የጥቁር ሕዝቦች ደማቅ ታሪክ የኢትዮጵያውያን ድንቅ ድል ዓድዋ በጥበብ ተደጋግሞ ተወስቷል። ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ነፃነት የከፈሉት ትልቁ መስዋዕትነት በኢትዮጵያውያን የጥበብ ሰዎች ለዓለም ተዋውቋል።ያ ልዩ ታሪክ በልዩነት ጎልቶ እንዲታይ ኪነጥበብ ኃያል አበርክቶ ነበራት።
የትናንት ሁነት ዛሬ ላይ በተለያየ መልኩ ተኳሽቶ ላላየው ላልሰማው ይተላለፋል። ኪነጥበብ ያለፈን አቅርባ ታመላክታለች፤ የሞተን ቀስቅሳ ህያው ታደርጋለች። ጥበብ ምልከታዋ ጥልቅ፣ እይታዋ ሩቅ፣ መጎናፀፊያዋ በውበት የደመቀ ነውና ሁሉንም ሰብስባ በአንድነት ገሀድ ታደርጋለች። የጥበበኞች ምድር የሆነችው ኢትዮጵያም በጠቢባን ልጆቿ ታሪኳ ተቃኝቷል።
ጥበብ በባህሪው ገላጭ ነውና ያኔ እዚያ ታሪካዊ ቦታ ላይ የሆነውን እውነት ገልጦልናል። ያን መስዋዕትነት በብዕሩ ፣ያንን ጀግንነት በቀለሙ፣ ድንቅ የነበረውን የአርነት ተጋድሎ በክራሩ ኢትዮጵያዊ ጥበበኛ ሲገልጠው ኑሯል። ዛሬም ኃያሉ እውነት በተለየ መንገድ መቅረቡን ቀጥሏል። በወጣትና አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ዓድዋ ተወስቷል። የአገሪቱን ነፃነት ጠብቀው ያቆይዋት አባቶች ገድል፤ ክብሯ እንዳይደፈር የተሟገቱላት እናቶች መስዋትዕነት በብዙ ተዘክሯል።
ለአፍሪካውያን የነፃነት ችቦ የለኮሰው ዓድዋ በኢትዮጵያዊን ሙዚቀኞች ከፍ ብሎ ደምቆ ተነስቷል። የዛሬ የዘመን ጥበብ ገፃችን እነዚህ ዓድዋ ላይ ትኩረት አድርገው ከፍ ያለ ቦታ ላይ የተቀመጡ የሙዚቃ ሥራዎችን ይቃኛል። ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የከፍታ ታሪክ፣ የኢትዮጵያውያን አንፀባራቂ ድል ከዘከሩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሙዚቃዎች መካከል ጎልተው የወጡትን መረጥን እንጂ በጉዳዩ ላይ የተሠሩ በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን ልብ ይሏል።
ኑ አድዋ ላይ እንክተት..ያ የጥቁር ንጉሥ አለና
የወኔው እሳት ነደደ…ለአፍሪቃ ልጆች ድል ቀና
ባልቻ አባቱ ነፍሶ …መድፉን ጣለው ተኩሶ
ሳልል ወይ ሆሆ ሆሆ….
በዜማና በግጥሙ ይዘት ከፍ ያለው ይህ የጥበብ ሥራ አባቶች የነበራቸውን ወኔ፣ አገራቸውን ከጠላት ወረራ ለመታደግ ያደረጉትን የጀግንነት ተግባር በልዩነት ያነሳል፤ይዘክራልም። የቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ጥቁር ሰው ” የተሰኘው ዓድዋን የተመለከተ ዜማ።
በዚህ ሥራ የዓድዋን ታላቅ ድል የጊዜውን የኢትዮጵያ መሪ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ጀግንነት፣ ቆራጥነትና የአመራር ጥበብ፣ የጦርነቱ ተሳታፊ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችን ተጋድሎ በጥበብ ባመረ ዜማ በስርቅርቅ ድምፁ አድማጭ ጋ አድርሶ ያንን ታላቅ ድል እንዲያስቡ አድርጓል።
ይህን ታላቅ ታሪክ፣ የኢትዮጵያውያንን ድል እየዘከረ፣ ዛሬ ላይ ትናንት የሆነውን በብዙ የገለፀ ጥበብ ሥራ በከያኒው ተቀምሮ በሙዚቃዊ ጥበብ ተዋዝቶ ታሪክ እንድንገነዘብ ተደርጓል። አድዋ ላይ በጀግንነት የተዋደቁ ኢትዮጵያውያን፣ እዚያ ተራራ ላይ ለአገራቸው መስዋዕትነት የከፈሉ ታላላቅ የጦር መሪዎች ማንነት፣ ባህሪና ጀግንነት ምስል ከሳች በሆነ መልኩ አስደምጦናል። እነ ራስ አሉላን ከነጦር መሣሪያቸው፣ የእነ መንገሻን ድል አድራጊነት ቴዎድሮስ ካሳሁን በሙዚቃው ጠቅሶ አሳውቆናል።
ፋኖው አባ ራስ አሉላ
ሳንጃ ጎራዴው ቀላ
አዛዥ የጦሩ ባሻ
ድል ነው ካለ መንገሻ …
በጦርነቱ ኃያል ጀግንነት የፈፀሙ ጀግኖች እየዘከረ በዚያ ታሪካዊ ሁነት ስለኢትዮጵያ የተወደቁ ድንቅ አገር ወዳዶችን እያነሳ አጀብ በሚያሰኝ ስንኝ ባማረ ዜማ ይገልፃል። ጥበብ የሩቁን አቅራቢ የተመለከተውን በጥልቀት ዳሳሽ ነውና ይህን መብቱን ተጠቅሞ ፒያሳ ጊዮርጊስ ያለውን የአፄ ምኒሊክ ሐውልት ሲመለከት የተሰማውን በጥበብ ገልፆ አጋብቶብናል።
ጊዮርጊስ ፈረሱ ቆሞ ሳይ
ድል ቀናኝ ሳልል ዋይ
አባቴ ወኔውን ተኮሰው
ምኒልክ ጥቁር ሰው
እያለ የጦር ሜዳውን ተጋድሎ፣ ለአገር የተከፈለውን ታላቅ መስዋዕትነት ጥበብ መሠረት አድርጎ አሳይቶናል። በዚህ አላበቃም፤ እዚያ ታሪካዊው ተራራ ዓድዋ ላይ የተካፈሉትን ጀግና የጦር መሪ በቅፅል ስማቸው አባ መላ በመባል የሚታወቁትን ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን በዚሁ የታሪክ መዘክር በሆነው ሥራው አንስቷቸዋል። በጦር ሜዳው ውሏቸው የሠሩትን ታላቅ ጀብድ ጠቅሷል።
ዳኛው ያሉት አባመላ
ፊት ሐብቴ ዲነግዴ
ሰልፉን በጦር አሰመረው
ፊት ሆኖ በዘዴ
እያለ ዓድዋ ላይ በማዋጋትና በመዋጋት የተለያ የጦር ስልት የነበራቸው የጦር ሜዳው መለኛ ፊትአውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን ያነሳል። በጦርነቱ ወቅት ያበረከቱትን ትልቅ አስተዋፅዖ ይዘክራል። መነሻ ቦታቸውና ታሪካቸውን በሚናገሩት ቋንቋ የተፈጠሩበት ማኅበረሰብ ልሳን በሆነው ኦሮምኛ ዜማ በኃያሉ እንዲህ ብሎ ያሞግሳል።
ኢጆሌ ቢያኮ ጀጀባዳ መሌ
ጀዴቶ ከኤ ያገሬ ኮበሌ
ዱበት ኢንዴምኑ አልከን ተኤ ጉያ
ዲናፍ ሒላኑ ኢትዮጲያ
ኢጆሌ ቢያኮ
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የንጉሠ ነገሥታቸውን አገር ተወረረች፤ ተነስ አዋጅ ሰምተው ወደ ዓድዋ የተመሙት ኢትዮጵያውያንና የፈፀሙት ታላቅ ገድል በዚህ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ሥራ ጥቁር ሰው ተሰኝቶ በሚሊዮኖች ተደምጧል። ዓድዋን በታሰበ ቁጥር ቴዲ፣ ቴዲ በታሰበ ቁጥር ጥቁር ሰው ተያይዘው ይነሳሉ።
በህብር ያጌጠችው ኢትዮጵያ በዓድዋ ታላቅ ድል ነፃነቷን ጠብቃ ዛሬ ድረስ ሳትደፈር የቆየችው ኢትዮጵያ ዛሬ በጥበብ ልጆቿ የእነዚያን ጀግኖች ሥራ መዘከርዋን ቀጥላለች። ዓድዋ ላይ የተጋደሉ ጀግኖች እዚያ ቦታ ላይ ራሳቸውን ሰውተው ፣አገራቸውን ያቆሙ ብርቱዎች፣ ዛሬም ድረስ በተለያየ መልኩ ይዘከራሉ።
ከዛሬ 125 ዓመታት በፊት የሆነ የሆነውን ያንን ታላቅ ጀብድ፣ከምዕተ ዓመት በላይ የሆነውን ያንን ድንቅ ድል በጥበበኛዋ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባውም በልዩነት ተወስቷል። ዓድዋን የእስዋን ያህል የገለፀ፣ ያንን ድልና መስዋዕትነት የእጅጋየሁን (ጂጂን) ያህል ያወደሰ ከወዴት ይኖር ይሆን? ያስባለችበት የዜማዋን መጠሪያ ራሱን ታሪካዊውን ሁነትና ቦታ በመውሰድ “ዓድዋ” ብላዋለች።
ስለ ዓድዋ የጂጂን ያህል በጥበብ አጉልቶ ለዓለም የገለፀ፤ ተቀኝቶ ልዕልናውን ያረጋገጠ የሙዚቃ ሥራ ለማግኘት ብዙ መድከም ይጠይቃል። ይህች ድንቅ አቀንቃኝ ዓድዋ በተሰኘ ዜማዋ የታሪካዊ ሁነቱን አጠቃላይ ገፅታ፣ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት፣ በጦርነቱ የከፈሉትን መስዋዕትነት እና የድሉን ድምቀት በነጠሩና ብዙ በሚገልፁ ቃላት ተጠቅማ አቀንቅናለች።
የሰው ልጅ ክቡር፣… ሰው መሆን ክቡር፣
ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን፣ሰውን ሲያከብር፣
ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ለራሱ የሚሰጠው ታላቅነት በማንሳት ይህንን ውድ ነገሩን ለአገሩ ሳይሰስት የሰጠበትን ሁነት በልዩ ገለፃ በተዋበ ዜማ ስታሰማን የዓድዋና መስዋዕትነት፣ የድሉና የአርበኞች ቆራጥነት ፍንትው አድርጎ ይገልፃል። “ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን፣ሰውን ሲያከብር”በዚህ ሥራዋ የሰው ልጅ ታላቅነት፣ የአዳም ዘርን ክብር አጉልታ በመጀመር ይህ ክብሩ ለታላቅና ከራሱ የበለጠ ለሚወዳትና ለሚያከብራት አገሩ ራሱን ቤዛ ያደረገበትን እውነት በዚህ መልክ ለማሳየት ተጠቅማበታለች።
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ።
በወቅቱ በዚህች አገር ላይ፣ በዚህ ጀግና ሕዝብ የተፈፀመ ኃያል ድል በዘከረው የአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው ዜማ ለዚህች ምድር ክብር የተከፈለ መስዋዕትነት በነጠረ አገላለፅ ተሰኝቷል። ከያኒዋ እያደር ሲሰሙት አዲስ፤ ከርሞ ሲያዳምጡት በብዙ የሚመነዝሩት ትርጓሜ የያዘ፤ ሲመረምሩት የሚደንቅ ፍቺ የሚሰጥ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ሥራዋ ነው። ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ላከበራት አገሩ የከፈለው መስዋዕትነት በሚገባ ተገልጧል።
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፣
ዛሬ ላይ ትናንት ሆነ ተብሎ የሚነገረው ታሪክ በምን ያህል ውድ ዋጋ እንደተገኘ ስለዚያ ኢትዮጵያውያን የሆኑትንና የከፈሉትን ይነግረናል። ይች በደምና በአጥንት ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች ምድር ፤ጠባቂዎቿ የዋሉላትን፤ የከፈሉላትን መስዋዕትነት በብዙ ነገር ግን አጥረውና ተመጥነው በጥበበኛዋ በተቋጠሩ ስንኖች ብዙ ይነግሩናል።
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር፣
ትናገር ዓድዋ፣ ትናገር ትመስክር፣
ትናገር ዓድዋ፣ ትናገር አገሬ፤
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ።
መስዋዕትነቱ ልጆቿ የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ ምክንያት ሆኗል። በማንነታቸውና በባህላቸው እንዲፀኑ ረድቷቸዋል። ኢትዮጵያውያን ከሰው ፊት በነፃነት እንዲቆሙ መኩሪያ ሆኗቸዋል። ይሄንንም እጅጋየሁ በዚሁ ዜማዋ እንዲህ ስትል አዚማዋለች።
በኩራት፣ በክብር፣
በደስታ፣ በፍቅር፣
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን፣
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን።
ስንኙ፤ የዚያ ዘመን መስዋዕትነት ዛሬም ድረስ የቆየ ነፃነት ማጎናፀፉ፣ የዚያ ዘመን ተጋድሎ ዛሬም ድረስ የፈጠረው ወኔና ራስን መሆን ያስገኘው ውጤት መሆኑን ያመላክታል።
አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት፣
መቼ ተነሱና የወዳደቁት፣
ያ ትልቅ ድል ፈፅሞ በሚገባው መጠን እንዳልተዘከረ፤ያ የጥቁሮች የነፃነት ቀን ገና እንዳልተወሳና እዚያ ምድር ላይ የተዋደቁት በሥራቸው ልክ ውዳሴና ምስጋና ዛሬ ድረስ እንዳላገኙ ለዚህም መሥራትና ታሪካቸውን እያወጣን መግለፅ፣ ሥራቸውን ማስተዋወቅ እንደሚገባን የሚነግር፣ታሪካችን ሳይገለጥ መኖሩን የሚያስታውሰን ነው።
ምስጋና ለእነሱ ለዓድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፣
ያኔ አፍሪካውያን በነጮች ተወረው ነፃነታቸውን አጥተው ሉዓላዊነታቸውን ተነጥቀው ነበርና ኢትዮጵያውያን የተቀዳጁትን ድል ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ በተለይ ለአፍሪካውያን የነፃነት ችቦ ለኩሷል። ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለተበደሉ ጥቁሮች፣ ተንቀው ተደፍረው ለነበሩት አፍሪካውያን ሁሉ ጭምር ሆኗል።
የጥቁር ድል አምባ፣ ዓድዋ፣
አፍሪካ፣ እምዬ ኢትዮጵያ፣
ተናገሪ ……..ተናገሪ
የድል ታሪክሽን አውሪ።
ከዚህች የሙዚቃው ዓለም ንግስት በተጨማሪ ይህንን ታላቅ ድል ከዘከሩ ድምፃውያን መካከል ዝነኛው ድምፃዊ ሮፍናን በተለየ እይታ ትናንት ዓድዋ ላይ የተጋደሉ ጀግኖችን በማወደስ ዛሬ ያንን ድንቅ ታሪክና ድል መድገሚያ ሌላ እድል እንዳለን ያነሳል። የእኛን ዓድዋ ዛሬ ላይ በምን ማደስ እንዳለብን ያንን ድል በምን መድገም እንዳለብን ያስገነዝባል።
ዓድዋ ከራስ ጀመረ
ራሱን ያሸነፈ ለ ሰው ተረፈ
ሁሉም ትውልድ ዓድዋ አለው
የኔም ዓድዋ ልቤ ላይ ነው
ጀግና ማለት ይቅር ባይ ነው
በይቅር በይነት ሰፊ ልብ የተራራቅንበትን ሀሳብ ማቅረብ፣ የተጣላንበትን ማስታረቅ፣ የተለያየንበትን ማቀራረብ እንችላለንና ያኔ አድዋ ላይ አንድ ሆነው ያገኙት ድል እና አንድነት ዛሬ እኛ እርስ በርሳችን ይቅር ተባብለን ድሉን እንድንደግመው በጥበብ አዋዝቶ ይነግረናል። የዓድዋን ድል ዛሬ ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በምን መልክ መድገም እንዳለብን በብዙ ያሳየናል።
ኢትዮጵያውያን ከምስራቅና ምዕራብ ከሰሜንና ደቡብ አንድ ላይ ዘምተው፣ ከመሐል አገር ተነስተው ዓድዋ ላይ ትልቅ ጀብድ የፈፀሙት ጀግኖች ኢትዮጵያውያንን የጥበብ ባለሙያዎች ከብዙው ጥቂቱን በዚህ መልክ ዳሰን አበቃን። ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2014