የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ቻምፒዮናዎች መካከል አንዱ የፔፕሲ ክለቦች ቻምፒዮና ነው፡፡ ይህ ውድድር ለ39ኛ ጊዜ ዘንድሮ የተካሄደ ሲሆን፤ ለአምስት ቀናት በሩጫ፣ ውርወራ እና ዝላይ ስፖርቶች አትሌቶችን ሲያፎካክር ቆይቷል፡፡ ከ1991 ዓም ጀምሮ በሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ስፖንሰር አድራጊነት እየተካሄደ የሚገኘው ውድድሩ በከተማዋ የሚገኙ ክለቦች ከማፎካከር ባለፈ ተተኪ ስፖርተኞችንም ለመፍጠር እንዲሁም ለሌሎችም መነሳሳትን ለመፍጠር ይጠቅማል፡፡
በፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈራሁ ገብሬ፤ በአንደኛ ዲቪዚዮን የተመዘገቡ 7 ክለቦችና በተያዘው ዓመት የተመዘገበውን ጨምሮ 13 የሁለተኛ ዲቪዚዮን በጥቅሉ 20 ክለቦችን የሚያሳትፍ ውድድር መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ክለቦቻቸውንም ወክለው ከ1ሺ በላይ የሚሆኑ አትሌቶች በቀጣይ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ላይ ክለባቸውንና ከተማ አስተዳደሩን ለመወከል ሲፎካከሩ ቆይተዋል፡፡ ፌዴሬሽኑም ክለቦች አትሌቶቻቸውን በሚገባ አዘጋጅተው በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ የገመገመ ሲሆን፤ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በርካታ ክብረወሰኖች መሻሻላቸውን ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰባት የውድድሩ ክብረወሰኖች ሲሻሻሉ(ሶስት የሜዳ ተግባራትና አራት የመም)፤ አምስት የሚሆኑት በወንዶች ሁለቱ ደግሞ በሴት አትሌቶች ነው፡፡
በውድድሩ በርካታ አበረታች የሆኑ ነገሮች የታዩ ቢሆንም በአንጻሩ ፈታኝ ሁኔታዎችም እንዳሉ ነው የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ የሚጠቁሙት፡፡ ይኸውም የውድድር ሜዳውን የሚመለከት ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ስታዲየም በእድሳት ምክንያት እንዲሁም የአበበ ቢቂላ ስታዲየምም የሩጫ ውድድሮች ባለፈ የሜዳ ተግብራትን ማስተናገድ የማይችል መሆኑን ተከትሎ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በአካዳሚው ማድረግ አስገዳጅ ሆኗል፡፡
የመጀመሪያው ጉዳይ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከአዲስ አበባ ስታዲየም አንጻር ርቀት ያለው በመሆኑ አትሌቶች ለእንቅስቃሴ አዳጋች መሆኑ ነው፡፡ ሌላው አካዳሚው የራሱ ሰልጣኞች ያሉት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በማለዳ መጀመር ያለባቸው ውድድሮችን ሰዓቱን ጠብቆ ማካሄድ አልተቻለም፡፡ ሰልጣኞች የዕለት መርሃ ግብራቸውን እስከ 2ሰዓት ከሰላሳ ካከናወኑ በኋላ ውድድሩ የሚካሄድ በመሆኑ ውድድሩ የሚጠናቀቅበትን ሰዓት ወደ ኋላ ከመግፋት ባለፈ ሙቀቱ ለተመልካችም ሆነ ለተወዳዳሪዎች አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
ይህ ሁኔታ በዚህ ውድድር ላይ ብቻ የተስተዋለ ሳይሆን የተለመደ ከመሆኑ ባለፈ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአትሌቲክስ ስፖርት የሚሆን የማዘውተሪያ ስፍራ አለመኖሩ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ጽህፈት ቤት ኃላፊዋም አብዛኛዎቹ ክለቦች የተቀመጡላቸውን መስፈርቶች አያሟሉ እንጂ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን በሚል ደረጃ እንደተሰጣቸው ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና የአብዛኛዎቹ ችግር የማዘውተሪያ ስፍራ ነው፡፡ ከተወሰኑ ክለቦች ባለፈ አብዛኛዎቹ ካምፕ ጭምር የሌላቸው ሲሆን፤ አትሌቶቻቸውን የሚያሰለጥኑ በኪራይ ሜዳዎች ነው፡፡ ሜዳ እያሰሩ ያሉትም እጅግ ጥቂትና አቅም ያላቸው ክለቦች ብቻ ናቸው፡፡ ስልጠና ውጤታማ እንዲሆን የማዘወተሪያ ስፍራ እንደሚያስፈልገው እሙን መሆኑን ተናግረው፣ ይህ ሁኔታ ሲጠናከር ውጤትም ይመዘገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ኃላፊዋ ይጠቁማሉ፡፡
የማዘወተሪያ ስፍራዎች ጉዳይ እንደ ከተማ ሲፈተሽም ከፍተኛ ክፍተት መኖሩ ይታያል፡፡ ለአብነት ያህል ክፍለከተሞች በየስፍራው የሚገነቧቸው ሜዳዎች የሶስት በአንድ በመሆኑ ከኳስ ስፖርቶች ባለፈ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ በርግጥ የመሮጫም ሆነ ለሜዳ ተግባራት ስፖርቶች የሚሆን ማዘወተሪያ ለመገንባት ሰፊ ቦታ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ማዘውተሪያዎቹ የግድ መም ባይሆኑም የአሸዋ መሮጫ እንዲሁም ጥርጊያ ሜዳዎችን በማዘጋጀት አትሌቶችን ማሳተፍ ይቻላል፡፡ ይህንንም ፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ ለክፍለ ከተሞች የሚያነሳው ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ፤ በጉዳዩ ላይ ከከተማ አስተዳደሩ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ዳይሬክቶሬት ጋር የተነጋገረበት መሆኑን ኃላፊዋ ይጠቁማሉ፡፡ እንደ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያሉ ስታዲየሞችም በተጨማሪነት አትሌቲክስንም የሚያካትቱበት ሁኔታ እንዲፈጠርም ሊታሰብ ይገባል፡፡
ፌዴሬሽኑ ባለው አቅም ጥረት እያደረገ ሲሆን፤ ፌዴሬሽኑ የጃንሜዳ ትምህርትና ስልጠና ማዕከልን ጥርጊያ በማስደረግ ለውድድርና ስልጠና አመቺ ለማድረግ ችሏል፡፡ የአሸዋ ትራክ ለማስገንባትም በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ፌዴሬሽኑ የገንዘብ አቅም የሌለው በመሆኑ ከቁጥጥር እና ድጋፍ ባለፈ ሊያደርገው የቻለው ነገር የለም፡፡ በቀጣይም አቅም በማሰባሰብና ባለሃብቶችንም በማሳተፍ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም