
መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኘው ጋሸና ከተማ ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ተነስቶ በወልድያ ወደ ባህር ዳር እና ጎንደር እንዲሁም ከሰቆጣ በላልይበላ ወደ ዋድላ ደላንታ፣ ደሴ፣ አዲስ አበባ የሚወስዱት አውራ ጎዳናዎች መገናኛ ዕምብርት ናት። ታዲያ ከተማዋ ካላት ስትራቴጂካል ጠቀሜታ አንጻር ጁንታው ለወረራ ወደ አማራ ክልል ዘልቆ ሲገባ በእግር በፈረስ ብሎ ተሽቀዳድሞ ይቺን ከተማ ይዞ ነበር። በዚህም ጁንታው ለወራት ከተማዋን ካምፕ አድርጎ የወታደራዊ ስምሪት መስጫ፣ ማሰልጠኛና ምሽግ አድርጓት ቆይቷል። በከተማዋ በአራቱም ማዕዘን ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የኮንክሪት ምሽግ ሰርቶ እንደ ዳቦ ከላይ እሳት ከታች እሳት ሲያነድባት ከርሟል።
የጥፋት ቡድኑ የሽንፈትን ካባ ተከናንቦ እግሬ አውጭኝ ብሎ ከተማዋን ለቆ እስከፈረጠጠባት ቅጽበት ድረስም ዕፅዋትን ጨምሮ ፈጣሪ በአምሳሉ የፈጠረው ክቡር የሰው ልጅ ያለ ርህራሄ ከሞራል በታች ተገሏል። ተዋርዷል። ሕጻናትና እናቶች ተደፍረዋል። ከተራ የግለሰብ ንብረት የውሃ መጠጫ ብርጭቆ እስከ መንግሥት ተቋማት እና ፋብሪካዎች ድረስ በከተማዋ ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል። ጥቂት የማይባሉ የጋሸና ከተማ ነዋሪዎችም በጁንታው ታፍነው ቀኑ የዓመት ያህል እረዝሞባቸው በጭንቀትና በሰቀቀን ወራት አሳልፈዋል።
በኋላም በ “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በጋሸና ግንባር በተደረገው እልህ አስጨራሽ ጦርነት
“ወፍራም ሰው ሲቀጥን፣ ቀጭኑ ሲወፍር፤
ጥቁር ሰው ሲቀላ፣ ቀዩ ሲጠቁር፤
እንኳን ባልንጀራ፣ ጥሎ የሚሸሸው፤
ልብ አይታመንም አብሮ የሚበላሸው።”
ሲል ተወዳጁ ዘፋኝ ባህሩ ቃኘ እንዳዜመው የወገን ጦር በከተማዋ በአራቱም ማዕዘናት የተሠሩ የጠላት ምሽጎችን ደረማምሶ ከተማዋን ከጠላት ኃይል ነጻ ለማውጣት በተደረገው ታሪካዊ ጦርነት የወንዶች ቁና ጎልተው የወጡበት፣ ስለኢትዮጵያ አያሌ ጀግኖች የወደቁበት እና ጠላት አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ እንደቅጠል የረገፈበት ከተማ ናት። በዚህም ስለ አገራቸው ጀግኖች አባቶቻችን እንደተዋደቁበት ዓድዋና መቅደላ ሁሉ፤ የዚህ ዘመን ጀግኖች ታሪክ የሠሩባት ጋሸና ከተማ በታሪክ ማህደር ስሟ በደማቅ ቀለም ተከትቧል።
ጁንታው በጋሸና ግንባር አይቀጡ ቅጣት ሲቀጣ እንደሰካራም እየተውረገረገ ጓዙንና አስከሬኑን እያንጠባጠበ ከአማራ ክልል ተለቃቅሞ ሊወጣ ችሏል። በእውር ድንብር የገባው የጁንታው ጀሌም መውጫ ቀዳዳው ጠፍቶበት በገባበት ተዳፍኖ ቀርቷል።
‹‹በጦር ሜዳ ከተገኘው ድል በኋላም በሰፈነው የሰላም አየር ከተማዋ ከጦር አውድማነት ተላቃ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ከገባች ሰነባብታለች። የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ልማቷን እያፋጠነች ትገኛለች። የጋሸና ከተማ ካላት ስትራቴጂካል ጠቀሜታ ባሻገር ለኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር ኢንቨስተሮችን እጇቿን ዘርግታ እየጠበቀች ነው ›› ሲሉ የጋሸና ከተማ አስተዳደር ከተማና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ወረታ ይናገራሉ።
እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፤ ጋሸና በመስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ፣ አየር ንብረቷ ለኑሮና ለጤና ተስማሚ የሆነች ከተማ ናት። በዚህም በአራቱ አቅጣጫ የሚመጡ እንግዶች ማረፊያ ናት። በተለይ የከባድ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ሲመጡ የሚያድሩባት እና በበግ ጥብሷ የምትታወቅ ከተማ ናት።
ከተማዋ በዙሪያዎ ብዙ ታሪካዊ ቦታዎች ያሏት ሲሆን ከእነዚህ መካከል የዳግማዊ ላልይበላ እና የቤተ ዮሐንስ ቅዱስ ገብርኤል ፍልፍል ዋሻዎች ለአብነት ይጠቀሳሉ። የጭራ መድኃኒዓለም ታሪካዊ ገዳም ያሉባትና የቅኔ መፍለቂያ የሆነች ከተማ ነች። ለኑሮ ተስማሚና ምቹ የአየር ጸባይ፣ ለጥ ያለ ሜዳማ የእርሻ ቦታዋም ትታወቃለች። አብዛኛው የአካባቢው ነዋሪዎችም በእንስሳት እርባታና በእርሻ የሚተዳደሩ ናቸው። ጋሸና ከምትታወቅበት ምርቶች መካከል በተለይ በስንዴ፣ በገብስ፣ በአፕል እና ስጋ ምርት ትታወቃለች።
ጋሸና ቢዘሩባት አብቃይ፣ ቢኖሩባት ለኑሮ ተስማሚ፣ ወጥቶ ወርዶ ሠርቶ ለማትረፍ ስትራቴጂካል ቦታ ናት። መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። ሕዝቦቿም እንግዳ ተቀባይና ሰላም ወዳድ ናቸው። በተለይ የጋሸና ከተማ ወጣቶች ከሌላው ለየት የሚያደርጋቸው አገራዊ እሳቤ ያላቸው፣ ሰላም ወዳድና እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። በጥቅሉ ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ፣ ከሕዝቦቿ እንግዳ ተቀባይነት እና ከምግቧ አንጻር በዞንና በክልል ጋሸና ከተማ “የደጋዋ ሙሽራ” እየተባለች ትጠራለች።
በዚህም ከተማዋ ያላትን ስትራቴጂካል ጠቀሜታ እና ተፈጥሮ ሀብት መሠረት ያደረጉ አምስት ለአገር እድገት ዋልታና ማገር የሆኑ ፋብሪካዎች በከተማዋ ተገንብተዋል። የመጀመሪያው በከተማዋ የሚገኝው በአገር አቀፍ ደረጃ ምርቱ የሚታወቅ የዱቄት ፋብሪካ ነው። ይህ ፋብሪካ ከ165 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው። ሌላው በከተማዋ የሚገኘው የቆርቆሮና የሚስማር ፋብሪካ ነው። ይህ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቅቆ ማሽን ከውጭ በማስገባት የማሽን ተከላ ላይ ያለ ነው። ፋብሪካውም ገና ወደ ምርት ሂደት ሳይገባ ከ60 በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
እንዲሁም በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከእርሻና እንስሳት እርባታ በተጨማሪ የሚተዳደሩት በባህርዛፍ ምርት በመሆኑ ጋሸና እና ዙሪያ ገባዋ በባህርዛፍ ምርት ይታወቃል። የሰሜኑን ክፍል የባህርዛፍ ምርት ፍላጎት መጋቢም ናት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥናት ተደርጎበት የጣውላ (የፕላይ ውድ)ና የችፑድ ፋብሪካዎች በከተማይቱ እንዲከፈቱ ተደርጓል። ከዚህ ባሻገር ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ያላት ከተማ በመሆኗ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካም በከተማይቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አቶ መላኩ ጁንታው ለወረራ ወደ አማራ ክልል ዘልቆ በገባ ወቅት ከተማዋ ካላት ስትራቴጂካል ጠቀሜታ አንጻር ለወራት ካምፕ አድርጓት እንደነበር አውስተው፤ ዙሪያውን በምሽግ ታጥራ በላይ እሳት በታች እሳት ሲነድባት ከርሟል። በዚህም ትልቅ ውድመት ደርሶባታል። የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ሰብዓዊና ማኅበራዊ ቀውስ ደርሷል። በተለይ በከተማዋ ዙሪያ ያሉ ቀበሌ አርሶ አደሮች በጦርነቱ አዝመራቸው በእሳት ወድሞባቸዋል። በኋላም በአገር አቀፍ በጦር ሜዳው ለተመዘገበው ድል ወሳኝ የሚባል ጦርነት የተካሄደባት ከተማ ናት።
በጦር ሜዳ ከተገኘው ድል በኋላ በሰፈነው የሰላም አየር ጋሸናን ወደ ነበረችበት ለመመለስ የከተማ አስተዳደሩ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመንግሥት ሠራተኞች፣ ከአገር ሽማግሌዎች እና ከወጣቶች ጋር በየደረጃው ውይይት በማድረግ ከተማዋን ቢቻል ከነበረችበት በላይ ካልሆነ ግን ወደ ቀደመው አቋሟ ለመመለስ መግባባት ላይ ተደርሶ እቅድ ተይዟል። በተያዘው እቅድ መሰረት በከተማዋ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባትና የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
በጦር ሜዳ ከተገኝው ድል በኋላም በሰፈነው የሰላም አየር የከተማዋ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለኢንቨስተሮች ከሚያስገኝው ጠቀሜታ ባለፈ ለኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር ኢንቨስተሮች ወደ ከተማዋ መጥተው መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠራ ነው። ከ100 ሺ ሄክታር በላይ ለኢንቨስትመንት የሚተላለፍ ቦታ በሳይት ፕላን ታስሮ ተቀምጧል። ቦታው ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆነና መሠረተ ልማት የተሟላለት ነው። ስለዚህ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚጠይቁ አልሚዎች የሚተላለፍ ይሆናል ብለዋል።
ከተማዋ በቂ የውሃ አቅርቦት ያላት ስለሆነች ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት ዛሬ ውሃ ለጠየቀ አልሚ ነገውኑ ውሃ ማስገባት ይቻላል። ለኢንቨስትመንት የተመረጡ ቦታዎች ምቹ መንገድ ተሠርቶላቸዋል። ባለሀብቶች መጥተው ወደ ኢንቨስትመንቱ ሲገቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንዳይገጥማቸውም ቀድሞ የትራንስፎርመር ዝግጅት ተደርጓል። ከክልሉ አራት ትራንስፎርመር ተጠይቆ የተፈቀደ ሲሆን በቅርቡ በኢንቨስትመንት ሳይት አካባቢዎች ተከላ ይደረጋል።
ስለዚህ ከተማዋ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ስለሆነች ከላይ ከተጠቀሱት ፋብሪካዎች በተጨማሪ በተለያየ ዘርፍ መሰማራት ይቻላል። ለአብነትም በጨርቃጨርቅና ጋርመንት፣ በግንባታ ግብዓት /በተፈጨ ጠጠር፣ ሲሚንቶ ፋብሪካ…./፣ በእንስሳት እርባታና በሥጋ ፋብሪካ አልሚዎች ቢሰማሩ ከተማዋ ካላት ተፈጥሯዊ ሃብት አንጻር ውጤታማ ይሆናሉ።
ሌላው በከተማዋ ያለውን የዱቄት ፋብሪካ ታሳቢ በማድረግ የዱቄት ማሸጊያ ከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ መክፈት አዋጭ ነው። እንዲሁም በከተማዋ ዙሪያ ካሉ ታሪካዊ መስህብና በቀን ወደ ከተማዋ ጎራ ከሚሉ እንግዶች አኳያ በሆቴልና አገልግሎት ዘርፍ አልሚዎች ቢሠማሩ ትርፋማ ይሆናሉ። ኢንቨስተሮች በእነዚህና በሌሎች ዘርፎች ላይ በመሠማራት ውጤታማ ወይም አትራፊ መሆን ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮ አልሚዎችን ለመቀበል እጁን ዘርግቶ እየጠበቀ ነው። ከውጭም ከውስጥም ወደ ከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ባለሀብቶችን እጃቸውን ስመን ተቀብለን እንደ እንቁላል ተንከባክበን መልካም መስተንግዶ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
“የደጋዋ ሙሽራ” በሚል ቅጽል ስም የተሰጣት ጋሸና ከተማ ኢንቨስተሮች ለማልማት ቢመጡ አትራፊ ይሆናሉ። ምክንያቱም በተለይ ወደፊት የምስራቅ አማራ አካባቢ ማዕከል ትሆናለች ተብላ ትልቅ ዕቅድ ታቅዶባት የተለያዩ ልማቶች እየተካሄደባት የምትገኝ ከተማ ናት። ከዚህ አኳያ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ ቢመጡ የሚፈልጉትን የኢንቨስትመንት ቦታ መሠረተ ልማቶችን አሟልተን ለማስረከብ ዝግጁ ከመሆን ባለፈ በአክብሮትና በእንክብካቤ ለማስተናገድም ዝግጁነታቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የጥፋት ቡድኑ ከተማዋን በወረራ ይዞ በቆየባቸው ወራት ከተራ የግለሰብ ንብረት የውሃ መጠጫ ብርጭቆ እስከ መንግሥት ተቋማት እና ፋብሪካዎች ድረስ በከተማዋ ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል። በኋላም በጦር ሜዳው ለተገኘው ድል ወሳኝ የሚባል ጦርነት የተካሄደባት ከተማ ናት። በጦርነቱም ከፍተኛ ውድመት ደርሶባታል። በጦር ሜዳ ከተገኘው ድል በኋላ በሰፈነው የሰላም አየር ከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላትና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት የወደመውን መልሶ ለመገንባትና የተዘረፈውን ለመተካት ተግቶ እየሠራ ነው።
የጦርነት አውድማ ሆና የከራረመችው ጋሸና ጦርነቱ ሰፊ ጥፋትና ውድመት አድርሶባታል። ስለዚህ ኅብረተሰቡ የወደመውን እና የተዘረፈውን እያየ ቆዝሞ እንዳይቀመጥ እና ወደ ልማት እንዲገባ ለማድረግ ከተማይቱ ወደ ነበረችበት ከተቻለም ከዛ በላይ እንድትሆን በሚደረገው እርብርብ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ሲሉም ጠይቀዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2014