት ከፍ/ ብ/ህ/ቁ 2950 አኳያ ለመመርመር ሲባል መዝገቡ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ተደርጎ ተጠሪም ቀርቦ የስር ፍርድ ቤቶች ውሣኔ ላይ የተፈጠረ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለመኖሩን ጠቅሶ የቀረበውን የሰበር አቤቱታ ባለመቀበል የስር ፍርድ ቤቶች ውሣኔ ፀድቆ ከበቂ ወጪና ኪሣራ ጋር ይወሰንለት ዘንድ በመጠየቅ መልሱን የሰጠ ሲሆን አመልካችም የበኩሉን የመልስ መልስ ሰጥቶበታል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መዝገቡ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡
እንደመረመርነው ‹‹አመልካች የቀረበለትን አዲሱን የኪራይ ዋጋ በዝምታ በመቀበልና መጋዘኑን የቀድሞ የኪራይ ውል ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ሳያስረክብ መጠቀሙን የቀጠለ በመሆኑ በአዲሱ ዋጋ እንደተስማማ ተቆጥሮ የኪራዩን ገንዘብ በዚህ ስሌት ዋጋ አመልካች ሊከፍል ይገደዳል በሚል ተጠሪ የሚከራከር ሲሆን፤ አመልካች ደግሞ በተጠሪ የቀረበውን የኪራይ ዋጋ እንደማልቀበልና እንደማልስማማበት ሐሳቤን ገልጬ ስቃወም ስለነበረ በዝምታ እንደተቀበልኩ ተቆጥሮ የሚወሰድበት የሕግ አግባብ የለም በማለት ይከራከራል፡፡
በመሆኑም በዚህ ጉዳይ አመልካች በተጠሪ የቀረበለትን አዲሱን የመጋዝን ኪራይ ዋጋ በፍትሐ ብሔር ቁጥር 1684 ድንጋጌ ስር በተመለከተው መልኩ በዝምታ ተቀብሎ እንደተስማማበት ሊቆጠር ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለው መፍትሔ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በተጠሪ የቀረበለትን የኪራይ ዋጋ ማሻሻያ መጠን አስመልክቶ አመልካች በመቃወም ምላሽ የሰጠ ስለመሆኑና ይህንኑ ምላሽ የሰጠበትን የጽሑፍሰነድም በማስረጃነት ቆጥሮ ለስር ፍርድ ቤት በማቅረብ የተከራከረ ስለመሆኑ ከቀረቡት ውሳኔ ግልባጮች መገንዘብ ተችሏል፡፡
ተጠሪም የኪራይ ማሻሻያውን አመልካች በዝምታ ተቀብሎታል በሚል በደፈናው መከራከሩን እንጂ በፍትሐ ብሔር ቁጥር 1684 (2) ስር እንደተመለከተው ለምላሹ በቂ ጊዜ ተቆርጦለት በዚያው በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ አመልካች መልስ ሳይሰጥ በመቅረቱ የማሻሻያ ዋጋውን እንደተቀበለ ይቆጠራል በሚል የቀረበ ክርክር የለም፡፡
ምላሹ የተቆረጠ የጊዜ ገደብ ስለመኖሩ የተገለፀ ነገር ካለመኖሩም ባሻገር በዚህ ረገድ የቀረበ ክርክርም ባለመኖሩ በተጠሪ የቀረበውን የኪራይ መጠን ማሻሻያ ዋጋ ድርድር ወይም ሐሳብ አመልካች በደረሰ በወሩ ወይም ከዚህም በበለጠ ጊዜ ውስጥ አመልካች የተቃውሞ ሐሳቡን በመግለጽ ምላሹን ከሰጠ ድርድሩን በዝምታ ተቀብሎታል ተብሎ ሊወሰድ የሚቻልበት የሕግ አግባብ አይኖርም በተጠሪ የቀረበለትን የኪራይ መጠን ዋጋ ማሻሻያ ሐሳብ ከላይ በተገለፀው መልኩ አመልካች በዝምታ እንደተቀበለ የሚቆጠርበት አግባብ የለም የሚል መደምደሚያ ላይ ከተደረሰ ደግሞ የኪራይ መጠኑ በፍትሐ ብሔር ቁጥር 2950(1) ስር እንደተገለፀው በሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ተወስኗል ለማለት አይቻልም፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ምንም እንኳ የቀድሞው የኪራይ ውል ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ አዲሱ የኪራይ ልክ በሕጉ አግባብ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ተወስኖ ያልታወቀ ቢሆንም አመልካቹ መጋዘኑን መጠቀም የቀጠለ በመሆኑ ላገኘው አገልግሎት ኪራይ ሊከፍል ይገደዳል፡፡
ምን ያህል የኪራይ ልክ ሊወሰን ይገባል የሚለውን በተመለከተ አመልካች የቀድሞውን የኪራይ ውል መነሻ በማድረግ በወር ብር 5ሺህ 109 መሆን አለበት ብሎ የሚከራከረውም ሆነ ተጠሪ በወር ብር 13 ሺህ 800 መሆን አለበት የሚለው ክርክር ከላይ በተገለፀው መልኩ የሁለቱንም ወገኖች ስምምነት መነሻ ያደረገ ባለመሆኑ በፍትሐ ብሔር ቁጥር 2950(2) ስር በተመለከተው መልኩ የኪራይ ልኩ በተዋዋይ ወገኖቹ ሥምምነት ሳይወሰን የቀረ እንደሆነ የማዘጋጃ ቤት ባለስልጣናት በወሰኑት በታሪፍ መሠረት ወይም ይህ በሌለ ጊዜም የአካባቢውን የወቅቱን ነፃ ገበያ ዋጋ መነሻ በማድረግ ሊወሰን እንደሚገባ መገንዘብ ይቻላል ሲል ሃሳቡን ያጠቃልላል፡፡
በተጨማሪም የሰሜን ጎንደር መስተዳድር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን የመጋዘኑን ወርሃዊ የኪራይ መጠን ከላይ በተገለፀው መልኩ በማዘጋጃ ቤቱ የተወሰነ ታሪፍ ካለ በዚያ መሠረት ይህ ከሌለ ደግሞ የአካባቢውን ልማድ ወይም ወቅታዊ ነፃ ገበያ ዋጋ መነሻ በማድረግ መወሰን ሲገባ የአመልካች ፍቃድና ስምምነት የሌለበትን ወርሃዊ ኪራይ ክፍያ ብር 13ሺህ 800 በመቀበልና በዚህ አስልቶ መወሰኑና እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ይህን ስህተት ማረም ሲገባ ማፅናቱ በውሳኔዎቹ ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል ይላል፡፡
ውሳኔ…
በዚህ ጉዳይ የሰሜን ጎንደር መስተዳድር ዞን ከፍትኛ ፍርድቤትም ሆነ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት የመጋዘኑን ወርሃዊ ኪራይ መጠን ብር 13ሺ800 እንደሆነ በመወሰድና ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን የኪራይ ገንዘብ በዚህ በማስላት ያልተከፈለውን ብር 387 ሺህ 990 ነጥብ 45 አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል የተወሰነው የውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348 (1) መሠረት ተሻረ።
የሰሜን ጎንደር መስተዳድር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የራሱ መዝገብ ቁጥር 05667 የሆነውን በማንቀሳቀስ ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ወርሃዊ የኪራይ መጠን እላይ በፍርዱ ክፍል ውስጥ በተገለፀው መልኩ ግራ ቀኙን በድጋሚ አከራክሮ በመስማት አጣርቶ ከወሰነ በኋላ ያልተከፈለውን የኪራይ ገንዘብ በዚያ በማስላት ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥበት በፍ/ብ/ ስ/ስ ህ/ቁ 343(1) መሠረት በመመለስ ተወስኗል።
በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር ምክንያት ግራ ቀኙ ያወጡትን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ የተባሉ ሲሆን፤ መስከረም 24 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተሰጥቶ የነበረው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል የሚል ውሳኔ ተሰጥቷል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 26 /2014